በኦሮሚያ ክልል በምዕራብ ወለጋ ዞን ጊምቢ ወረዳ ቶሌ ቀበሌ ቅዳሜ ሰኔ 11 ቀን 2014 ዓ.ም. በንፁኃን ላይ የተፈጸመውን ጭፍጨፋ፣ የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር አወገዘ፡፡
ሚኒስቴሩ በንፁኃን ላይ የደረሰውን ጭፍጨፋ ያወገዘው ሐሙስ ሰኔ 16 ቀን 2014 ዓ.ም. በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን አዳራሽ፣ የኢትዮጵያ ሴቶች ማኅበራት ቅንጅት ባዘጋጀው ‹‹የሴቶች የሰላም ግንባታ መርሐ ግብር›› ላይ ነው፡፡
የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር) እንደተናገሩት፣ በኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት እየተከሰቱ ያሉ ጦርነቶች፣ ግጭትና የተፈጥሮ አደጋዎች ማኅበረሰቡን ለከፋ ሥነ ልቦና፣ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ ዳርጎታል፡፡
በዚህ በአስከፊና አሰቃቂ ድርጊት ይበልጥ ተጋላጭ የሆኑት ደግሞ ሴቶችና ሕፃናት መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡ በምዕራብ ወለጋ ዞን ጊምቢ ወረዳ ቶሌ ቀበሌ የተፈጸመው ጭፍጨፋ የብዙ ንፁኃንን ደም ማፍሰሱን፣ አሰቃቂና ኢሰብዓዊ ድርጊት መሆኑን ሚኒስትሯ ተናግረዋል፡፡
በዚህ ጭፍጨፋ በርከት ካሉ የኅብረተሰብ ክፍሎች በአብዛኛው ሴቶችና ሕፃናት መሆናቸውን ገልጸው፣ ይህንን ኢሰብዓዊ ድርጊት ሚኒስቴር መሥሪያ ቤታቸው በፅኑ ያወግዛል ብለዋል፡፡
ችግር፣ ጦርነትና ግጭት ባለበት ጊዜ ተንቀሳቅሶ ለመሥራት አስቸጋሪ መሆኑን፣ ችግሮች ከመከሰታቸው በፊት ሰላም ለማምጣት መሥራት የሚጠበቅበት ወቅት መሆኑን ሚኒስትሯ አብራርተዋል፡፡
የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ወ/ሮ ሳህለ ወርቅ ዘውዴ በበኩላቸው፣ ኢትዮጵያ በርካታ ውጣ ውረዶች እያለፈች መሆኑንና አሁንም እያለፈች ትገኛለች ብለዋል፡፡
የሰላም ዕጦት እርስ በርስ እንደሚያፋጅ፣ ለዚህም ከፍተኛ ዋጋ እየከፈሉ ያሉት ንፁኃን ዜጎች መሆናቸውን፣ በተለይም ደግሞ ሴቶችና ሕፃናት የችግሩ ገፈት ቀማሽ እንደሆኑ አስረድተዋል፡፡
ባለፉት ቀናት የተፈጸመውን የንፁኃን ዜጎች ጭፍጨፋ ያወሱት ፕሬዚዳንቷ፣ ሊከሰት የማይገባው መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡ በሌሎች ጉዳዮች መገዳደል ሊኖር እንደሚችል የጠቆሙት ፕሬዚዳንቷ፣ ነገር ግን በማንነትና በሃይማኖት ምክንያት ሰዎች መገደል እንደሌለባቸው ተናግረዋል፡፡
ይህንን ጉዳይ ‹‹አይሆንም››፣ ‹‹ትክክል አይደለም›› ማለት እንደሚገባ ገልጸው፣ የቀይ መስመር ድንበርን ሲታለፍና ዝምታ ሲበዛ የሚከሰት መሆኑን አስረድተዋል፡፡
የሰላም ዕጦት ብዙዎች ያለቁበትና ሴቶች ለፆታዊ ጥቃት የታገለጡበት መሆኑን ተናግረዋል፡፡