Tuesday, December 5, 2023

የወንጀል ሕግ ሥነ ሥርዓት ረቂቅ የፖሊስን ሥልጣን ይጋፋል የሚል ትችት ቀረበበት

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

ላለፉት 15 ዓመታት በዝግጅት ላይ የቆየው የወንጀል ሕግ ሥነ ሥርዓትና የማስረጃ ረቂቅ ሕግ፣ ዓቃቤ ሕግ የወንጀል ምርመራ እንደሚያደርግ መደንገጉ ከፌዴራል ፖሊስ፣ ከፌዴራል ፍርድ ቤቶችና አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ፍትሕ ቢሮ ትችት ቀረበበት፡፡

ረቂቅ ሕጉ ዓቃቤ ሕግ በያዘው የምርመራ መዝገብ ውጤታማ ሥራ ያላከናወነ መርማሪ ፖሊስ በሌላ መርማሪ ፖሊስ እንዲተካ ሥልጣን ሰጥቶ መደንገጉ፣ በፌዴራል ፖሊስ በኩል “የፖሊስን ሥልጣን ይጋፋል” የሚል ወቀሳ ቀርቦበታል፡፡

ከ1954 ዓ.ም. ጀምሮ እያገለገለ ያለውን የሥነ ሥርዓት ሕግ ለመለወጥ የወጣው ይህ ረቂቅ ሕግ፣ በሚኒስትሮች ምክር ቤት ፀድቆ ወደ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተላከው በ2013 ዓ.ም. ነበር፡፡ ረቂቅ ሕጉ በ1996 ዓ.ም. ለወጣው የወንጀለኛ መቅጫ ሕግ የሥነ ሥርዓትና መረጃ አካሄድን የሚመራ ሲሆን፣ እስካሁን ድረስ የወንጀል ክሶች እየተመሩ ያሉት ከ60 ዓመታት በፊት በወጣው የሥነ ሥርዓት ሕግ ነው፡፡

በዝግጅት ላይ ዓመታትን ያስቆጠረው ይህ ሕግ፣ እንደ የጥፋተኝነት ድርድር (Plea Bargain) እና ባህላዊ የዕርቅ ሥርዓቶችን በአማራጭ የፍትሕ ዓይነቶች ያቀርባል፡፡

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሕግ፣ ፍትሕና የዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ፣ ሰኔ 18 ቀን 2014 ዓ.ም. የተለያዩ ባለድርሻ አካላት በተገኙበት በረቂቅ ሕጉ ላይ የሕዝብ ይፋ ውይይት አድርጓል፡፡

በውይይቱ ወቅት ከእዚህ ቀደም በረቂቅ ሕጉ ላይ የተሰጡ አስተያየቶች ተካተው መስተካከላቸው በጥሩ ጎን ቢነሳም፣ ‹‹አሁንም ያልተስተካከሉ ጉዳዮች አሉ›› የሚል ሐሳብ ከፍርድ ቤትና ከፖሊስ ተነስቷል፡፡

ከተነሱ ትችቶች መካከል አንዱ ረቂቅ ሕጉ የፖሊስ ሥልጣን የሆነውን ምርመራ የማድረግ ሥራ ለዓቃቤ ሕግም ይሰጣል የሚለው ይገኝበታል፡፡ ረቂቅ ሕጉ የዓቃቤ ሕግ ተቋምን ተግባርና ኃላፊነትን ሲዘረዝር፣ ‹‹የወንጀል ምርመራን ይመራል፣ አስፈላጊ ሆኖ ሲያገኘውም በራሱ ምርመራ ያከናውናል›› የሚል አንቀጽ አካቷል፡፡

ይህንን ጉዳይ በመጀመርያ ያነሱት የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ሰለሞን አረዳ ሲሆኑ፣ ‹‹ፖሊስ የፖሊስን፣ ዓቃቤ ሕግ የዓቃቤ ሕግን ሥራ መሥራት አለበት፤›› በማለት የተቋማት የኃላፊነት መደበላለቅ መኖር እንደሌለበት አስታውቀዋል፡፡

አክለውም፣ ‹‹ዓቃቤ ሕግ በዋናነት ክስ የመምራት ሒደቱን ኃላፊነት ቢረከብ፤ ፖሊስ የምርመራ ሥራውን ቢሠራ፣ እንዲሁም ለዜጎች መብትና ጥቅም ሲባል ደግሞ አንዱ የአንዱን ሥራ የመቆጣጠር ኃላፊነት በግልጽ መቀመጥ አለበት፤›› ሲሉ አስረድተዋል፡፡

በረቂቅ ሕጉ ላይ ዓቃቤ ሕግ ምርመራ የሚያደርግ መርማሪ ፖሊስን በሌላ እንዲቀየር የማድረግ ሥልጣን መሰጠቱን የጠቀሱት ምክትል ፕሬዚዳንቱ፣ ፖሊስና ዓቃቤ ሕግ የተለያዩ ተቋማት ሆነው ሳለ ጣልቃ መግባትን እንደሚያስከትል ገልጸዋል፡፡

ሁለቱ አካላት የተለያዩ የመሆናቸው ጉዳይ በፌዴራል ፖሊስ ረዳት ኮሚሽነር ብርሃኑ አበበም ተወስቷል፡፡ ረዳት ኮሚሽነሩ ፖሊስ በሚቋቋምበት አዋጅ የተሰጠው የራሱ ሕጋዊ ሥልጣን እንዳለው በመግለጽ፣ ዓቃቤ ሕግ ምርመራ ያደርጋል ከሚለው ባሻገር ምርመራ ይመራል መባሉንም ተቃውመዋል፡፡

ሁለቱ አካላት አንዳቸው በአንዳቸው ውስጥ ጣልቃ ሳይገቡ ቁጥጥር የሚደራረግቡት (Check and Balance) መዘርጋትን እንደሚደግፉ የገለጹት ረዳት ኮሚሽነር ብርሃኑ፣ ዓቃቤ ሕግ ምርመራን የሚመራ ከሆነ ፖሊስ ትዕዛዝ ጠባቂ ይሆናል የሚል ቅሬታ አሰምተዋል፡፡ አክለውም፣ ‹‹የምንጠባበቅ ከሆነ የሕዝቦችን ሰላምና ደኅንነት ለማስከበር በጣም አስቸጋሪ ይሆናል፣ ስለዚህ የአንዱን ሙያ ለአንዱ መስጠት አስቸጋሪ ነው፤›› ብለዋል፡፡

በረቂቅ ሕጉ ላይ፣ ‹‹በያዘው የምርመራ መዝገብ ውጤታማ ሥራ ያላከናወነ መርማሪ ፖሊስ በሌላ መርማሪ ፖሊስ እንዲተካ ያደርጋል፤›› የሚለው አንቀጽም፣ በፌዴራል ፖሊስ ወቀሳ ደርሶበታል፡፡ ረዳት ኮሚሽነሩ፣ ‹‹ፖሊስ የራሱ መተዳደሪያ ደንብ አለው፣ አዋጅ አለው፣ [መርማሪ ፖሊስ] ሲያጠፋ በራሱ በኩል በዲሲፕሊን ነው የሚቀጣው፤›› ብለው፣ ይህ አንቀጽ የአንድን ተቋም ሥልጣን ለሌላ የሚሰጥ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ ቀጥለውም ይህ አሠራር ቀስ በቀስ ፖሊስ የራሱ በጀት የማይበጅትበትንና ሠራተኛ የማይቀጥርበት ሁኔታ እንደሚፈጥር ሥጋታቸውን ገልጸው፣ “ይህ ተደርጎም አይታወቅም” በማለት ትችት አቅርበዋል፡፡

በተጨማሪም ረቂቁ የፖሊስ ተቋምን ተግባርና ኃላፊነት ሲዘረዝር፣ ‹‹የዓቃቤ ሕግ የምርመራ መዝገብን አስመልክቶ ከዓቃቤ ሕግ የሚሰጠውን ትዕዛዝ ይፈጽማል›› በሚል የተቀመጠውም ድንጋጌ ትችት ተነስቶበታል፡፡ ረዳት ኮሚሽነሩ፣ ‹‹ማስገደድ ካለው በፍርድ ቤት በኩል የፍርድ ቤት ትዕዛዝ ይፈጽማል ተብሎ በግዴታ ቢቀመጥ ነው እንጂ፣ የዓቃቤ ሕግ ትዕዛዝን ይፈጽማል ተብሎ በግዴታ መቀመጡ ሁለቱን ተቋማት የሚያሻክር ዓይነት ነው፤›› በማለት ተቃውመዋል፡፡

በረቂቁ ላይ የተቀመጠውን ዓቃቤ ሕግ ምርመራ የማድረግ ጉዳይን በሚመለከትም የአዲስ አበባ ፍትሕ ቢሮም ጥያቄ አቅርቦበታል፡፡ ቢሮውን የወከሉት አቶ ጀማል ሳለህ፣ ዓቃቤ ሕግ ምርመራን የመምራቱ ጉዳይ አስፈላጊ መሆኑን እንደሚያምኑበት ቢገልጹም፣ ‹‹[ዓቃቤ ሕግ] ምርመራ ያደርጋል የሚለው ግን አሁንም ትኩረት ቢሰጥበት፤›› ብለዋል፡፡

በውይይቱ ላይ ተገኝተው ማብራሪያ የሰጡት የፍትሕ ሚኒስትር ደኤታ አቶ ዓለምአንተ አግደው ለተነሳው ትችት ምላሽ ሲሰጡ፣ በረቂቅ ሕጉ ላይ የምርመራ ሥራ የፖሊስ ኃላፊነት መሆኑ በግልጽ መቀመጡን ጠቅሰዋል፡፡ ‹‹በኋላ ላይ ክስ የሚያቀርብ ዓቃቤ ሕግ ነው፣ ስለዚህ በትክክል ማስረጃ ስለመሰብሰቡ፣ ማስረጃዎች ስለመሟላታቸው ከወዲሁ ማረጋገጥ መቻል አለበት፤›› የሚል መከራከሪያ በማቅረብ፣ ከምርመራ ጋር በተያያዘ ለዓቃቤ ሕግ የተሰጠውን ሥልጣን ደግፈዋል፡፡

ይህ ዓይነቱ አሠራር በብዙ አገሮች የተለመደ መሆኑን የጠቀሱት ሚኒስትር ደኤታው፣ ‹‹እንዲያውም ምርመራን ከመምራት አልፎ ዓቃቤ ሕግ ሳያውቅ ምርመራ የማይጀመርባቸው አገሮች አሉ፤›› ብለዋል፡፡ አክለውም፣ ‹‹ለቼክ ኤንድ ባላንስ የተቀመጠ ነው፣ የፖሊስ ተቋምን የሚነካ ተደርጎ ከቤቱ በተገለጸው አግባብ እንዳልሆነ መታወቅ አለበት፤›› ሲሉም አስረድተዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -