Sunday, July 14, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ዳሸን ባንክ በ230 ሚሊዮን ብር ያስገነባውን የመረጃ ማዕከል አስመረቀ

ተዛማጅ ፅሁፎች

ዳሸን ባንክ ዘመናዊ የባንክ አገልግሎትን ለማስፋት ለአንድ ዓመት ብቻ 1.5 ቢሊዮን ብር በመመደብ የተለያዩ የአይቲ መሠረተ ልማቶችን መገንባቱንና ሌሎች ባንኮች ጭምር ሊጠቀሙበት የሚችል ሰርቨር ማዕከሉን ለአገልግሎት አብቅቷል፡፡

የዳሸን ባንክ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ አስፋው ዓለሙ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ዘመናዊ የባንክ አገልግሎትን ለማስፋፋት የአይቲ መሠረተ ልማቶች ወሳኝ በመሆኑ፣ ይህንኑ በየዓመቱ በጀት እየመደበ በመሥራት ላይ ይገኛል፡፡ በዚህም ክንውኑ በ2014 በጀት ዓመት ብቻ 1.5 ቢሊዮን ብር ለዚሁ መሠረተ ልማት ግንባታና ተያያዥ ሥራዎች በጀት በመመደብ በመስራት ላይ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ በኢትዮጵያ በግል ዘርፉ የመጀመርያ የሚባለውን ሰርቨር ማዕከል የገነባውም ዘንድሮ ለቴክኖሎጂ ማስፋፊያ ከያዘው በጀት መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ሰሞኑን የተመረቀው ሰርቨር ከ230 ሚሊዮን ብር በላይ የፈጀ መሆኑን የገለጹት አቶ አስፋው፣ ባንኩ ከምሥረታው ጀምሮ በአይቲ ቴክኖሎጂ መሠረተ ልማቶች ላይ ትኩረት በመስጠት እየሠራ ያለው ሥራ ባለፉት አሁንም የቀጠለ ሲሆን፣ ሌሎች አዳዲስ የአይቲ ሥራዎች ለአገልግሎት እንደሚበቁም ገልጸዋል፡፡  

ሰሞኑን ያስመረቀው ሰርቨር ከራሱ አገልግሎት አልፎ ለሌሎች ባንኮችም አገልግሎት የሚሰጥ እንደሆነም ታውቋል፡፡ በዚህ ሰርቨር አገልግሎት ዙሪያ አቶ አስፋው እንደገለጹት፣ የመረጃ ማዕከሉ ከፍተኛ ኃይል ያላቸውን ከአንድ ሺሕ ያላነሱ ሰርቨሮችና ሌሎች ተያያዥ የኔትዎርክ መሣሪያዎችን የማስተናገድ አቅም አለው፡፡ በጥገና ወቅትም መደበኛ የባንኩ ሥራ ሳይቋረጥ ዓመቱን በሙሉ አገልግሎት መስጠት የሚችል እንደሆነም ጠቅሰዋል፡፡

‹‹ለደንበኞቻችን ከጅምሩ በገባነው ቃል መሠረት ወደር የለሽ የባንክ አገልግሎት ማግኘታቸውን ከማረጋገጥ እኩል አገራችንም በዘርፉ የሚኖራትን ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነት ከፍ ለማድረግ ያለንን ከድርጅታዊ ጥቅም ከፍ ያለ ቁርጠኝነት የሚያሳይ ህያው ምስክር ነው፤›› ያሉት አቶ አስፋው በዕለቱ የተመረቀው የደረጃ 3 ዳታ ሴንተር እንደ ዓላማ ይዞት የተነሳው፣ ያልተስተጓጎለ የኢንፎርሜሽን ኮሙዩኒኬሽን ቴክኖሎጂ አገልግሎት ለመስጠት እንደሆነም አክለዋል፡፡ ከዚህም ሌላ ኃይልና በቴሌኮም አገልግሎት መስመር መቆራረጥ በሚያጋጥምበት ወቅት በጣም አነስተኛ የአገልግሎት መቋረጥ ይዞ መጓዝ፣ የጥገና አስፈላጊነቶችንና ተያያዥ ወጪዎችን ለመቀነስ፣ የዕድገትና የመስፋፋ አቅምን ለመገንባት የሚያስችል እንደሆነም የአቶ አስፋው ገለጻ ያመለክታል፡፡ ማዕከሉ የኢንፎርሜሽን ኮሙዩኒኬሽን ቴክኖሎጂ ደኅንነትን የበለጠ ለማጠናከር፣ የመረጃ ማዕከሉ ሰርቨሮች፣ ፋዬርዎል፣ ራውተርና ሰዊቾች ላይ 365 ቀናት በትክክል የማይቋረጥ አቅምን መገንባት፣ ለክላውድ ሬዲ ዳታ ሴንተር እንዲኖረንና፣ ለሌሎች አካላት ማዕከሉን በማጋራት ገቢ ማግኘትን ጭምር ያለመ ነው፡፡ ዳሸን ባንክ ከዛሬ ሃያ ስድስት ዓመት በፊት አገልግሎቱን ሲጀመር የሒሳብ መረጃዎቹን በኮምፒዩተር ቋት በመመዝገብ በኢትዮጵያ የመጀመርያው ባንክ እንደሆነ ባንኩ አስታውቋል፡፡ ከዚያን ጊዜ አንስቶ በኢትዮጵያ የቴሌኮም መሠረተ ልማት ዕድገት በሚፈቅድለት አቅም ልክ እየተከተለ በርካታ የዘመናዊ ቴክኖሎጂ ትሩፋት የሆኑ አሠራሮችንና የባንክ አገልግሎት አሰጣጥ ሥርዓቶችን ለአገር ማስተዋወቅ መቻሉንም አቶ አስፋው ተናግረዋል፡፡

በዚህ ማዕከል ምረቃ ፕሮግራም ላይ የተገኙት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ ይናገር ደሴ (ዶ/ር) እንደገለጹት ደግሞ፣ ይህ ማዕከል ለሌሎችም ምሳሌ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ አያይዘውም ብሔራዊ ባንክ ከዚህ በኋላ ባንኮችን የሚመዝነው በአይቲ ቴክኖሎጂና አገልግሎታቸው ጭምር መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች