Saturday, August 13, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisment -
  - Advertisment -

  ጭፍጨፋን በጋራ የማያወግዝ የፖለቲካ ዓላማ ለማንም አይጠቅምም!

  በዓለም ላይ የማንኛውም መንግሥት ተቀዳሚ ኃላፊነት ዜጎችን ከማንኛውም ዓይነት ጥቃት መከላከልና ሕግና ሥርዓት ማስከበር ነው፡፡ ይህንን ኃላፊነት መወጣት የማይችል መንግሥት እንዳለ አይቆጠርም፡፡ በኢትዮጵያ ላለፉት አራት ዓመታት ያህል በተለያዩ አካባቢዎች በተፈጸሙ ጥቃቶች በርካታ ጭፍጨፋዎች፣ ማፈናቀሎች፣ ዘረፋዎችና ለማመን የሚያስቸግሩ ነውረኛና አሳፋሪ ድርጊቶች ታይተዋል፡፡ ሰብዓዊ ፍጡርን ከእነ ሕይወቱ እሳት ውስጥ ከመክተት ጀምሮ ዘቅዝቆ መስቀል፣ ሕፃናትና አረጋውያንን፣ ነፍሰ ጡሮችንና አቅመ ደካማዎችን ዘግናኝ በሆነ መንገድ መግደልና በጅምላ መቅበር ድረስ የከፉ ነውሮች ተፈጽመዋል፡፡ ከአዲስ አበባ ጫፍ ከቡራዩ እስከ ምዕራብ ወለጋ ጊምቢ ድረስ በንፁኃን ላይ የተፈጸሙ አረመኔያዊ ጭፍጨፋዎችን መንግሥት ማቆም ባለመቻሉ፣ መንግሥት በሕይወት ስለመኖሩ ብዙዎችን እያጠራጠረ ነው፡፡ ንፁኃንን በማንነታቸው በመለየት እየተፈጸመ ያለው ወንጀል ጠያቂ በማጣቱ፣ አሁንም ኢትዮጵያ የደም ምድር እየሆነች የሕግ ያለህ እየተባለ ነው፡፡ በክልልም ሆነ በአገር አቀፍ ደረጃ ራሳቸውን ያደራጁ የፖለቲካ ድርጅቶች ጥቃትን በጋራ ያውግዙ፡፡ ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች ጥቃትን የትግል መሣሪያ ከማድረግ በመቆጠብ፣ መንግሥት ሕግ እንዲያስከብር ማስገደድ አለባቸው፡፡

  ሰሞኑን በኦሮሚያ ክልል በምዕራብ ወለጋ ዞን ጊምቢ ወረዳ በሰላማዊ ሰዎች ላይ የተፈጸመው ጭፍጨፋ፣ ከዚህ ቀደም በተደጋጋሚ በአካባቢው የተፈጸሙ ጭፍጨፋዎች ማጠናከሪያ ሆኖ መቀጠሉ አስደንጋጭ ነው፡፡ ኢትዮጵያውያን በማንነታቸው ምክንያት እንደ አውሬ እየታደኑ በገፍ መጨፍጨፋቸው አልቆም እያለ፣ ለአገር ህልውና ሥጋት የሚደቅን ቀውስ ሲፈጠርና በአጠቃላይ ኢትዮጵያን ወደ ለየለት ትርምስ ሊከት የሚችል ሥርዓተ አልበኝነት ሲናኝ በሕግ ማለት ተገቢ ነው፡፡ ሰላማዊ ሰዎችን በማንነታቸው እያጠቁ መግደል፣ ማፈናቀል፣ ንብረታቸውን መዝረፍ፣ አካላዊና ሥነ ልቦናዊ ጉዳት ማድረስ እየተለመደ ኢትዮጵያ የሲኦል ምድር እየሆነች ነው፡፡ በአንድ አካባቢ በተፈጸመ ጥቃት በመቶዎች የሚቆጠሩ ወገኖች መጨፍጨፋቸው ከአስደንጋጭነቱ ቀጥሎ የሚመጣው፣ ኢትዮጵያ በዚህ ሁኔታ ወዴት እያመራች ነው የሚለው ነው፡፡ የፌዴራል መንግሥቱም ሆነ የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት በተደጋጋሚ ይህንን መሰሉን ጥቃት እንዲያስቆሙ፣ በኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽንና በተለያዩ ወገኖች ጥያቄዎች ሲቀርቡላቸው ነበር፡፡ ነገር ግን የጥቃቱ ሰለባዎች የሚከላከልላቸው በማጣታቸው ዘግናኝ የሆነ ጭፍጨፋ ተፈጽሞባቸዋል፡፡ አሁን መንግሥት ኃላፊነቱን መውሰድ ሲኖርበት፣ ፓርላማው ደግሞ አስቸኳይ ስብሰባ ጠርቶ የማያዳግም ውሳኔ ማሳለፍ ይጠበቅበታል፡፡

  በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የሚፈጸሙ ግድያዎችና ጭፍጨፋዎች ከመጠን በላይ ከመለመዳቸው የተነሳ፣ እያንዳንዱ ቀን እንዴት በሰላም ያልፋል የሚለው ሥጋት ብዙዎችን ድባቴ ውስጥ እየከተተ ነው፡፡ በተለይ ደግሞ በምሥራቅና በምዕራብ ወለጋ ንፁኃን ሰላማዊ ሰዎች ያለ ጥፋታቸው በማንነታቸው እየተለዩ የሚጨፈጨፉበት ምክንያት፣ የጨፍጫፊዎቹ ማንነት፣ ለጭፍጨፋዎቹ የሚሰጠው ምላሽና በአጠቃላይ የሚስተዋሉ አስከፊ ነገሮች ብዙዎችን ተስፋ እያስቆረጡ ነው፡፡ በሰሞኑ ጭፍጨፋ እጁ አለበት የተባለው ኦነግ ሸኔ በቃል አቀባዩ አማካይነት ድርጊቱን መካዱ፣ ለብዙዎች እንቆቅልሽ ሆኖባቸዋል፡፡ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በአሸባሪነት የተፈረጀው ኦነግ ሸኔ ጭራሽ ጣቱን ወደ መንግሥት ሲቀስር፣ የሕዝብን ደኅንነት የማስጠበቅ ኃላፊነት ያለበት መንግሥት ድርጊቱን ከማውገዝ በዘለለ ተዓማኒነት ያለው መረጃ መስጠት ይጠበቅበታል፡፡ ከዚህ በዘለለም ጭፍጨፋውን በፈጸመ ማንኛውም ኃይል ላይ ሕጋዊም ሆነ የኃይል ዕርምጃ ወስዶ አስተማማኝ ሰላም ማስፈን አለበት፡፡ በአሁኑ ጊዜ ከአዲስ አበባ ከተማ ወጣ ለማለት ከፍተኛ ጭንቅ ነው ያለው፡፡ ኢትዮጵያ በተለያዩ አቅጣጫዎች ያልታወጀ ጦርነት እየተካሄደባት ያለች ነው የምትመስለው፡፡

  ኢትዮጵያ ውስጥ ከዚህ በፊት የማይታወቁ አደገኛ ግድያዎች እየተለመዱ ነው፡፡ ከጭነት መኪና ላይ ሰዎችን አስወርደው ሲረሽኑ የሚያሳይ ተንቀሳቃሽ ምሥል በማኅበራዊ የትስስር ገጾች ላይ ሲንሸራሸር ማየት፣ በኢትዮጵያ ምድር እንግዳ ነገር ነው፡፡ የሰው ልጅ ከአውሬ የባሰ ድርጊት በገዛ ወገኑ ላይ ሲፈጽም እንደ ተራ ነገር ማየት ሲለመድ፣ ከዚህ በኋላ ምን ዓይነት ሰቅጣጭ ድርጊቶች እንደሚከተሉ በቀላሉ መረዳት ይቻላል፡፡ ሰሞኑን ኢትዮጵያ የዓለም አቀፍ ሚዲያዎች መነጋገሪያ ርዕስ የሆነችበት የምዕራብ ወለጋው ጭፍጨፋ፣ ሰላማዊ ሰዎች እንደ ዶሮ የተፈጁበትን ሰቆቃ ነው ለዓለም ያስተዋወቀው፡፡ መንግሥትን ጭምር በጣም ያስተቸው ደግሞ ይህ ሁሉ ዘግናኝ ጭፍጨፋ ከተፈጸመ በኋላ፣ ብሔራዊ የሐዘን ቀን ታውጆ ብሔራዊ ሰንደቅ ዓላማ ለምን ዝቅ ብሎ እንዲሰቀል አልተደረገም የሚለው ነው፡፡ በምዕራብ ወለጋ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በማውጣትና ኮማንድ ፖስት በማቋቋም ሌሎች ወገኖችን ከመታደግ በተጨማሪ፣ በድርጊቱ ፈጻሚዎች ላይ ፈጣን ማጣራት በማድረግ ወደ ዕርምጃ አለመገባቱም ጥያቄ አስነስቷል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ መንግሥት ጨፍጫፊዎችን ለሕግ ያቅርብ እየተባለ ነው፡፡

  የኢትዮጵያን ፖለቲካና ፖለቲከኞችን መርህ አልባ ጉዞ ፍንትው አድርጎ እያሳየ ያለው በማንነት ላይ የተመሠረተ ጥላቻ፣ ጥቃት፣ ግድያ፣ ማሳደድ፣ ማፈናቀል፣ ዘረፋና ሌሎች የጭካኔ ድርጊቶችን ነው፡፡ የፖለቲካው ሒሳብ እየተወራረደ ያለው በተገዳዳሪ ፖለቲከኞች መካከል ሳይሆን፣ ሆን ተብሎና ታቅዶ በንፁኃን ላይ በሚፈጸም የእርኩሰት ድርጊት ነው፡፡ በዚህም ምክንያት ወላጆች ልጆቻቸውን፣ ልጆች ወላጆቻቸውን፣ በአጠቃላይ ተጎጂዎች ወገኖቻቸውን በግፍ እየተነጠቁ የብዙዎችን ዕንባ ማበስ እያቃተ ነው፡፡ የመንግሥት የአስተዳደርና የፀጥታ መዋቅሮችን ተማምኖ መንቀሳቀስ ባለመቻሉ፣ ንፁኃን ያለ ጥፋታቸው በአስከፊ ሁኔታ እየተገደሉ ነው፡፡ በኦሮሚያ ክልል ውስጥ የሚንቀሳቀሰው ኦነግ ሸኔ የሚቆጣጠረው አንድም ቀበሌ አለመኖሩ የዛሬ ወር ተገልጾ፣ እንዲህ ለመግለጽ የሚያዳግት ጭፍጨፋ በሰላማዊ ሰዎች ላይ መፈጸሙ ሲሰማ የሚፈጥረው ስሜት ምንድነው? መንግሥት በተደጋጋሚ እንዲህ ያለውን አሳዛኝ ድርጊት እንደማይታገስ ሲገልጽ ነበር፡፡ ነገር ግን በማንነት ላይ ያነጣጠረው ጥቃትና ጭፍጨፋ ግን በአስፈሪ ሁኔታ እንደ ቀጠለ ነው፡፡ የዜጎችን ደኅንነት የመጠበቅ ግዴታም ሆነ ኃላፊነት ያለበት መንግሥት፣ ከራሱ መዋቅር ጀምሮ እስከ ሌሎች ኃይሎች ድረስ የማያዳግም ዕርምጃ መውሰድ ካልቻለ የኢትዮጵያና የኢትዮጵያውያን መከራ ማቆሚያ አይኖረውም፡፡

  የሰላም፣ የአብሮ መኖር፣ የመከባበር፣ የመተዛዘንና የመተሳሰብ ምድር በነበረችው ኢትዮጵያ ውስጥ አንዱ ሌላውን ወገኑን እንደ ጠላት እየቆጠረ ሲገድል ያስደነግጣል፡፡ ለዓመታት ኑሮዋቸውን ከመሠረቱበት፣ ልጆች ወልደው ካሳደጉበትና ከማኅበረሰቡ ጋር ድርና ማግ ሆነው ከኖሩበት ቀዬና አካባቢ በማንነታቸው ምክንያት ንፁኃን ሲታረዱ መጪው ጊዜ ያስፈራል፡፡ በሕግ ጭምር ዋስትና ያገኘው በገዛ አገር በየትም ሥፍራ የመዘዋወር፣ የመኖር፣ የመሥራትና ሀብት የማፍራት ተፈጥሯዊ መብት ተጥሶ ንፁኃን ሲጨፈጨፉና ሲሳደዱ የኢትዮጵያ መፃኢ ዕድል ያሳስባል፡፡ ይህ ሁሉ ግፍ አልበቃ ብሎ እንዲህ ዓይነቱን አስነዋሪ ድርጊት ለማውገዝ የማንነት ሠልፍ ማሳየት ሲጀመርም ሰብዓዊነት ይረክሳል፡፡ ለኢትዮጵያ ህልውና የምታስቡ በሙሉ ይህንን አረመኔያዊ ድርጊት ለማውገዝ ሰብዓዊነት ብቻ በቂ ነው፡፡ በብሔርም ሆነ በዜግነት ወይም በሌላ አደረጃጀት የፖለቲካ ፓርቲ የመሠረታችሁ ሁሉ፣ ይህንን ግፍ በማውገዝ ሕግና ሥርዓት እንዲከበር ካላደረጋችሁ መኖራችሁ ፋይዳ የለውም፡፡ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጥቃትን የትግል መሣሪያ ከማድረግ ተቆጠቡ፡፡ ጭፍጨፋን በጋራ የማያወግዝ የፖለቲካ ዓላማ ለሕዝብም ሆነ ለአገር አይጠቅምም! 

  በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

  በወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት የተሰበሰበው ከፍተኛ ሀብት ጥቅም ላይ እየዋለ አይደለም ተባለ

  በኢትዮጵያ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት የተሰበሰበው የተቀማጭ ገንዘብ መጠን...

  የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሁለተኛው ተርባይን ኃይል ማመንጨት ጀመረ

  ሦስተኛ ዙር ሙሌት በዛሬው ዕለት እንደሚጠናቀቅ ይጠበቃል የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ...

  በቴሌ ብር የማይሠሩ ማደያዎች ቀነ ገደብ ተቀመጠባቸው

  ሚኒስቴሩ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጋር ለመሥራት እየመከረ ነው በኢትዮጵያ...

  የማስተማር ሙያ ሥልጠና ባልወሰዱ መምህራን ላይ አስገዳጅ ውሳኔ ተላለፈ

  ለአሥር ዓመት ሥልጠናውን ያልወሰዱ መምህራን ከመምህርነት ሙያ ይወጣሉ የግል ትምህርት...
  - Advertisment -

  ትኩስ ፅሁፎች

  የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሁለተኛው ተርባይን ኃይል ማመንጨት ጀመረ

  ሦስተኛ ዙር ሙሌት በዛሬው ዕለት እንደሚጠናቀቅ ይጠበቃል የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ...

  የክላስተር አደረጃጀት ፖለቲካዊ ውዝግብ

  መንግሥት የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ይባል የነበረውን አደረጃጀት...

  በወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት የተሰበሰበው ከፍተኛ ሀብት ጥቅም ላይ እየዋለ አይደለም ተባለ

  በኢትዮጵያ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት የተሰበሰበው የተቀማጭ ገንዘብ መጠን...

  የድሬዳዋ ነፃ የንግድ ቀጣና ምሥረታና ተጠባቂ ዕድሎቹ

  ነፃ የንግድ ቀጣናዎች የልዩ ኢኮኖሚ ቀጣናዎች አካል ሲሆኑ፣ በውስጣቸው...
  spot_img

  ተዛማጅ ፅሁፎች

  የሥጋት ደመና ተወግዶ ሰላም ይስፈን!

  ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በደቡብ የአገሪቱ ክፍል ክልል ለመሆን የፈለጉ የተለያዩ ዞኖች እየተሰባሰቡ ለፌዴሬሽን ምክር ቤት ጥያቄ እያቀረቡ ናቸው፡፡ ለብቻችን ክልል መሆን አለብን የሚሉ ዞኖችም...

  በአገር ጉዳይ አንዱ ባለቤት ሌላው ባይተዋር መሆኑ ይብቃ!

  ኢትዮጵያ የታፈረችና የተከበረች አፍሪካዊት አገር ናት፡፡ ለመላው የዓለም ጥቁር ሕዝቦችና ለአፍሪካውያን ነፃነትም ተምሳሌት ናት፡፡ የጥንቶቹ ኢትዮጵያውያን አገራቸውን የሚያኮራ ተግባር ፈጽመው ያለፉት፣ ከአገራቸው በፊት የሚቀድም...

  የማንም ሥልጣንና ጥቅም ከኢትዮጵያ አይበልጥም!

  የታላቁ ህዳሴ ግድብ ሦስተኛ ዙር የውኃ ሙሌት በስኬት መጠናቀቁ፣ የኢትዮጵያን የወደፊት ብሩህ ጊዜ አመላካች ነው ቢባል ማጋነን አይሆንም፡፡ ይህ የአፍሪካ ታላቅ ግድብ ፕሮጀክት ዕውን...