Tuesday, November 28, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

‹‹ከዚህ በኋላ በማዕድን ዘርፍ የሚገ ባ ኩባንያ ለኢትዮጵያ አጋር መሆን የሚችል ብቻ ይሆናል›› የማዕድን ሚኒስትር ታከለ ኡማ (ኢንጂነር)

ተዛማጅ ፅሁፎች

ባሳለፍነው ሳምንት አጋማሽ የማዕድን ሚኒስቴር በዚህ ወቅት ያለውን የአገሪቱን የማዕድን ዘርፍ እንቅስቃሴና ያለፉት ወራት የዘርፉን አፈጻጸም እንዲሁም የገቡትን ውል ማክበር ያልቻሉ ኩባንያዎች ላይ ዕርምጃ መውሰዱን አስመልክቶ የጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቷል፡፡ መግለጫውን የሰጡት የማዕድን ሚኒስትሩ ታከለ ኡማ (ኢንጂነር) በዕለቱ ሪፖርተርን ጨምሮ ከጋዜጠኞች ለተነሱላቸው የተለያዩ ጥያቄዎች የሰጡትን ምላሽ ኤልያስ ተገኝ እንደሚከተለው አቅርቦታል፡፡

ጥያቄ፡- ሰሞኑን 900 በላይ የሚሆኑ ኩባንያዎች የማዕድን ፈቃድ የተሠረዘበት ምክንያት ምንድነው?

ታከለ (ኢንጂነር) የፖለቲካና የኢኮኖሚ ሪፎርም መደረግ ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ መንግሥት የማዕድን ዘርፉ የአገሪቱ የኢኮኖሚ ምሰሶ ይሆናል ብሎ በማመን በርካታ የሪፎርም ሥራዎች እንዲሁም የአዋጅና የፖሊሲ ማስተካከያዎች እንዲከናወኑ አድርጓል። በቀጣይም የሚሠሩ ሥራዎች ይኖራሉ፡፡ ላለፉት አራት፣ አምስትና አሥር ዓመታት የማዕድን ፍለጋ፣ የማዕድን ምርት ማምረትና ወደ ውጭ ለመላክ በርካታ ኩባንያዎች ፈቃድ ወስደዋል፡፡ ከእነዚህ ውስጥ የተሻለ ሥራ የሠሩ አሉ፡፡ በዚያው ልክ ፈቃድ ወስደው መንግሥትና ሕዝብ ከእነሱ የሚጠበቀውን ያልሠሩ፣ ፈቃድ ሲወስዱ ባቀረቡት የሥራ ፕሮግራም ልክ ያልሠሩ፣ በአገሪቱ የሕግ ማዕቀፍ መሠረት ሚናቸውን ያልተወጡ ኩባንያዎች ላለፉት ወራት ተለይተዋል፣ ተገምግመዋል፣ ተጠንተዋል፡፡ ከሚመለከተው የመንግሥት ተቋማት ጋር በመሆንም ስለእነዚህ ኩባንያዎች ሰፊ ውይይት ተደርጓል። ሰፊ ጥናትና ግምገማ ከተደረገ በኋላም በመንግሥት ደረጃ አቋም ተይዟል። ይኸውም በአገር ደረጃ ለታቀደው የኢኮኖሚ ሪፎርም በተለይም የማዕድን ዘርፉ ለግብርና፣ ለማኑፋክቸሪንግና ለወጪ ንግድ እንዲሁም አጠቃላይ  አገራዊ ምርትን ማሳድግ አንፃር የሚኖረውን ፋይዳ ከግምት በማስገባት በዘርፉ ያሉ ተዋንያን ሁሉ በኢኮኖሚ ሪፎርም ማዕቀፍ ውስጥ እንዲሠሩ ይፈለጋል፡፡ ይህንን መሠረት በማድረግም ፈቃድ የወሰዱ ኩባንያዎችን የመለየት ሥራ ተከናውኖ በአጠቃላይ ከ900 በላይ ለሚሆኑ ኩባንያዎች የተሰጡ ፈቃዶች ተሰርዘዋል፡፡ ዕርምጃ ከተወሰደባቸው መካከል የማዕድን ፍለጋ ፈቃድ የወሰዱ ኩባንያዎች ይገኙበታል፡፡ በማዕድን ፍለጋ ላይ ያሉ ኩባንያዎች በትንሹ አራት፣ አምስት፣ ስድስትና እስከ አሥር ዓመታት የረባ ውጤት ሳያመጡ የቆዩ አሉ፡፡ በእነዚህ ዓመታት መንግሥት የጣለባቸው አደራ አለ፣ መንግሥትና ሕዝብ ከእነሱ የሚፈልገው ነገር አለ፡፡ ይህንን ስላላሟሉ በአጠቃላይ በፍለጋ ላይ የተሰማሩ ውጤት ያላመጡ፣ በገቡት ውል መሠረት ያልሠሩ ኩባንያዎች ፈቃድ ተሰርዘዋል፡፡ በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ የማዕድን ፈቃድ ወስደው ፈቃዱን ማዕድን ለማውጣትና ለአገራዊ ምርትም ይሁን ለውጭ ንግድ ለመጠቀም በተገባው ውል መሠረት ባለመሥራታቸው የተሰረዙ ናቸው። ሦስተኛ ከወርቅ ውጭ ያሉ፣ ወርቅ የሚሸጠው በብሔራዊ ባንክ ስለሆነ፣ ከወርቅ ውጭ ያሉ የማዕድናት ዝውውርና ንግድ ለማከናወን ፈቃድ ወስደው እስካሁን መንግሥትና ሕዝብ በሚፈልገው መንገድ ሚናቸውን ያልተወጡ፣ የተሰጣቸውን ፈቃድ ለኮንትሮባንድ ንግድ የተጠቀሙ፣ በአጠቃላይ በሕገወጥ መንገድ የኢትዮጵያን ማዕድን ወደ ውጭ የሚሸጡ ከ800 በላይ ኩባንያዎች ተሰርዘዋል፡፡ ይኼ ጥናት ጊዜ ወስዶ፣ በጥንቃቄ የተሠራ፣ ኃላፊነት የተሞላበት፣ የሚሠሩትን ለማበረታት፣ የማይሠሩትንና በኢትዮጵያ ሕግ የማይዳኙ፣ አንዳች ዓይነት ጉልበት ያሳዩትን ሕግና ሥርዓት ለማስያዝ የተደረገ የመንግሥት ውሳኔ ነው፡፡

ጥያቄ፡ በኦጋዴን የተፈጥሮ ጋዝ ለማልማት ፈቃድ የተሰጠውን የቻይናው ፖሊ ጂሲኤል ኩባንእና በወለጋ የወርቅ ማዕድን ለማምረት የተሰማራው የብሪታኒያው ከፊ ጎልድ (ቱሉ ካፒ) ኩባንያ ፈቃዳቸው ከተሰረዘባቸው ውስጥ ተካተዋል? 

ታከለ (ኢንጂነር) የከፊ ሚነራልስ (ከፊ ጎልድ) እና የፖሊጂሴኤል ፈቃዶች እ.ኤ.አ. በጁን 30 ቀን 2022 ስለሚቋረጥ ይኼኛው እነሱን አያጠቃልልም፡፡ ለምንድነው ያልተጠቃልለው ከተባለ፣ ለእነሱ የሰጠናቸው የስድስት ወር የጊዜ ገደብ በመኖሩና ይህ የጊዜ ገደብ የሚጠናቀቀው በቀጣዩ ሳምንት ጁን 30 በመሆኑ ነው፡፡ ለምሳሌ ፖሊጂሴኤል ለተፈጥሮ ጋዝ ልማት ካስገባው 4.2 ቢሊዮን ዶላር በወረቀት ደረጃ (ፕሮፖዛል ደረጃ) ፕሮጀክቱን ለማስጀመር የሚያስፈልገው ወይም ዲዩቲ ሼር የሚባለው 30 በመቶ ወጪ ወይም 1.2 ቢሊዮን ዶላር እስከ ጁን 30 ቀን ድረስ እንዲያስገባ የጊዜ ገደብ ተሰጥቶታል፡፡ ይህንን 1.2 ቢሊዮን ዶላር በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ አስመዝግቦ ወይም ደግሞ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ከሚያውቀው ባንክ ማረጋገጫ (አፕሩቫል) ካላመጣ ሰኔ 30 ላይ ምንም መግለጫ መስጠት ሳያስፈልግ ይቋረጣል፡፡ ከኬፊ ሚነራልስም ከ340 ሚሊዮን ዶላር ውስጥ የሚፈለገው 80 ሚሊዮን ዶላር ነው፡፡ የኬፊ ሚነራልስ ኢኪዩቲ ሼር ሲሆን፣ ይህም ቱሉ ኬፒ የሚባለው ነው እነሱም በተቀመጠላቸው ቀነ ገደብ ውስጥ ካመጡ ይቀጥላሉ ካላመጡ ፈቃዳቸው በቀጥታ እንዲቋረጥ ተወስኗል፡፡

ጥያቄ፡ የማዕድን ሚኒስቴር ለኩባንያዎች ፈቃድ ከመስጠቱ በፊት የኩባንያዎችን አቅም የሚፈተሽበት፣ መሥፈርት ማሟላታቸውን የሚገመግምበት ሥርዓት አለው? ፈቃድ ከተወሰደስ በኋላ ኩባንያዎች ሥራቸውን በአግባቡ እያከናወኑ ስለመሆናቸው የሚቆጣጠርበት ሥርዓት አያስፈልገውም? የሕግ ጥሰት በፈጸሙት ላይቃዳቸውን ከመሰረዝ ባለፈ የሕግ ተጠያቂነት አይኖርም?

ታከለ (ኢንጂነር) ማዕድናትን የሚሸጡ የኮምፒተንሲ (የብቃት ማረጋገጫ) ወረቀት ወይም ፈቃድ ያላቸው ወደ 800 የሚሆኑት ኩባንያዎች ያደረጉት ወንጀል ነው ሊባል ይችላል፡፡ አንደኛ በኮንትሮባንድ በኩል ስለሚወጣ የእኛ አገር ደግሞ በተለይም በማዕድን ዘርፍ ብዙ ተዋናይ ያለበት ነው፡፡ ይህንን ከፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽንና ከክልል የፀጥታ ተቋማት ጋር እየተሠራበት ነው፡፡ ዋናው ግን የሰዶ ማሳደድ ሥራ መሥራት ሳይሆን፣ ከዚህ በፊት የነበረውን ሥራ  በሪፎርም፣ በሕግና በአዋጅ ማስተካከያ ሥርዓት ማስያዝ ያስፈልግ ነበር። አንዳንዱ የእኛ ሕግ ራሱ ክፍተት ነበረበት፡፡ ብዙ ክልከላ ዕገዳ ያለበት ስለሆነ ክልከላና ዕገዳ ባለበት አገር ደግሞ ብዙ ነገር ወደ ሕገወጥ መንገድ ስለሚያመራ እኛ ያደረግነው ክልከላዎችንና ዕገዳዎችን ሙሉ በሙሉ ማንሳት ነው፡፡ ለምሳሌ አንደኛው አንድ ሰው ሳፋየር ወይም ኦፓልና ሌሎች ማዕድናትን ወደ ውጭ ለመላክ የሚያስፈልገውን ስታንዳርድና ጥራት (ኳሊቲ) ማሟላታቸው የሚረጋገጠው በቴክኖሎጂ ሳይሆን፣ የሚኒስትር መሥሪያ ቤቱ ሰዎች በዓይን ዓይተው ደረጃው ይኼ ነው፣ ዋጋ ይኼን ያህል  አያወጣም (አያመጣም) የሚል ኋላ ቀር አሠራር ነበር፡፡ ይኼ በራሱ ለሌብነት መንገድ ስለሚከፍት ሙሉ በሙሉ በመንግሥት ተጠንቶ ተነስቷል፡፡ ማንኛውም ሰው የገዛውን ጌጣ ጌጥም ሆነ ማዕድናት በገዛው ዋጋ በዚህ ደረጃ እሸጣለሁ ካለ፣ የእሱን በማመን ሙሉ በሙሉ እንዲሸጥ ይደረጋል፡፡ ይኼ ብዙ ነገር ይፈታል፡፡ በዚህ ጉዳይ መንግሥት የሚጠበቅበትን ያስተካከለ ሲሆን፣ እነሱ ደግሞ ማስተካከል የሚገባቸው ጉዳዮች ነበሩ፡፡ በተሰጣቸው ጊዜ ያላስተካከሉት ናቸው አሁን ላይ የተሰረዙት፡፡ ነገም ቢሆን እነዚህ ኩባንዎች መንግሥት አሁን ባስቀመጠው ሥርዓት  እንነግዳለን፣ እንሠራለን ካሉ አሁንም በሩ ክፍት ነው፡፡ ወንጀል መሆኑ እንዳለ ሆኖ ዋናው ሰዎችን ከሶ ወደ ክስ ሒደት ውስጥ ማስገባት ሳይሆን ሰዎችን አስተምሮ ወደ ተሻለ የንግድ ሥርዓት እንዲገቡ ማድረግ ነው፡፡ ለማዕድን ኩባንያዎች የሚሰጠው ፈቃድ ሁለት ዓይነት ነው፡፡ አንደኛው የፍለጋ ፈቃድ ሲሆን፣ ሌላኛው ደግሞ ፍለጋውን ካጠናቀቀ በኋላ የሚሰጠው የምርት ፈቃድ ነው፡፡ በዚህ ወቅት ብዙ የማዕድን ፖሊሲ፣ አዋጅ ተስተካክሏል፡፡ የመንግሥት አንዱ አንጓ ሆኖ መጥቷል፡፡ በተለይ የምርት ፈቃድ ከዚህ በፊት በሚኒስትሮች ምክር ቤት ብቻ ሲሰጥ ነበር፡፡ ባለፉት ሁለት ዓመታት በድምሩ ወደ 16 ፈቃድ ብቻ ነው የተሰጠው፣ ስምንት የከሰል፣ ስምንት የወርቅ፡፡ ከዚያ ውጭ እየተደረገ የነበረው ሥርዓት መገንባት ነው፡፡ የካዳስተር ሥርዓት የተገነባ ሲሆን፣ የካዳስተር ሥርዓት ኩባንያዎች፣ ግለሰቦች ኢትዮጵያ ውስጥ ማዕድን እንፈልጋለን ካሉ፣ ማመልከቻ ያስገባሉ፣ ማመልከቻቸው በደንብ ከተጣራ በኋላ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በኩል ውጭ ባሉ የኢትዮጵያ ሚስዮኖችና ዲፕሎማቶች በኩል ይጣራል ወይም ዱደሊጀንስ የሚባለው ጉዳይ ይሠራል፡፡ ይኼ የማጣራት ሥራ ከዚህ ቀደም ባለመኖሩ ኩባንያዎች በብዛት ውጤታማ አልሆኑም፡፡ ወደ ኢትዮጵያ ይመጡ የነበሩ ኩባንያዎች ደላላ ኩባንያዎች ነበሩ፡፡ በግለሰብ ደረጃ ኢትዮጵያውያንን በማምጣት አንድና ሁለት በመቶ ሼር ሰጥተው ፈቃድ (ላይሰንስ) ከወሰዱ በኋላ 10 እና 20 ዓመታት ይቆያሉ፡፡ የቱሉ ካፒም ሆነ ፖሊሲጂኤል ሌሎች ስማቸው ያልተጠቀሰና የተሰረዙት ብዙዎቹ እንደዚህ ናቸው፡፡ ከዚህ በኋላ የሚሠራው ኩባንያዎች ባስገቡት ወረቀት ሳይሆን፣ ከወረቀት ባሻገር በውጭ ጉዳይ በኩል በሚገኙ ሚሲዮኖች እንደ ዱደሊጀንስ ተሠርቶ የተረጋገጠ ኩባንያ፣ ልምድ ያለው፣ ካፒታልና ቴክኖሎጂ ያለው ለኢትዮጵያ አጋር (ፓርትነር) መሆን የሚችል ኩባንያ ብቻ ይሆናል፡፡ አንዳንዶቹ ሰላዮች ናቸው፡፡ ለስለላ የሚገቡ ብዙ ኩባንያዎች አሉ፡፡ ስለዚህ አሁን የተወሰደው ዕርምጃ ይህን ጭምር ለማስተካከል የተወሰደ ነው፡፡ ከዚህ በኋላ የምንሠራቸው በጣም የተጣራ፣ ውስን የሆኑ ኩባንያዎች፣ የሚታወቁና በዓለም አቀፍ ደረጃ ልምድ ያላቸው ይሆናሉ፡፡ እንደዚህ ዓይነት ኩባንያዎች ባይመጡም እኛ ራሳችን ሄደን ለምነናቸው፣ ማድረግ ያለብንን ታክስ ማበረታቻዎች (ኢንሴንቲቭ) ሁሉ ሰጥተን እንዲመጡ እናደርጋለን፡፡ በአሁኑ ወቅት በማዳበሪያና በብረት ዘርፍ ላይ እየሠራን ያለነው በዚህ መንገድ ነው፡፡ መንግሥት ቅድሚያ የሚሰጣቸው ናቸው የተባሉ አምስትና ስድስት ምርቶች ላይ በሚኒስቴር ደረጃ እየተመራ ኩባንያዎችን ራሳችን መርጠን ነው ወደ ሥራ የምናስገባው እንጂ፣ እንደ ከዚህ ቀደሙ የመጣውን ሰው ብቻ እያስተናገድን መሬት እየሸነሸንን፣ እየሸጥን ምርት ውስጥ አንገባም፡፡ አሁን የተደራጀው ሥርዓትና አሠራር ቀጥሎ ለሚመጣው ኩባንያም ሆነ ለእኛም በጣም ጥሩ ነው፡፡ ውስን ኩባንያዎችን እናስገባለን፣ እነዚህ ኩባንያዎች ይታወቃሉ፣ ልምዳቸው ይታወቃል፣ ከዚህ በኋላ ‹‹ሰላም ላለ›› ሰው ሁሉ ፈቃድ እንደማይሰጥ ማረጋገጥ እወዳለሁ፡፡

ጥያቄ፡ ኮንትሮባንድን በተመለከተ በዘርፉ ያለው ችግር በጥናት እንደቀረበ ይታወቃል በማን የተጠና ጥናት ነው ምን ዓይነት ግኝቶችን አሳየ?

ታከለ (ኢንጂነር) ኮንትሮባንድን በተመለከተ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኢኮኖሚክስ ትምህርት ክፍል፣ የማዕድን ሚኒስቴርና ብሔራዊ ባንክ ያሉበት ጥናት ላለፉት ስድስት ወራት ተጠንቷል፡፡ ስድስት ወርቅ አምራች የሆኑ ወረዳዎችን ወይም ቦታዎችን ተመርጠው ተጠንተዋል፡፡ በጥናቱ አንደተረጋገጠው ከምናመርተው ወርቅ 50 በመቶ ብቻ ወደ ብሔራዊ ባንክ ይኼዳል፡፡ ሁለት መሠረታዊ ነገሮች አሉ፡፡ አንደኛው ብሔራዊ ባንክ አንድ ግራም (ኦውንስ) ወርቅና ከብሔራዊ ባንክ ውጭ በኮንትሮባንድ የሚሸጥበት በዶላር ስለሆነ ያንን ዶላር ወደ አገር መልሰው በኮንትሮባንድ ዶላሩን በፓራለል ወይም በብላክ ማርኬት ይዘረዝሩታል፡፡ ስለዚህ በመሀል ያለው ከ35 እስከ 40 በመቶ ትርፍ አለው፡፡ ይኼንን ጥናቱ ስላረጋገጠው፣ ከብሔራዊ ባንክና ከሚመለከታቸው አካላት ባለፈውም ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተገኙበት ያለፉት አሥር ወራት የአገር ልማት ግምገማ ሲደረግ አንዱ አቅጣጫ የተሰጠበት እንዲስተካከል ነው፡፡ አሁን ላይ ከዓለም አቀፍ ዋጋ 35 በመቶ በላይ ብሔራዊ ባንክ እንዲገዛ፣ ከዚህ ቀደም ከ25 ኪሎ ግራም በላይ ያመጣ ሰው ነበር 29 በመቶ ፕሪምየም ነበር የሚያገኘው፣ አሁን አምራቹን ለማበረታት 50 ግራም ያመጣ ሰው ሁሉ 35 በመቶ ፕሪምየም ይጠቀማል፡፡ ይህ በአንድ በኩል ኮንትሮባንዱን ለመከላከል ነው፡፡ ኮንትሮባንድ ሄዶ ሄዶ የተሻለ ዋጋ ፍለጋ ነው፡፡ በእርግጥ አንዳንዱ ከዚህ አልፎ አገር ለመጉዳት ነው፡፡ የተሻለ ዋጋ ፍለጋ የሚደረግበትን የኮንትሮባንድ ንግድ ለመከላከል ብሔራዊ ባንክ ከሚሸጠው አንድ ግራም ወርቅ በዓለም አቀፍ ዋጋ ከሚሸጠው 35 በመቶ ተጨማሪ እንዲገዛ ተወስኗል፡፡ ሁለተኛ አምስት ኪሎ ግራም የነበረ ወርቅ ወደ 50 ግራም ያወረድንበት ዋና ምከንያት አምስት ኪሎ ግራም ወርቅን እነዚህ አዘዋዋሪ ያልኳቸው ሰዎች (850ዎቹ) ይገዙትና አንድ ቦታ ያከማቻሉ፡፡ የተሻለ ዋጋ ካገኙ ይሸጣሉ፡፡ የተሻለ ዋጋ ካላገኙ በኮንትሮባንድ በኩል ወደ ውጭ ይሸጡታል፡፡ በዚህ ምክንያት አንደኛ በመሀል ያለውን ሰንሰለት አስተካከለው ሁለተኛ 29 የነበረውን ፐርሰንት አሁን ካለው ነባራዊ ሁኔታ ወደ 35 በመቶ ከፍ አደረግን፡፡ አምስት ኪሎ የሚለውን ለነጋዴው ብቻ ያደላውን አሠራር አምራቹ ራሱ በቀጥታ እንዲጠቀም ወደ 50 ግራም አወረድን፡፡ 50 ግራም ያመረተው ባህላዊ ወርቅ አምራች ባንክ ይዞ ቢሄድ በ50 ግራም 35 በመቶ ከዓለም አቀፉ ዋጋ በላይ ያገኛል፡፡ ኮንትሮባንዱን በአንድ በኩል በፖሊስና ድንበር በመዝጋት ብቻ መከላከል አይቻልም፡፡ በእርግጥ እሱ አንዱ መንገድ ነው ነገር ግን በጣም ወሳኝ ነገር የዋጋ ጉዳይ ስለሆነ (የተሻለ ዋጋ ለመፈለግ ስለሆነ ስደት የሚመጣው) ያንን ለማስተካከል ከትይዩ (ፓራለል) ገበያ ጋር ተመሳሳይ የሆነ 35 በመቶ ተወስኗል፡፡

ጥያቄ፡ ዕርምጃ  የተወሰደባቸው  ኩባንያዎች  በየት  አካባቢ ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ናቸው?

ታከለ (ኢንጂነር) ዕርምጃ የተወሰደባቸው ኩባንያዎች በብዛት ያሉት በኦሮሚያና ቤንሻንጉል አካባቢ ነው፡፡ ሶማሌና አፋርም አሉ፡፡ በተለይ የወርቅና ታንታለም ኦሮሚያ ጉጂ አካባቢ ነው፡፡ እነዚህ ኩባንያዎች የዛሬ 10 እና 15 ዓመት ከአምስትና ሰባት ዓመት በፊት የገቡ ናቸው፡፡ አሁን ግን እንደዚህ ዓይነት አካሄዶችን አንፈቅድም፣ በኢትዮጵያ ሀብት (ሪሶርስ) ማንም መቀለድ አይችልም፡፡ መንግሥትም መቀለድ አይችልም፣ ግለሰብም መቀለድ አይችልም፡፡ የማንቀልድበት ጉዳይ ደግሞ አሁን ያለንበት አገራዊና ዓለም አቀፋዊ ሁኔታ በአገር ሀብት እንዳንቀልድ ያደርገናል፡፡ የአገራችንን ዕምቅ ሀብት የመጠቀም አዝማሚያ ውስጥ ገብተናል፡፡ ማዕድናቶቻችን መውጣትና ወደ ምርት መግባት አለባቸው፡፡ አገራዊ ኢኮኖሚው ማደግ አለበት፡፡ በዓለም አቀፍ ደረጃ የተዛባውን (ዲስትራክት) የአቅርቦት ጉዳይ በአገር ደረጃ ካላመረትን እንደ አገርም መቀጠል አንችልም፡፡ ለዚህ ነው መንግሥት ግብርናም ሆነ ማዕድን ላይ ትኩረት እየሰጠ ያለው፡፡

ጥያቄ፡ የአብዛኞቹ ዕርምጃ የተወሰደባቸው ኩባንያዎች ፍቃዳቸው እንዲሰረዝ የተዳረጉበት ዋነኛ ምክንያት ምንድነው ጥያቄ?

ታከለ (ኢንጂነር) ኦሮሚያም ላይ ይሁን ቤንሻንጉል ላይ ያቋረጥነው ላይሰንስ ከፀጥታ ጋር ምንም አይገናኝም፡፡ ካስቀመጥናቸው መሥፈርቶች ውስጥ አንድ ኩባንያ ለምሳሌ ባለፉት አምስት ዓመት  ፍለጋ ላይ እሰማራለሁ ብሎ ነበር፣ ፍለጋው ፀጥታ ከሚባለው በፊት ነበር የነበረው፡፡ ለምሳሌ ቱሉ ካፒ የዛሬ አሥር ዓመት ነው ላይሰንስ የወሰደው፣ ፀጥታ የሚባለው የመጣው ከአንድ ዓመትና አንድ ዓመት ተኩል ወዲህ ነው፡፡ የተጠቀሱት ከስድስት ዓመት በፊት የተገመገሙ ግመገማዎች ናቸው፡፡ ለአንድ ዓመት ተኩል ተቸግረዋል ቢባል እንኳን፣ እኛ ያደረግነው አጠቃላይ ለሥራው ከሚያስፈልገው 340 ሚሊዮን ዶላር ኩባንያዎች ወይም ባንኮች የሚሰጧቸው (ዴት ፋይናንሲንግ) ኩባንያው፣ ግን በራሱ አቅም ከራሱ ባንክ (ኢኩቲ ሼር) በትንሹ 30 በመቶ ማሳየት አለበት፡፡ ይኼ መሆን የነበረበት ወደ ኢትዮጵያ ሲመጡ ነበር፣ ለዚያ ነው የነበሩት አሠራሮች መጥፎዎች ነበሩ ያልኩት፡፡ ቱሉ ካፒ ከ340 ሚሊዮን 30 በመቶ የሆነውን 89 ሚሊዮን ዶላር ነው፡፡ ይኼ ራሴ ኢትዮጵያ መጥቼ ኢንቨስት ሳደርግ 89 ሚሊዮን ዶላር አለኝ፣ ቀጥሎን ያለውን ደግሞ ከባንክና ከሌሎች አደርጋለሁ ብሎ ነው የገባው፡፡ ጥያቄው አሁን ያንን 30 በመቶ አሳይ ነው፡፡ ሌላ ምንም አልተጠየቀም እሱንም አሳይ የተባለው ብሩን ሳይሆን በዚህ ባንክ ውስጥ ለዚህ ፕሮጀክት የተመደበ ብር አለው የሚል ማረጋገጫ ከሰጠን፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ደግሞ አመሳክሮ ይኼ (ኤክስ የተባለው) ኩባንያ ኢትዮጵያ ውስጥ ላለው ፕሮጀክት ዴዲኬትድ ነው የሚለውን ያረጋግጣል፡፡ ይኼንን ማምጣት ያልቻሉ ኩባንያዎች ናቸው፡፡ እኛ ጥቂት ነገር ነው የጠየቅናቸው፡፡ የትኛውም ኩባንያና መንግሥት ይኼንን አያደርገውም፡፡ መጀመርያ ፍቃዱን ሲወስዱ ነበር ብሩን ወደ ብሔራዊ ባንክ ማስገባት የነበረባቸው፡፡ ወደ ሚኒስትር መሥሪያ ቤቱ ከመጣሁበት ያለፉት ሁለት ዓመታት ጀምሮ አንዱ ሳደርግና ስረዳ የነበረው ይኼንን 30 በመቶ አሳዩ የሚለውን ነው፡፡ ፖሊጂሲኤልንም ይኼንን ነበር አሳዩ ያልናቸው አላሳዩንም፡፡ ቱሉ ካፒም ይኼንን ማሳየት አልቻለም፡፡ ጉጂ ላይ ያለው ቀንጢቻ ታንታለም ይኼንን ማሳየት አልቻለም፣ ዋይኤምጂ የሚባለው እንዲሁ ጉጂ ላይ ያለው ማሳየት አልቻለም፡፡ የዘረዘርኳቸው ኩባንያዎች የራሳቸውን 30 በመቶ አኩዩቲ ሼር ማሳየት ያልቻሉ ናቸው፡፡ ከፀጥታ ጋር አይገናኝም፡፡ ለምሳሌ 30 በመቶ አስገብቶ ቤኒሻንጉል ላይ የሚሠራ ቢሆን፣ ሁለትና ሦስት ዓመት እንሰጠዋለን፡፡ ሁለተኛ ማንም የማያደርገውን ነገር ነው ያደረግነው፡፡ ከብሔራዊ ባንክ ጋር በመሆን ያንን 30 በመቶ ብሔራዊ ባንክ ቢያስቀምጥ ኤልሲ ኢሹ እንዳይኖር ዶላር እንዲጠቀም ነው ደረግነው፡፡ የትኛውም ክልላዊም ሆነ ዓለም አቀፍ መንግሥት ይኼን አያደርገውም፡፡

ጥያቄ፡ ለአንድ  ሺሕ የተጠጉ ኩባንያዎችን ከማዕድን ዘርፉ ማውጣት ቀላል ዕርምጃ አይደለም፡፡ በኢንዱስትሪ ኢንቨስትመንትና በማዕድን ሥራ ላይ የሚሳተፉ የውጭ ኩባንያዎች ከገበያው ሲወጡ የዲፕሎማሲ ጉዳዮችን ሊያበላሹ ይችላሉ፡፡ መንግሥት እንደነዚህ ያሉ ጉዳዮችን አንዱ የሚያዘገይበት ምክንያት የዲፕሎማሲውን ጉዳይ እያስታመመ  ስለሆነ  ነው  ተብሎ ይታሰባል፡፡ ፈቃዳቸው የተሰረዙ የውጭ ኩባንያዎች ላይ ያለውን ጉዳይ እንዴት ትመለከቱታላችሁ? በዚህ ወቅት ማዕድን በመፈለግና በማምረት ሥራ የሚገኙ ኩባንያዎች ቁጥራቸው ምን ያህል ይሆናል?

ታከለ (ኢንጂነር) ኩባንያዎች ከዚህ ሲወጡ በዲፕሎማሲ በኩል ምንድነው እየተሠራ የነበረው? ለሚለው ከውጭ ጉዳይና ከሚመለከታቸው አካላት ጋር፣ በነገራችን ላይ ይኼ ውሳኔ የተሰጠው የዛሬ ስድስት ወር ነው፡፡ ነገሮችን ስናጣራ፣ ከውጭ ጉዳይ ጋር፣ ከኩባንያዎቹ ጋር ከአገራቸው ሚኒስትሮችና አምባሳደሮች ጋር ሰፋፊ ጊዜዎችን ወስደን አንዳንዱን የማይገባ ተጨማሪ ርቀት ሄደን የረዳናቸው አሉ፡፡ ሌላው ቀርቶ የእኛን ሕግና አዋጅ እየጣስን በደብዳቤና በሌላ መልኩ እሹሩሩ የማለትም ነገር ነበር፡፡ እርግጠኛ ነኝ በዚህ ደረጃ ኩባንያ ኢትዮጵያን የመክሰስ ሞራል አይኖረውም ፡፡ ከሚገባው በላይ ሄደን፣ እረድተናቸው፣ በአገራችን ሀብት ለምነናቸው እንዲቆዩ፣ እንዲያለሙ ማድረግ ያለባቸውን ነገር እንዲያደርጉ ነው ያደረግነው በዚህ ደረጃ ሞራል አላቸው ብዬ አላስብም፡፡ እነዚህ ሁሉ ከወጡ ሌሎች አሉ ወይ? ለሚለው በፍለጋ ላይም ሆነ በምርት ላይ ያሉ በጣም ብዙ ኩባንያዎች አሉ፡፡ አገራዊ ኢኮኖሚያችን አንዱ የሚፈልገው በአገር ደረጃ የምናመርታቸው ሸቀጦችን ወይም ግብዓቶችን ነው፡፡ እነዚህም ማዳበሪያ፣ ብረት፣ የኮንስትራክሽን ማቴርያሎችና ኬሚካሎች ናቸው፡፡ በዚያ ደረጃ መንግሥት ከውጭ የምናስገባቸውን አንድ ሁለት ሦስት ብሎ ቅደም ተከተል አስቀምጦ ለዛ የሚያስፈልጉ ኩባንያዎችን እየመረጥን ነው፡፡ ሁለተኛ ወደ ውጭ የምንሸጣቸው ምርቶች ከሆኑት አንዱ ወርቅ ነው፣ የዓለም አቀፍ ተሞክሮ እንደሚያሳየው ብዙ ኩባንያዎችን በማስገባት አይደለም፡፡ በጣም የታወቁ ሁለት ሦስት አራት ኩባንያዎች ካስገባን ከዚያ በታች ያለውን በባህላዊ መንገድ ከተመረተ 30 ወይም 40 ቶን ከተመረተ በቂ ነው፡፡ የእኛ ዕቅድ እስከ አምስት ዓመት 30 ቶን ማምረት ነው፡፡ ለ30 ቶን የሚያስፈልጉን ኩባንያዎች ባለፈው በካቢኔ የሰጠናቸው አሉ፣ በጣም ጥሩ እመርታ (ፕሮግረስ) ያሳዩ አሉ፡፡ በዚያውም ልክ ዕርዳታና ድጋፍ የሚፈልጉ አሉ፣ እነሱን በዚያ ደረጃ ነው የምናግዛቸው፡፡

ጥያቄ፡ የተፈጥሮ ጋዝን በመጠቀም የማዳበሪያ ፋብሪካዎችን ለማቋቋም የሚያስችል የአዋጭነት ጥናት ሚያደርጉ ድርጅቶችን ለመጋበዝ ከሁለት ሳምንት በፊት የወጣው ዓለም አቀፍ ጨረታ ያለበት ደረጃ ቢገለጽ?

ታከለ (ኢንጂነር) የማዳበሪያው ጉዳይ ላይ የፍላጎት ማሳወቂያ አውጥተናል፣ የምንፈልጋቸውን ኩባንያዎች አላገኘንም፡፡ በርካታ ኩባንያዎች ማለትም 30 የሚሆኑ አመልክተዋል፡፡ ነገር ግን የማዳበሪያ ጥናት አንዳንድ ኩባንያዎች ያዩት ሰፐርማርኬት የመትከል ያህል ቀላል አድርገው ነው፡፡ ማዳበሪያ ፋብሪካ ማለት በጣም ውስብስብ (ኮምፕሌክስ) ነው፡፡ ሰፊ የቴክኖሎጂ፣ ኢኮኖሚክስ ጥናት የሚጠይቅ ነው፡፡ 30 የሚደርሱ ኩባንያዎች አመለከቱ፡፡ ነገር ግን ዝም ብለን ስናያቸው፣ የምናውቃቸውም ስለሆኑ አምስት ቀን ተጨማሪ ጊዜ ሰጥተናቸዋል፡፡ ሌሎች ትላልቅ ኩባንያዎች እንዲገቡ አንዳንዶቹንም እያበረታታን ነው፡፡ እንዲገቡና እንዲያጠኑ፣ ምክንያቱንም ይኼ አገራዊ ፕሮጀክት ነው አገራዊ ፕሮጀክት ላይ ደግሞ ዝም ብለን ጨረታ በሚመስል መልኩ ነገር ግን ትንንሽ ኩባንያዎችን አስገብተን እንዲበላሽ አንፈልግም፡፡ ከዚህ በፊት ሁላችንም እንደምናውቀው ያዩ ማዳበሪያ አንዱ የተበላሸበት ዋና ምክንያት እንደ ቀላል ፕሮጀክት ታይቶ ነው፡፡ አምስት ተጨማሪ ቀን ሰጥተናል ፕሮግረሱ ጥሩ ነው፡፡ ከአምስት ቀን በኋላ ኩባንያዎች ፍላጎታቸውን (ኢንተረስታቸውን) ያስገባሉ፣ ከዚያ በኋላ ከፍተኛ ስኪል ያላቸውን ቴክኒካል ቡድን (ቲም) እናደራጃለን፣ ያ ቴክኒካል ቲም ይገመግማል (ኢቫሉዌት) ያደርጋል፡፡ በሌላ በኩል ከጨረታው ውጭ ሌሎች ኩባንያዎችንም እየጋበዝን ነው፡፡ አንዳንዱ ይኼኛውን ዓለም አቀፍ ጥናት ያደረጉም ስላሉ ኢትዮጵያን እንዲረዱ እየጋበዝናቸው ነው፡፡ ሦስት አራት አማራጮችን እናስቀምጣለን፣ የተሻለ አማራጭ ወስደን ጥናቱን በተቻለ መጠን በትንሽ ብር፣ ቢቻል ደግሞ በነፃ ማስጠናትም እንፈልጋለን፡፡ ምክንያቱም በዚህ ሰዓት እኛ የምንፈልገው የእኛ ልጆች አውቀው ከኩባንያ ጋር ሠርተው የፋብሪካውን ተከላ ማፈጠን ነው፡፡

ጥያቄ፡ በማዕድን ዘርፉ ብዙ ሪፎርሞችና የሕግ ማሻሻያዎች ተደርገዋል፣ ነገር ግን በአሁን ወቅት ምን ያህል ኢንቨስተሮችን የሚያሠራ ሁኔታ (ሲችዌሽን) አለ? 

ታከለ (ኢንጂነር) የማዕድን ሚኒስቴር ዋና ትኩረት የሚያደርገው የማዕድን ሀብት ያለባቸው ክልሎችን ነው፡፡ ከክልሎች ደግሞ በርካታ የማዕድን ሀብት ያላቸው ላይ ነው ብዙ ትኩረት የምናደርገው፡፡ ስለዚህ በፌዴራል ደረጃ የሚሠራውን ሪፎርም ወደ ክልል፣ ከክልል ወደ ወረዳ የማውረድ ሥራ አሁን በተጀመረው ልክ እናወርዳለን፡፡ ለምሳሌ ወርቅ፣ ብረት የሚያመርቱ ክልሎች አሉና አንዱ ነገር አስቻይ ሁኔታዎችን መፍጠር ነው፡፡ አስቻይ የሚባለው ሁኔታ ሦስት መሥፈርት ነው፡፡ አንደኛው ፖሊሲው ይጋብዛል ወይስ አይጋብዝም? ነው፡፡ ከዚህ በፊት የማዕድን ፖሊሲ ራሱ አልነበረም፡፡ አሁን ያለው በተፈጥሮ ጋዝም ይሁን፣ በነዳጅ፣ በማዕድናት፣ በጂኦተርማልና ሌሎች ከዚህ በፊት የነበረው ፖሊሲ ተቀይሮ አሁን ፖሊሲው ጋባዥ ነው፡፡ ሁለተኛ አዋጅ ነው፡፡ ከዚህ በፊት የነበሩ ከልካይ የነበሩ አዋጆች ነበሩ፣ አሁን ያለው አዋጅ ከኢትዮጵያ ሕዝብና መንግሥት ጋር አጋር (ፓርትነር) መሆን የሚፈልግ ኩባንያን አይከለክልም፡፡ ኔጎሼት ነው የምናደርገው፡፡ ከዚህ በፊት በሕግ ውስጥ ማንኛውም ሰው መጥቶ ፈቃድ ይወስዳል  እኛ ግን የምንፈልገው ፈቃድ መስጠት ሳይሆን፣ እኛ ወደ ምንፈልገው ልማት የሚሄደውን ኩባንያ የታክስ ማበረታቻ አድርገን፡፡ ከሦስት ዓመት በፊት የነበረው የታክስ ማበረታቻዎች በመንግሥት ደረጃ ወደ ስድስት፣ ሰባትና ዘጠኝ ከፍ ተደርገዋል፡፡ ለአንድ ኢንቨስተር እነዚህ ነገሮች ወሳኝ ናቸው፡፡ ሦሰተኛው ከውጭ የሚገቡም ይሁን በአገር ደረጃ የሚያስፈልጋቸው የመንግሥት ድጋፍ፣ የመሠረተ ልማት፣ ቪዛ፣ ዋንስቶፕ ሾፕ የሚባሉ መንግሥት ከጉምሩክ ጀምሮ አጠቃላይ በዚህ ዓውድ ውስጥ የሚንቀሳቀሱ የመንግሥት ተቋማትን በዚህ ደረጃ ራን (ያንቀሳቅሳል) ያደርጋል፡፡ ስለዚህ ይኼንን ኢኔብል የሚደርጉ ኩባንያዎች ወደ ኢትዮጵያ መጥተው እንዲሠሩ የሚደርጋቸው ወሳኝ ነገሮች ናቸው፡፡ እስከ ታች መውረድ አለብን የተወሰኑ ቦታዎችን አውርደናል፡፡ ሁለተኛው ኩባንያዎች ከውጭ ሳይመጡ ካሉበት አገር ሆነው የራሳቸውን አፕሊኬሽን (ማመልከቻ)  አፕሎድ (የሚያቀርቡበት) የካዳስተር ሥርዓት ገንብተናል፡፡ እሱ ብቻ ግን በቂ አይደለም፡፡ ያመለከተው ኩባንያ ማን ነው? የኋላ ታሪኩ (ባክራውንዱ) ወይም ምን ሠርቶ ያውቃል የሚለው ደግሞ ዲዩ ደሊጀንስ ይሠራል፡፡ ይኼንን ከጨረስን በኋላ ፈቃድ (ላይሰንስ) ከመስጠታችን በፊት (የፍለጋም ይሁን የምርት) ከዚህ በፊት ያልነበረ አሁን እያደረግነው ያለው ነገር በፍለጋ ላይ ያለ ኩባንያ ምርት ላይ ሲገባ ከምርት ከመንግሥት  የሚቀነስ (ከኢትዮጵያ ብር) የሚቀነስ፣ ለምሳሌ አንድ ኩባንያ በፍለጋ ላይ ስምንት መቶ ሚሊዮን አወጣሁ ካለ 800 ሚሊዮን ዶላሩ በምርት ላይ ይመለስለታል፡፡ ያንን 800 ሚሊዮን ዶላር የት ላይ እንዳወጣ አናውቅም ነበር፡፡ ለምሳሌ አንዱ መሥፈርት እያደረግነው ያለው ጉዳይ ኩባንያው  ወደ ኢትዮጵያ ሲመጣ የኢትዮጵያ አየር መንገድን ካልተጠቀመ አንከፍልም፡፡ ግዴታም የለብንም፡፡ ሁለተኛ በኢትዮጵያ ውስጥ የሚንቀሳቀሱ ባንኮችን ተጠቅሟል አልተጠቀመም? የሚሉ መሥፈርቶች አሉ፡፡ አንዳንዱ በራሳችን አገርና ሀብት ላይ እና ራሳችን ተጫውተናል እንደ መንግሥት፣ ትክክል ያልሆነ ነው፡፡ ለኩባንያው በምርት ጊዜ የሚመለስ ካለ ብሩ መንቀሳቀስ ያለበት እዚህ አገር ውስጥ ነው፣ ይህንን አስተካክለናል፡፡ አንዳንዶቹ ወጪያቸው የት እንዳለ ማሳወቅ ስለማይፈልጉ ይኼንን አይፈልጉትም፡፡ እነዚህ ኩባንያዎች ደላሎች ናቸው፡፡ ትክክለኛ ኩባንዎች አይደሉም፡፡ ከዚያ ባሻገር በመንግሥት ደረጃ በሕግ፣ በአሠራር ያሉ ነገሮች በጣም የተሻለ ብቻ ሳይሆን ማንኛውም ኩባንያ ከውጭም ሆነ ከአገር ውስጥ መጥቶ ኢንቨስት ለማድረግ ከዚህ በፊት ያልነበረ አስቻይ ሁኔታ መንግሥት ፈጥሯል፡፡

ጥያቄ፡ በሲሚንቶ እጥረትና የምርት ሁኔታ ላይ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ምን እየሠራ ነው?

ታከለ (ኢንጂነር) ጥያቄው የሲሚንቶ ዋጋ ጨምሯል ቀንሷል ሊሆን አይገባውም፡፡ ኢትዮጵያ በትንሹ የሚያስፈልጋት 50 ሚሊዮን ቶን ነው፡፡ እኛ ግን በዓመት እያመረትን  ያለነው አምስት ሚሊዮን ቶን ነው፡፡ በአምሰት ሚሊዮን ቶን ምርትና በ50 ሚሊዮን ቶን ፍላጎት መካካል ያለው የአቅርቦትና የፍላጎት ችግር ነው፡፡ ስለዚህ በሁለት መንገድ እየፈታን ነው፡፡ አንደኛው ያሉን ፋብሪካዎች በሙሉ አቅማቸው እንዲያመርቱ የሚያስፍልጋቸውን ግብዓት ክልሎች ከመቼውም ጊዜ በላይ በተለይም ግብዓቱን የሚያቀርቡት የኦሮሚያ፣ ቤኒሻንጉልና ደቡብ ምዕራብ ክልሎች ግብዓቶቹ ሳይቆራረጡ የእያንዳንዱ ኬላ ላይ ሳይገደብ እንዲሠሩ ነው፡፡ ሁለተኛ የፀጥታ ጉዳይ ነበር ሙሉ በሙሉ ፋብሪካዎችና ኳሪ ሳይቶች እየተጠበቁት ያሉት በሚሊተሪ ነው፡፡ ሦስተኛ የዶላር ጉዳይ ነበር መንግሥት ሙሉ በሙሉ ፈቶላቸዋል፡፡ አሁን የቀረው በመሀል ያለው የንግድ ሰንሰለት ነው፡፡ ከንግድ ሚኒስቴር ጋር አንድ ላይ በመሆን መሀል ያለውን ኤጀንት ሙሉ በሙሉ እንዲወጣ፣ ፋብሪካው ምርቱን ቀጥታ እንዲሸጥ፣ የመንግሥት ፕሮጀክቶች ቀጥታ እንዲወስዱ፣ የቀረው ደግሞ ኮታ ተሠርቶለት ክልሎችና የከተማ አስተዳደሮች በራሳቸው ቦታ እንዲሸጡ ነው፡፡ ይኼኛው የሦስት ወር ወይም የአንድ ዓመት ፕሮጀክት ሊሆን ይችላል፡፡ ዋናው ጥያቄ ትላልቅ ኩባንያዎች በአገር ደረጃ መጥተው፣ ያሉት ፋብሪካዎች የማምረት አቅማቸውን እንዲጨምሩ፣ አዲስ ኩባንያዎች ደግሞ ገብተው ሲሚንቶ እንዲያመርቱ ነው፡፡ ዋናው ጥያቄ ትላልቅ ኩባንያዎች ወደ አገር ውስጥ መጥተው፣ ያሉት ፋብሪካዎች ምርቶቻቸውን እንዲጨምሩ (ፕሮዳክሽን እንዲጨምሩ) ሲሚንቶ እንዲያመርቱ ነው፡፡ ምክንያቱም የእኛ ፍላጎትና አቅርቦት በፍፁም አይገናኝም፡፡ ኢትዮጵያ የመቶ ሚሊዮን ሕዝብ አገር ናት ይህንን ከጂዲፒ አንፃር ሲሰላ በትንሹ የሚያስፈልገን መቶ ሚሊዮን ቶን ነው፡፡ 50 ሚሊዮን ብናደርገውም የሚያስፈልገን ያን ያህል ነው፡፡ ነገር ግን የምናመርተው አምስት ሚሊዮን ቶን ነው፡፡ አልደረስንበትም ለዛ ነው መንግሥት ኩባንያዎች የሲሚንቶ ፋብሪካዎች እንዲገነቡ መንግሥት ብዙ ነገር እያደረገ ያለው፡፡ ለምሳሌ ሲሚንቶን ለማበረታት የታክስ ሆሊዴይ ካደረግን ሦስትና  አራት ዓመታት ሆኖናል፡፡ ከዚህ በፊት ግብዓቶች እንዲጠቀሙ ያደረግነው ከወጣቶች እንዲጠቀሙ ነበር፡፡ አሁን ራሳቸው እንዲያመርቱ አድርገናል፡፡

ጥያቄ፡ እነዚህ ኩባያዎች ላይሰንስ ወስደው ሲሠሩ በተለያየ መንገድ ምርት መጨመር አልቻሉም፣ ወርቅን  ብንወስድ  ሳይታወቅ ያወጣሉ ይኼንን ሚኒስትር መሥሪያ ቤቱ በምን መንገድ ነው የሚከታተለው ወይም ሲከታተል የቆየው?

ታከለ (ኢንጂነር) አዋጅ ላይ አንዱ ያስተካከልነው ይኼንን ነው፡፡ ከዚህ በፊት የነበረው አዋጅ ላይ የኮንስትራክሽን ማቴሪያልና ባህላዊና አነስተኛ ወርቅ ምርት ክልሎች ይሰጣሉ ይላል፡፡ ይኼ ሁለት መሠረታዊ የሆኑ ስህተቶች አሉበት፡፡ አንደኛ ወርቅ ማለት በጣም አላቂ የሆነ ውድ ሜታል ነው፡፡ አንዳንድ የውጭ ኩባንያዎች ምን ያደርጋሉ፣ ወጣቶችን ወይም የተወሰኑ ሰዎችን ታች ያደራጁና 40/60 ወይም 70/30 ቀመር ሠርተው፣ ከፊት ለፊት ያለው ኢትጵያዊ ኩባንያ አድርገው ይንቀሳቀሱ፡፡ ከኋላ ማሽን የሚያቀርበውና ወርቁን ይዞ የሚወጣው ከኋላ ያለ ሌላ ሰው ነው፡፡ ይኼንን በአዋጅ አስተካክለናል አንዳችም የውጭ ኩባንያው ከክልል ጋር መሥራት የለበትም የፌዴራል መንግሥት እስካላወቀው ድረስ አንድ የተስተካከለው ይኼ ነው፡፡ ሁለተኛ የኮንስትራክሽን ማቴሪያል ተብሎ ትላልቅ የከሰልን የእምነ በረድን ጥቁር ድንጋይ የሚፈጩት ወደ ክልል የወረደበት አሠራር ስህተት ነበር፡፡ አንዱ በዚህ አገር የጀስቲስ ኢሹ አለ ተብሎ ከፖለቲካ ኢኮኖሚ ሪፎርም በፊት የነበረው ነገር ይኼ ነው፡፡ አንድ አገር ነው ያለችን ይኼንን አንድ አገር የምናሳድግበት የራሱ ዓውድና ሕግ ያስፈልገዋል እንጂ በተበጣጠሰ መንገድ መሄድ አንችልም አዋጁ የተስተካከለው ይኼ ነው፡፡

በአዲሱ አዋጅ በቅርብ ጊዜ በፓርላማ የሚፀድቀው አሁን የተጠየቀውን ጥያቄ ይመልሳል፡፡ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የተጠናው ጥናት የሚያሳየው 50 በመቶ ብቻ ነው ወደ ባንክ የሚመጣው ኮንትሮባንድ የሚባለው አንዳንዱ ከኮንትሮባንድም ይዘላል፡፡ ብዙ ቻይኖች እዚህ ውስጥ ተዋናይ ናቸው ማሽን ያቀርባሉ ወርቁን ካመረቱ በኋላ ለምሳሌ አሥር ኪሎ ካመረቱ ፈቃዳቸው እንዳይነጠቅ አንድ ኪሎ ያቀርቡና የቀረውን ይዘው ይኼዳሉ መንግሥት ይኼንን ለመቆጣጠር በአዋጅ ደረጃ ነው ያስተካከለው አንዱ የምንፈታው ይኼ ነው በአዋጅ ይስተካከላል፡፡

ጥያቄ፡ ፍቃዱ ሲሰረዝ እነዚህ ኩባንያዎች መሥሪያ ያደረጉት የተወሰነ ካፒታል ይኖራል፣ ማሽነሪም ሆነ ሌላ ለዚህ ጉዳይ ማካካሻ ታደርጋላችሁ ወይስ ማሽናቸውን ትተው ነው የሚወጡት?

ታከለ (ኢንጂነር) ምንም ይዘው ስላልመጡ የምንክሰው ነገር አይኖርም፡፡ ግልጹን ለመናገር ፈቃዳቸው የተሰረዘ ኩባንያዎች በብዛት ሌቦች ናቸው፡፡ በብዛት ኮንትሮባንዲስቶች ናቸው፡፡ በብዛት ደላለሎች ናቸው በብዛት ሰላዮች ናቸው ለእነዚህ የምንከፍለው ምንም ነገር የለም፡፡

ጥያቄ፡ የወርቅ መግዣ ዋጋን ብሔራዊ ባክ ወደ 35 በመቶ ከፍ አድርጎታል፣ ይኼ ማለት ብሔራዊ ባንክ በትይዩ (ብላክ) ገበያ ነው እየገዛ ያለው መልሶ ደግሞ በኦፊሺያል ኤክስቼንጅ ነው እየሸጠ ያለው፡፡ በዚህ ደግሞ ምንዛሪ ሉዝ እያደረገ ነው ይኼ ጉዳይ እንዴት ይታያል?

ታከለ (አንጂነር) ዘ ሎው ኦፍ ክሬሽን የሚገባ ቲዎሪ አለ፡፡ ለምሳሌ የእኛ ብር ከዶላር አንፃር ምንድነው የሚለውን ስናይ፣ እኛ በዚህ ሰዓት የምንፈልገው ወርቅ ነው፣ ይህንን የምንፈልገው ወርቅ በዶላር ስለሆነ ሪዘርቭ ነው፡፡ ያንን ኦፍሴት ለማድረግ መንግሥት የሚከፍለው ዋጋ ነው፡፡ 30 በመቶ ከዓለም አቀፍ ዋጋ በላይ ስንገዛ የምንፈልገው ዶላሩን ወይም ወርቅ ነው፡፡ ይኼ ደግሞ የሆነው በተለይ አምራቹን ለማበረታት ስለሆነ አምራቹ 50 ግራም እየሆነ ሲሄድ ከዓለም አቀፉ ዋጋ ላይ ሲደመር 35 በመቶ በኢትዮጵያ ብር ያገኛል፡፡ ይኼ ደግሞ ዋና የታሰበበት ምክንያት ኮንትሮባንድን ለመከላከል ወይም ወርቅ ከአገር ሳይወጣ እዚሁ ለማስቀረት ነው፡፡ አንድ በቅርቡ የምንጀምረው ነገር አለ ኩባንያዎችን እየመረጥን ነው፡፡ የወርቅ ሪፋይን ብዙ ነገሮችን የሚፈታልን ነው ይህንን በአገር ደረጃ ወርቅን ሪፋይን ማድረግ ከቻልን አሁን የምናነሳቸውን ብዙ ነገሮች እናስቀራለን፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች