Friday, September 29, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን ከ352 ሺሕ ኩንታል በላይ የምርጥ ዘር ሊያቀርብ ነው

ተዛማጅ ፅሁፎች

በቅርቡ ለተቋቋመው የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ ተጠሪ የሆነው የኢትዮጵያ ግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን፣ በ2015/16 የምርት ዘመን ለአርሶና አርብቶ አደሩ እንዲሁም በግብርና ዘርፍ ለተሰማሩ ባለሀብቶችና ለሌሎች ተጠቃሚዎች የሚደርስ ከ352 ሺሕ ኩንታል በላይ የምርጥ ዘር ለማዘጋጀት እንቅስቃሴ መጀመሩን አስታወቀ፡፡

ኮርፖሬሽኑ ይህንን ያስታወቀው ለ2014/15 የሰብል ዘመን ለመኸር እርሻ የሚውሉ የተለያዩ የሰብል ምርጥ ዘሮች፣ የአፈር ማዳበሪያና ሌሎች ግብዓቶችን ሥርጭት፣ እንዲሁም ለ2015/16 የሰብል ዘመን የሚቀርቡ የምርጥ ዘር መሬት ዝግጅት አስመልክቶ ለሚዲያ አካላት በተዘጋጀ የመስክ ምልከታ ወቅት ነው፡፡

ኮርፖሬሽኑ 22 የሰብል ዓይነቶችንና 69 ዝርያዎችን ብዜት በራሱ፣ በኮንትራት እርሻዎችና በአርሶ አደር ማሳዎች እንደሚያለማ ተገልጾ፣ ይህም በአገር ደረጃ ከሚያስፈልገው የምርጥ ዘር ፍላጎት ውስጥ 30 ከመቶ የሚሆነውን የሚያቀርብ መሆኑ ታውቋል፡፡

የኢትዮጵያ ግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን የኮርፖሬት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት ኃላፊ አቶ ጋሻው አይችሉህም ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ በ2013/14 የምርት ዘመን 14,608 ሔክታር መሬት በዘር በመሸፈን 281,852 ኩንታል ዘር የተመረተ ሲሆን፣ ከዚህም ውስጥ እስከ ሰኔ አጋማሽ ድረስ 155,348 የተበጠረ ምርጥ ዘር ለተጠቃሚዎች መሠራጨቱን አስታውቀዋል፡፡

ምርጥ ዘር የሰብልን ምርታማነት ከሚያሳድጉና በጥናትም እንደተለየው 50 በመቶውን የሚሸፍኑ ግብዓቶች መሆናቸውን የተናገሩት አቶ ጋሻው፣ ኮርፖሬሽኑም ለቀጣዩ የምርት ዘመን የሚሆን 365 ሺሕ ኩንታል የምርጥ ዘር ለማምረትና ያንንም ለአርሶ አደሩ ለማቅረብ ዝግጅት ላይ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የምርጥ ዘርን በማባዛት ረገድ ኮርፖሬሽኑ ተጨማሪ መሬቶች እንደሚያስፈልጉት የተገለጸ ሲሆን፣ ይህንን የዘር ማባዣ መሬት እጥረት ለመቅረፍ የቆላማ አካባቢዎች ወዳሉባቸው ክልሎች ገብቶ የማልማት እንቅስቃሴ መጀመሩ ተመላክቷል፡፡ ለአብነትም አዲስ በተዋቀረው የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል 1,070 ሔክታር መሬት ማግኘቱ ተገልጾ፣ በተጨማሪም 10,000 ሔክታር መሬት ለማግኘት ጥያቄ እንደቀረበና ከዚህም ውስጥ 6,000 ሔክታር የሚደርሰውን ወደ ውጭ የሚላኩ የቅባት እህሎችን ማምረት የኮርፖሬሽኑ ዋነኛ ዕቅድ መሆኑ ተጠቅሷል፡፡

አቶ ጋሻው አያይዘው እንደገለጹት፣ ከደቡብ ምዕራብ ክልል ባሻገር አዳዲስ የምርጥ ዘር ማባዣ መሬቶች ለማግኘት ከቤኒሻንጉል ክልላዊ መንግሥት ጋር ሰፊ ውይይት ተደርጎ ከሞላ ጎደል መሬት ለማግኘት የሚያስችል ደረጃ መደረሱን፣ በጋምቤላ ክልል እንደዚሁ መሬት በቅርቡ ለማግኘት መቃረባቸውን አስታውቀዋል፡፡ ኮርፖሬሽኑ በዚህ ወቅት ያለው 14,608 ሔክታር መሬት በቂ ስላልሆነ በአፋርና ሶማሌ ክልሎች ገብቶ ለመሥራት መታቀዱ ተገልጿል፡፡

ግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን ከዚህ በተጨማሪ በተለያዩ የኮርፖሬሽኑ ሱቆች ለተጠቃሚዎች (ባለሀብቶች) የሚቀርብ የአፈር ማዳበሪያ፣ አግሮ ኬሚካል የእርሻ መሣሪያዎችና ሜካናይዜሽን አገልግሎት በመላው አገሪቱ ተደራሽ ለማድረግ ሰፊ እንቅስቃሴ እያደረገ እንደሚገኝ የተገለጸ ሲሆን፣ ለአብነትም እስከ ሰኔ 12 ቀን 2014 ዓ.ም. ድረስ ከሦስት በሊዮን ብር በላይ ዋጋ ያላቸውን የአፈር ማዳበሪያ፣ አግሮ ኬሚካሎች፣ የእንስሳት መድኃኒትና የኬሚካል መርጫ መሳሪያዎች ለተጠቃሚዎች ማቅረቡን አስታውቋል፡፡

በኢትዮጵያ ግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን የአሰላ ግብርና ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ብርሃኑ የሺጥላ ለሪፖርተር እንዳስታወቁት፣ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቱ በጎንዴ ኢተያ አካባቢ መሥራች ዘር እርሻ በማባዛት፣ በአሰላ ዘር ማምረቻ፣ ማዘጋጃና ማሠራጫ ማዕከል ላይ በማዘጋጀት ለአርሶ አደሮችና ለዘር አምራቾች ያሠራጫል ብለዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቱ የእርሻ ተረፈ ምርት የሆኑትን አገዳ፣ ገለባ እንዲሁም በማሳ ዙሪያ ያሉ ሳሮችን በዙሪያ ላሉ አርሶ አደሮች ድጋፍ እንደሚደረግ ተገልጿል፡፡

60 ሺሕ ኩንታል ዘር በማስገባት ወደ 53 ሺሕ የሚደርስ ንፁሕ ዘር በማውጣት 30 ሺሕ ኩንታል ምርጥ ዘር ለአርሶ አደሩ ማከፋፈላቸውን የተናገሩት አቶ ብርሃኑ፣ በዚህ ወቀት 15 ሺሕ ኩንታል የሚሆን ጤፍ በአራት ዝርያዎች መዘጋጀቱ ተናግረው፣ ሌሎች የሰብል ዝርያዎችን እንዲሁ ዝግጁ መደረጋቸውን አስታውቀዋል፡፡  

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች