Friday, December 1, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊየብቁ መምህራን ዕጦት የትምህርት ጥራት ዋናው ፈተና?

የብቁ መምህራን ዕጦት የትምህርት ጥራት ዋናው ፈተና?

ቀን:

በኢትዮጵያ ከታች ጀምሮ እስከ ከፍተኛ ትምህርት ድረስ ያለው የትምህርት አሰጣጥ ጥራት የጎደለው መሆኑ ታምኖበት የተሻሻለ የትምህርት ፍኖተ ካርታና ሥርዓተ ትምህርት ተቀርፆ በከፊል ወደ ሥራ ተገብቷል፡፡ በ2015 ዓ.ም. ደግሞ ሙሉ ለሙሉ ተግባራዊ ይደረጋል፡፡

ለትምህርት ጥራት ሥርዓተ ትምህርት መቅረፅ ወይም የትምህርት ፖሊሲን ማሻሻል ብቻ ውጤት የማያመጣ በመሆኑም፣ ብቁ መምህራንን ለማፍራት ጥረት እየተደረገና ሥልጠና እየተሰጠ ይገኛል፡፡ ሆኖም የትምህርትን ጥራት ለማስጠበቅ ትልቁን ሚና የሚጫወቱት መምህራን ላይ የብቃት ችግር እየገጠመ ስለመሆኑ በተደጋጋሚ ተነግሯል፡፡

በአዲስ አበባ ደረጃ ይህንን ችግር ለመፍታት ከሙዓለ ሕፃናት እስከ 12ኛ ክፍል ያሉ የግልም ሆነ የመንግሥት ትምህርት ቤት መምህራንን ተጨማሪ ሥልጠና ከመስጠት በተጨማሪ፣ በየዓመቱ የብቃት ምዘና እየተሰጠም ይገኛል፡፡ ይህ መሻሻሎችን እያሳየ ቢሆንም፣ በመምህራን ብቃት ማነስ ላይ የሚነሱ መሠረታዊ ችግሮች መነሳታቸው አልቀረም፡፡

በመምህርነት የሠለጠኑ ባለሙያዎችን በብቃት ማግኘት አለመቻል በተለይ የግል ትምህርት ቤቶች ትልቁ ፈተና ሆኗል፡፡ ፊዚክስ ተምረው እንግሊዝኛ ለማስተማር የሚያመለክቱበት፣ ኢንጂነሪንግ ተምረው አማርኛ ወይም ሒሳብ ለማስተማር የሚመጡበት በርካታ ከማስተማር ውጪ የተለያዩ የዲግሪ ባለቤቶች ለሥራ ፍለጋ እንደ ክፍት የሥራ መደብ የሚመጡበትም ከሆነ ሰንብቷል፡፡

በአንዱ ትምህርት ብቁ መምህር ተገኝቶ በሌላው ማጣት፣ ብቁ የተባሉና በተማሪዎቻቸውም ሆነ በትምህርት ቤቱ ምስጉን የሚባሉ መምህራን ከሥራ መልቀቅም ሌላው ችግር ነው፡፡

አንድ የግል ትምህርት ቤት ባለቤት እንደነገሩንም፣ ብቁ መምህራንን ለማግኘት ከባድ ነው፡፡ ከባድ ብቻ ሳይሆን የለም ማለት ይቻላል፡፡ በሚፈለገው የትምህርት ዘርፍና መንግሥት ባስቀመጠው ደረጃ ልክ መምህራን አለማግኘትም የትምህርት ዘርፉ ፈተና ነው፡፡ ለዚህም በትምህርት ቤታቸው ያጋጠማቸውንና የሌሎችም ችግር የሆነውን ለአብነት ያነሳሉ፡፡

ትምህርት ቤታቸው ላወጣው ሁለት እንግሊዝኛ መምህር ማስታወቂያ፣ 123 የኢንጂነሪንግ ምሩቃን ነበር ያመለከቱት፡፡ ለእያንዳንዱ ትምህርት ለሚወጣ ማስታወቂያ በብዛት የሚያመለክቱት ኢንጂነሪንግ ምሩቃን በመሆናቸው፣ የመምህራን የሥራ ቅጥር በሚተዋወቅበት የቴሌግራም ግሩፕ ላይ ‹‹እባካችሁ ኢንጂነሮች አታመልክቱ›› እስከመባል ደርሷል፡፡

እንደ አስተያየት ሰጪው፣ ብቁ አስተማሪ የለም፣ ፔዳጎጂ የተማረ አይገኝም፡፡  በሥራ ላይ እየለመዱ ብቁ ይሆናሉ ተብሎ እንደ ረዳት አስተማሪ እንዲሠሩ ሲደረግም፣ ጥቂት ዕውቀት ይዘው ይለቃሉ፣ ማስተማር ባያውቁም ማስተማርን ቀላል አድርገው ያያሉ፡፡ ፊዚክስ ተመርቀው ሒሳብ አያቅተንም፣ ሶሻል ተምረው አማርኛ አያቅተንም ብለው መምጣታቸውም የችግሩ አካል ነው፡፡

የማስተማር ክህሎትም ሆነ የፈተና አወጣጥ የማይችሉና መምህርነትን ለገቢ ማግኛ እንጂ ዕውቀት ይዘውና በፍላጎት የማይመርጡት መሆኑን ከችሮቹ ውስጥ ነው ብለው ያነሳሉ፡፡

ለማስተማር ፍላጎት የሌላቸው በመሆኑ ሁለትና ሦስት ሳምንት አስተምረው የሚቀሩ መብዛታቸውን፣ ከዚህ በፊት ተማሪ በትኖ ከሥራ መልቀቅ እንደማይቻል፣ ታሞ እንኳን ለመቅረት ፈቃድ እንደሚጠየቅ፣ አሁን ላይ ግን ለተማሪ የሚያስብ መጥፋቱን ተናግረዋል፡፡

መምህራንን ለማብቃት ሥልጠና እንዲያገኙ በክረምት ክልል ድረስ በመላክ ዩኒቨርሲቲ እንዲገቡ በግላቸው ቢያስተምሩም፣ ሁለት ዓመት እንዲያገለግሉ የሚያስገድድ ሕገ አለመኖሩና አለመተግበሩ፣ ከዚህ ቀደም ሁለት ዓመት ማስተማር ግድ እንደነበረ፣ አስተማሪነት ለመሥራት የቅጥር ውል የገባ መምህር አሥር ወር /የትምህርት ጊዜ/ የመሥራት ግዴታ የነበረበትና ጊዜያዊ መቅጠር የማይቻል የነበረ ቢሆንም፣ አሁን ላይ ይህ በመቅረቱ በተለይ ከኮቪድ በኋላ ለሦስት ወራት ብቻ ፈርመው የሚቀጠሩ መምህራን መብዛታቸው ችግሩን አባብሶታል ይላሉ፡፡

እንደ የግል ትምህርት ቤት ባለቤቷ፣ ፔዳጎጂ የተማረ ብቁ መምህር የማግኘት ችግር እንዳለ የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ ያውቃል፡፡ ነገር ግን የሙዓለ ሕፃናት መምህራን እንኳን ቢታይ፣ ሕጉ ላይ በዘርፉ የሠለጠነ መምህር መቀጠር እንዳለበት ቢጠይቅም፣ አንድዬውና የሙዓለ ሕፃናት መምህራንን የሚያሠለጥነው ኮተቤ ዩኒቨርሲቲ፣  በቂ መምህራን እያሠለጠነ አይደለም፡፡ በግል ዘርፍ የነበሩት ተቋማትም ተዘግተዋል፡፡ በመሆኑም ለሙዓለ ሕፃናት ጭምር መምህር ማግኘት ከባድ ነው፡፡ ትምህርት ቢሮ ደግሞ በዘርፉ የሠለጠነ አልቀጠራችሁም ብሎ የትምህርት ቤቱን ውጤት ዝቅተኛ ያደርገዋል፡፡

ትምህርት ቢሮ አዲስ ባወጣው ረቂቅ መመርያ መሠረት በፔዳጎጂ ያልሠለጠነ ማስተማር አይችልም፡፡ ነገር ግን ይህንን የመንግሥትም ሆነ የግል ትምህርት ቤቶች ሊተገብሩት አይችሉም ሲሉም ያክላሉ፡፡

በረቂቅ ደረጃ የተቀመጠውም፣ በኢንጂነሪንግ የተመረቁ ባለሙያዎችን በመምህርነት እንዳትቀጥሩ የሚል ነው፡፡ ይህ ተግባራዊ ሲሆን ደግሞ፣ ብቁ መምህራን አይደለም አስተማሪ የሚባል ማግኘት አይቻልም፡፡ በመሆኑም በመንግሥት በኩል ያለው አሠራርም ሆነ መምህራንን ለማግኘት ያለው ፈተና ለዘርፉ ፈተና ሆኗል፡፡

በመምህርነት ሲታይ የሒሳብ መምህራን የተሻሉ ሲሆን፣ ፊዚክስም ጥሩ ሊባል ይችላል፡፡ በተረፈ በዕውቀት ደረጃ ሲታይ በጀማሪነት ከተቀጠሩ መምህራን ውስጥ ቤት ውስጥ የሚያስጠኑ እንጂ ክፍል ውስጥ ቆመው ተማሪን እያስተማሩ የማይመስሉ መምህራንም ጥቂት አይደሉም፡፡

ከሌላ ትምህርት ቤት ያገኘነው መረጃ ደግሞ፣ መምህራን ተብለው ከተቀጠሩት ውስጥ ከመጽሐፍ ላይ የከበዳቸውን ትምህርት እየዘለሉ የሄዱ መምህራን በቁጥጥር ወቅት አጋጥመዋል፡፡

በመምህርነት ሙያ በተገቢ ሁኔታ የሠለጠኑ በተለይ መንግሥት ባስቀመጠው ደረጃ መሠረት ማግኘት አለመቻሉ፣ በገበያው ላይ የብቁ መምህራን እንዲከሰት እጥረት አድርጓል፡፡

የመምህራን በገበያ ሊይ በበቂ ቁጥር አለመገኘት፣ የተቀጠሩትም ቢሆኑ የመምህርነት ሙያ የሚፈልግባቸውን ብቃት፣ ዕውቀትና ክህሎት አለማሟላታቸው መምህራን በተቀጠሩባቸው የግል ትምህርት ቤቶች ውስጥ ያላቸው ቆይታ በጣም አጭር መሆኑ ብቃት ላይ ችግር መፍጠሩን በግል ትምህርት ቤቶች ማኅበር ከዚህ ቀደም የቀረበ ዳሰሳ ያሳያል፡፡

ይህን ሥር የሰደደ ችግር ለመፍታት በትምህርት ሚኒስቴርም ሆነ በአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ በከተማዋ ያሉ መምህራን ክህሎታቸውን ለማዳበርና በመማር ማስተማሩ ሒደት ለማብቃት የተለያዩ ሥራዎችን ሲሠሩ ቆይተዋል፡፡

በተለይም ከትምህርት ጥራት ጋር ተያይዞ የሚነሱ ችግሮችን ለመግታትና የመምህራንን የማስተማር ክህሎት ለመፈተሽ፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የትምህርትና ሥልጠና ጥራት ቁጥጥር ባለሥልጣንም ከ2004 ዓ.ም. ጀምሮ የሙያ ብቃት ምዘና ፈተናዎችን እየሰጠ ይገኛል፡፡

የምዘና ፈተናውም፣ የመምህራንና የትምህርት ቤት አመራር፣ ከአፀደ ሕፃናት እስከ 12ኛ ክፍል የሚያስተምሩ የመንግሥት፣ የግልና ሌሎች መንግሥታዊ ባልሆኑ ተቋማት የሚሠሩ መምህራን፣ ርዕሰ መምህራን፣ ሱፐር ቫይዘሮች እንዲሁም በመምህራን ማሠልጠኛ ኮሌጆችና ዩኒቨርሲቲዎች የሚገኙ መምህራን የሚካተቱበት ነው፡፡

ለመምህራን የሚደረገው ምዘናም የግል ትምህርት ቤቶችን ያካተተ ሲሆን፣ ይህም ለነባርና ወደ ሙያው ለሚገቡ ጀማሪ መምህራን፣ የትምህርት ቤት አመራር ከትምህርት ይዘትና ከማስተማር ሥነ ዘዴ አንፃር የነበረባቸውን ክፍተት የሚፈትሽ ነው፡፡

ከ2013 ዓ.ም. ጀምሮ በመመሪያው መሠረት ምዘናው በግል ትምህርት ቤቶች መምህራንና የትምህርት ቤት አመራሮች ላይ ተተግብሯል፡፡ ይህም መምህራን የሙያ ብቃት ምዘና ለመመዘን የሚያስችለውን መሥፈርት ለማሟላት ተነሳሽነት እንዲኖራቸው አስችሏል፡፡

ከምዘና ውጤቶች አንፃር ሲታይ፣ የተመዛኞች ውጤት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለ ነው፡፡ በ2013 ዓ.ም. 4,116 መምህራንና የትምህርት ቤት አመራሮች የጽሑፍ ምዘና ወስደዋል፡፡ ከዚህ ውስጥ 1,600 የማኅደረ ተግባር ምዘና ፈተና ወስደው 1,584 ብቁ መሆናቸውን ባለሥልጣኑ ዘንድሮ መጋቢት ላይ የምዘና ውጤት ይፋ ሲያደርግ አስታውቋል፡፡

ከ2005 ዓ.ም. እስከ 2013 ዓ.ም. ድረስ 11,106 የመጀመርያ ደረጃ ትምርት ቤቶች ነባር መምህራን የተመዘኑ ሲሆን፣ ከእነዚህ ውስጥም ማለፊያ ውጤቱን ከ62.5 በመቶ በላይ ያስመዘገቡት 35 በመቶ ናቸው፡፡

ባለሥልጣኑ ምዘናውን ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ እስከ 2014 ዓ.ም. ድረስ 17,849 የመጀመርያና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች መምህራን የሙያ ብቃት የጽሑፍ ምዘና የወሰዱ ሲሆን፣ ከነዚህ ውስጥም 5,913 በጽሑፍ ምዘና ማለፊያ ውጤት ከ62.5 በመቶ በላይ አምጥተዋል፡፡

ፔዳጐጂ የተማሩ መምህራን ማግኘት ችግር ቢሆንም፣ ባለሥልጣኑ ምዘናውን ለማከናወን ካስቀመጠው መሥፈርት አንዱ መምህራኑ የፔዳጎጂ ሥልጠና መውሰድ አለባቸው የሚለው ነው፡፡ ዲግሪ ወይም ዲፕሎማ ስላላቸው ብቻ ምዘና አይወስዱም፡፡ የፔዳጎጂ ሥልጠና ከወሰዱ በኋላ ወደ ጽሑፍ ምዘና የሚገቡ ሲሆን፣ ፈተና ከ62 በመቶ በላይ ሲያመጡ ለማኅደረ ተግባር ምዘና ይቀርባሉ፡፡

የማኅደረ ተግባር ምዘናው ከ20 በመቶ የሚያዝ ሲሆን፣ የጽሑፉ ደግሞ ከ62 በመቶ በላይ ማምጣት አለባቸው፡፡

በምዘናው የወደቁ መምህራንም ሆኑ የትምህርት ቤት አመራሮች መመርያው ላይ በተቀመጠው ሕግ መሠረት የአቅም ግንባታ ተሰጥቷቸው በቀጣይ ዓመት ዳግም ይመዘናሉ፡፡

ከሦስት ጊዜ በላይ ፈተና ወስደው የወደቁ መምህራን ሆኑ የትምህርት ቤት አመራሮች ወደ ሌላ ሙያ እንዲዘዋወሩ የማድረግ ሥራ ወደፊት ይሠራል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

ከ2008 ዓ.ም. ጀምሮ በተከታታይ ለአምስት ዙር ከኮተቤ ዩኒቨርሲቲ ተመርቀው ወደ ሥራ ከመሰማራታቸው በፊት 2879 የሙያ ብቃት የጽሑፍ ምዘና የወሰዱ ቢሆንም፣ ከእነዚህ ውስጥ 206 ወይም ሰባት በመቶው ብቻ ማለፊያ ውጤት አስመዝግበዋል፡፡

የትምህርት ቤቶች ባለቤቶችና ትምህርት ሚኒስቴርም ሆነ ትምህርት ቢሮዎች የሚያነሱትን የመምህራን ብቃት ችግር፣ ለመምህራንና ለትምህርት ቤት አመራር የተሰጠው የሙያ ብቃትና የጽሑፍ ምዘና ውጤት ያሳያል፡፡

ከአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ ያገኘነው መረጃ እንደሚያሳየው፣ በመምህራን ብቃት ላይ ያለውን ችግር ለመቅረፍ በከተማዋ ለሚገኙና በግልም ሆነ በመንግሥት ትምህርት ተቋማት ለሚያስተምሩ መምህራን በቢሮው ወጪ የትምህርት ደረጃቸውን እንዲያሻሽሉ ቅድመ ሁኔታዎች እየተመቻቸ ነው፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የመቃወም ነፃነት ውዝግብ በኢትዮጵያ

ስሟ እንዳይገለጽ የጠየቀችው በአዲስ አበባ ከተማ በተለምዶ የሾላ አካባቢ...

የሲሚንቶን እጥረትና ችግር ታሪክ ለማድረግ የተጀመረው አጓጊ ጥረት

በኢትዮጵያ በገበያ ውስጥ ለዓመታት ከፍተኛ ተግዳሮት በመሆን ከሚጠቀሱ ምርቶች...

የብሔር ፖለቲካው ጡዘት የእርስ በርስ ግጭት እንዳያባብስ ጥንቃቄ ይደረግ

በያሲን ባህሩ በሪፖርተር የኅዳር 9 ቀን 2016 ዓ.ም. ዕትም “እኔ...