Monday, December 4, 2023

ፓርላማው ጠቅላይ ሚኒስትሩንና ካቢኔያቸውን በደብዳቤ ጠርቶ አለመገኘታቸው ቅሬታ አስነሳ

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

ከ13 ቢሊዮን ብር በላይ ያልተወራረደ ሒሳብ ተገኘ

የአብን አባላት ከአጀንዳ አቀራረብ ጋር በተያያዘ ለማስያዝ የፓርላማውን ስብሰባ አቋርጠው ወጥተዋል

በፌዴራል ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት በቀረበው የፌዴራል መንግሥት መሥሪያ ቤቶች የ2013 በጀት ዓመት የፋይናንስ ሕጋዊነትና የክዋኔ ኦዲት ሪፖርት ስብሰባ ላይ፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩና ካቢኔያቸው እንዲገኙ በደብዳቤ ተጠርተው አለመገኘታቸው ቅሬታ አስነሳ፡፡

የመንግሥት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች የቋሚ ኮሜቴ ሰብሳቢ አቶ ክርስቲያን ታደለ ለምክር ቤቱ አባላት እንዳስታወቁት፣ የፌዴራል መንግሥት መሥሪያ ቤቶች የ2013 በጀት ዓመት የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች የኦዲት ሪፖርት በሚቀርብበት መደበኛ ስብሰባ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትሩና ካቤኔያቸው እንዲቀርቡ በደብዳቤ ጥያቄ ቀርቦ ነበር፡፡

‹‹የኦዲት ሪፖርት የሚቀርበው መንግሥት ሥራዎችን ለመሥራት፣ ፖሊሲና ፕሮግራሞችን ለማስፈጸም፣ የበጀት ጥያቄ አቅርቦ በጀት ከፀደቀ በኋላ የምክር ቤት አባላት የበጀት አጠቃቀሙ ውጤታማ ነው ወይ? ሕግና ሥርዓቱን ተከትሎ የሄደ ነው ወይ?፣ ፍትሐዊነቱስ እንዴት ነው? የሚለውን ለመዳሰስ ነው፤›› ያሉት አቶ ክርስቲያን፣ ሪፖርቱ ሲቀርብ አስፈጻሚ አካላት መኖር ይገባቸዋል፡፡

በየዓመቱ በጀት ሲፀድቅ በቀጥታ የቴሌቪዥን ሥርጭት ቢታይም፣ የበጀት አጠቃቀሙ ግን በቀጥታ የቴሌቪዥን ሥርጭት አለመተላለፉ ቅሬታ እንደፈጠረባቸው ያስታወሱት የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ፣ ጉዳዩ እንደ ቀላል ታይቶ የሚታለፍ ስላልሆነ በምክር ቤቱ በኩል ቁርጥ ያለ ውሳኔ እንዲተላለፍ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የፌዴራል ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት የተለያዩ የኦዲት ግኝቶችን ቢያቀርብም፣ አስፈጻሚው አካል እንዲያስተካክል የሚጠበቅበትን ጉዳይ በምክር ቤት ቀርቦ ከማዳመጥ ይልቅ፣ እንደ መደበኛው ሕዝብ በቴሌቪዥን ሊከታተል እንደማይገባው ቋሚ ኮሚቴው አስገንዝቧል፡፡

ቋሚ ኮሚቴው በ2013 የበጀት ዓመት በምክር ቤቱ የፀደቀው በጀት የፋይናንስ አስተዳደር አዋጅ ደንብና መመርያ በሚፈቅደው መሠረት በትክክል ሥራ መዋሉን ለማረጋገጥ፣ የፌዴራል ዋና ኦዲተር ባከናወነው ዋና ኦዲት በርካታ የሒሳብ አያያዝ ግድፈት ስለመኖራቸውና የውስጥ ቁጥጥር ድክመቶች እንዳሉ፣ እንዲሁም አፈጻጸማቸው ከሕግና ከተዘረጋው አሠራር ውጪ መሆናቸውን ሪፖርቱ ያሳያል ብሏል፡፡

የፌዴራል ዋና ኦዲተር ወ/ሮ መሠረት ዳምጤ ባቀረበቡት ሪፖርት የ171 የፌዴራል መንግሥት ባለበጀት መሥሪያ ቤቶች የኦዲት አስተያየት የቀረበ ሲሆን፣ ስድስት መሥሪያ ቤቶችና አራት የገቢዎችና የጉምሩክ መሥሪያ ቤቶች በወቅታዊ የፀጥታ ችግርና ሒሳብ በወቅቱ ባለማዘጋታቸው ሪፖርታቸው አልቀረበም፡፡

በተደረገው ኦዲት ከታዩ ዋና ዋና ግኝቶች የጥሬ ገንዘብ ጉድለት አንዱ ሲሆን፣ ከዚህ አኳያ በጋምቤላና በደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲዎች በድምሩ ከ1.5 ሚሊዮን ብር በላይ የጥሬ ገንዘብ ጉድለት መገኘቱ ታውቋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም በሐዋሳ፣ በሚዛን ቴፒ፣ እንዲሁም በቀብሪ ደሃር ዩኒቨርሲቲዎች በድምሩ ከአንድ ሚሊዮን ብር በላይ በክፍያ መመርያ ከተወሰነው የገንዘብ መጠን በላይ በጥሬ ገንዘብ ወይም በቼክ ወጪ የተደረገ ሒሳብ መገኘቱ ሪፖርት ተደርጓል፡፡

በበጀት ዓመቱ መጨረሻ ባለ በጀት መሥሪያ ቤቶች ያልተጠቀሙበትን ጥሬ ገንዘብና በባንክ የሚገኝ ገንዘብ፣ ለገንዘብ ሚኒስቴር ፈሰስ እንዲያደርጉ ቢጠበቅም፣ በወራቤ ኮምፕርሄንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ለረዥም ዓመታት ፈሰስ ሳይደረግ በባንክ ውስጥ የተጠራቀመ 87.9 ሚሊዮን ብር ገቢ ሒሳብ መገኘቱን የዋና ኦዲተር ሪፖርት አመላክቷል፡፡

በ133 መሥሪያ ቤቶችና በ26 ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቶች በሰነድ ሒሳብ በወቅቱ 13.1 ቢሊዮን ብር አለመወራረዱን፣ በአራት መሥሪያ ቤቶች ደግሞ 10.1 ሚሊዮን ብር ከሥራ ተቋራጮች የሚፈለግ ያልተሰበሰበ ወይም ያልተወራረደ ቅድሚያ ክፍያ መገኘቱ ተገልጿል፡፡

የጤና ሚኒስቴር፣ የብሔራዊ አደጋ ሥጋትና ሥራ አመራር ኮሚሽን፣ የቀድሞዎቹ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር፣ የውኃ ልማት ፈንድ ጽሕፈት ቤት፣ እንዲሁም የባህር ዳርና የጂግጂጋ ዩኒቨርሲቲዎች በወቅቱ ያልተወራረደ ውዝፍ ተሰብሳቢ ሒሳብ ከተገኘባቸው ተቋማት ተጠቃሾቹ መሆናቸውን ሪፖርቱ አስታውቋል፡፡

ዘጠኝ መሥሪያ ቤቶች 175.4 ሚሊዮን ብር የገቢ ሒሳብ ሪፖርት ሳያካትቱ የተገኙ መሆናቸውን፣ በ41 መሥሪያ ቤቶችና በአንድ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት 139.7 ሚሊዮን ብር የተሟላ ማስረጃ ሳይቀርብ በወጪ መመዝገቡ ተገልጿል፡፡

የዋና ኦዲተር ሪፖርት እንደሚያሳየው በአጠቃላይ ከ583.8 ሚሊዮን ብር በላይ የመንግሥት የግዥ አዋጅ፣ ደንብና መመርያ ያልተከተለ ግዥ ተፈጽሟል፡፡ ይህንን ከፈጸሙ መሥሪያ ቤቶች መካከል የሰላም ሚኒስቴር፣ የባህር ዳር፣ የጂንካ፣ የወላይታ ሶዶና የቡሌ ሆራ ዩኒቨርሲቲዎች ተጠቃሾቹ ናቸው፡፡

በኢትዮ ኢንጂነሪንግ ግሩፕ ሥር የሚገኘው የአዳማ ማሽነሪ ማምረቻ ከ2003 እስከ 2007 ዓ.ም. በወቅቱ በነበረው የምንዛሪ ዋጋ ከ4.8 ቢሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ የግብርና ማሽነሪ ግዥዎች የፈጸመ ቢሆንም፣ እስከ የካቲት 2014 ዓ.ም. ድረስ ከ5,825 በላይ የሚሆኑት አገልግሎት መስጠት በማይችሉበት ሁኔታ ሳይሸጡ ተከማችተው መገኘታቸው ለምክር ቤት አባላት በሪፖርቱ ተገልጿል፡፡

ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት የኮንስትራክሽን ሥራዎች ኮርፖሬሽን ከፕሮጀክት ግንባታ አፈጻጸም ጋር በተገናኘ ከፍተኛ ክፍተት እንደተገኘበት፣ ለአብነትም የተለያዩ ሥራዎችን ያከናወነበትን ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ መሰብሰብ አልቻለም ሲል አስታውቋል፡፡

በምክር ቤቱ፣ በአስፈጻሚ አካላትና በፌዴራል ዋና ኦዲተር ትኩረት ሊያገኙ የሚገኙ አንኳር ሐሶቦችን ቋሚ ኮሚቴው ያቀረበ ሲሆን፣ በቀረበው የኦዲት ግኝት መሠረት ስማቸው የተጠቀሱትም ሆነ ያልተጠቀሱ መሥሪያ ቤቶች በደረሳቸው የዋና ኦዲተር ሪፖርት መሠረት የማስተካከያ ዕርምጃ እየወሰዱ በየሦስት ወሩ ለዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤትና ተጠሪ ለሆኑባቸው ተቋማት ማሳወቅ ይገባቸዋል ተብሏል፡፡

በፌዴራል ዋና ኦዲተር በሚቀርቡ ተከታታይ ሪፖርቶች በአንድ የምርጫ ዘመን ለሦስት ጊዜያት አስተያየት መስጠት ያልተቻለባቸው መሥሪያ ቤቶችና የጎላ ችግር ያለባቸው ሆነው በመገኘታቸው፣ ተቀባይነት የሚሳያጣ አስተያየት የተሰጠባቸውን መሥሪያ ቤቶችን የመሩ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ለመንግሥት የሥራ ኃላፊነት ብቁ እንዳይሆኑ ቋሚ ኮሚቴው አስሳቧል፡፡

ከዚህ ባሻገር የኦዲት ጥራትና ተቀባይነት ለማሳደግ እንዲቻል ለኦዲተሮች የደኅንንት ከለላ እንዲደረግላቸው፣ እንዲሁም በኦዲት ሥራ ተሰማርተው የሥነ ምግባር ችግር ያለባቸው ስለመሆኑ ሥልጣን በተሰጠው አካል ሲረጋገጥ፣ በየትኛውም የመንግሥት መሥሪያ ቤት ውስጥ እንዳይቀጠሩ ገደብ ይደረግ ዘንድ ተጠይቋል፡፡

ዶ/ር ደሳለኝ ጫኔ
ዶ/ር ደሳለኝ ጫኔ

በተያያዘም የምክር ቤቱ አንደኛ ዓመት 14ኛ መደበኛ ስብሰባ ቃለ ጉባዔ ከመፅደቁ በፊት የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል ደሳለኝ ጫኔ (ዶ/ር)፣ የአብን የምክር ቤት አባላት እንዲያዝላቸው የሚገባ ቀዳሚ አጀንዳ እንዳለ ጥያቄ ቢያቀርቡም፣ አፈ ጉባዔ ታገሰ ጫፎ ባልተያዘ አጀንዳ ላይ ውይይት እንደማይደረግ ተናግረዋል፡፡

ከአቶ ክርስቲያን ታደለ በስተቀር በምክር ቤቱ የአብን ተወካዮች ስብሰባውን አቋርጠው ወጥተዋል፡፡ ደሳለኝ (ዶ/ር) በማኅበራዊ የትስስር ገጻቸው፣ ‹‹በወለጋና በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች በሚኖሩ አማራዎች ላይ እየተፈጸመ ያለውን ጅምላ ግድያ፣ የዘር ማፅዳትና ፍጅት ምክር ቤቱ ቀዳሚ አጀንዳው አድርጎ እንዲወያይበት አጀንዳው እንዲያዝ ብንጠይቅም፣ የምክር ቤቱ አፈ ጉባዔ በመከልከላቸውና አፈና ስለተፈጸመብን ስብሰባውን አቋርጠን ለመውጣት ተገደናል፤›› ብለዋል።

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -