በምሥራቅ ወለጋ በቱሉ ካፒ የሚገኘውን የወርቅ ክምችት ለማወጣት ፈቃድ የተሰጠው የብሪታኒያው ከፊ ጎልድና በኦጋዴን የተገኘውን የተፈጥሮ ጋዝ ለማልማት ፈቃድ የተሰጠው የቻይናው ፖሊ ጂሲኤል ኩባንያዎችን ጨምሮ ከ900 በላይ ድርጅቶች የማዕድን ፍለጋ፣ ማምረትና ኤክስፖርት ማድረግ ፈቃድ ተሰረዘ።
የማዕድን ሚኒስቴር በምዕራብ ኦሮሚያ በቱሉ ካፒ የተገኘውን የወርቅ ክምችት አውጥቶ ለገበያ እንዲያቀርብ ፈቃድ ከሰጠው የብሪታኒያው ኩባንያና በሶማሌ ክልል በኦጋዴን ዞን የተገኘውን የተፈጥሮ ጋዝ እንዲያለማ ፈቃድ ከሰጠው የቻይናው ፖሊ ጂሲኤል ኩባንያ በተጨማሪ፣ የጂምስቶን፣ የታንታለም ማዕድናትን የማምረት እንዲሁም የተመረቱ ማዕድናትን ኤክስፖርት የማድረግ ፈቃድ የተሰጣቸው የአገር ወስጥ ኩባንያዎችን ፈቃድ እንደተሰረዘ ሪፖርተር ከታማኝ ምንጮቹ አረጋግጧል።
ለአብነት ያህልም የጂምስቶን ማዕድን የማምረትና ኤክስፖርት የማድረግ ፈቃድ የተሰጣቸው 591 የአገር ውስጥ ኩባንያዎች ፈቃድ መሰረዙን ሪፖርተር ከምንጮቹ አረጋግጧል። አብዛኞቹ ኩባንያዎች የማዕድን ፈቃድ ካወጡ በኋላ ተግባራዊ እንቅስቃሴ እያደረጉ ባለመሆናቸውና ማዕድን ለማውጣት የተሰጣቸውን ቦታ እንኳ አይተው የማያውቁ በመኖራቸው፣ ፈቃዳቸውን በመንጠቅ ለእውነተኛ አልሚዎች ለማስተላለፍ ሲባል መወሰኑን አንድ የማዕድን ሚኒስቴር ከፍተኛ የሥራ ኃላፊ ለሪፖርተር ተናግረዋል።
የማዕድን ሚኒስቴር በተለይም በኦጋዴን የተገኘውን የተረጋገጠ የተፈጥሮ ጋዝና በቱሉ ካፒ የሚገኘውን ከፍተኛ የተረጋገጠ የወርቅ ክምችት ለማልማት ፈቃድ ተሰጥቷቸው፣ ልማቱን ያጓተቱን የብሪታኒያና የቻይና ኩባንያዎች ፈቃድ በመሰረዝ ቁርጠኛ ለሆኑና የገንዘብም ሆነ የቴክኒክ አቅሙ ላላቸው ኩባንያዎች ለመስጠት ማቀዱንም ሪፖርተር ከሚኒስቴሩ ከፍተኛ ባለሥልጣናት ለማወቅ ችሏል።
የማዕድን ሚኒስቴር የብሪታኒያውን ከፊ ጎልድ (የእህት ድርጅቱን ቱሉ ካፒ ጎልድ ማይኒንግ) እና በኦጋዴን የተፈጥሮ ጋዝን የማልማት ፈቃድ የተሰጠውን የቻይናው ፖሊ ጂሲ ኤል ወደ ምርት ሒደት እንዲገቡ ተደጋጋሚ ማስጠንቀቂያ በመስጠት ለረዥም ጊዜ ጉዳዩን ሲያስታምም እንደነበር ሪፖርተር በተደጋጋሚ መዘገቡ ይታወሳል።
በቱሉ ካፒ የተገኘውን የወርቅ ክምችት ለማውጣት ከሰባት ዓመት በፊት ፈቃድ የወሰደው ከፊ ጎልድ ፕሮጀክቱን ለመጀመር በቂ የፋይናንስ አቅም እንደሌለው የማዕድን ሚኒስቴር የሚያምን ሲሆን፣ ኩባንያው በበኩሉ በፕሮጀክቱ አካባቢ ያለው የፀጥታ ችግር አስፈላጊውን ፋይናንስ ከአበዳሪዎች እንዳያገኝ እክል እንደሆነበት ይገልጻል።
ይህንን አለመግባባት ለመፍታት የማዕድን ሚኒስቴርና የኩባንያው አመራሮች ያለፈው ጥር 30 ቀን 2014 ዓ.ም. ተገናኝተው ምክክር ያካሄዱ ሲሆን፣ ይህንንም ተከትሎ የማዕድን ሚኒስቴር ለስድስት ወራት የሚቆይ ተጨማሪ የጊዜ ማራዘሚያ ለኩባንያው እንደፈቀደ ይታወቃል።
በዚህም መሠረት ከየካቲት 1 ቀን 2014 ዓ.ም. አንስቶ እስከ ሐምሌ 1 ቀን 2014 ዓ.ም. ድረስ የሚቆይ የስድስት ወራት የጊዜ ማራዘሚያ ተፈቅዶለት የነበረ ቢሆንም ኩባንያው በተፈቀደለት ጊዜ ውስጥ ያሳየው ተጨባጭ ነገር ባለመኖሩ ፈቃዱ መሰረዙን የሚኒስቴሩ ባለሥልጣን ገልጸዋል።
በተመሳሳይ፣ በሶማሌ ክልል ኦጋዴን ዞን የተገኘውን የተፈጥሮ ጋዝ ለማውጣት ፈቃድ የተሰጠው የቻይናው ኩባንያ ፖሊ ጂሲኤል ወደ ምርት ሒደት መግባት ባለመቻሉ ተደጋጋሚ ማስጠንቀቂያ ሲሰጠው ቆይቷል።
ከጥቂት ወራት በፊት በማዕድን ሚኒስትሩ ተፈርሞ ለፖሊ ጂሲኤል ኩባንያ የተላከው የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ ደብዳቤ በሶማሌ ክልል የተገኘውን የተፈጥሮ ጋዝ ለማምረት ከሚያስፈልገው አጠቃላይ የኢንቨስትመንት ካፒታል ውስጥ 30 በመቶውን (1.26 ቢሊዮን ዶላር) አስከ ሰኔ 23 ቀን 2014 ዓ.ም. ድረስ በብሔራዊ ባንክ እንዲያስመዘግብና ቀሪውን የኢንቨስትመንት ካፒታል ኩባንያው በገለጸው መልኩ በብድር ስለማግኘቱ ማስተማመኛ እንዲያቀርብ የሚል ነበር።
ኩባንያው በተሰጠው የጊዜ ገደብ ውስጥ የተባለውን ባለመፈጸሙ በኦጋዴን ዞን በሚገኙ አራት የተፈጥሮ ጋዝ ማምረቻ ቦታዎች ላይ የተሰጠው የማምረት ፈቃድ እንደተሰረዘ ለማወቅ ትችሏል። የተፈጥሮ ጋዙ በሞሮኮ ባለሀብት በድሬዳዋ ከተማ ሊገነባ ታስቦ ለነበረው ማዳበሪያ ፋብሪካ አንደኛው ግብዓት ሲሆን፣ ይህ ግብዓት በወቅቱ ባለመድረሱ ምክንያት ይገነባል የተባለው የማዳበሪያ ፋብሪካ ተስተጓጉሏል። በአሁኑ ወቀት የተፈጥሮ ጋዙን የሚያመርት ሌላ የውጭ ኩባንያ እየተፈለገ ሲሆን በዚህ ዘርፍ የተሰማራ አንድ የቱርክ ኩባንያ በኡጋዴን ያለውን የተፈጥሮ ጋዝ ክምችት ቦታ ባለፈው ሳምንት መጎብኘቱ ይታወሳል።
የማዕድን ሚኒስቴር በወሰደው በእነዚህ ዕርምጃዎች ላይ ሰሞኑን ይፋዊ መግለጫ እንደሚሰጥ ምንጫችን ጨምረው ገልጸዋል።