Monday, March 4, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ደላሎችን ከአትክልትና ፍራፍሬ ምርቶች ግብይት የሚያስወጣ ዕርምጃ እንዲወሰድ ተጠየቀ

ተዛማጅ ፅሁፎች

በአትክልትና ፍራፍሬ ምርቶች ግብይት ውስጥ ባለው የደላሎች ጣልቃ ገብነት የተቸገሩ የሆልቲካልቸር አምራቶችና ላኪዎች፣ መንግሥት ደላሎችን ከገበያው የሚያስወጣ ዕርምጃ እንዲወስድ ጠየቁ፡፡

ይህ ጥያቄ የቀረበው የኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት በሆልቲካልቸር የተሰማሩ ባለድርሻ አካላት ከምርት እስከ ግብይት ባለው ሒደት ውስጥ ያሉ ተግዳሮቶችንና ዕድሎችን አስመልክቶ፣ ሰኔ 18 ቀን 2014 ዓ.ም. በአዳማ ደምበል ቪው ሆቴል ባዘጋጀው የምክክር መድረክ ላይ ነው፡፡

የአትክልትና ፍራፍሬ አምራች አካባቢዎች በተለያየ የአመራረት ዘዴ እያመረቱ ቢሆንም፣ እስከ አርሶ አደሩ ማሳ በዘለቀ የደላሎች ሰንሰለት ምርቶቹን አምራች አርሶ አደሮች በርካሽ ዋጋ፣ ተጠቃሚው ደግሞ በከፍተኛ ዋጋ ለመሸጥና ለመሸመት መገደዳቸው በውይይቱ ተሳታፊዎች ተገልጿል፡፡

ተሳታፊዎች በውይይቱ ወቅት ደላሎች የአትክልትና ፍራፍሬ ምርቶች ባሉባቸው አካባቢዎች ገብተው ዋጋ የሚወስኑ፣ አርሶ አደሩ ማሳ ድረስ ሚዛን ይዘው ግብይት የሚያከናውኑ፣ ይባስ ብሎም የአርሶ አደሩን ምርት የመሰብሰብና የማዘግየት ድርጊት በእነሱ ፍላጎት ላይ የተመሠረት እንዲሆን የሚያስችል ደረጃ ላይ ደርሰዋል ብለዋል፡፡

በአዲስ አበባም ሆነ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የሚገኙት የኅብረት ሥራ ማኅበራት በሚፈለገው ልክ አምራቹ ድረስ ዘልቀው አለመግባታቸው፣ እንዲሁም ያላቸው አቅም ውስን መሆኑና በቴክኖሎጂ ረገድም የደረጁ አለመሆናቸው በመሀል የሚገባው ደላላ ሚናው ከፍተኛ እንዲሆን አደርጎታል ተብሏል፡፡  

በኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት የግብርና ኮሜርሻላይዜሽን ክላስተር ዳይሬክተር ዳኛቸው ሉሌ (ዶ/ር) ለሪፖርተር እንዳስታወቁት፣ አርሶ አደሮች አምርተው ገበያው የሚወርድበት፣ በርካሽ ዋጋ እየሸጡ ተጠቃሚው በውድ ዋጋ መግዛቱ፣ መሀል ላይ ያለውን ችግር አመላካች ነው፡፡ በተለይም ከደላላ ጋር ተያይዞ ያለውን ክፍተት በጊዜ መፍታት አስፈላጊ መሆኑን አስምረውበታል፡፡

በአቮካዶ ብቻ ሳይሆን በሌሎች የሰብል እህል ምርቶች ላይ ከገበያና ከደላላ ጋር የተያያዘ ችግር እንደሚስተዋል የሚናገሩት ዳኛቸው (ዶ/ር)፣ ለምሳሌ ስንዴ በበጋ ሆነ በክረምት ቢመረትም በሚመረተው ልክ ወደ የተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ተጓጉዞ ለተጠቃሚው መድረስ አቅቶ ነው ወይ ተብሎ ቢጠየቅ ችግሩ ሌላ ሆኖ ሊገኝ ይችላል ብለዋል፡፡

አርሶ አደሩ ያመረተበት ቦታ ላይ ሆኖ ምርቱን የት ቦታ ላይ በምን ያህል ዋጋ እሸጣለሁ? የሚለውን የሚያውቅበት ቴክኖሎጂ ሲቀርብ ችግሩን ማቃለል እንደሚቻል ተገልጾ፣ በዚህ ረገድ ኢንስቲትዩቱ ናሽናል ማርኬት ኢንፎርሜሽን ሴንተር የሚባል የነፃ ጥሪ የሚያስተናግድ ማዕከል አደራጅቶ ጥቅም ላይ ማዋሉ ተጠቁሟል፡፡ ያም ሆኖ በአገር አቀፍ ደረጃ ከአትክልትና ፍርፍሬ ምርቶች የሚገኘውን ጥቅም ለማስጠበቅ፣ መንግሥት በዚህ ላይ ያሉትን ክፍተቶች ማሻሻል የግድ እንደሚለው ተመላክቷል፡፡

ዳኛቸው (ዶ/ር) እንዳስረዱት፣ የግብርና ምርት ተመርቶ ብዙኃኑ ተጠቃሚ ጋር ሳይደርስ ቀጥተኛ ባልሆነ መንገድ ድንበር የሚሻገር ነው፡፡ ይህም ከግብርና ዘርፍ የሚገኘውን ጥቅም አገሪቱ ሳትሆን ግለሰቦች ይበልጥ እንዲጠቀሙበት ምክንያት ሆኗል፡፡ 

የሚመለከታቸው አካላት አንድ ላይ መጥተው የቱ ጋ ነው ችግሩ? ማን ምን ሊያደርግ ይገባል? የሚለውን ተከፋፍለው ካልሠሩ በስተቀር በዚህ ላይ ለውጥ ማምጣት እንደማይቻል ዳይሬክተሩ ጨምረው ገልጸዋል፡፡

ለገበያ አሻጥሩና አርሶ አደሩን ለመጥቀም መላ ከሆኑት ጉዳዮች የኩታ ገጠም ግብርና ዘዴ አንዱ መሆኑ የተገለጸ ሲሆን፣ ይህም የክላስተር አካሄድ መሬትን አንድ ላይ አገናኝቶ ከማረስ አንስቶ እስከ መጨረሻው የግብይት ሥርዓት ድረስ አብሮ የሚሄድ፣ አርሶ አደሮችን ከእርሻ ተነስተው ተቋማት መሥርተው ምርቶቻቸውን የሚያቀርቡበት ደረጃ ለማድረስ የታለመ አካሄድ መሆኑን ዳኛቸው (ዶ/ር) አስረድተዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች