ጋዜጠኛ በቃሉ አላምረው ከእስር ተፈታ
‹‹ወግድ ይሁዳ›› የሚል መጣጥፍ በማቅረብና በተለያዩ ዩቲዩቦች በመቅረብ በመንግሥት ላይ ትችት በማቅረብ የሚታወቁት የ70 ዓመቱ አዛውንት አቶ ታዲዮስ ታንቱ፣ የመገፋፋትና ግዙፍ ያልሆነ የማሰናዳት ተግባር፣ የጥላቻ ንግግርን ማሰራጨት፣ ሐሰተኛ ወይም የሚያደናግር መረጃ የማሠራጨትና የስም ማጥፋትና የማዋረድ ወንጀል ክሶች ተመሠረተባቸው፡፡ ከአቶ ታዲዮስ ጋር በተመሳሳይ ወንጀል አቶ ጌጥዬ ያለው የተባለ ግለሰብም ተከሷል፡፡
የፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ የመሠረተው ክስ እንደሚያስረዳው፣ ተከሳሾቹ የእርስ በርስ ጦርነት በማስነሳት፣ በመንግሥትና ሕገመንግሥታዊ ሥርዓቱ ላይ ወንጀል እንዲፈጸምና የፌዴራልም ሆነ የክልል ሥርዓት እንዲፈራርስ ወይም እንዲለወጥ በማሰብ ሲንቀሳቀሱ እንደነበር አብራርቷል፡፡
ተከሳሾቹ የወንጀል ድርጊቱን ለመፈጸም የተዘጋጁት ወይም የፈጸሙት የወንጀል ሕግ አንቀጽ 32(1ሀ)፣ አንቀጽ 257(ሀ)፣ አንቀጽ 337፣ አንቀጽ 244(1) እና የጥላቻ ንግግርና ሐሰተኛ መረጃ ሥርጭትን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የወጣውን አዋጅ ቁጥር 1885/12 አንቀጽ 4 እና አንቀጽ 7(4)፣ እንዲሁም የኮምፒዩተር ወንጀል አዋጅ ቁጥር 958/2008 አንቀጽ 14(3) ድንጋጌዎችን በመተላለፍ መሆኑን ዓቃቤ ሕግ በክሱ ጠቅሷል፡፡
አቶ ታዲዮስ ራስ ሚዲያ በተባለ የዩቲዩብ ቻናል ‹‹የኢትዮጵያ ሕዝብ ሌላ አማራጭ የለውም፣ ጭቆናው በዝቷል፣ አመጽ ለማንሳት ጊዜው አሁን ነው፣ እስከመቼ ተኝተን እንሞታለን፣ የአገዛዙን ጠንካራ ጎን በደንብ አጥንተን ማን ከማን ጋር ተሰልፏል? እንዴት ብንሄድ የመንግሥትን ስስ ብልት አግኝተን ቦርቡረን እናስወግደዋልን? ወዘተ፤›› በማለት ሕዝቡን ለአመጽ እንዲነሳሳ ሲሠሩ እንደነበር ዓቃቤ ሕግ በክሱ በዝርዝር አቅርቧል፡፡
አቶ ጌጥዬ የተባለው ተከሳሽም የዩቲዩቡ አዘጋጅና አቅራቢ በመሆን ‹‹ይህንን ጨፍጫፊ፣ አፈናቃይ፣ ገዳይ መንግሥት፣ እንደ መንግሥት ተቀብለን መቀጠል አለብን ወይ? ፋኖ እንደ ውጭ ወራሪ መታገል የለበትም ወይ? ታክሲና አውቶቡስ ሥራ እንዲያቆሙ በማድረግ ሰላም መንሳት፣ አደባባይ ወጥተን እንደ አንበሳ ሆነን መንግሥትን መቀየር ባንችል፣ ቁንጫ ሆነን ውስጥ ውስጡን ሰርሥረን ሰላም በመንሳት ምቾች አሳጥተን ይኼንን ሥርዓት ማስወገድ አለብን…ወዘተ፤›› በማለት ቅስቀሳ ሲያደርግ እንደነበርም ዓቃቤ ሕግ በዝርዝር በክሱ አስፍሯል፡፡
ተከሳሾቹ ሀሌታ ቴሌቭዥን በተባለ የዩቲዩብ ቻናል አማራ በሌሎች ዘሮች እንደሚጠላና ሁሉም አማራን ለማጥፋት መነሳቱን በመቀስቀስ፣ የአማራ ተወላጆች በሌሎች ተወላጆች ላይ የጦር መሣሪያ እንዲያነሱ በማድረግና ሌሎችም ቅስቀሳዎች በማድረግ፣ የመገፋፋትና ግዙፍ የማሰናዳት ተግባር ወንጀል መፈጸማቸውን በክሱ አብራርቷል፡፡
ተከሳሾቹ ሰላም በተባለ የዩቲዩብ ቻናል አማካይነት ባሠራጩት የጥላቻና የሐሰተኛ ወሬ፣ ‹‹የትግራይ ሕዝብ እንደ ሕዝብ ከሃዲ ነው፡፡ ሕዝቡ ራሱ የዓለም ውሸታም ነው፡፡ የጥበብ መጀመሪያ እግዚአብሔርን መፍራት ነው፣ የሞኝነት መጀመሪያ ደግሞ ትግሬ ኢትዮጵያዊ ነው ብሎ ማሰብ ነው፡፡ ሸክም እንጂ እነሱ ወገን ሆነው አያውቁም፤›› የሚል የጥላቻና የሐሰት ንግግሮችን ማሠራጨታቸውንም ዓቃቤ ሕግ በክሱ ገልጿል፡፡
ራስ ሚዲያ በተባለ የዩቲዩብ ቻናልም ባሠራጩት የጥላቻና የሐሰት ንግግር፣ የኦሮሞ ማኅበረሰብና በወላይታ ማኅበረሰብ ላይ ከፍተኛ የሆነ የጥላቻና የሐሰት ንግግሮችን ማሠራጨታቸውን ዓቃቤ ሕግ በክሱ አብራርቷል፡፡ በአጠቃላይ ተከሳሾቹ የጥላቻ ንግግር፣ የሚያደናግር መረጃ በማሠራጨት፣ እንዲሁም በሕዝብ ደኅንነት ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎችንና የስም ማጥፋትና ማዋረድ ወንጀሎችን ፈጽመዋል በማለት ዓቃቤ ሕግ በሁለቱም ተከሳሾች ላይ ክስ መሥርቷል፡፡
በሌላ በኩል ሁከትና ብጥብጥ በማስነሳት ወንጀል ተጠርጥሮ ከአንድ ወር በፊት ታስሮ የነበረው የአልፋ ሚዲያ ባለቤትና አዘጋጅ ጋዜጠኛ በቃሉ አላምረው በአሥር ሺሕ ብር ዋስ ትናንት ሰኔ 21 ቀን 2014 ዓ.ም. ፈቃድ ከእስር ተፈቷል፡፡