የዛሬ 32 ዓመት በወርኃ ሚያዝያ 1982 ዓ.ም. አራት ኪሎ የሚገኘው ፖስታ ቤት ጎራ እላለሁ፡፡ በወቅቱ ከፖስታ ቤቱ በተከራየሁት ሳጥን የመጣልኝ መልዕክት ካለ በማለት ነበር እዚያ የተገኘሁት፡፡ የመልዕክት መቀበያ ሳጥኔን ስከፍት አንድ ነጭ ፖስታ ውስጡ አለ፡፡ የላኪው ስም ብቻ የሠፈረበት ፖስታ የእኔን ስምና ሙሉ አድራሻ ይዟል፡፡ ፖስታውን ካወጣሁ በኋላ ከፖስታ ቤቱ አጠገብ የነበረው ‘ጆሊ ባር’ በረንዳ ላይ ጥግ ይዤ ተቀመጥኩ፡፡ አስተናጋጁ ቡና እንዲያመጣልኝ አዝዤ ፖስታውን ከፍቼ ውስጡ ያለውን አንድ ገጽ ወረቀት አወጣሁ፡፡ ልቅም ባለ በሚያምር የእጅ ጽሑፍ በመጻፉ ለንባብ ይጋብዛል፡፡ ማንበብ ጀመርኩ፡፡
‹‹ለተወዳጁ ሰለሞን አየለ! ሰላም ላንተ ይሁን፡፡ ይህንን ደብዳቤ የምጽፍልህ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሠራተኛ ስሆን፣ የሥራ መደቤም የደንበኞች አግልግሎት ነው፡፡ በምሽቱ የትምህርት ፕሮግራም በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ኢኮኖሚክስ እማራለሁ፡፡ የምኖረው ፒያሳ አደባባይ ፕላዛ የሚባለው ሆስቴል ውስጥ ነው፡፡ የወር ደመወዜም 460 ብር ነው፡፡ ዕድሜዬ ደግሞ 26 ደርሷል፡፡ አንተን የማውቅህ በደንበኝነት እኛ ቅርንጫፍ ስትመጣ ነው፡፡ በምን እንደሆነ አላውቅም ትዳር መሥርተን ብንኖር ደስ ይለኛል፡፡ ለማንኛውም ከታች በሠፈረው አድራሻ ጻፍልኝና ሐሳብህን ልወቅ፡፡ የዓይን አፍቃሪህ ሰ.ሙ.፡፡ በዓይነ ሥጋ ለመገናኘት ያብቃን፤›› የሚለውን ጽሑፍ ሳነብ በአንድ በኩል ተገረምኩ፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ እኔ በማላውቃት ሴት እንዲህ ዓይነት የፍቅር ግብዣ ሲቀርብልኝ ደስ አለኝ፡፡
ከሥራ እንደወጣሁ በፍጥነት አምስት ኪሎ አካባቢ ወደሚገኘው ቤቴ አመራሁ፡፡ ከሰዓት በኋላውን በሚገባ በማሰላሰል የያዝኳቸውን ዋና ዋና ነጥቦች አደራጅቼ ስለነበር፣ እኔም ጽሑፌን እየቀሸርኩ በደስታና በፍቅር የታጀቡ ቃላት የተሞሉበት ሁለት ገጽ ደብዳቤ ጻፍኩ፡፡ እንደማይነጋ የለም በጠዋት ተነስቼ አራት ኪሎ ፖስታ ቤት ቴምብር አስለጥፌ በጥንቃቄ የመልዕክት ማጠራቀሚያው ውስጥ አስገባሁ፡፡ መልሱን እየተንቆራጠጥኩ መጠበቅ ጀመርኩ፡፡ አራት ኪሎ ሥላሴ ቅርንጫፍ ወይም ፒያሳ አራዳ ጊዮርጊስ ቅርንጫፍ በደንበኝነት እመላለስ ስለነበር፣ የትኛው ዘንድ ትሆን በማለት በቀን ሁለቴ ቅርንጫፎቹን መጎብኘት ሥራዬ ሆነ፡፡ መልስ ስጠባበቅ ቀናት አልፈው ሳምንታት፣ ሳምንታት አልፈው ወራት፣ ወራት አልፈው ዓመቱ ነጎደ፡፡ በዚህ መሀል በወርኃ ግንቦት 1983 ዓ.ም. ኢሕአዴግ አዲስ አበባን ተቆጣጠረ፡፡
ያንን መላ ህዋሳቴን የተቆጣጠረ ደብዳቤ ልክ እንደ ስጦታ ዕቃ በነጋ በጠባ እያየሁ ስብሰለሰል ብኖርምና ምንም ምላሽ ቢጠፋም፣ እኔ ግን ለአሥር ያህል ጊዜያት ደብዳቤ መጻፌን ባልናገር ሐሰተኛ ያደርገኛል፡፡ በሁለቱም ቅርንጫፎች ‹‹ሰ.ሙ.›› በሚል ምኅፃረ ቃል የሚጠሩ ሴት ሠራተኞች መኖራቸውን ለማወቅ ከፍተኛ ጥረት ባደርግም አልተሳካልኝም፡፡ በዚህ መሀል በ1985 ዓ.ም. ስኮላርሽፕ አግኝቼ እንግሊዝ አገር ሊድስ የሚባል ከተማ ሄድኩ፡፡ ከሊድስ ዩኒቨርሲቲ የማስተርስ ዲግሪዬን ይዤ በተመለስኩ በዓመቱ የአሁኗን ባለቤቴን ተዋውቄ፣ አዲስ ሕይወት ለመጀመር በ1989 ዓ.ም. ትዳር መሠረትኩ፡፡ ሦስት ልጆችም አፈራን፡፡ ይህ በዚህ እያለ የዛሬ ዓመት በሚያዝያ ወር የፋሲካ በዓል ሰሞን በኢሜይል አንድ መልዕክት ደረሰኝ፡፡ የላኪው አድራሻ ላይ ‹‹S.M›› ሲል፣ የመልዕክቱ የውስጠኛው ሰሌዳ ላይ ‹‹Message from Distant Lover›› ይላል፡፡ የሆነ ነገር ውስጤን ነዘረው፡፡
መልዕክቱን ከፍቼ ማንበብ ጀመርኩ፡፡ ‹‹ለተወዳጁ ሰለሞን አየለ፡፡ እንደምን አለህልኝ፡፡ ምንም እንኳን ከሃያ ዓመታት በላይ ቢሆነውም እንደማትረሳኝ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ በእርግጥ ባለትዳርና የሦስት ልጆች አባት መሆንህን ባውቅም፣ አሁንም ድረስ ውስጤ የተዳፈነው ፍቅር እንድረሳህ አያደርገኝም፡፡ ግን ምን ያደርጋል? በዚያ ያልታሰበ አጋጣሚ ያንን ደብዳቤ ጽፌልህ ካነሳሳሁህ በኋላ፣ በተከታታይ ለጻፍክልኝ ደብዳቤዎች ምላሽ መስጠት አለመቻሌ አሁንም ድረስ ይቆጨኛል፡፡ ምን ይደረግ ብለህ ነው? በወቅቱ ጦር ሜዳ የነበረው ኮሎኔል አባቴ በደርግ ተረሽኖ ሐዘን ላይ ተቀምጠን ሳለ፣ በወንድሞቼ አነሳሽነት ድንገት ሳይታሰብ በሞያሌ አድርገን ኬንያ ገባን፡፡ ኬንያ ለወራት ከቆየን በኋላ ወደ ካናዳ ሄደን ሕይወትን እንደገና ለመጀመር ላይ ታች ስንል ዓመታት ነጎዱ፡፡ ሥራ፣ ትምህርት፣ አገር መላመድ፣ ማኅበረሰብ መደባለቅ ሲባል ሌላ ዓለም ውስጥ ተገባ…›› የሚሉ ሐሳቦች ያሉበት ጽሑፍ ለደቂቃዎች አነበብኩ፡፡ በመጨረሻም ‹‹የጥንቷ የርቀት አፍቃሪህ ሰ.ሙ. (ዶ/ር)›› ብሎ ተጠቃለለ፡፡
እሷ እንዳለችው የልጆች አባትና ባለትዳር ብሆንም ይህንን ጉድ ለባለቤቴ አሳየሁዋት፡፡ ከበፊት ጀምሮ ታሪኳን ነግሬያት ስለነበር እሷም በጣም ተገረመች፡፡ ባለቤቴ በጣም ጥሩ ሰው ስለሆነች መልስ እንድጽፍላት አበረታታችኝ፡፡ በኋላ ከኢሜይል ምልልሳችን የተረዳሁት ካናዳ ውስጥ የአንድ ኮሌጅ መምህር ስትሆን፣ ዕድሜዋም 58 ደርሷል፡፡ ትዳር ግን የላትም፡፡ እኔ በፖስታ ሳጥን መገልገል ካቆምኩ 21 ዓመታት አልፈዋል፡፡ የምጠቀምበትን የኢሜይል አድራሻ ከየት አገኘች የሚለው ደግሞ አሳሰበኝ፡፡ እሷ እንደነገረችኝ ከሆነ ግን እዚህ አገር ባለች ጓደኛዋ አማካይነት ስለእኔ ብዙ ታውቃለች፡፡ ከእነዚያ ሁሉ ዓመታት በኋላ እንደ አዲስ መጥታ በትዳሬ ጣልቃ መግባትም አትፈልግም፡፡ በቀደም ዕለት ለሁለት ልጆቼ ካናዳ ስኮላርሺፕ እንዳገኘችና ይህንንም የምታደርገው ያኔ ያንከራተተኝችን ለመካስ እንደሆነ ስትነግረኝ በጣም ገረመኝ፡፡ በጣም ደነገጥኩ፡፡ ባለቤቴ ይኼንን የምሥራች ስትሰማ፣ ‹‹‘ስትፈልግ ያጣኸውን ሲፈልግህ ታገኘዋለህ’ የሚባለው አገራዊ ብሒል አሁን ሠራ፤›› ስትለኝ የባሰ ደነገጥኩ፡፡ ‹‹የአንተ ልጆች ለእኔም ልጆቼ ናቸው፤›› በማለት እንደገና ዶ/ር ሰ.ሙ. ልጆቹ ለመጪው የትምህርት ዘመን እንዲዘጋጁ ስትነግረኝ ግራ ገባኝ፡፡ አንዳንዴ ቁጭ ብዬ ሳስበው የሕይወት ዕንቆቅልሽ ከመብዛቱ የተነሳ በምን እንደምንደሰትና እንደምንደነግጥ ግራ ይገባኛል፡፡ ዓለም ማለት አንዱ ገጽታው ይኼ ይሆን?
(ሰለሞን አየለ፣ ከጃክሮስ)