‘ደብርዬ’ ደብሪቱ (ታላቅ እህታቸው እንደሚጠሩአቸው) ‘ረቂቅ’ ሴት ናቸው (ዘንድሮ ሰው ‘ክፉ’ አይባልም)፡፡
አበበች የሥልጣን፣ የጉልበት ችሎታ መጠኑ ገደቡ የት እንደሚደርስ መገመት ይከብዳታል፡፡ በቀጣፊነቱ የሚኮራ ጉልበታም ብቻ እንደሆነ በወ/ሮ ደብሪቱ ይገባታል፡፡
‹‹በይ እረዳሻለሁ›› አሏት፡፡
ነገሩም ሕመሙም አበሳጭቷት ተነጫነጨች፡፡
‹‹እንዴ? ምን ልሁን ነው … ጥጋብ እኮ ነው እናንተዬ›› አሉ፡፡
ወደ ሐያ የሚሆኑ የሽንኩርት እራሶች መክተፍ ነበረባት፡፡ ከማቀዝቀዣ የወጣ የበሬ ሽንጥ ሥጋ መክተፊያው እንጨት ላይ ቀይ የሕፃን ልጅ ሹራብ መስሎ ወድቆአል፡፡ የተባ ቢላ መሐሉ ላይ ተጋድሞ፡፡ ቢላውና ሹራቡ ሽርክ ይመስላሉ፡፡ ፍቅርኛ ነገሮች ምናምን …
‹‹ስልክ ላድርግ መጣሁ›› ብለው ወጡ ደብሪቱ፡፡
ሥራ የሚያመልጡበት ጥበባቸው ረቂቅ ነው፡፡ እንደ ባህላችንም ነው፡፡ ዛሬ የመሥራት አቅም ሲጠፋ፣ ሐሞት ሲሞት ፖለቲከኛ ይኮናል፡፡ ይቀላል፡፡ ማላገጥ ሕግና ዓላማ ይሰጠዋል፡፡ ዓላማ ሳይደርስ ተመሃል ጎዳና እያቦኩ ቢቀርም … በሌላ እያሳበቡ መውደቅ ነው፡፡
‘ስልክ ልደውል’ ይሉና እንግዲህ ለሁለት ሰዓት ያህል ይጠፋሉ፡፡ ከጠዋት እስከ ማታ ፈሳቸውን እየጠጣ ያ አልጋ አለማነጠሱ ደብሪቱ እራሳቸውንም ይገርማቸዋል፡፡ ጌትነትን ካልተኙበት ምኑ ጌትነት ሆነ፡፡ እመቤትነትም፡፡
ልጃቸው እንኳን አንድ ቀን አፏ ተስቶት ብትተቻቸው ‘አንቺም አልጋሽ የቢሮ ወንበር ነው’ ብለው ጆሮዋን ሲገርፏት እንደ ቀንድ አውጣ ተሰብስባ የሽሙጥና የኩርፊያ ልጋጓን ከመጐተት በስተቀር ቆማ አልመለሰችላቸውም፡፡ ማንንም ሰው ዝም የማሰኘት ችሎታ አላቸው፡፡
‹‹በል አንተ›› ብለው ሳይጠቁሙት ወሬ የሚጀምረውን ምሳሌ ጠቅሰው ‘መናገርን’ እስኪረግም ይወቁታል፡፡ መልካም ለመሆን ከፈለጉ ደግሞ የወደቀ ምራቅ ይመልሳሉ፣ ግመል ያሰክራሉ የአንድን የሰው ፀባይ የማያልቅ የሚቃረን የሚፋቀር ጐን ይሰጡታል፡፡ ‘ድንቅነት’ በእሳቸው ምላስ ሺሕ ፊት አላት … ‘ርግማን’ እልፍ ፊት አላት፡፡
እና ስልክ ለመደወል ቢጠፉ ለአካባቢው ሆነ ለማንም አይገርምም፡፡ የሚበቃ ምክንያት አላቸው፡፡ ባይኖርም ይሰጣሉ፡፡ ከሰጡ ደግሞ መቀበል ድንቅ ነው፡፡
አበባ ሥጋውን አመቻችታ ለመቁረጥ መስመር ስትፈልግ ልስላሴውና ቅዝቃዜው ማረካት፡፡ ቁርስዋንም ስላልበላች ቁርጥ ለመሞከር የድልህ ዕቃ አውጥታ ትንሽ ድልህ መክተፊያው ጣውላ ላይ ጠብ አድርጋ እየከተፈች አልፎ አልፎ ጥሬ ሥጋ እየዋጠች ሥራዋን ቀጠለች፡፡ ራስ ምታቱ ግን ኦ! ኦ! ያው ነው፡፡ ሻሽዋን አጠንክራ አናቷ ዙሪያ መጠምጠሙ ነው በትንሹም ቢሆን ያዋጣት፡፡
ስልክ መደወያ ቦታው በደብሪቱ የፈጠራ ችሎታ የሚወሰን ስለሆነ፣ ጭን የመሰለ ሰውነታቸውን ተሸክመው ማድ ቤት ሲገቡ መጀመሪያ ያዩት ግራ ጐኑ ላይ ቡግንጅ ያበቀለ የመሰለውን የአበባን ፊት ነው፡፡ ይሔ ቡግንጅ ደግሞ እንደ አናሳ ፍጡር ይነቃነቃል፡፡ ደማቸው ፈላ፡፡
‹‹ለራስሽ ደገስሽው?››
ቢላውን ቀምተው ቃጡባት ‹‹አንገቷን ማለት ነው›› አሉ፡፡ ብዙ ጊዜ ተደራሲያቸው ባይታይም፡፡ በነጠላ አይናገሩም ሲበሽቁ … የጐዳቸው አንድ ሰው ተከታይ አለው፤ እና ‹‹እናንተን ምን ማድረግ ይሻላል?›› ይላሉ … እሳቸውም ተከታይ አላቸው ግን አማራጭ ብዜቱን ገለልተኛ በግምት የሚመጠን ያደርጉታል፡፡
‹‹ምን ቢያደርጓቸው ይሻላል … ሴት ደረቅ እንጀራ አነሳት? … ቢበሉት ከቂጥ በላይ አይሆን … ‘ቂጣም ያሰኛል’›› አሉ፡፡
- አዳም ረታ ‹‹ሕማማትና በገና›› (2004)