Thursday, November 30, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊሴቶችን በሰላምና ደኅንነት ላይ የሚያሳትፍ መርሐ ግብር  ይፋ ሆነ

ሴቶችን በሰላምና ደኅንነት ላይ የሚያሳትፍ መርሐ ግብር  ይፋ ሆነ

ቀን:

በኢትዮጵያ ሰላምና ደኅንነት እንዲጠበቅ ሴቶች ወሳኝ ሚናቸውን የሚወጡበት ብሔራዊ የድርጊት መርሐ ግብር ይፋ ሆነ፡፡

‹‹የኢትዮጵያ ሴቶች ለሰላም ግንባታ›› የሚል መሪ ቃል ያለውን የድርጊት መርሐ ግብር በተባበሩት መንግሥታት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን አዳራሽ  ሰኔ 16 ቀን 2014 ዓ.ም.  ይፋ የሆነው ፕሬዚዳንት ሳህለ ወርቅ ዘውዴ በተገኙበት ነው፡፡

መድረኩን ያዘጋጀው የኢትዮጵያ ሴቶች ማኅበራት ቅንጅት (ኢሴማቅ) ሲሆን፣ መርሐ ግብሩ በዋናነት የሴቶችን አቅም ለማጎልበት፣ ሴቶች ለሰላምና ደኅንነት እንዲቆሙና የሰላም እንቅስቃሴዎችን እንዲያስተባብሩ ያለመ መሆኑ በወቅቱ ተገልጿል፡፡

 ፕሬዚዳንት ሳህለ ወርቅ ዘውዴ በሥነ ሥርዓቱ ላይ እንደተናገሩት፣ በኢትዮጵያ የተፈጠሩ ግጭቶች ንፁኃን ሕይወታቸውን እንዲያጡ ከማድረጋቸውም በተጨማሪ ሴቶችንና ሕፃናትን ለከፍተኛ ጉዳት ዳርገዋል፡፡ 

 ‹‹በሰላም ዕጦት የተነሳ በርካታ ንፁኃን መገደላቸውን፣ በቅርቡ በንፁኃን ላይ የተፈጸመው ዘግናኝ ጭፍጨፋ የጭካኔነትና የአረመኔነት ጥግንም አሳይቶናል፤›› ያሉት ፕሬዚዳንቷ፣ ለዚህም ዋነኛ ሰለባ የሆኑት ሴቶችና ሕፃናት እንደመሆናቸው መጠን በሰላምና ግጭት አፈታት ላይ ወሳኝ ሚና ማኖር ይገባል ሲሉም አክለዋል፡፡

የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ በኦሮሚያ ክልል በወለጋ የተፈጸመውን አሰቃቂ ግድያ አውግዘው፣ በጭፍጨፋው ሴቶችና ሕፃናት አብዛኛውን ቁጥር እንደሚይዙ በመጥቀስ፣ ሴቶች የግጭት ሰለባና ተጠቂ ቢሆኑም፣ ሰላምን ለማስፈን ቁልፍ ሚና እንዳላቸው አስረድተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ሴቶች የሰላም ግንባታ መርሐ ግብር ወቅታዊና አስፈላጊ መሆኑን የገለጹት ሚኒስትሯ፣ መሥሪያ ቤታቸው ሰላምን ለማምጣት በጋራ ለመሥራት ፈቃደኛ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የአገር ደኅንነት የተጠበቀና የበለጠ አስተማማኝ እንዲሆን የሴቷ በሰላም ግንባታና ጥበቃ ላይ ተሳታፊነት ዋስትና መሆኑን ያመለከቱት የኢትዮጵያ ሴቶች ማኅበራት ቅንጅት (ኢሴማቅ) ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ ሳባ ገብረ መድኅን፣ በተለያዩ የኢትዮጵያ አካባቢዎች በነበሩ ግጭቶች በይበልጥ ተጋላጭና ተጎጂ የሆኑት ሴቶችና ሕፃናት መሆናቸውን አንስተው፣ የማኅበራቱ ቅንጅት ዘርፈ ብዙ ድጋፎች ማድረጉን አስታውሰዋል፡፡

በሰላም ዕጦት የተጎዱ ሴቶችና ሕፃናትን መደገፍ ዘላቂ መፍትሔ ባለመሆኑ፣ የሴቶች የሰላም ግንባታ መመሥረት አስፈላጊነቱን ጠቁመዋል፡፡

እንደ ባለድርሻ አካላት ሴቶች በሰላም አጀንዳ ላይ ራሳቸውን ማደራጀት ጀምረዋል ያሉት ወ/ሮ ሳባ፣ የኢትዮጵያ ሴቶች ሰላም ገንቢዎች ተቋም በኢትዮጵያ በዓይነቱ የመጀመርያ እንደሆነ አውስተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ሴቶች የሰላም ግንባታ መርሐ ግብር ዕውን መሆኑን ተከትሎ የምሥረታው የመጨረሻ ምዕራፍ ተሳታፊዎችና መሥራች አባላት ቃለመሀላ ፈጽመው የደረት አርማ አድርገዋል፡፡

የተባበሩት መንግሥታት የፀጥታው ምክር ቤት ውሳኔ 1325፣ ግጭቶችን በመከላከልና በመፍታት፣ በሰላም ድርድር፣ በሰላም ግንባታና ሰላም ማስበር፣ በሰብዓዊ ምላሽና ከግጭት በኋላ መልሶ ግንባታ ላይ የሴቶችን ጠቃሚነት ያረጋግጣል፡፡

ሰላምና ደኅንነትን ለመጠበቅና ለማስፈን በሚደረገው ጥረት ሁሉ የእኩልነትና ሙሉ ተሳትፎ አስፈላጊ መሆኑን አጽንኦት ሰጥቷል፡፡ በተጨማሪም ሁሉም ግጭት ውስጥ ያሉ አካላት ሴቶችና ልጃገረዶችን ፆታን መሠረት ያደረጉ ጥቃቶች፣ በተለይም አስገድዶ መድፈርና ሌሎች ፆታዊ ጥቃቶችን ለመከላከል ልዩ ጥንቃቄ ይጠይቃል፡፡

በተያያዘ ዜና ከፋና ወጊ የሴቶች ሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች አንዷ የሆኑት ወ/ሮ ዘውዴ አበጋዝ የኢትዮጵያ ሴቶች ካጋጠሟቸው መሠናክሎች ለመታደግ ለዓመታት ላበረከቱት በዋጋ የማይተመን አስተዋፅዖ ኢሴማቅ የስንዱ ሽልማትን አበርክቶላቸዋል፡፡

‹‹ስንዱ ሽልማት›› በኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት መንግሥት ዘመን (1923-1967) በነበረው ፓርላማ የመጀመርያዋ ኢትዮጵያዊት የፓርላማ አባል በነበሩት ወ/ሮ ስንዱ ገብሩ የተሰየመ ነው፡፡

የሴቶች መብት ተሟጋቿ ወ/ሮ ዘውዴ ባስተላለፉት መልዕክትም፣ ‹‹የሰላም ግንባታ ከልብ ቅንነት መደረግ ያለበት ነገር ብቻ ስለሆነ አስተውለን ማድረግ ይኖርብናል፤›› ብለዋል፡፡

   

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የመቃወም ነፃነት ውዝግብ በኢትዮጵያ

ስሟ እንዳይገለጽ የጠየቀችው በአዲስ አበባ ከተማ በተለምዶ የሾላ አካባቢ...

የሲሚንቶን እጥረትና ችግር ታሪክ ለማድረግ የተጀመረው አጓጊ ጥረት

በኢትዮጵያ በገበያ ውስጥ ለዓመታት ከፍተኛ ተግዳሮት በመሆን ከሚጠቀሱ ምርቶች...

የብሔር ፖለቲካው ጡዘት የእርስ በርስ ግጭት እንዳያባብስ ጥንቃቄ ይደረግ

በያሲን ባህሩ በሪፖርተር የኅዳር 9 ቀን 2016 ዓ.ም. ዕትም “እኔ...