Monday, December 4, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የባህር ትራንስፖርት ድርጅት ካፒታሉን ወደ 90 ቢሊዮን ብር ለማሳደግ ጥያቄ አቀረበ

ተዛማጅ ፅሁፎች

የኢትዮጵያ ባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎት ድርጅት፣ ካፒታሉን ወደ 90 ቢሊዮን ብር እንዲያሳድግ እንዲፈቀድለት መጠየቁን አስታወቀ፡፡ ድርጅቱ አሁን ያለው የተከፈለ ካፒታሉ በ2008 ዓ.ም. ተፈቅዶለት ከነበረው 20 ቢሊዮን ብር እንዳለፈ ገልጿል።

ላለፈው አንድ ዓመትም ይህንን የማሳደግ ጥያቄ ሲጠይቅ የቆየ መሆኑን፣ በአሁኑ ጊዜም አዲስ ለተቋቋመውና ድርጅቱን ጨምሮ ከፍተኛ አቅም ያላቸውን 27 የመንግሥት ልማት ድርጅቶችን አቅፎ ለሚይዘው፣ ለኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ ጥያቄውን እንዳስገባ፣ የድርጅቱ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ሮባ መገርሳ ተናግረዋል።

‹‹የዛሬ ዓመት አካባቢ ጥያቄ አቅርበን ነበር፣ ግን ምላሽ አላገኘንም፡፡ አሁንም እንዲፈቀድልን ለኢንቨስትመንት ሆልዲንግ ጥያቄ አቅርበናል፤›› ብለዋል፡፡

ባለፈው ሳምንት በአዲሱ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሕንፃ ውስጥ ተካሂዶ በነበረው የድርጅቶቹ ይፋዊ የትውውቅ መድረክና የመጀመርያው አጠቃላይ ጉባዔ ላይ፣ ስለድርጅታቸው አጠቃላይ ገለጻ ያደረጉት ዋና ሥራ አስፈጻሚው፣ ድርጅታቸው በከፍተኛ አቅም ላይ እንዳለና በጥሩ እንቅስቃሴ ላይ መሆኑን ተናግረዋል።

ድርጅቱ ባለፉት ዘጠኝ ወራት 36 ቢሊዮን ብር ገቢ ማስገኘቱን፣ ከታክስ በፊት ትርፉ ከአራት ቢሊዮን ብር በላይ እንደሆነ ዋና ሥራ አስፈጻሚው ተናግረዋል። ድርጅቱ እንዳቀደው ከሆነ የሙሉ ዓመቱ ገቢ 46 ቢሊዮን ብር እንደሚሆን፣ ከዚህም 4.6 ቢሊዮን ብር ትርፍ ከታክስ በፊት ለማስመዝገብ ታስቦ ነበር።

ድርጅቱ በባህር ትራንስፖርት አገልግሎት ላይ ተሰማርተው የሚገኙ አራት የመንግሥት ልማት ድርጅቶች ውህድ ሆኖ እንደ አዲስ በ2003 ዓ.ም. በ940 ሚሊዮን ብር መነሻ ካፒታል መቋቋሙ የሚታወስ ሲሆን፣ በ2008 ዓ.ም. የተከፈለ ካፒታሉን 3.7 ቢሊዮን ብር አድርሶ በዚሁ ዓመት ደግሞ የተፈቀደለት ካፒታሉ 20 ቢሊዮን ብር አድርሶ ነበር።

‹‹ከ2008 ዓ.ም. ጀምሮ ለተከታታይ አምስት ዓመታት ሙሉ ለሙሉ ካፒታሉን ከፍሎ የዛሬ ዓመት 20 ቢሊዮን ብር የተከፈለ ካፒታል ላይ ደርሶ ነበር፡፡ እንዲያውም 2.5 ቢሊዮን ብር እላፊ ሀብት ሆኖ አስመዝግቧል፤›› ሲሉ ዋና ሥራ አስፈጻሚው ለተሰብሳቢዎች አስረድተዋል፡፡

የአገር ውስጥም ሆነ የውጭ ባንኮች ምንም ዓይነት ዕዳ እንደሌለበት በአሁኑ ጊዜ በባንኮች ውስጥ 25 ቢሊዮን ብር የሚደርስ ገንዘብ እንዳለው ተገልጿል። እንዲሁም በውጭ አገር በሚገኙ ባንኮች 300 ሚሊዮን ዶላር የሚሆን የውጭ ምንዛሪ እንዳለውና የውጭ አገር ባንኮችንም እንደሚጠቅም አቶ ሮባ አክለዋል፡፡

ቴክኖሎጂን በተመለከተ 400 ሚሊዮን ብር ወጪ የተደረገበት በመገንባት ላይ ያለ (Tier III) የዳታ ማዕከል እንዳለው ተጠቁሟል፡፡

ድርጅቱ 342 የሚጠጉ የወደብ መዳረሻዎች እንዳሉት፣ ሁለት ነዳጅ ማመላለሻዎችን ጨምሮ 11 መርከቦችና 16,000 ኮንቴይነሮች የህዳሴ ግድብን ጨምሮ በበርካታ የአገር ውስጥ የውኃ ማጓጓዣና መዝናኛ ሥራ ድርጅቱ አሁን ያሉትን 1,300 ጀልባዎች አዘምኖ ለመሰማራት ማቀዱን ዋና ሥራ አስፈጻሚው ገልጸዋል። 

በቅርቡ በ100 ቢሊዮን ብር ካፒታል የተቋቋመው የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ በአቶ ማሞ ምሕረቱ ዋና ሥራ አስፈጻሚነት እየተመራ፣ የኢትዮጵያ ባህር ትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ አገልግሎት ድርጅትን ጨምሮ እንደ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክን፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድን፣ ኢትዮ ቴሌኮምን፣ የፈዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽንን፣ የኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅትንና የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎትን የመሳሰሉ 27 የመንግሥት ልማት ድርጅቶች ያስተዳድራል።

መንግሥት በኢንቨስትመንት ሆልዲንግ ሥር ከተቋቋሙት ድርጅቶችም ዓመታዊ 540 ቢሊዮን ብር ገቢ ይጠብቃል፡፡ በኢንቨስትመንት ሆልዲንግ ሥር ያሉት 27 የልማት ድርጅት አጠቃላይ ሀብታቸው ሁለት ትሪሊዮን ብር መሆኑን አቶ ማሞ ገልጸዋል፡፡  

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች