Thursday, May 23, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

በዶሮና እንቁላል ላይ ተከስቷል የተባለው ያልታወቀ በሽታ ወደ ሰው እንደማይተላለፍ እንዲገለጽ ተጠየቀ

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ዶሮ አርቢዎች፣ የግብርና ሚኒስቴር በዶሮና የለማ እንቁላል ላይ የጣለባቸው ዕገዳ መቼ እንደሚነሳና ተከስቷል ስለባለው በሽታ የሚደረገው ጥናት በምን ደረጃ ላይ እንደሚገኝ፣ እንዲሁም በሽታው ወደሰው አይተላለፍም ተብሎ እንዲገለጽ ዓርብ ሰኔ 17 ቀን 2014 ዓ.ም. በተቋሙ በመገኘት ጥያቄ አቀረቡ፡፡

በመገናኛ ብዙኃን ስለበሽታው መከሰት እንደተሠራጨው ሁሉ፣ በሽታው ወደ ሰው እንደማይተላለፍና ኅብረተሰቡ ዶሮና እንቁላል እንዲመገብ በተመሳሳይ መንገድ እንዲተላለፍ ጠይቀዋል፡፡

‹‹ዕገዳው ከተላለፈበት ቀን ጀምሮ ለ15 ቀናት ከፍተኛ ኪሳራ እየገጠመን ነው፡፡ ለምግብነት የሚውሉ እንቁላሎችን ሳንሸጥ አሁን ላሉት ዶሮዎች መኖ መግዛት አቅቶናል፤›› ብለዋል፡፡

ከተከሰተው የዶሮ በሽታ የበለጠ ዶሮዎቹ በመኖ እጥረት እንዳይሞቱ ሥጋታቸውን ገልጸው፣ የዶሮ በሽታው በአሁኑ ጊዜ ከፍተኛ መቀዛቀዝ ያሳየ በመሆኑ የግብርና ሚኒስቴር ይህን በመገንዘብ አፋጣኝ ውሳኔ እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል፡፡

ጉዳዩን በተመለከተ ቅሬታቸውን ሲቀበሉ የነበሩት በግብርና ሚኒስቴር የዶሮ ዕርባታ ዘርፍ ዳይሬክተር፣ ዕገዳው በዶሮ አርቢዎች ላይ ኪሳራ እንደሚያስከትል ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ይገነዘባል ብለዋል፡፡ ከ15 ቀናት በፊት ተከስቶ የነበረው በሽታ በሁሉም የዶሮ ዕርባታ ድርጅቶች ላይ ሳይሆን፣ በጥቂት አርቢዎች ላይ በመሆኑ ሥርጭቱ ሳይጨምር አሁን በሽታው እየተቀዛቀዘ መምጣቱን ዳይሬክተሩ ገልጸዋል፡፡ እየቀነሰ የመጣውን በሽታ ሙሉ በሙሉ ለመቆጣጠርና ዶሮና እንቁላል እንዴት ወደ ኅብረተሰቡ መሠራጨት እንደሚችሉ አዲስ መመርያ ተዘጋጅቷል ብለዋል፡፡

የበሽታውን ምክንያትና የቁጥጥር ሥራ የሚያከናውን በሚኒስትር መሥሪያ ቤቱ ኮሚቴ መቋቋሙን፣ ኮሚቴው ችግሩን ሙሉ ለሙሉ ለመቅረፍ በተቀናጀ መንገድ እየሠራ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡

ዶሮ አርቢዎች ቅሬታቸውን ለግብርና ሚኒስቴር ሲያቀርቡ የተቋሙ ኃላፊዎችን ደግሞ ዕገዳውን ለማንሳት፣ የዶሮ አርቢዎች ዕገዛ ያስፈልጋል ማለታቸው ተሰምቷል፡፡

የግብርና ሚኒስቴር፣ የዶሮ ዕርባታ ድርጅቶች ዶሮና እንቁላል ወደ ገበያ እንዳያቀርቡ ያስተላለፈው ዕገዳ ባለመነሳቱ፣ ኬላ ላይ ገንዘብ እየከፈሉ ሕገወጥ ድርጊት የሚፈጽሙትን በመጠቆም በጋራ መሥራት እንደሚያስፈልግ፣ የግብርና ሚኒስቴር ኃላፊዎች ማሳሰባቸውም ታውቋል፡፡

የግብርና ሚኒስቴር ሰኔ 3 ቀን 2014 ዓ.ም. ለዶሮ አርቢዎችና ላኪ ድርጅቶች በጻፈው ደብዳቤ መሠረት ወደ አዲስ አበባ ሊገቡ የነበሩና ወደ ውጭ የሚላኩ የተፈለፈሉ ጫጩቶችና እንቁላሎች በመታገዳቸው፣ የዶሮ ዕርባታ ድርጅቶች ኪሳራ እየገጠማቸው ስለሆነ ዕገዳውን ተላልፈው ምርቶቹን እየሸጡ መሆናቸውን ኃላፊዎቹ አስታውቀዋል፡፡

ይህንን ድርጊት የሚፈጽሙት ሁሉም የዶሮ አርቢዎች አለመሆናቸውን፣ ቁጥራቸው ጥቂት የሆኑ ድርጅቶች መኖራቸውን ኃላፊዎቹ አክለው ገልጸዋል፡፡ ሰኔ 10 ቀን 2014 በግብርና ሚኒስትር ደኤታ ፍቅሩ ረጋሳ (ዶ/ር) የተመራ ቡድን ከዶሮ ዕርባታ ድርጅቶችና ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ባደረገው ስብሰባ፣ ዕገዳው ለአጭር ቀናት ቆይቶ ሰኞ ሰኔ 13 ቀን 2014 ዓ.ም. እንደሚነሳ አስታውቆ ነበር፡፡

በስብሰባው ላይ ኅብረተሰቡን የማረጋጋት ሥራ መሥራት እንደሚያስፈልግ ተጠቁሟል፡፡ ነገር ግን የተራዘመው የዕገዳ ጊዜ አልፎ ብዙ ሺሕ ጫጩቶችን እያስወገዱ ቢሆንም፣ ለምግብነት የሚውሉ እንቁላሎችም ባለመሸጣቸው፣ ድርጅቶቹ ከፍተኛ ኪሳራ እየደረሰብን ነው ብለዋል፡፡

ከአንድ ወር በፊት በተለያዩ አካባቢዎች ተከስቷል የተባለው ስሙ ያልታወቀው የዶሮ በሽታ ምክንያት፣ የግብርና ሚኒስቴር ያስተላለፈው ዕገዳ በገበያው ውስጥ የምርት እጥረት እንዲኖርና ድርጅቶቹ እንዲከስሩ ምክንያት መሆኑን አርቢዎች ይናገራሉ፡፡

ሰኔ 3 ቀን 2014 ዓ.ም. የግብርና ሚኒስቴር፣ ‹‹በተለያዩ ቦታዎች የዶሮ ሞት ክስተት እያጋጠመ በመሆኑ ችግሩ ተጣርቶ መፍትሔ እስከሚሰጥበት ድረስ የዶሮና የዶሮ ውጤቶች ገቢና ወጪ ላልተወሰነ ጊዜ ታግዷል፤›› ሲል፣ በግብርና ሚኒስቴር የኳረንቲን ኢምፖርት ኤክስፖርት ኢንስፔክሽንና ሰርተፊኬሽን ዳይሬክተር ወንድማገኝ ደጀኔ (ዶ/ር) የተፈረመ ደብዳቤ መውጣቱ አይዘነጋም፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች