በአንድ ወቅት በቅርቡ ከሥልጣናቸው የተሰናበቱትን የፊሊፒንስ ፕሬዚዳንት በተመለከተ የወጣውን ዜና መቼም ቢሆን አልረሳውም፡፡ የዜናው ርዕስ ‹‹የፊሊፒንስ ፕሬዚዳንት ሙሰኛ ባለሥልጣናትን ከሔሊኮፕተር ላይ እወረውራለሁ›› ነው የሚለው፡፡ በመጀመሪያ ብደነግጥም ሰውዬው እየቀለዱ ይሆን እንዴ በማለት ዜናውን ማንበብ ቀጠልኩ፡፡ ሰውዬው በፍፁም እየቀለዱ አይደሉም፡፡ ይልቁንም ከዚህ በፊት እንዲህ ያለ ድርጊት መፈጸማቸውን በግልጽ እየተናገሩ ነበር፡፡ ፕሬዚዳንት ሮድሪጎ ዱቴርት በወቅቱ በምርጫ አሸንፈው ሥልጣን ላይ የወጡ ቢሆኑም፣ ከዚህ ቀደም ዓቃቤ ሕግና የከተማ ከንቲባ ነበሩ፡፡ እሳቸው ግን ሙሰኛም ሆነ የዕፅ አዘዋዋሪ ‹‹ወንጀለኛ›› ስለሆነ በሕግ ሳይሆን፣ አስፈላጊው ዕርምጃ ይወሰድበታል ነው ይሉ የነበሩት፡፡
ከዚህ ቀደም በአስገድዶ ደፋሪዎች፣ በአጋቾችና በዕፅ አዘዋዋሪዎች ላይ ራሳቸው ግድያ መፈጸማቸውን፣ ፕሬዚዳንት ሆነው የመንግሥት ባለሥልጣናት ሙስና ሲፈጽሙ ካገኙ፣ በመብረር ላይ ካለ ሔሊኮፕተር ላይ ወደ መሬት እንደሚወረውሩ ዝተው ነበር፡፡ ‹‹ከዚህ በፊት በአስገድዶ መድፈርና በግድያ የተጠረጠረ ቻይናዊ ከሔሊኮፕተር ላይ ወርውሬያለሁ፡፡ አሁንም እንዲህ ዓይነቱን ዕርምጃ ከመውሰድ የሚገታኝ የለም…›› ካሉ በኋላ፣ ወንጀልን መከላከልና የሕዝቡን ደኅንነት ማስጠበቅ የሚቻለው እሳቸው ‹‹ወንጀለኛ›› በሚሏቸው ሰዎች ላይ የማያዳግም ዕርምጃ በመውሰድ ብቻ እንደሆነ አስረግጠው ተናግረው ነበር፡፡
ፕሬዚዳንት ዱቴርት ሥልጣን ላይ ከወጡ ወዲህ በዕፅ አዘዋዋሪዎች ላይ በወሰዱት ወታደራዊ ዕርምጃ 6,000 ያህል ሰዎች መገደላቸው በዜናው ውስጥ ተካቶ ተዘግቧል፡፡ በዚህ የተነሳ የአገር ውስጥም ሆኑ ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ተቆርቋሪዎች ከሕግ ውጪ በሚወሰድ ዕርምጃ ንፁኃን እየተገደሉ መሆኑን፣ ይህም በፊሊፒንስ ዜጎች ላይ ከፍተኛ የሆነ ፍራቻ መፍጠሩን በተለያዩ ዘገባዎች መጠቀሱን በዜናው ተካቷል፡፡ እሳቸው ግን ዳቫኦ የምትባለው ከተማ ከንቲባ በመሆን ለ22 ዓመታት ሲሠሩ፣ ሞተር ብስክሌት በመጠቀም ጭምር ‹‹ወንጀለኞች››ን ይገድሉ እንደነበሩ በይፋ መናገራቸው ከማስገረሙም በላይ ድንጋጤ መፈጠሩ የዜናው አካል ነበር፡፡
እሳቸው በተገኙበት ቦታ የሚገድሏቸው ሰዎች፣ በሕጋዊው የፖሊስ ኦፕሬሽን መሠረት የሚገደሉ ናቸው በማለት ይሞግታሉ፡፡ ሌላው ቀርቶ በአንድ ወቅት እሳቸው ከከተማ ውጪ በነበሩበት ጊዜ ፖሊስ በቁጥጥር ሥር ያዋላቸው ስድስት ግለሰቦች ‹‹ዕድለኛ ናቸው›› ብለዋል፡፡ ግለሰቦቹ የተያዙት ከግማሽ ቶን በላይ ዕፅ ተገኝቶባቸዋል ነው ተብለው ሲሆን፣ እሳቸው ከከተማ ውጪ መሆናቸው በጀ እንጂ ‹‹ይገደሉ ነበር›› ብለዋል፡፡ ‹‹እኔ በዋና ከተማዋ ማኒላ አለመኖሬ ዕድለኞች ናቸው፡፡ እኔ እዚያ ብኖርና ከእነ ዕፃቸው ባገኛቸው ዕጣ ፈንታቸው ተረሽኖ መሞት ነበር…›› በማለት ንግግር አድርገዋል፡፡ ‹‹ፈፅሞ ድራማ ለመሥራት አንሞክር፣ እኔ ራሴ ነበርኩ የምረሽናቸው…›› የሚለው ንግግር የዓለም መነጋገሪያ እንደሆነ በተለያዩ ዘገባዎች መውጣቱንም አስታውሳለሁ፡፡
እንግዲህ ወገኖቼ ልብ በሉ፡፡ ምንም እንኳ ተርጣሪዎችን በሕጋዊ መንገድ በቁጥጥር ሥር አውሎ ለሕግ ማቅረብ የግድ ቢሆንም፣ ንፁኃንን የሚጨፈጭፉ አረመኔዎች አገርን ሲያተራምሱ ግን የኃይል ዕርምጃ የግድ መሆኑን እዚህ ላይ መገንዘብ ተገቢ ነው እላለሁ፡፡ የመንግሥት ሕግ የማስከበር ኃላፊነት በሥርዓቱ ካልተመራ እንደ ፊሊፒንሱ የቀድሞ ፕሬዚዳንት ዱተርቴ፣ ሕገወጥነትን በማስከተል በአገር ላይ ተገቢ ያልሆኑ ድርጊቶች እንዲፈጸሙ መንገዱን ያመቻቻል፡፡ ነገር ግን ሕዝብና መንግሥት ሲናበቡና ሕግ የማስከበር ተግባሩ ለአገር የሚበጅ ሲሆን፣ አገር የሚያወድሙ የጠላት ተላላኪዎች ንፁኃንን እየጨፈጨፉ እንዳሻቸው አይፈነጩም፡፡ ለዚህም ነው መንግሥት ቆፍጠን ብሎ ከሕዝብ ጋር ሕግና ሥርዓት ማስከበር አለበት መባል የሚኖርበት፡፡
አንድ ጊዜ መገናኛ አካባቢ ለሥራ ጉዳይ እሄዳለሁ፡፡ ንብረትነቱ የጀግናው ሻለቃ ኃይሌ ገብረ ሥላሴ ከሆነው ማራቶን ሞተር የሚገኝበት ሕንፃ አለፍ ብዬ ወደ መገናኛ ታክሲ መናኸሪያ ሳዘቀዝቅ፣ ሁለት ፖሊሶች አንድ ሰው ይዘው እየደበደቡ ወደ ላይ ይወጣሉ፡፡ ሁለቱ ፖሊሶች በያዙት አጭር ጥቁር ቆመጥ እየቀጠቀጡት አጠገቤ ሲደርሱ ሰውዬው ከአፉና ከአፍንጫው ደም ቡልቅ ይላል፡፡ በቀጥታ ወደ እነሱ በመሄድ፣ ‹‹በሕግ አምላክ!›› ስላቸው ቆሙ፡፡ አንዱ ወዲያው ዘሎ ላዬ ላይ ለመከመር ሲንደረደር ዞር አልኩበት፡፡ ተንገዳግዶ በሁለቱ እጆቹ መሬት ከነካ በኋላ ተፈናጥሮ በመነሳት ቆመጡን ማወናጨፍ ሲጀምር አሁንም፣ ‹‹በሕግ አምላክ!›› በማለት ስጮህ በአካባቢው የነበሩ ሰዎች መሀላችን ገቡ፡፡ አካባቢው በአንዴ በሰዎች ተወረረ፡፡ ብዙ ንትርክ ተፈጥሮ በስንት ገላጋይ ተለያየን፡፡
ሌላውን ሀተታ ልተወውና ፖሊስ ያልተፈረደበትን ተጠርጣሪ አይደለም እጅ ከፍንጅ የተያዘን ቀማኛ ሕግ ፊት ማቅረብ እንጂ መማታት የለበትም፡፡ ሕጉ፣ ‹‹ማንም ተጠርጣሪ እስኪፈረድበት ድረስ ንፁህ ነው ተብሎ የመገመገት መብት አለው›› ይላል፡፡ ብዙ ቦታ ግን ፖሊሶቻችን የያዙትን ሰው ለምን ይደበድባሉ? አስቸጋሪ ሰው ቢያጋጥማቸው እንኳ አረጋግተው ወደ ሕግ ማቅረብ ለምን ይቸግራቸዋል? የሚለው በጣም ያሳስበኛል፡፡ ለዚህ ጉዳይ የሚመለከታቸው ሁሉ አንድ መላ ቢፈልጉ ጠቃሚ ነው፡፡ በሌላ በኩል ከመንግሥት ባለሥልጣናት ጀምሮ የእኔ ቢጤው ዜጋ ድረስ ለሕግ የበላይነት ክብደት አለመስጠት፣ በአገር ላይ የሚያመጣውን ትልቅ ችግር መገንዘብ ያስፈልገናል፡፡ ሁላችንም ብንሆን ጊዜ ሲያጋድልብን ወይም ባላሰብነው ጊዜ ችግር ሲገጥመን ከሕግ በላይ ምንም መተማመኛ ሊኖረን አይገባም፡፡ ፍትሕ ያጡ ሰዎች ይህንን ይረዱታል ብዬ አስባለሁ፡፡ ሕግ ባለበት አገር ሕገወጦች ንፁኃንን ሲጨፈጭፉ፣ ሲያሰቃዩና ሲያስለቅሱ ከማየት የበለጠ አሳዛኝ ነገር የለም፡፡ ‹‹ነግ በእኔ›› ማለት ካልተቻለ ሁላችንም የሕገወጦች ሰለባ እንሆናለን፡፡ እስኪደርስብን ድረስ ግን ላይሰማን ይችላል፡፡ ሕመሙ ከባድ ነው፡፡ የሰሞኑ የምዕራብ ወለጋ ጭፍጨፋ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ እንዲቆም ማድረግ ካልተቻለ መጨረሻችን ይመስላችኋል?
(ተሾመ ተፈራ፣ ከአራት ኪሎ)