በአዲስ ገመቹ
የ1952 ዓ.ም. የኢትዮጵያ ንግድ ሕግ ሥራ ላይ ከዋለ ስድስት አሥርት ዓመታት በላይ ያስቆጠረ ከመሆኑ ጋር ታያይዞ በእነዚህ ዓመታት የተለወጡ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ከኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ጋር የተያያዙ ሁነቶችን በቀድሞ ሕግ በአግባቡ ማስተናገድ አስቸጋሪ በመሆኑ፣ የቀድሞ ንግድ ካሉበት ክፍተቶች አንፃር ዓለም ባንክ በየዓመቱ የሚሠራው የንግድ አመቺነት (Ease of Business Doing) በሚመለከት በሚሰጠው ምዘና ኢትዮጵያ ዝቅተኛ ውጤት ስታገኝ መቆየቷ፣ እንዲሁም የንግድ ሕጉን በመሻሻል የኢኮኖሚ እንቅስቃሴን ለማስፋፋት እንዲሁም ኢንቨስትመንትን ለማበረታት የታሰበ በመሆኑ፣ የንግድ ሕጉ አዋጅ ቁጥር 1243/2013 ሆኖ ተሻሽሎ ወጥቷል፡፡
የታሰበለትን ዓላማ ለማሳካት የንግድ ሕጉ የተለያዩ ለውጦችን ይዞ ቀርቧል፡፡ ይሄውም አስቀድሞ ከነበሩት የንግድ ተቋማት ውስጥ ለምሳሌ ተራ የሽርክና ማኅበርን ቀሪ በማድረግ ሌሎች አዳዲስ የንግድ ተቋማት ዓይነቶችን አስተዋውቋል፡፡ ለአብነት ያህል ባለ አንድ አባል ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር (One Man Company) እና ኃላፊነቱ የተወሰነ የሽርክና ማኅበር (Limited Liablity Partnership) ይጠቀሳሉ፡፡ ከዚህ በተጨማሪ አዲሱ የንግድ ሕግ በኩባንያዎች ውስጥ አነስተኛ ድርሻ ይዘው የሚገቡትን ባለሀብቶች የተሻለ ጥበቃ እንዲያገኙ አዳዲስ ድንጋጌዎች አካቷል፡፡ የአክሲዮን ማኅበራት ተቆጣጣሪ ቦርድ (Superviosry Board) ሊኖራቸው የሚችል መሆኑ፣ አስፈላጊ ሆኖ ካገኙት ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ሆነው የተደራጁ የንግድ ተቋማት የዳይሬክተሮች ቦርድ እንዲኖራቸው አማራጭ ማቅረብ፣ የአክሲዮን ማኅበር ሥራ አስኪያጅ የዳይሬክተሮች ቦርድ አባል ሆኖ መመረጥ የሚችል ስለመሆኑ፣ ጠቅላላ ጉባዔም ሆነ የቦርድ ስብሰባ በኤሌክትሮኒክስ መንገድ ሊደረግ የሚችል ስለመሆኑ፣ በቀድሞ ንግድ ሕግ የአክሲዮን ማኅበራት የቦርድ ጸሐፊ በሚል ይታወቅ የነበረው የማኅበር ጸሐፊ በሚል መተካት፣ የመተዳደሪያ ደንብ ቀሪ መሆን፣ ከማኅበሩ ጋር ቅርበት ያላቸው ሰዎች መዝገብ የመያዝ አስፈላጊነት እንዲሁም የዳይሬክተሮች ቦርድ አባላት ከሚያስተዳድሩት ማኅበር በጠቅላላ ጉባዔ ካልተፈቀደ በስተቀር ብድር የማግኘት መብታቸው መገደብና የመሳሰሉት አዲዲስ ለውጦች ናቸው፡፡ እነዚህን ሁሉ ለውጦች ምንነትና ይዘት ለመዳሰስ ጊዜና ቦታ የማይፈቅድ በመሆኑ፣ በዚህ ጽሑፍ የዳይሬክተሮች ቦርድ አባላት ከሚያስተዳድሩት ማኅበር ስለሚወስዱት ብድር የሚመለከተውን ክልከላ ይዘትና ሰፋት ለመዳስስ እንሞክራለን፡፡
በአክሲዮን ማኅበር ውስጥ የዳይሬክተሮች ቦርድ አባላት ሚና
የዳይሬክተሮች ቦርድ አባላት የሚመረጡት በባለአክሲዮኖች እንደ መሆኑ መጠን፣ ዋና ዓላማና ተግባራቸው የባለአክሲዮኖችን ጥቅምና መብት ማስከበር ነው፡፡ በዚህም ሥራቸው የንግድ ማኅበሩ የተሻለ ቁመና ላይ እንዲገኝና ስኬታማ እንዲሆን የማኅበሩን የንግድ ሥራ በባላይነት ይቆጣጠራል፡፡ ጠቃሚ ውሳኔዎች እንዲተላለፉ፣ እንዲሁም የማኅበሩ አደጋ ተጋላጭነት ለመቀነስ የሚያስችሉ ተቋማዊ አሠራሮች የተዘረጉ መሆኑን ያረጋግጣል፡፡ በአጠቃላይ የዳይሬክተሮች ቦርድ አባላት በዋናነት የማኅበሩን የቢዝነስ ስትራቴጅ የመቅረፅና አፈጻጸሙን የመገምገም፣ ኦዲተሮችን የመሾምና ሥራቸውን መከታተል፣ የማኅበሩን ሥራ አመራር አባላት የመሾምና የመቆጣጠር እንዲሁም የማኅበሩን ሥራ አፈጻጸም የመገምገምና የመሳሰሉትን ተግባራት ያከናውናሉ፡፡
የዳሬክተሮች ቦርድ ሥራ ማኅበሩን በበላይነት የመቆጣጠር እንደ መሆኑ፣ ይህንኑ ሥራ በአግባቡ ለመከወን እንዲቻል ከማንኛውም ተፅዕኖ ነፃ (Independent) ሆነው በጥንቃቄ (Duty of Care) እና በታማኝነት (Duty of Loyalty) ሥራቸውን መፈጸም ያለባቸው ስለመሆኑ በጉዳዩ ዙሪያ የተጻፉ ምርምሮች ያመላክታሉ (Charles M.Elson & Chirstopher J. Gyves, The Enron Failure and Corporate Governance Reform)፡፡ የቦርድ አባላት ነፃ መሆን አለባቸው ሲባል የማኅበሩን አመራር ለመቆጣጠርና ሥራቸውን ለመከታተል በሚያስችል አስተዳደራዊ ነፃነት ለማግኘት የማኅበሩን የዕለት ተዕለት ሥራ ከሚመራው አካል በበቂ ርቀት (Arm’s Length) መገኘት ይጠበቅባቸዋል፡፡ በበቂ ርቀት መገኘት ማለት የዳይሬክተሮች ቦርድ አባላት ከማኅበሩ ጋር የሚኖራቸው የንግድ ወይም ሌላ ግንኙነት የዳይሬክተሮች ቦርድ አባላት ተፅዕኖ ሥር ሊከት የሚችል መሆን የለበትም፡፡ የዳይሬክተሮች ቦርድ አባላት በንግድ ሥራ አመራር በቂ ልምድ ያካበቱና ስኬታማነታቸው የተመሰከረላቸው እንኳን ቢሆኑ፣ ከአክሲዮን ማኅበሩ ጋር ያላቸው ቅርበት የተመጠነ ካልሆነ በስተቀር የአክሲዮን ማኅበሩን ወደ አደጋ ሊወስዱ የሚችሉ ምልክቶችን ለይተው ዕርምጃ ለመውሰድ አዳጋች ስለሚሆን ግንኙነቱ ጥንቃቄ የተሞላበት ሊሆን ይገባዋል፡፡ ከዚህ አንፃር በማኅበሩና በዳይሬክተሮች ቦርድ አባላት መካከል የሚደረጉ የንግድ ግንኙነቶች በጥንቃቄ ካልተያዙ በስተቀር፣ የጥቅም ግጭት በመፍጠር የማኅበሩን ህልውና ሊፈታተኑ የሚችሉ ሁነቶች ሊከሰቱ ይችላሉ፡፡
ሌላው የዳይሬክተሮች ቦርድ አባላት ሥራቸውን በጥንቃቄ መሥራት ለሥራቸው ስኬት ወሳኝ ይሆናል፡፡ በዚህ ግዴታቸው የዳይሬክተሮች ቦርድ አባላት ውሳኔ ሲያስተላልፉ ምክንያታዊ ትጋት ማድረግ ያለባቸው ሲሆን፣ ለዚህም ሲባል ለሚያስተላልፉት ውሳኔ በቂ መረጃ ያላቸው መሆኑንና መረጃውንም መርምሮ አስፈላጊውን ውሳኔ ለማስተላለፍ በቂ ጊዜ መውሰድ ይኖርባቸዋል፡፡
ከዚህ በተጨማሪ የዳይሬክተሮች ቦርድ አባላት ሥራቸውን በታማኝነት ማከናወን ይጠበቅባቸዋል፡፡ ከላይ ለመግለጽ እንደተሞከረው የዳይሬክተሮች ቦርድ የሚሠሩት ለማኅበሩና ለባለአክሲዮኖች ጥቅም ብቻ ሊሆን ይገባል፡፡ ይህም ማለት የዳይሬክተሮች ቦርድ በሥራቸው ሁሉ ከራሳቸው ጥቅም ይልቅ የባለአክሲዮኖችን ጥቅም ማስቀደም ያለባቸው መሆኑን፣ በሚያከናውኗቸው ተግባራት ሁሉ ከጥቅም ግጭት ነፃ በሆነ መልኩ ሥራቸውን ማከናወን እንዳለባቸው ይታወቃል፡፡ በተለይ ዳይሬክተሮች ራሳቸውን እንደ ግለሰብ ወክለው ከማኅበሩ ጋር የሚደርጉት ግንኙነት ከላይ ከተጠቀሱት መርሆች አንፃር መቃኘት ይኖርበታል፡፡ ይህንኑ ዓላማ ለማስፈጸም በሚመሰል አኳኃን አዲሱ የኢትዮጵያ ንግድ ሕግ ጠቅላላ ጉባዔ ካልፈቀደ በስተቀር፣ የዳይሬክተሮች ቦርድ አባላት ከሚያስተዳድሩት ማኅበር ብድር መበደር የማይችሉ ስለመሆኑ በአንቀጽ 307 ላይ ተመልክቷል፡፡ ሆኖም ይህ ክልከላ አዲስ እንደ መሆኑ መጠን ይዘቱና ስፋቱ ሁሉንም ዓይነት የንግድ ማኅበራት ይመለከታል ወይስ ለተወሰኑት ብቻ ነው? የሚለውን ከዚህ እንደሚከተለው ለማየት እንሞክራለን፡፡
የዳይሬክተሮች ቦርድ አባላት ከሚያስተዳድሩት ተቋም መበደር ይችላሉ?
በብዙ አገሮች የንግድ ማኅበራት ለሚያስተዳድሯቸው የቦርድ አባላት ብድር መስጠት ግልጽ የሕግ ክልከላ የተጣለበት ተግባር ሆኖ ቆይቷል (Jayne W. Barnard, Corporate Loans to Directors and Officers:Every Business Now a bank?)፡፡ የእንዲህ ዓይነቱ ገደብ ዋና ዓላማ የዳይሬክተሮች ቦርድ አባላት ከሚጠበቅባቸው የታማኝነት ግዴታ በተቃረነ አኳኃን የማኅበሩን ሀብት ለራሳቸው ጥቅም እንዳያውሉ፣ በዚህም ምክንያት የጥቅም ግጭት እንዳይፈጠር፣ ብሎም ሌሎች የንግድ ተግባራት ሊውል የሚችል የማኅበሩ ሀብት እንዳይመዘበር፣ በዚህም ምክንያት አነስተኛ ባለአክሲዮኖች ጥቅም እንዳይጎዳ በማሰብ ነው፡፡ ሆኖም የዳይሬክተሮች ቦርድ አባላት እንደ ማንኛውም ግለሰብ በግላቸው የተለያዩ የንግድ እንቅስቃሴዎች ላይ እንደ መሳተፋቸው መጠን፣ ብድር የሚፈልጉ በመሆኑና ከንግድ ሕጎች መዘመን (Modernization of Corporate Laws) ጋር ተያይዞ፣ እንዲሁም ብድር ለዳይሬክተሮች ቦርድ አባላት መስጠቱ የማኅበሩን የንግድ ዓላማ (To Serve Corporate Purpose) የሚያሳካ እስከሆነ ድረስ ከተወሰነ ገደብ ጋር የዳይሬክተሮች ቦርድ አባላት ከሚያስተዳድሩት ተቋማት ብድር እንዲወስዱ የሚፈቅዱ አገሮች አሉ፡፡
በዚህም መሠረት አንዳንድ አገሮች የባለአክሲዮኖች ጠቅላላ ጉባዔ የሚፈቅድ ከሆነ ወይም ደግሞ ሌሎች የቦርድ አባላት የሚፈቅዱ ከሆነ አንድ የዳይሬክተሮች ቦርድ አባል ከሚያስተዳድርው ማኅበር ብድር መውሰድ እንደሚችል ይደንግጋሉ፡፡ በእንዲህ ዓይነት ሁኔታ የዳይሬክተሮች ቦርድ አባላት ብድር ሲወስዱ የሚሰጠው ብድር፣ ማኅበሩን የሚጠቅም ወይም ደግሞ የማኅበሩን ጥቅም የማይጎዳ ስለመሆኑ ማረጋገጥ አስፈላጊ ነው፡፡ ሆኖም አንድ የዳይሬክተር ቦርድ አባል የሚወስደው ብድር ማኅበሩን ይጠቅማል ወይም ደግሞ የማኅበሩን ጥቅም አይጎዳም? የሚባለው በምን ዓይነት ሁኔታ ነው የሚለው ሊታይ ይገባል፡፡ አንድ ዳይሬክተር የሚወስደው ብድር ለማኅበሩ ይጠቅማል አይጠቅምም? የሚለውን እንዲወስን የቀረበለት የጠቅላላ ጉባዔ ወይም ደግሞ የዳይሬክተሮች ቦርድ ምን ዓይነት መሥፈርት ሊጠቀም ይገባል? ለእንዲህ ዓይነቱ ጉዳይ ግልጽ መሥፈርት ወይም መለኪያ ከሌለ ውሳኔ የሚሰጠው አካል በጉዳዩ ላይ ያለ ምንም መመርያ ውሳኔ እንዲሰጥ ከማድረጉም በላይ፣ ውሳኔውን የሚሰጡት የዳይሬክተሮች ቦርድ አባላት ከሆኑ ለራሳቸው የሚያደላ ውሳኔ የማስተላለፋቸው ዕድል የሰፋ ይሆናል፡፡ ይህ ከሆነ ደግሞ ብድሩ ለማኅበሩ ያለውን ጥቅም ምንነት ግልጽ የሆነ መሥፈርት ሳይቀመጥ ዳሬክተሮች ብድር እንዲወስዱ መፍቀድ ያለ ምንም መሥፈርት ብድር ከመፍቀድ የተለየ ውጤት የለውም፡፡
የንግድ ማኅበራት ብድር በሚሰጡበት ወቅት ብድሩ የማኅበሩን ዓላማ ያሳካል ወይስ አያሳካም? የሚለው አንዱ መሥፈርት ስለመሆኑ በተለየዩ ጥናታዊ ጽሑፎች ላይ ሰፍሮ ይገኛል (Jayne W. Barnard, Corporate Loans to Directors and Officers: Every Business Now a bank, Gerald Ventin, Corporate Governance Lessons of Enron)፡፡ ከዚህ አንፃር ሲታይ ብድር መስጠቱ በዳይሬክተሮች ቦርድ ወይም በጠቅላላ ጉባዔ ምክንያታዊ ዕይታ ማኅበሩን የሚጠቅም ስለመሆኑ ውሳኔ ላይ ከተደረሰ በቂ መሥፈርት ነው ማለት ይቻላል፡፡ እዚህ ላይ የማኅበሩ ጥቅም ሲባል ቀጥተኛ ወይነም ኢቀጥተኛ ሊሆን ይችላል፡፡ ለምሳሌ አንድ የዳይሬክተሮች ቦርድ አባል ከሚያስተዳድረው ተቋም ብድር ማግኘት ለንግድ ማኅበሩ ያለው የባለቤትነት ስሜት፣ የሥራ ትጋትና ታማኝነት የሚጨምር በመሆኑ፣ እንዲሁም ከሌላ አበዳሪ ተቋም ብድር የሚፈልጉበትን ጊዜና ጉልበት በማስቀረት ሙሉ ትኩረታቸውን በሚያስተዳድሩት ተቋም ላይ እንዲሆን የሚያስችል በመሆኑ፣ በዚህ ምክንያት ማኅበሩ ቀጥተኛ ያልሆነ ጥቅም ያገኛል ሊባል ይችላል፡፡
ቀጥተኛ ጥቅም ሊባል የሚችለው ደግሞ ማኅበሩን ለሚያስተዳድሩት የቦርድ አባላት የሚሰጠው ብድር ለማኅበሩ ጠቃሚ ነው የሚባለው የአክሲዮን የገበያ ዋጋን ከፍ የሚያደርግ ከሆነ፣ የማኅበሩን የገበያ ድርሻ የሚያሻሽል ከሆነ፣ የማኅበሩን ውጤታማነት የሚያሳድግ፣ በብድሩ ምክንያት የማኅበሩ ወሳኝ ደንበኞች ጋር ያለ ግንኙነት የሚጎልበት/የማይዳከም ከሆነ ወይም የማኅበሩን ገጽታ የሚያሳድግ ከሆነ ለዳይሬክተሮች ቦርድ አባላት የሚሰጥ ብድር ለማኅበሩ ጠቃሚ ነው ተብሎ ሊወሰድ ይችላል (Jayne W. Barnard, Corporate Loans to Directors and Officers: Every Business Now a bank)፡፡
በተለይ ከባንክ ሥራዎች ውጪ የተሰማራ የንግድ ማኅበር ብድር መስጠት ዋናው ሥራው (Chartered Power) ባለመሆኑ፣ ብድር ለዳይሬክተሮች ቦርድ አባላት ሲፈቅድ እጀግ ውሱን በሆኑ አጋጣሚዎች ብቻ መሆን አለበት፡፡ ምክንያቱም ሙሉ ትኩረትና ሀብቱ በዋናው ሥራ ላይ መዋል ያለበት በመሆኑ ጥንቃቄና ኃላፊነት የተሞላበት የተጠና ውሳኔ ሊያሳልፍ ግድ ይለዋል፡፡ በመሆኑም ማኅበሩ ለዳይሬክተሮች ቦርድ አባላት የሚሰጠው ብድር ዋናውን ዓላማ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የሚደግፍ ሊሆን ይገባል፡፡
በጠቅላላው የዳሬክተሮች ቦርድን በሚመለከት ብድር ይህን ካልን በቅርቡ ፀድቆ ሥራ ላይ የዋለው የንግድ ሕግ ለዳይሬክተሮች ቦርድ አባላት ስለሚሰጥ ብድር ምን ይላል የሚለውን እንመልከት፡፡
ለዳይሬክተሮች ቦርድ የሚሰጥ ብድር በኢትዮጵያ ንግድ ሕግ
በንግድ ሕጉ አንቀጽ 307(1) መሠረት የባለአክሲዮኖች ጠቅላላ ጉባዔ ካልፈቀደ በስተቀር፣ አንድ አክሲዮን ማኅበር ለማኅበሩ የቦርድ አባላት ብድር መስጠት እንደማይችል በግልጽ ተደንግጎ ይገኛል፡፡ ከዚህ ለመረዳት እንደሚቻለው የኢትዮጵያ ንግድ ሕግ የዳይሬክተሮች ቦርድ አባላት ከሚያስተዳድሩት ማኅበር ብድር እንዳይወስዱ ሙሉ ለሙሉ አልተከለከሉም፡፡ ሆኖም ብድር ለማግኘት በቅድሚያ ከጠቅላላ ጉባዔ ፈቃድ ማግኘት ይጠይቃል፡፡ ይህም ማለት የንግድ ማኅበሩ ጠቅላላ ጉባዔ በሚያካሄድበት ወቅት ወይም በሌላ አመቺ ጊዜ ጉባዔ አካሂዶ ብድር ለመስጠት ካልተስማማ በስተቀር፣ የዳይሬክተሮች ቦርድ አባላት ብድር ማግኘት አይችሉም፡፡ እዚህ ላይ እንደ ጥያቄ ሊነሳ የሚችለው የታሰበው/የቀረበው የብድር ጥያቄ በመጠን ተለይቶ በየጊዜው ለጠቅላላ ጉባዔ መቅረብ አለበት? ወይስ አንድ ጊዜ ብቻ ብድር ለዳይሬክተሮች ቦርድ አባላት ለመስጠት ፈቃድ ከጠቅላላ ጉባዔው ማግኘት በቂ ነው? የሚለው ነው፡፡ ከላይ እንደተገለጸው ብድር ለዳይሬክተሮች ቦርድ የተፈቀደው በልዩ ሁኔታ ሲሆን፣ የጠቅላላ ጉባዔው ዕውቅናና ፈቃድ አስፈላጊ መሆኑን ዓይተናል፡፡ ከዚህ አንፃር የሕጉ ዓላማ በእያንዳንዱ ብድር ጥያቄ በቂ የሆነ ውይይትና ክርክር ተደርጎበት በመሆኑ፣ በደምሳሳው ለአንድ ጊዜ የቀረበ የብድር ጥያቄ የሕጉን ዓላማ ያሳካል ተብሎ አይታሰብም፡፡ ምክንያቱም የሕጉ ዋና ዓላማ ማኅበሩ ከተቋቋመለት ተግባር ውጪ የሚሠራው ነገር እንዳለ ታውቆ በቂ ቁጥጥር ሥርዓት መዝርጋት እንዲቻል ይመስላል፡፡ ስለሆነም ጠቅላላ ጉባዔው ስለቀረበው የብድር ጥያቄ ምንነትና ይዘት አውቆ እንዲወያይበት ዝርዝር ጉዳይ ቀርቦ ውሳኔ ሊሰጥበት ይገባል፡፡
በአንቀጽ 307(1) የተጣለው ገደብ ሁሉንም ዓይነት የንግድ ማኅበራት ይመለከታል?
እንግዲህ ንግድ ሕጉ ሲቀረፅ ሁሉን ዓይነት የንግድ ማኅበራት ታሳቢ ያደረገ እንደ መሆኑ መጠን፣ እያንዳንዱ የሕግ ድንጋጌ በየትኛውም ዓይነት የንግድ ሥራ ዘርፍ ላይ የተሰማሩ የአክሲዮን ማኅበራትን ያካትታል የሚል ክርክር ማቅረብ ይቻል ይሆናል፡፡ ነገር ግን ብድር ለዳይሬክተሮች ቦርድ መስጠትን በሚመለከት የተቀመጠው ገደብ መደበኛ ሥራቸው (Chartered Power) ብድር መሰጠት የሆኑ የንግድ ተቋማት፣ ማለትም እንደ ባንክ ያሉትን አይመለከትም የሚሉ አሉ፡፡ ይህ አቋም የባንኮች የዕለት ተዕለት ሥራ ብድር መስጠት እንደ መሆኑ፣ በየዕለቱ የሚሠራና በባንኩ የማኔጅመንት አባላት ሊከናወን የሚችልን ተግባር በዓመት አንድ ጊዜ ከበዛ ሁለት ጊዜ ለሚሰበሰብ ጠቅላላ ጉባዔ እንዲቀርብ መጠየቅ የማኅበሩን ሥራ ከማስተገጓጎል ባለፈ፣ አፈጻጸሙን አስቸጋሪ ይሆናል የሚል መነሻ ያለው ነው፡፡ ይልቁንም ሕጉ ታሳቢ ያደረገው መደበኛ ሥራቸው ከብድር ውጪ የሆኑ ማኅበራት ለዳይሬክተሮች ቦርድ አባላት ብድር ለመስጠት የሚችሉበትን ዕድል ላለመዝጋት ያለመና ይኸውም ሲፈጸም ሕግና ሥርዓት በተከተለ መልኩ እንዲከወን ያለመ ነው ማለት ይቻላል፡፡ ከንግድ ሕጉም ሆነ ከልምድ ለመረዳት እንደሚቻለው በአብዛኛው ለጠቅላላ ጉባዔ የሚቀርቡ አጀንዳዎች የማኅበሩ አጠቃላይ አስተዳደራዊ ሥራዎች ናቸው እንጂ፣ የዕለት ተዕለት ሥራ የሚመለከት አይደለም፡፡ በተጨማሪም የዳይሬክተሮች ቦርድ አባላት ከሚያስተዳድሩት ባንክ የሚወስዱትን ብድር በሚመለከት የብሔራዊ ባንክ መመርያዎች አስቀድመው በሥራ ላይ ያሉ በመሆኑ፣ ከላይ የተገለጸው የንግድ ሕጉ ድንጋጌ ለባንኮች ተግባራዊ ይሆናል ማለት አስቸጋሪ ይሆናል፡
ለምሳሌ የብሔራዊ ባንክ መመርያ ቁጥር SBB/53/2012 ከአንድ ማኅበር ጋር ግንኙነት ስላላቸው ሰዎች (Credit Exposure to Single and Related Counter Parties) ሊሰጥ የሚገባውን ከፍተኛ የብድር መጠን በተመለከተ የወጣው መመርያ፣ ለዚህ ጉዳይ አግባብነት ያለው ነው፡፡ በዚህ መመርያ አንቀጽ 3.7 መሠረት የዳይሬክተሮች ቦርድ አባላት ከማኅበሩ (ባንኩ) ጋር ግንኙነት ያላቸው ሰዎች ስለመሆናቸው ተመልክቷል፡፡ በተጨማሪም በዚህ መመርያ አንቀጽ 6.2 መሠረት ለአንድ የዳይሬክተሮች ቦርድ አባል ሊሰጥ የሚገባው ከፍተኛ የብድር መጠን ከማኅበሩ (ባንኩ) ዋና ገንዘብ 15 በመቶ በላይ መሆን የሌለበት ስለመሆኑ ተመልክቷል፡፡ በመሆኑም ከማኅበሩ (ባንኩ) ዋና ገንዘብ 15 በመቶ በላይ እስካልሆነ ድረስ የዳይሬክተሮች ቦርድ አባላት ከባንኩ እንደማንኛውም ደንበኛ ሆነው ብድር ለመውሰድ ይችላሉ (SBB/53/2012 አንቀጽ 6.4 ይመለከቷል)፡፡ ሆኖም ይህም ገደብ ሊሠራ የሚችለው የዳይሬክተሮች ቦርድ አባላት ከባንኩ ለሚወስዱት ብድር ከጥሬ ገንዘብ፣ ወይም የጥሬ ገንዘብ ምትክ የሆነ መያዣ ያላቀረቡ እንደሆነ ነው (SBB/53/2012 አንቀጽ 7 ይመለከቷል)፡፡ በሌላ አባባል የዳይሬክተሮች ቦርድ አባላት ለሚወስዱት ብድር የሚያቀርቡት መያዣ ጥሬ ገንዘብ ወይም የጥሬ ገንዘብ ምትክ የሆነ እንደሆነ፣ የዳይሬክተሮች ቦርድ አባላት ከሚያስተዳድሩት ባንክ ለሚወስዱት ብድር ያለ ገደብ ብድር ሊወስዱ ይችላሉ ማለት ነው፡፡ ሆኖም በብሔራዊ ባንክ መመርያ ቁጥር SBB/53/2012 አንቀጽ 10 መሠረት ከባንኩ ዋና ገንዘብ አሥር በመቶ በላይ ብድር የወሰዱ ሰዎች ስም ዝርዝር ለብሔራዊ ባንክ የሚላክ በመሆኑ፣ ብሔራዊ ባንክ በዚሁ መመርያ አንቀጽ 6.5 መሠረት ማንኛውንም ብድር በየትኛውም ጊዜ የማገድ ሥልጣን ያለው በመሆኑ፣ የዳይሬክተሮች ቦርድ አባላትም ሆነ ሌሎች ሰዎች የሚወስዱት ብድር ከቁቁጥር ውጪ ነው ሊባል አይችልም፡፡
በአጠቃላይ በንግድ ሕጉ አንቀጽ 307(1) የተቀመጠው የብድር ገደብ ባንኮችን የማይመለከትና ከባንኮች ውጪ ለሆኑ የንግድ ማኅበራት የተደነገገ ነው ማለት የሚቻል ቢሆንም፣ የባንኮች ዳይሬክተሮች ቦርድ አባላት ብድር ያለ ገደብ ከሚያስተዳድሩት ባንክ ይወስዳሉ ማለት አይደለም፡፡ ይልቁንም የባንኮች ዳይሬክቶሮች ቦርድ አባላት ከሚያስተዳድሩት ባንክ የሚወስዱት ብድር፣ ከላይ በተጠቀሰው የብሔራዊ ባንክ መመርያ መሠረት የሚገዛ ስለመሆኑ ሊታወቅ ይገባል፡፡
ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊው የሕግ ባለሙያ ሲሆኑ ጽሑፉ የእሳቸውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡