ከሁለት ሳምንታት ወዲህ ከፍተኛ የናፍጣ እጥረት በአዲስ አበባ ከተማ እየተፈጠረ ሲሆን ለምን እጥረቱ እንደተፈጠረ በሚሰጡት ምላሽ ላይ መንግሥትና የነዳጅ አቅራቢዎች ሊግባቡ አልቻሉም፡፡
ማደያዎችና ነዳጅ አመላላሾች እጥረቱ የተፈጠረው ከጂቡቲ የሚመጣ ነዳጅ በመጥፋቱ ነው በማለት መኪኖቻቸው ለቀናት ነዳጅ አጥተው ጂቡቲ መስመር ላይ መቆማቸውን ገልጸዋል፡፡
‹‹ከሁለት ሳምንታት ወዲህ በተለይ የናፍጣ እጥረት ተፈጥሯል፡፡ ይህም እጥረት የተከሰተው ጂቡቲ ላይ ተቀብለን የምናመጣው ናፍጣ ስለሌለ ነው፡፡ መኪኖቻችን ለቀናት ያለሥራ እየቆሙ ነው፤›› ሲሉ አቶ ኤፍሬም ተስፋዬ፣ የኢትዮጵያ ነዳጅ አዳዮች ማኅበር ቦርድ አባል ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡
ሪፖርተር ያነጋገራቸው የነዳጅና ኢነርጂ ባለሥልጣን ኃላፊዎች ደግሞ እጥረቱን የፈጠሩት ነዳጅ አከፋፋዮችና ማደያዎች እንደሆነ ይገልጻሉ፡፡
‹‹ከጂቡቲ ወደ ኢትዮጵያ በየቀኑ የሚጫነው ነዳጅ ባለፉት ሁለት ሳምንታት ውስጥ ከፍተኛ ጭማሪ አሳይቷል፡፡ በፊት በቀን ዘጠኝ ሚሊዮን ሊትር (በአማካይ) ይገባ የበረው በዚህ ሳምንት በአማካይ 9.294 ሚሊዮን ሊትር እየባ ነው›› ሲሉ የነዳጅና እነርጂ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ሆነው በቅርቡ የተሾሙት ወ/ሮ ሳህሬላ አብዱላሂ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡
ከጂቡቲ እየተጫነ ያለው 200 ሺሕ ሊትር ነዳጅ አዲስ አበባ ሳይደርስ በተለያየ ሰበብ መንገድ ላይ ቆይቶ እየተያዘ መሆኑን ዳይሬክተሯ ገልጸዋል፡፡ ሰኞ ሰኔ 20 ቀን 2014 ዓ.ም. አሥር ማደያዎች በአዲስ አበባ ውስጥ ነዳጅ እያላቸው መኪኖችን ሲመልሱ የተገኙ ሲሆን፣ በነጋታው 14 ነዳጅ የጫኑ ቦቴዎች አፋር ውስጥ ተደብቀው መገኘታቸውን ወ/ሮ ሳህረላ ተናግረዋል፡፡
ነዳጅ አከፋፋዮችና ማደያዎች አዲሱ የነዳጅ ውጤቶች ተመን ከሐምሌ አንድ ጀምሮ መተግበር እስኪጀምር፣ በእጃቸው የገባውን ነዳጅ ላለመሸጥ አዝማሚያ ማሳየታቸው እጥረት እየፈጠረ መሆኑ ዋናው ምክንያት እንደሆነ ተናግሯል፡፡
መንግሥት የነዳጅ ድጎማን ቀስ በቀስ ለማንሳት የወሰነው ውሳኔ ከሐምሌ 1 ቀን ጀምሮ የሚገበር ሲሆን፣ ይህም የነዳጅ ውጤቶችን ዋጋ ከፍ እንደሚያደርግ ይጠበቃል፡፡ ይህም ማለት አከፋፋዮችና ማደያዎች ከቀነ ገደቡ በፊት በድጎማ በዝቅተኛ ዋጋ የገዙትን ነዳጅ ከሐምሌ አንድ በኋላ ከፍ ባለው በአዲሱ ዋጋ ይሸጣል ማለት ነው፡፡ ድጎማው ሲነሳ በሊትር እስከ ዘጠኝ ብር ጭማሪ ሊኖር እንደሚችልና ይህም በአንድ ቦቴ እስከ 450 ሺሕ ብር ተጨማሪ ገቢ የሚያስገኝ እንደሆነ ባለሥልጣናቱ ገልጸዋል፡፡
‹‹ዋናው የእጥረቱ ምክንያት እስከ ድጎማው መነሳት ነዳጅ ለመያዝ መሞከር (Hoarding) ነው፡፡ የመኪና እጥረትም አይደለም፡፡ ጂቡቲ ላይ መዘግየት ያጋጠመው ለአንድ ቀን ሲሆን እሱም የጂቡቲዎች በዓል ቀን ስለነበር ነው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚሸጠው ነዳጅ በየቀኑ እየቀነሰ የመጣ ሲሆን፣ ከጂቡቲ የሚጫነው ግን ጭማሪ አሳይቷል፤›› ሲሉ አቶ አባይነህ አወል፣ በነዳጅ አቅራቢ ድርጅት የአቅርቦትና ሽያጭ ኃላፊ ገልጸዋል፡፡
ናፍጣ ከአጠቃላይ የነዳጅ ውጤቶች አቅርቦት ውስጥ እጥረት ሲያጋጥም አሁን የመጀመርያው ነው፡፡ አብዛኛው ጊዜ የሚፈጠረው የዲዝል እጥረት ነበር፡፡
በተለይ ማደያዎች ነዳጅን በብዛት ዴፖ ውስጥ መያዝ እየተው መምጣታቸው ለእጥረቱ አስተዋጽኦ እንዳደረገ አቶ አባይነህ ይገልጻሉ፡፡ ‹‹ማደያዎችና አከፋፋዮች ነዳጅ የሚወስዱት በብድር መሆኑ ቀርቶ በካሽ ክፈሉ ከተባሉ ወዲህ፣ የባንክ ወለድ በመፍራት ነዳጅ በብዛት ዴፖ ውስጥ መያዝ ትተዋል፡፡››
ወ/ሮ ሳህረላ ግን ድጎማው እስኪነሳ አንሸጥም ብለው በጫካ ውስጥ ጭምር ነዳጅ ጭነው ተደብቀው እየተያዙ ያሉትን እየፈለጉ መያዝና ነዳጅ ወደ ገበያው እንዲደርስ የማድረግ ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል፡፡