የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድንና የኢትዮጵያ ቡና አጥቂ አቡበከር ናስር ወደ ደቡብ አፍሪካ አምርቷል፡፡ ባለፈው ጥር ወር ለደቡብ አፍሪካው ማሜሎዲ ሰንዳውንስ ፊርማውን አኑሮ፣ በእናት ክለቡ የቆየው አቡበከር በኢትዮጵያ እግር ኳስ ድንቅ ጊዜያትን አሳልፏል፡፡ የፕሪሚየር ሊግን የጎል ክብረ ወሰን መስበር የቻለው አጥቂው፣ ዓርብ ሰኔ 17 ቀን 2014 ዓ.ም. የሊጉን የመጨረሻ ጨዋታ ከአርባ ምንጭ ጋር አድርጓል፡፡ በዕለቱም ለተጫዋቹ ደማቅ ሽኝት የተደረገለት ሲሆን፣ ክለቡ ኢትዮጵያ ቡና መለያ ዓርማውን በፍሬም አሠርቶ በስጦታ መልክ አበርክቶለታል፡፡
በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ከታዩ ድንቅ ተጫዋቾች ውስጥ የሚመደበው የጎል አዳኙ አቡበከር፣ በደቡብ አፍሪካ መልካም ጊዜ ሊኖር እንደሚችል ይገመታል፡፡ ተጫዋቹ ማሜሎዲ ሰንዳውንስ ከመቀላቀሉ አስቀድሞ የበርካታ አገር ክለቦች ተጫዋቹን ለማስፈረም ፍላጎት ማሳየታቸው ይታወሳል፡፡
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታ ግብፅን በረታበት ዕለት ተጫዋቹ ያሳየውን እንቅስቃሴ የተመለከቱ በርካታ ክለቦች ተጫዋቹን ለማስፈረም ዳግም ፍላጎት ያሳዩ ነበሩ፡፡ ሆኖም ተጫዋቹ ከደቡብ አፍሪካዋ ክለብ ጋር ውል ማሰሩን ተከትሎ ጥያቄዎቹን ሳይቀበል ቀርቷል፡፡
አቡበከር በሊጉ ያሳየውን ብቃት ተከትሎ ጥያቄ ቀርቦለት የነበረው ከግብፅ፣ ከአልጄሪያና ከታንዛኒያ ክለቦች ብቻ ሳይሆን በስፔን በዲቪዚዮን ደረጃ የሚጫወተው የጆርጅያ ክለብ ጭምር ነበር፡፡
ከ2006 እስከ 2008 ዓ.ም. ለሐረር ከተማ እግር ኳስ ክለብ ከተጫወተ በኋላ፣ ኢትዮጵያ ቡናን ተቀላቅሎ ክለቡን ለአራት ዓመታት አገልግሏል፡፡ ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከ17 እና ከ23 ዓመት በታች ተጫውቷል፡፡ የካሜሮን የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታን ጨምሮ፣ ኢትዮጵያ ከስምንት ዓመታት በኋላ በተካፈለችበት የካሜሮን አፍሪካ ዋንጫ ላይ ተካፋይ መሆን ችሏል፡፡
ለአይቮሪኮስቱ የአፍሪካ ዋንጫ የምድብ ማጣሪያ ጨዋታ የዋሊያዎቹ ቁልፍ ተጫዋች ሆኖ እያገለገለ ይገኛል፡፡ አቡበከር በዘንድሮ ቤትኪንግ ኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ውድድር በ20 ጨዋታዎች 14 ጎሎችን በማስቆጠር በቀዳሚነት ተቀምጦ ነበር፡፡
በአቡበከር በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የኢትዮጵያ ቡናን መለያ ለብሶ መጫወት ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ፣ 70 ጎሎችንና አምስት ሦስታን (ሀትሪኮችን) አስቆጥሯል፡፡ የዓመቱ የሊጉ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ (በአንድ የውድድር ዓመት 29 ጎሎችን በማስቆጠር ክብረ ወሰን መጨበጥ ችሏል)፣ የሊጉ ኮኮብ ተጫዋች እንዲሁም የፕሪሚየር ሊጉ ምርጥ ወጣት ተጫዋች መባል ችሏል፡፡