Monday, December 4, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

በበራሪ ወረቀት የሚታደሉ ማስታወቂያዎች በክፍያ እንዲሆኑ የሚደነግግ ደንብ ወጣ

ተዛማጅ ፅሁፎች

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በጎዳና ላይ በሚበተኑ በራሪ ወረቀቶች የሚተላለፉ ማስታወቂያዎች፣ ለከተማ አስተዳደሩ ክፍያ ሳይፈጸምባቸው እንዳይሠራጩ የሚደነግግ ደንብ አወጣ፡፡

በአዲሱ የከተማ አስተዳደሩ የውጭ ማስታወቂያ ደንብ ቁጥር 128/2014 መሠረት፣ በበራሪ ወረቀቶች የሚሠራጩ ማስታወቂያዎችን ጨምሮ ሁሉንም የውጭ ማስታወቂያዎች መጠቀም የሚቻለው፣ ይዘታቸው በከተማው ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ ታይቶና በከተማው የግንባታ ፈቃድና ቁጥጥር ባለሥልጣን ፈቃድ ሲሰጥ ብቻ ነው፡፡

የባለሥልጣኑ የሕዝብ ግንኙነትና ኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት አቶ አረጋዊ ማሩ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ባለሥልጣኑ በከተማው በሚገኙ 400 የማስታወቂያ ቢል ቦርዶች ላይ ባደረገው ጥናት፣ ከ200 በላይ የሚሆኑ ፈቃድ የሌላቸው መሆኑን አረጋግጧል፡፡ ብዙዎቹ ከደረጃ ውጪ የሆኑና መነሳት በሚገባቸው ጊዜ ያልተነሱ ናቸው ብለዋል፡፡

‹‹በተለይ ከ2003 ዓ.ም. ወዲህ ብዙዎቹ የውጭ ማስታወቂያዎች እንዲህ ዓይነት ችግር ያለባቸው ናቸው፡፡ ተገቢውን ሥርዓትና አካሄድ የጠበቁ አይደሉም፤›› በማለት አስረድተዋል፡፡

አሁን የወጣው ደንብ ይኼንን ጉዳይ ‹‹ሥርዓት ለማስያዝ›› እና የከተማ አስተዳደሩ ማግኘት ያለበትን ገቢ ለማስገኘት ያለመ መሆኑን የገለጹት ዳይሬክተሩ፣ ደንቡ ባለፈው ሳምንት መጨረሻ በከተማው ካቢኔ መፅደቁን ተናግረዋል፡፡

ደንቡ በመሬት፣ በሕንፃ፣ በንግድ ድርጅት፣ በአጥር ወይም በማናቸውም መሰል አካል ላይ የሚተከል፣ የሚለጠፍ ወይም በማናቸውም መንገድ የሚሠራጭ የውጭ ማስታወቂያን የሚመለከት ሲሆን፣ ባለሥልጣኑ የማስታወቂያውን የቆይታ ጊዜ የሚወስነው ማስታወቂያው የተዘጋጀበትን መሣሪያና ስምምነት መሠረት በማድረግ ነው፡፡ በባለሥልጣኑ ፈቃድ ያገኘ የውጭ ማስታወቂያ ፈቃዱ የሚጠናቀቅበትን ጊዜ በማስታወቂያ ሰሌዳው ላይ መጻፍ ይገደዳል፡፡

በተንጠልጣይ ነገር፣ በፖስተር፣ በስቲከር፣ በተባዛ በራሪ ወረቀት፣ በብሮሸር፣ ሊፍሌት፣ በፍላየር፣ በድምፅ ካሴት፣ በድምፅ ማጉያ መሣሪያ የሚሠራጩ ማስታወቂያዎችም የሚመሩት በዚሁ ደንብ ነው ተብሏል፡፡

ከወቅታዊ ሁኔታ ጋር በተያያዘ ለአጭር ጊዜ የሚተከል፣ የሚለጠፍ ወይም በማናቸውም መንገድ የሚሠራጭ የውጭ ማስታወቂያ የሚተላለፈው ወቅታዊ ሁነቱ ከመከናወኑ በፊት ከአንድ ወር በላይ ላልበለጠ ጊዜ ሲሆን፣ ሁነቱ ከተጠናቀቀ በኋላ ከሰባት ቀናት በላይ መቆየት እንደማይችል ደንቡ ደንግጓል፡፡

ደንቡ በመኪና በመንቀሳቀስ የሚነገሩ ማስታወቂያዎችንም የሚመለከት ነው፡፡ በዚህ መንገድ የሚሠራጩ ማስታወቂያዎች ፈቃድ የሚሰጣቸው በቀን ውስጥ ለተገደበ ሰዓት ብቻ ይሆናል፡፡ ከተፈቀደለት ሰዓት ውጪ በመኪና ላይ የማስታወቂያ ሥራ ሲሠራ የተገኘ አሽከርካሪ 1,600 ብር ቅጣት የሚጣልበት ሲሆን፣ ማስታወቂያው በመኪናው ላይ የተለጠፈ ከሆነ እንዲያነሳ ይደረጋል፡፡

የውጭ ማስታወቂያ በማናቸውም መንገድ ከማሠራጨቱ በፊት ለፈቃድ ሰጪው የአገልግሎት ክፍያ መክፈል እንዳለበት ተደንግጓል፡፡ በምሥልና በጽሑፍ የሚሠራጭ የውጭ ማስታወቂያ የክፍያ ተመን በማስታወቂያ ሰሌዳው ስፋት በሜትር ካሬና በቆይታ ጊዜው የሚሰላ ሲሆን፣ በድምፅ የሚተዋወቅ የውጭ ማስታወቂያ በሚወስደው ጊዜ ይሰላል ተብሏል፡፡ የእነዚህ የተለያዩ የክፍያ ተመኖች ዝርዝር በተያዘው ሳምንት መጨረሻ ላይ በሚወጣው መመርያ እንደሚወሰን ዳይሬክተሩ አቶ አረጋዊ ተናግረዋል፡፡

የሃይማኖት ተቋማት፣ የፖለቲካ ድርጅቶች፣ ለትርፍ ያልተቋቋሙ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች፣ የዲፕሎማቲክ ተቋማት፣ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች፣ ለእምነት ወይም ለዓላማ ማስፈጸሚያ እንዲውሉ በተፈቀዱላቸው ቦታዎች ወይም ንብረቶች ላይ የሚካሄዱ የማስተዋወቅ ሥራዎች ከአገልግሎት ክፍያ ነፃ ይሆናሉ። ሰዎችን ለመርዳት በመኪና የሚደረጉ የማስተዋወቅ ሥራዎችም ፈቃድ በማውጣት ብቻ ከክፍያ ነፃ እንደሚከናወኑ ገልጸዋል፡፡

ከተፈቀደለት ይዘት ውጪ ማስታወቂያውን ካሠራጨ፣ እንዲሁም ለሕግ ወይም ለሕዝብ ሞራል ተቃራኒ የሆነ መልዕክት እንደሚያስተላልፍ ከተረጋገጠ፣ በቅድሚያ የማስታወቂያው ባለቤት በአንድ ቀን ወይም በ24 ሰዓት የጊዜ ገደብ ውስጥ እንዲያነሳ የማስጠንቀቂያ ጽሑፍ እንዲደርሰው በማድረግ የማስታወቂያ ሥራው ይቋረጥበታል። ማስታወቂያ አስተላላፊው በደረሰው ማስጠንቀቂያ መሠረት ለማንሳት ፈቃደኛ ካልሆነ ባለሥልጣኑ በራሱ ወጪ አንስቶ ንብረቱን በመውረስ፣ ለማንሳት ያወጣውን ወጪ ከባለቤቱ በሕግ እንደሚጠይቅ ደንቡ አስቀምጧል፡፡ በተጨማሪም ደንቡ ይኼ አካል በከተማው ክልል በማንኛውም ቦታ ምርቱንም ሆነ አገልግሎቱን የማስተዋወቅ ሥራ ለመሥራት ጥያቄ ቢያቀርብ ለአንድ ዓመት እንዳይሳተፍ እንደሚደረግ ደንግጓል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች