Wednesday, February 28, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ለአፈር ማዳበሪያ ግዥና ሥርጭት ከ64.5 ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ ተደርጓል

ተዛማጅ ፅሁፎች

ፋኦ ለትግራይ ክልል የማዳበሪያ ግዥ ለመፈጸም ጥያቄ አቀረበ

መንግሥት ለ2014/15 የሰብል ዘመን እንዲውል ወደ አገር ውስጥ ላስገበው የአፈር ማዳበሪያ ግዥ፣ ማጓጓዣና ሌሎች ወጪዎች ከ64.5 ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ ማውጣቱ ተገለጸ፡፡

የኢትዮጵያ ግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን እንዳስታወቀው፣ ለተያዘው ዓመት የሰብል ዘመን 12,876,623.5 ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ግዥ ተፈጽሟል፡፡

መንግሥት ከውጭ ለተገዙ የኤንፒኤስ (NPS)፣ ኤንፒኤስ ቦሮን (NPSB)፣ እንዲሁም የዩሪያ ማዳበሪያ የትራንስፖርትና ሌሎች አስተዳደራዊ ወጪዎች ሳይጨመሩ ከ50 ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ ማውጣቱ የተገለጸ ሲሆን፣ ከዚያ ውጪ ለመርከብ ማጓጓዣ፣ ለከረጢትና ለአስተዳደራዊ ወጪዎች ከ14.5 ቢሊዮን ብር በላይ መውጣቱን የኢትዮጵያ ግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን የኮርፖሬት ኮምዩኒኬሽን አገልግሎት ኃላፊ አቶ ጋሻው አይችሉህም ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

ከተገዛው የአፈር ማዳበሪያ ውስጥ ከሞሮኮ ኦሲፒ (OCP) ኩባንያ የተገዛው ከ7.8 ሚሊዮን ኩንታል በላይ የአፈር ማዳበሪያ በ13 መርከቦች ተጓጉዞ በአገር ውስጥ ለአርሶ አደሩ እየቀረበ እንደሚገኝ፣ ኮርፖሬሽኑ አንድ ቶን ኤንፒኤስ የማዳበሪያ ዝርያውን በ650 ዶላር፣ እንዲሁም ኤንፒኤስ ቦሮንን ደግሞ አንዱን ቶን በ660 ዶላር መግዛቱ ተጠቁሟል፡፡

ከማዳበሪያ ዓይነቶቹ በውድነቱ የሚታወቀው የዩሪያ ማዳበሪያ በተለይም በሩሲያና በዩክሬይን ጦርነት ሳቢያ ምርቱ ከዓለም አቀፍ ገበያ መጥፋቱ ብቻ ሳይሆን፣ ሌሎች አምራች አገሮች ምርቱን ለመያዝ እንዳስገደዳቸው ተነግሯል፡፡ ከዚህ ባሻገር የገንዘብ አቅም ያላቸው አገሮች ደግሞ በገበያ ላይ ያለውንም ምርት በመቀራመታቸው፣ አንዱ ቶን የዩሪያ ማዳበሪያ መንግሥት ከ1,210 ዶላር በላይ በሆነ ዋጋ እንዲገዛ ምክንያት መሆኑን አቶ ጋሻው ገልጸዋል፡፡

ለዘንድሮ ምርት ፈርቲግሎብ (Fertiglobe) ከተባለው ዓለም አቀፍ የአፈር ማዳበሪያ አምራች ኩባንያ ከተገዛው 5,001,100 ኩንታል የዩሪያ ማዳበሪያ ውስጥ፣ ከ3.8 ሚሊዮን ኩንታል የሚሆነው በሰባት ዙር ከጅቡቲ ወደ አገር ውስጥ መግባቱን ያስታወቁት የኮሙዩኒኬሽን ኃላፊው፣ እስከ ሰኔ 30 ቀን 2014 ዓ.ም. ድረስ ቀሪው ተጓጉዞ ይጠናቀቃል የሚል እምነት እንዳላቸው ተናግረዋል፡፡

በተያያዘም የተለያዩ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ማዳበሪያን ብቻ ሳይሆን የምርጥ ዘርና ሌሎች የግብርና ግብዓቶችን ለትግራይ ክልል ለማዳረስ ጥያቄ አቅርበው፣ የግብርና ሚኒስቴር ፈቃድ እየሰጠ መሆኑን ሪፖርተር ለማረጋገጥ ችሏል፡፡

ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ይኼንን አስመልክቶ ለኢትዮጵያ ግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን (የኢትዮጵያ ምርጥ ዘር ድርጅት) እና ሌሎች አገሪቱ ውስጥ ላሉ ድርጅቶች ደብዳቤ እየተጻጻፈ ሲሆን፣ በደብዳቤው መሠረት አጋር አካላቱ ወደ ለትግራይ ክልል የሚላኩ የአፈር ማዳበሪያና ምርጥ ዘር ቅድሚያ ተሰጥቷቸው እንዲያገኙ እየተደረገ መሆኑም ታውቋል፡፡

ለአብነትም የዓለም የእርሻና የምግብ ድርጅት (ፋኦ) በትግራይ ክልል ለዘንድሮ የምርት ዘመን የሚያገለግል የአፈር ማዳበሪያና የምርጥ ዘር በግብርና ሚኒስቴር ይሁንታ፣ ከግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን ለመግዛት ጥያቄ ማቅረቡን ማረጋገጥ ተችሏል፡፡ ነገር ግን ፋኦ ምን ያህል መጠን ያለው ማዳበሪያና ሌሎች የግብርና ግብዓቶችን ለትግራይ ክልል ለመግዛት እንደፈለገ መጠኑን አላሳወቀም፡፡

ፋኦ በተጠናቀቀው አጋማሽ እንዳስታወቀው፣ አብዛኛው የትግራይ ክልል አርሶ አደሮች አስፈለጊውን የግብርና ዝግጅት አድርገው የዝናብ መምጣትን በመጠባበቅ ላይ ናቸው፡፡ ነገር ግን ውስን የሆነው የግብርና ግብዓቶች አቅርቦት፣ በተለይም ማዳበሪያና የምርጥ ዘር አቅርቦት የምርት ዘመኑ ዋነኛ ሥጋት መሆኑን አስታውቋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች