ካለፈው ሳምንት መጨረሻ አንስቶ የማዕከላዊና ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴዎች ውይይት ያደረገው ብልፅግና ፓርቲ ‹‹ሸኔን ከመፋለምና ከማጥፋት ውጪ ሌላ አማራጭ እንደሌለ›› አቅጣጫ ማስቀመጡን አስታወቀ፡፡
ፓርቲው፣ ፌዴራል መንግሥት በተለይም መከላከያ ሠራዊትና ፌዴራል ፖሊስ ለኦሮሚያ መንግሥት ድጋፍ የሚሰጡ ከሆነ ‹‹ጠላትን መምታት፣ ማዳከምና ማጥፋት›› የሚቻልበት ዕድል እንዳለ አቅጣጫ ማስቀመጡም ተነግሯል፡፡
ሸኔ በምዕራብ ወለጋ ግምቢ ወረዳ ቶሌ ቀበሌ የሚኖሩ ንፁኃን ላይ ካደረገው ጭፍጨፋ ጋር በተያያዘ ብልፅግና ፓርቲ የያዘውን አቋም አስመልክቶ የአማራና ኦሮሚያ ክልሎች ከፍተኛ አመራሮችና የፓርቲው ሥራ አስፈጻሚ አባላት ሰኞ ሰኔ 20 ቀን 2014 ዓ.ም. መግለጫ ሰጥተዋል፡፡
የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንትና የብልፅግና ፓርቲ ሥራ አስፈጻሚ አባል አቶ ሽመልስ አብዲሳ፣ ባለፉት ዓመታት አገሪቱ ባለፈችበት ሒደት ውስጥ የብሔርና የሃይማኖት ፅንፈኝነት አስተሳሰቦች በብዙ መልኩ ቦታ እያገኙ የመጡበት ሁኔታ መኖሩን ፓርቲው መገምገሙን ጠቅሰው፣ እነዚህን አስተሳሰቦች ለማዳከም የተወሰዱ ዕርምጃዎች ከፍተኛ ውስንነት ያለባቸው መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡
ይኼ ፅንፈኝነት ወደ ሽብርተኝነት ማደጉን የተናገሩት አቶ ሽመልስ፣ ‹‹መንግሥትን፣ የተደራጀ፣ የታጠቀ ኃይልን ከመታገል ውጪ ንፁኃንን፣ የእነሱን አስተሳሰብ የማይቀበል ላይ ኋላ ቀር የሆነ ዕርምጃ የመውሰድ አካሄድ ባለፉት ዓመታት እያደገ መጥቷል፤›› ብለዋል፡፡
አክለውም ‹‹ይኼ ፅንፈኝነት እያደገ ኢትዮጵያ ውስጥ አደገኛ አረም እየሆነ ነው ያለው፣ ይኼንን መንቀል ይኼንን ማስተካከል ግዴታ ነው፤›› በማለት ተናግረዋል፡፡
አቶ ሽመልስ፣ የሸኔ ቡድንም ይኼንን አካሄድ እንደተከተለና ቡድኑ አስተሳሰቡን ለመጫን እየሞከረ ያለው በኅብረተሰቡ ውስጥ ፍርሃት በመፍጠር መሆኑን አስረድተዋል፡፡ ፕሬዚዳንቱ ይኼንን ሲገልጹም ‹‹አንዳንዱ የሸኔ አባል አባቱን እየገደለ ነው ያለው፣ ሌላው ይቅር አባቱን፣ ወንድም ወንድሙን እያረደ ነው ያለው፤›› ብለዋል፡፡
በክልሉና በአገር አቀፍ ደረጃ በተወሰዱ ዕርምጃዎች ተበታትኖ የነበረው የሸኔ ኃይል፣ ጋምቤላና ደምቢ ዶሎ ከተሞችን እንዲሁም ግምቢ ወረዳን ለማጥቃት ዕቅድ አውጥቶ ሲንቀሳቀስ እንደነበር ተናግረዋል፡፡ ይሁንና ‹‹እንደ ዕቅዱ ስላልሄደለት›› ንፁኃንን መግደሉን ገልጸዋል፡፡
እንደ አቶ ሽመልስ ገለጻ ‹‹ሸኔ›› የግምቢውን ጭፍጨፋ የፈጸመው ሦስት ዓላማዎችን ለማሳካት ነው፡፡ ፕሬዚዳንቱ የመጀመሪያው ዓላማ ብለው የጠቀሱት ‹‹የአማራና የኦሮሞ ሕዝብን ለማለያየት›› የሚለውን ሲሆን ‹‹ትልቁ የሸኔ ዓላማ ይኼ ነው፤›› ብለዋል፡፡ ሁለተኛው ዓላማ በአገሪቱ ላይ ፍርሃት ማስፈን እንደሆነና በዚህም የዜጎች የመኖር ጉዳይ ጥያቄ ውስጥ እንዲገባ ማቀዱን አብራርተዋል፡፡ በሦስተኛ ደረጃም፣ ‹‹ሽብርተኝነት ራሱን እስኪበላ አይቆምም ያሉት›› አቶ ሽመልስ ‹‹የሸኔ›› አባላት የራሳቸውን ቤተሰቦች ጭምር ይገድላሉ የሚል ክስ አቅርበዋል፡፡
‹‹ይኼ ኃይል የእጁን እንዲያገኝ የማድረግ፣ የማፅዳት፣ ያለ ምሕረት ዕርምጃ የመውሰድ፣ ይኼንን በማድረግ የኢትዮጵያን አንድነት የማስቀጠል›› ሥራ መሠራት እንዳለበት ተናግረዋል፡፡
የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳደርና የብልፅግና ፓርቲ የሥራ አስፈጻሚ አባል ይልቃል ከፋለ (ዶ/ር) ይኼንን ጥቃት የፈጸሙት ኃይሎች፣ ጥቃቱን አገር ለማፍረስና አመራሩ እርስ በርሱ እንዲጋደል ለማድረግ እንደ መነሻ አድርገው እንደወሰዱት ገልጸዋል፡፡
የብልፅግና ፓርቲ ሥራ አስፈጻሚና ማዕከላዊ ኮሚቴ ከሰሞኑ ባደረጋቸው ስብሰባዎች፣ በምዕራብ ወለጋ የተፈጸመውን ጭፍጨፋ በፅኑ ማውገዙን ይልቃል (ዶ/ር) ተናግረዋል፡፡ አክለውም ‹‹ማዕከላዊ ኮሚቴው በጉዳዩ ላይ ተወያይቶ ያስቀመጠው አቅጣጫ ሸኔን ከመፋለምና ከማጥፋት ውጪ ሌላ አማራጭ እንደሌለ [ነው]›› ብለዋል፡፡
ለዚህም የፓርቲና የመንግሥት አመራሮች ግምባር ቀደም ኃላፊነት መውሰድ እንዳለባቸው ያሳሰቡት ይልቃል (ዶ/ር)፣ ‹‹በአዋሳኝ አካባቢዎች መረጃ እየተቀያየርን የጋራ ኮሚቴ እያዋቀርን የጋራ ጠላት የሆነውን በጋራ መዋጋት አለብን፤›› በማለት ተናግረዋል፡፡
‹‹ፌዴራል መንግሥት በተለይ መከላከያና ፌዴራል ፖሊስ ኃይሉን አጠናክሮ የኦሮሚያ መንግሥትን ከደገፈ፣ ጠላትን መምታት ማዳከምና ማጥፋት የሚቻልበት ዕድል እንዳለ አቅጣጫ ተቀምጧል፤›› በማለትም በሰሞኑ ውይይት ፓርቲው የያዘውን አቋም አስረድተዋል፡፡
‹‹አሁን ጠላቶቻችን ብዙ ናቸው›› ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ አማራ ክልል ከሕወሓትና ከሱዳን የጦርነት ነጋሪት እየተጎሰመበት መሆኑን ገልጸዋል፡፡ አክለወም ‹‹እነዚህን አብረን ተባብረንና ተቀናጅተን ብቻ ነው ማጥፋት የምንችለው፤›› በማለት ኢትዮጵያውያን ድጋፋቸውን እንዲሰጡ ጠይቀዋል፡፡