በመኮንን ዛጋ
ባለፉት ሦስት አሠርት ዓመታት ብሔራዊ ውይይቶች ለግጭት አፈታት ዘዴ፣ ለዘላቂ ሰላም ግንባታ፣ እንዲሁም ለፖለቲካዊ የተሳትፎና የማካተት ምኅዳሩን ለማስፋት የሚያስችሉ አዋጭ ማዕቀፎች መሆናቸው በተለያዩ አካላት ዘንድ ያለው ግንዛቤ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መጥቷል። ይህን መሰል ውይይት በዋናነት በአገር አቀፍ አካላት ባለቤትነት የሚከወን ሒደት ቢሆንም ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ፣ ብዙ ጊዜ ደግሞ ባለ ብዙ ወገን ክልላዊና ክፍለ አኅጉራዊ ድርጅቶች ከግጭቶቹ ተፈጥሯዊ ባህሪና የዓውድ ተለዋዋጭነት በመንተራስ፣ ብሔራዊ የውይይት ሒደቶችን በመደገፍ ረገድ ጉልህ ሚና ይጫወታሉ።
በአንዳንድ አገሮች ዘንድ ብሔራዊ ውይይት ለሰላማዊ የፖለቲካ ሽግግርና ለሁለንተናዊ ዘላቂ ለውጥ ምቹ ጥርጊያ መንገድ ማበጀት የሚያስችል አገር በቀል አቅም ለመፍጠር እንደ አንድ ሁነኛ መሣሪያ ለመገልገል ከፍተኛ ትኩረት እየሳበ የሚገኝ ጽንሰ ሐሳብ ቢሆንም፣ እስካሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ ግን ሁሉን ችግር በአንዴ ጠራርጎ በመምታት ዘላቂ ሰላም ለመፍጠር የሚያስችል አስማታዊ ጥይት ሲሆን አልታየም፡፡ ብሔራዊ ውይይቶች እንደ ፈርጃቸው በጣም ስኬታማ ሆነውባቸዋል የሚባሉ አገሮችን ሁኔታ እንኳ ብንመለከት፣ ሰላማዊ ማኅበረሰብን ለመገንባት ለሚደረገው ረዥምና አድካሚ መንገድ እንደ አንድ ዕመርታዊ ዕርምጃ ሆነው ነው የሚያገለግሉት፡፡
የተለያዩ የጥናትና ምርምር ሰነዶች እንደሚያሳዩት ከሆነ ደም አፋሳሽ ግጭቶች የከፋ ጉዳት ሳያደርሱ፣ የፖለቲካ ሽግግሮች ደግሞ ሰላማዊና ዘላቂ መፍትሔ ባበጀ መንገድ እንዲጠናቀቁ ለማድረግ አገሮች ሁሉን አቀፍ አገራዊ ውይይቶችን እንደ አማራጭ የችግር መፍቻ ሥልት መጠቀም ከጀመሩ ዋል አደር ብለዋል፡፡ በእርግጥ አገራዊ ውይይቶች በተደራጀ መንገድ እንኳ ባይሆን በተለያዩ አገሮች በልዩ ልዩ ቅርፅና ይዘት ሲከናወኑ ቆይተዋል፡፡ ሆኖም ከዚህ አንፃር መስተካከል የሚገባው የዕይታ ፈርጅ ደግሞ አገራዊ ውይይቶችን ለፖለቲካዊ ችግሮች ብቻ እንደ መፍትሔ የመቁጠር አዝማሚያን ነው፡፡ እንደ ምያንማር ያሉ አገሮች መሰል ውይይቶችን በቋሚነት በማዘጋጀት ማኅበረ-ኢኮኖሚያዊ ችግሮቻቸውን ከሞላ ጎደል ከመሠረቱ ለመፍታት እየተጠቀሙ ይገኛሉ፡፡
በሌላ በኩል በዓለም ላይ የተካሄዱ በርካታ አገራዊ ውይይቶች በአካሄዳቸው ወይም በውጤት ረገድ አሊያም በትግበራ ሒደት በስኬታማነት ወይም በመጨንገፍ የተጠናቀቁ ሲሆን፣ ለእነዚህ ውይይቶች የስኬት ወይም የውድቀት መንስዔ የሚሆኑ በርካታ መሠረታዊ ገፊ ምክንያቶችን በዝርዝር መግለጽ፣ ቢቻልም በዋነኝነት ተጠቃሹ መንስዔ ግን የውጭ ኃይሎች በአካባቢው ላይ ያሳደሩት ግፊት፣ የሚኖራቸው ሥልታዊ ፍላጎትና የጥቅም ግጭቶች ዋነኞቹ ናቸው፡፡
እንደሚታወቀው አገራችንም በበርካታ የግጭትና የቀውስ አዙሪት ውስጥም ሆና መሰል ውይይት ለማድረግ አዋጅ አፅድቃ፣ የምክክር ኮሚሽን አቋቁማና ኮሚሽነሮችን በመሾም እስከ ወርኃ ኅዳር ድረስ ለመከናወን ጊዜ የተቆረጠለት አገራዊ የምክክር መድረክ ለማዘጋጀት ደፋ ቀና እያለች ትገኛለች፡፡ በእርግጥ ይህ ኮሚሽን ከአዋጅ አወጣጡ እስከ ኮሚሽነሮች ሹመት ድረስ በርካታ የተዓማኒነትና አካታችነት ውዝግቦች እየተነሱበት ይገኛል፡፡ በርካታ መሻሻል ያለባቸው ነገሮች እንዳሉ ሆነው ኮሚሽነሮቹ ከተለያዩ የአገር ውስጥና የውጭ አገሮች ልዑካን ጋር ውይይት እያደረጉ መሆኑን ይገልጻሉ፡፡ በቅርቡም ከጀርመን፣ ከስዊድን፣ እንዲሁም ከሌሎች ተፅዕኖ ፈጣሪ አገሮችና ባለ-ብዙ ወገን ተቋማት ተወካዮች ጋር በቀጣይ ስለሚኖራቸው ተሳትፎ ውይይት አድርገዋል፡፡ በአንፃሩ ደግሞ እንደ ኦፌኮ፣ ኦነግና ሌሎች ጉልህ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ዓለም አቀፍ ገለልተኛ አካላት በውይይቱ እንዲሳተፉ እንዲደረግ ገዥውን መንግሥትና የውጭውን ማኅበረሰብ በብርቱ እየወተወቱ ይገኛሉ፡፡ ሆኖም ለብሔራዊ ውይይት ከአገርም ሆነ ከተቋማት የሚቀርቡ ዓለም አቀፍ የድጋፍ ማዕቀፎች ላይ ብርቱ ጥንቃቄ ማድረግ ተገቢ ነው፡፡
በእርግጥ እንደ እኛ ባለ ታዳጊ አገር ውስጥ የሚደረግ ውይይት የውጭ ተዋንያን ድጋፍ (ለምሳሌ የፖለቲካ፣ የዲፕሎማሲ፣ የፋይናንስና የሎጂስቲክስ አቅርቦትና የቴክኒክ ድጋፍ) ወይም ተቃውሞ በብሔራዊ ውይይቶች የሒደት፣ የውጤት፣ እንዲሁም የትግበራና የስኬት ደረጃ ላይ ይህ ነው የማይባል ጉልህ ተፅዕኖ ሊያሳድር እንደሚችል ሳይታለም የተፈታ ጉዳይ ነው፡፡ ሆኖም በውጭ አካላት ድጋፍና በአገር ውስጥ አካላት ባለቤትነት መካከል ተገቢውን ሚዛን ማኖር እጅግ አስፈላጊ ጉዳይ ነው፡፡ ምክንያቱም የኋለኛው የሕዝብን ቀልብ የመግዛት ዕድል፣ የሕጋዊ ቅቡልነትን፣ የግንዛቤ መጎልበትና በተጨባጭ የመተግበር ዕድሎችን ሊጨምር ስለሚችል ነው።
አንዳንድ ጊዜም እነዚህ ሒደቶች እጅግ በጣም በርካታ አገራዊ ሀብቶችንና የፖለቲካ አቅምን (ኃይልን) አሟጠው የሚወስዱ ሲሆን በተጓዳኝ የመንግሥትን ሕዝባዊ አገልግሎቶች የማቅረብ፣ አገርን የማስተዳደርና ፐብሊክ ሸቀጦችን የማቅረብ መሠረታዊ ኃላፊነቱን እንኳ ችላ እንዲል ያደርጋሉ፡፡ በአንዳንድ ወቅቶች ደግሞ ብሔራዊ ውይይቶች እንዲሁ ባልተፈለገ የግጭት አዙሪት አቅጣጫ ሊጓዙ፣ አካሄዳቸውን ሊያቋርጡ ወይም በጭራሽ የማይተገበሩ ምክረ ሐሳቦችን ሊያወጡ ይችላሉ፡፡ በአንፃሩ ደግሞ ብሔራዊ ውይይት መስመር የያዘ ፖለቲካዊ ለውጥን ለማኮላሸትና የሰላም ፀር የሆኑ አፍራሽ ሒደቶችን ለማገዝም ጥቅም ላይ ሲውል ተስተውሏል፡፡ ይኸውም አገራዊ የዴሞክራሲ ግንባታ ሒደቶችን ለማደናቀፍና ምርጫዎችን ሆነ ብሎ ወደ ሌላ ጊዜ ለማስተላለፍ፤ ሥልጣን ላይ ያለው መንግሥት ወይም የፖለቲካ ልሂቃን ነባራዊውን ሁኔታ ባለበት ለማቆየት (Maintain the Status Quo) በሚያደርጉት ጥረት ውስጥ፣ የመደራደር አቅማቸውን ለማጎልበት፣ እንዲሁም ዜጎች ለለውጥ እንዲያምፁ በገፋፏቸው ጉዳዮችና በተገለጹ ሥጋቶች ላይ ምንም ዓይነት እውነተኛ የዓላማ፣ የግብ ወይም የፖለቲካዊ ሥልት አካሄድ ለውጥ ሳይኖር የዜጎችን ቅሬታዎች ለማቀዛቀዝ ወይም ለማስቆም አገልግለዋል፡፡ በአጭር አገላለጽ በውጫዊና ውስጣዊ ኃይሎች የተቀናጀ የሴራ ድርጊት የተነሳ አገራዊ ውይይቶች በለውጥ ፈላጊ ኃይሎች ስሜት ላይ ቀዝቃዛ ውኃ ሲከልሱ በተደጋጋሚ ተስተውሏል፡፡
የክልላዊ ተዋናዮችና ድርጅቶች ሚና
አብዛኛውን ጊዜ ጠንካራ ክልላዊ ተዋናዮችና ድርጅቶች እንደ ኢጋድ፣ ኮሜሳ፣ አፍሪካ ኅብረት በአገር ደረጃ ደግሞ ድንበር ተጋሪዎቹ እንደ ጂቡቲ፣ ኤርትራ፣ ሱዳን፣ ኬንያ ወዘተ. የመሳሰሉት ጎረቤት አገሮች በአገራችን የውስጥ ጉዳይ አስፈላጊ የሆኑ ብሔራዊ ጥቅሞች ይኖሯቸዋል፡፡ በዚህ የተነሳ ብሔራዊ ውይይቶች በሚደረጉበት ወቅት ሒደቱን በመደገፍም ሆነ በመቃወም ረገድ ከፍተኛ ፖለቲካዊና ምጣኔ ሀብታዊ ጫና ለማድረግ ይዘጋጃሉ። ይህ ጫና ደግሞ አገራችን የባህር በር አልባ ከመሆኗ ጋር ተሳስሮ እንዲበረታ ይሆናል፡፡ ስለሆነም ይህንን ጫና ለመቋቋም የክልላዊ ተዋናዮችን ፍላጎት በአንድም ሆነ በሌላ መንገድ በሚገባው ልክ መረዳትና ለማካተት መሞከር ይገባል። የዓለም አቀፍ ተዋናዮች ሚና
እንደ የምዕራቡና የምሥራቁ ዓለም ኃያላን አገሮች ያሉቱ (ክልላዊ ያልሆኑ) ዓለም አቀፍ ተዋናዮች በጥቅሉ በአገራችን ላይ ያሏቸው ተጨባጭ መሻቶችና ጠቀሜታዎች እጅግ ያነሱ ቢመስሉም እጅግ ስትራቴጂካዊ ናቸው፡፡ ነገር ግን በውይይቱ ሒደት በሚሳተፉበት ጊዜ አንድን ሒደት ለመደገፍ ወይም ለመቃወም የሚያስችል ትልቅ ዲፕሎማሲያዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ወታደራዊ ኃይል አላቸው።
በበርካታ የታሪክ አጋጣሚዎች ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ብሔራዊ ውይይቶችን ያላግባብ ጥቅም ላይ ለማዋል የሚሠሩ ፖለቲካዊ አሻጥሮችን በማወቅም ይሁን ባለማወቅ በመደገፍ የበኩሉን የግብር አበርነት ሚና ተጫውቷል፡፡ እንዲሁም የጥቅማቸው ሸሪክ የሆነ አሻንጉሊት መንግሥትን በመደገፍ እውነተኛ ሽግግርና ለውጥን ለማዘግየትና ለአፋኝና ለጨቋኝ መንግሥታት ተጨማሪ የሐሳብ፣ የአቅምና የጊዜ ድጋፍን ለመግዛት ለታቀዱ ብሔራዊ ውይይቶች ድጋፍ ወይም ማረጋገጫ ሰጥተዋል፡፡ ስለሆነም ዓለም አቀፍ ተዋንያን ብሔራዊ ውይይትን ለመደገፍ ወይም ላለመደገፍ በሚወስኑበት ጊዜ ብሔራዊ ውይይቱ በአገር መሪዎች በኩል በቅን ልቦና የታቀደ፣ በሀቀኛ የሕዝብ ወኪሎች መካከል የሚካሄድ፣ በፅኑ ፖለቲካዊ ቁርጠኝነት የታገዘ መሆኑን ማረጋገጥ የግድ አስፈላጊ የመሆኑን ያህል አገር አቀፍ ተዋናዮችም የውጭ ኃይሎችን ድጋፍ በጥንቃቄ ሊመለከቱት ይገባል፡፡
የብሔራዊ ውይይት ዓላማዎችና ፍላጎቶች ክንውን ከቅን ፖለቲካዊ መሻት (Political Will) ከመመንጨታቸው በተጨማሪ፣ የአገራዊ ልሂቃንና የየአካባቢው ማኅበረሰብ ሱታፌና ባለቤትነት ለስኬታማነቱ ነጥብ ወሳኝ ነው፡፡ ያለ ጠንካራ ተቋም፣ በማኅበረሰቡ ተቀባይነትና ክብር በሌለው ብሔራዊ የውይይት አስተባባሪ አካል የማይካሄድና ከበቂ በላይ ወካይ ቁጥር ባላቸው የአገሪቱ የፖለቲካ ቡድኖች ጥምረት ሐሳቡ የማይገዛ ከሆነ፣ ብሔራዊ ውይይት ትርጉም ያለው ለውጥ የማምጣት ዕድሉ አናሳ ይሆናል፡፡ የተቃዋሚ ተወካዮችና መንግሥታዊ አካላት (ባለሥልጣናት) በእኩላዊ ጣምራነት ነፃና ገለልተኛ በሆነ መንገድ ብሔራዊ ውይይትን የማቀድ፣ የማደራጀት፣ የማመቻቸትና የፋይናንስና ሎጂስቲክስ ድጋፍ የማቅረብን ቁልፍ ኃላፊነት ሊወስዱ ይገባል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ከውጫዊ ዓለም አቀፍና ክልላዊ ወገኖች የሚቀርብ ዕርዳታና ድጋፍ አስፈላጊ ክፍተቶችን ሊሞላ የሚችል ቢሆንም እንኳን፣ የውጭ ድጋፍ አቅራቢዎች የውይይቱን መሠረታዊ ኃላፊነቶች በአገሪቱ ባለሥልጣናትና ተወካዮች ጫንቃ ላይ ሙሉ በሙሉ እንዲተው ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ አለባቸው፡፡
በእርግጥ በአገራዊ ውይይት ሒደት ውስጥ የውጭ ኃይሎች የሚያደርጉት ያልተገባ ጫና ተገቢ ያለ መሆኑ፣ እንዲሁም የውስጠ ዜጎች ብሔራዊ ባለቤትነት መሠረታዊ ቢሆንም ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ጠቃሚ ድጋፍ የሚያደርግባቸው ወሳኝ ነጥቦች አሉ፡፡ ለምሳሌ ያህል በዲፕሎማሲው በኩል ጉዳዩ የሚመለከታቸው አገሮች ወይም ባለ ብዙ ወገን ሁለገብ ድርጅቶች ብሔራዊ ውይይትን የሚያቋቁመውን የመጀመርያ ስምምነት ለማደራደር፣ ሁሉን አቀፍ፣ አካታችነትና አሳታፊ ሒደትን የሚያበረታቱ ሕዝባዊ መግለጫዎችን ለማቅረብ ሊረዱ ይችላሉ፡፡
እነዚህ ውጫዊ ኃይሎች የሚኖራቸው አዎንታዊ ሚና ምንም ሆነ ምን በሌሎች ቡድኖች ወይም በአጠቃላይ የሕዝቡ ዕይታ ዘንድ የውይይቱን ተዓማኒነት፣ ምሉዕነትና የነፃነት ስሜት ሊያደፈርስ ስለሚችል ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ አንድ የተወሰነ ቡድንን በሒደትም፣ በሐሳብም፣ በድርጊትም እንዳይደግፍ ብርቱ ጥንቃቄ ማድረግ አለበት። በቴክኒክ ዕርዳታው ረገድ እነዚህ ዓለም አቀፍ ተዋንያን፣ በተለይም ጥልቅ የትንታኔ ሐሳብና የዳጎሰ መረጃን በሚጠይቅ ተከታታይ የመደራደር ሒደት እምብዛም ፖለቲካዊ ልምድ የሌላቸውን ተወካዮች በሙያ በመደገፍ በብቃት የመሳተፍ አቅማቸውን ለመገንባት ሊሠሩ ይችላሉ፡፡ እንዲሁም እነዚህ ዓለም አቀፍ ተዋንያን የመወያየቱ ዋናው ኃላፊነቱና ውሳኔ የመስጠቱ ሥልጣን በአገራዊ ተዋንያኑ እጅ ላይ እንዳለ እንዲቆይ በማድረግ በብሔራዊ ውይይቶች ክንውን፣ ትግበራና ክትትል ላይ እጅግ አስፈላጊ ድጋፍ ማድረግ ይችላሉ፡፡ ይህ ድጋፍ ከብሔራዊ ውይይቱ መባቻ የሚወጡ የፖሊሲ ቅድሚያ ለሚሰጣቸው ጉዳዮች ተግባራዊነት የሚያስፈልግ የገንዘብ ድጋፍ ለማድረግ ፍላጎት ያላቸውን ለጋሽ ተቋማት ለማነሳሳትና ቁርጠኝነታቸውን ለማስጠበቅ ሊውል ይችላል፡፡
በሌላ በኩል እነዚህ ውጫዊ ተዋንያን በውይይቱ መደምደሚያ ላይ ያልተፈቱ አከራካሪ ጉዳዮች ሲያጋጥሙ፣ ሁሉም ወገኖች ስምምነት ላይ እንዲደርሱ የአገሪቱን ባለሥልጣናትንና ተወያዮችን ለማገዝ የሚያስችል የቴክኒክ መመርያ በመስጠት ክፍተቱን መሙላት ይችላሉ፡፡ ምንም እንኳ ድጋፉ አዎንታዊ ቢሆንም በተመልካች ዘንድ የሚፈጠር የአድሏዊነት አመለካከትን ለማስወገድ በጥንቃቄ መከናወን አለበት፡፡ ሌላው በብሔራዊ ውይይቱ የተደረሱ ስምምነቶችን አፈጻጸም ለመከታተል የአገር ውስጥ ሲቪል ማኅበረሰቡ ከዓለም አቀፍ ድጋፍም ተጠቃሚ ሊሆን ይችላል፡፡
የክልላዊና የዓለም አቀፍ ተዋናዮች ድጋፍ ወይም ተቃውሞ
በፖለቲካል ኢኮኖሚ ዓውድ ሲታይ ማንኛውም አገር ከሌሎች አገሮች ተነጥሎ የሚገኝ ደሴት አይደለም፡፡ በአንድም ሆነ በሌላ የሌሎች ውጫዊ አካላት የተፅዕኖ ጥላ፣ በአዎንታዊም ሆነ በአሉታዊ ደረጃ እንደሚያርፍበት ይታመናል፡፡ እነዚህ ኃይሎች ደግሞ በአንድ አገር ህልውና ውስጥ ሊያስጠብቁት የሚከጅሉት ጥብቅ ብሔራዊ ፍላጎት ያላቸው ክልላዊ ወይም ዓለም አቀፋዊ ቅርፅ የያዙ ሉዓላዊ አገሮች፣ እንዲያም ሲል የባለብዙ መድረክ ተሳትፎ ያላቸው ተቋማት ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ስለሆነም ይህንን ብሔራዊ ጥቅማቸውን ሳይሸራረፍ ለማስጠበቅ በብሔራዊ ምክክሮች ውስጥ የተለያዩ የውጭ ተዋናዮች በቀጥታም ሆነ በውክልና (By Proxy)፣ በነቢብ ወይ በገቢር ይሳተፋሉ። ከላይ ለመግለጽ እንደሞከርኩት እነዚህ ተዋናዮች ጎረቤት አገሮችን፣ ኃያላን አገሮችን፣ ዓለም አቀፍ የድጋፍ ቡድኖችን ወይም ክልላዊና ዓለም አቀፍ ድርጅቶችን ሊያካትቱ ይችላል፡፡
ክልላዊ ተዋናዮች ብዙውን ጊዜ በቅርብ ባሉ ጎረቤት አገሮች ውስጥ በሚፈጠሩ ቀውሶችና ወሳኝ የፖለቲካ ለውጦች ላይ የሚያስጠብቋቸው ተጨባጭ ጥቅሞችና እጅግ የበለጡ አሳሳቢ ፍላጎቶች ስላሏቸው፣ በብሔራዊ ውይይቶች ለሚገኙ ውጤቶች አዎንታዊም አሉታዊም ተፅዕኖአቸው የበለጠ ወሳኝ ይሆናል። በዚህ የተነሳ በአንድ አገር ብሔራዊ ውይይቶች በሚደረጉበት ወቅት ሒደቱን በቀጥታም ሆነ በእጅ አዙር በመደገፍም ሆነ በመቃወም ረገድ ከፍተኛ የፖለቲካ ጫና ለማሳደር ይዘጋጃሉ። እንዲሁም እነዚህ ወገኖች በግጭቱ ውስጥ ዋነኛ ተዋናይ ከሆኑ አካላት ጋር ቀደም ሲል በነበሩ ግንኙነቶች የተጠቀሙ ወይም ሲጠቀሙ የቆዩ፣ አሊያም ተጠቃሚ መሆን የሚፈልጉ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ በአንፃሩ ደግሞ ዓለም አቀፍ ተዋናዮች ነባራዊ ጥቅማቸውን ለማስጠበቅ ውይይቱን ለመደገፍ ወይም ለመቃወም የሚያስችል ትልቅ ዲፕሎማሲያዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ወታደራዊ ኃይል ሊኖራቸው ይችላል። ስለሆነም ተገቢውን የውይይቱ አዘጋጅ አካል ፖለቲካዊ ትንታኔና የሥጋት ምደባ በመሥራት የፈርጀ ብዙ ውጫዊ ተዋናዮችን ፍላጎት የአገሪቱን ብሔራዊ ጥቅም በማይነካ መንገድ በአንድም ሆነ በሌላ በሚገባው ልክ መረዳትና ጥቅማቸውን ለማካተት መሞከር አለበት።
ለውጫዊ ኃይሎች ተሳትፎ ገፊ የሆኑ ቁልፍ ጉዳዮች
እንደሚታወቀው ከመሠረታዊ ጽንሰ ሐሳባዊ ብያኔያቸውም ሆነ ከተለምዷዊው ገፊ ምክንያቶቻቸው እንደምንረዳው ከሆነ ብሔራዊ ውይይቶች ስንል በአገር አቀፍ ባለድርሻ አካላት የሚቀረፁ፣ በዜጎችና የፖለቲካ ልሒቃን ምሉዕ ባለቤትነት የሚያግዙና የሚመሩ የምክክር፣ የድርድር፣ የውይይትና መግባባት ስብጥር ሒደቶች ናቸው። ሆኖም አገራችን ከሌሎች ዓለማትና ተፅዕኖ ፈጣሪ አካባቢያዊና ዓለም አቀፋዊ ኃይሎች ፍፁም ተለይታ የምትኖር ባለመሆኗ እነዚህ መሰል ውይይቶች እንዲሁ በባዶ ሜዳ ያለ ምንም የቀጥታና የተዘዋዋሪ ጣልቃ ገብነት ሊከናወኑ አይችሉም፡፡ ስለሆነም በአንድም ሆነ በሌላ ለክልላዊና ዓለም አቀፋዊ አካላት፣ ለውጫዊ ነባራዊ ሁኔታዎችና ተዋናዮች ተፅዕኖ በእጅጉ የተጋለጡ መሆናቸው ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡ ይህንን የውጭ ኃይሎች የተፅዕኖ ስበትና ግለት ከሚያባብሱ ጉዳዮች መካከል ደግሞ አገሪቱ አሁን ያለችበት ውስጣዊ የፖለቲካ ሽግግርና የግጭት ሁኔታ፣ የምሥራቅ አፍሪካ የስበት ማዕከል መሆኗ፣ እንዲሁም ያላት የረጅም ጊዜ የአገር ግንባታ ሒደትና ሌሎች ምጣኔ ሀብታዊና ማኅበራዊ ሁኔታዎች ተጠቃሽ ናቸው፡፡
በመርህ ደረጃ ብሔራዊ ውይይቶችን የሚመሩ አገር አቀፍ ባለድርሻ አካላት የውጭ ተዋናዮች ሚና ላይ በምሉዕ የሚወስኑ ሲሆን፣ ተሳትፎአቸውንም የሚወስኑት ሒደቱን አዎንታዊ በሆነ መንገድ የሚደግፍ መሆኑን በማረጋገጥ ብቻ ነው። ሆኖም የሌሎች አገሮች የእስካሁኑ ልምድ እንደሚያሳየው የውጭ ኃይሎች በብሔራዊ ውይይት ሒደት ውስጥ የሚኖራቸው ተሳትፎ በአግባቡና በጥንቃቄ ካልተቀናጀ ወይም በዋናነት በመርህና በጥብቅ አሠራር ሥርዓት ሳይሆን በግል ተለዋዋጭ ፍላጎት የሚመራ ከሆነ፣ የሒደቱን ውጤታማነት እጅጉን ሊያዳክም ይችላል። እንዲሁም ከታለመለት የመግባባት ግቡ በመፋታት ለማያባራ ዘላቂ ግጭት መንስዔ ይሆናል፡፡
ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ደግሞ በዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ውስጥ ያሉ ዋነኛ ተዋናዮች ማለትም የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴሮች፣ ለጋሾች፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት፣ ዓለም አቀፋዊና ክልላዊ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችና ሌሎች አካላት፣ ወዘተ. ዘንድ ብሔራዊ ውይይቶችን የመደገፍ ከፍተኛ ተነሳሽነት የተፈጠረና በማንኛውም መስክ የመሳተፍ ፍላጎታቸውም እያደገ የመጣ ሲሆን፣ ተጨባጭ ድጋፍም እየሰጡ መጥተዋል። ለዚህ የድጋፍ ማዕቀፍ መበራከት አንዱ ተጠቃሽ ምክንያት ብሔራዊ ውይይቶች (ለማካሄድ በጣም በርካታ ሀብትና ጊዜ የሚፈጁ የሆኑት እንኳ ቢሆኑ) ከውጭ ጣልቃ ገብነቶች፣ በተለይም ከወታደራዊ ጣልቃ ገብነቶች ወይም የምጣኔ ሀብት ማዕቀቦች ጋር ሲነፃፀሩ እጅግ ወጪ ቆጣቢ በመሆናቸው ነው፡፡ ይኸውም አገራዊ ውይይቶች የፖለቲካ ሽግግሩንና የመንግሥታዊ ሥርዓት ለውጡን ኃላፊነት በአገራዊ ባለድርሻ አካላት ላይ በማድረግ፣ በዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ላይ የሚኖረውን ጫና ሊቀንስ ይችላል በሚል ዕሳቤ ነው።
እንደሚታወቀው ብሔራዊ ውይይቶች ከአገራዊ ባለድርሻዎች ባለቤትነትና የሉዓላዊነት መርሆዎች ጋር በእጅጉ የተጣጣሙና አብረው መሳ ለመሳ መጓዝ ያለባቸው ቢሆኑም፣ በአንፃሩ በምዕራባውያን ለጋሾች ዘንድ ደግሞ እነርሱ ከሚያራምዷቸው የርዕዮተ ዓለም፣ የፖለቲካል ኢኮኖሚና የዕድገት ፖሊሲ ማዕቀፍ ጋር የተጣጣመ መሆን አለበት የሚል የተንሸዋረረ ብርቱ ሙግት እያቀረቡ ነው፡፡ ለአብነት ያህል እ.ኤ.አ. በ1990ዎቹ አካባቢ የለጋሽ አገሮች የፖሊሲ ትኩረት አቅጣጫ የአገረ መንግሥታትን የገዘፈ የአድራጊነት ሚና ከጊዜ ወደ ጊዜ በእጅጉ በመቀነስ ወደ ፕራይቬታይዜሽን ማዕቀፍ ማሸጋገር፣ በትይዩ ደግሞ የሲቪል ማኅበረሰብ መዋቅሮችን በማስፋፋት ላይ አፅንዖት የሰጠ ነበር። ከ1990ዎቹ አጋማሽ ወዲህ ደግሞ የትኩረት ቀስቱ አቅጣጫ (ወይም ፔንዱለሙ) ወደኋላ እንዲዞር ተደርጓል፡፡ ለዚህ ለውጥ ዋነኛ ምክንያቱ ደግሞ በለጋሾች ዘንድ ሥራቸውን በሚገባ የሚያከናውኑ ጠንካራ መንግሥታዊ ተቋማትን አስፈላጊነት በሚገባ መረዳት ስለጀመሩ ነው። ይህም በመንግሥትና በሲቪል ማኅበረሰብ መካከል የሚፈጠር ትብብራዊ መደጋገፍ እንዲጨምር አድርጓል፡፡ ለዚህም ለስላሳ የሽግግር ሒደት ደግሞ ብሔራዊ ውይይቶች ተስፋ ሰጪ መሣሪያዎች ሆነው ተገኝተዋል።
በአገራዊ ውይይት ሒደት ውስጥ ያሉ የውጭ ተዋናዮች የምንላቸው ኃይሎች፣ ‹‹በምክክሩ ሒደት ውስጥ ቀጥተኛ የሆነ የአድራጊነት ተሳትፎ የሌላቸው፣ እንዲሁም በሒደቱ በሚወጡ ተተግባሪ ውጤቶች ላይ ቀጥተኛ ድርሻ የሌላቸው ተዋናዮች›› ናቸው፡፡ ሆኖም እነዚህ አካላት በሒደቱና በውጤቱ ላይ ቀጥተኛ ድርሻና ተሳትፎ የላቸውም ማለት ግን ምንም ፍላጎት የላቸውም ማለት አይደለም፡፡
እነዚህ ኃይሎች በመሰል ውይይቶች መካከል የሚያበረክቷቸው በጎም ክፉም ምልከታና አስተዋጽኦ የሚኖራቸው ቢሆንም፣ ይህ ጽሑፍ በዋነኛነት የውጭ ተዋናዮች የሚያበረክቱትን አዎንታዊ አስተዋጽኦ ለመዳሰስ የሚሞክር ነው፡፡ የውይይቱ አዘጋጅ አካላት ጎጂ ጎናቸውን በሚገባ በመረዳት ጠቀሜታቸውን ደግሞ በማጉላት እንደ ሁኔታው እንዲጠቀሙባቸው አበክሬ ለማሳሰብ ነው፡፡ ሆኖም የውጫዊ ተዋናዮች ተፅዕኖ በዘላቂነት መልካም ነው ብሎ ማሰብም አስፈላጊ አይደለም። ይኸውም በአንዳንድ ጎኖች የውይይቱን አጀንዳና የመግባባት መንፈስ ከዓውዱ ለጥጦ በማስወጣት የጉዳዩን ቋጠሮ የበለጠ ሊያወሳስቡ ይችላሉ፡፡ ለምሳሌ አንዱን ፓርቲ/የጎሳ ቡድን ወይም መደብ ከሌላው በላይ በመደገፍ ወይም በብሔራዊ ውይይቱ ውጤት ላይ ተፅዕኖ ለማሳደር በመፈለግ ጥቅማቸው ተጠብቆ እንዲቆይ ማድረግ ናቸው።
በብሔራዊ ውይይቶች ላይ ተፅዕኖ የሚያሳድሩ የውጭ ተዋናዮች እነ ማን ናቸው? ለሚለው ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት ያክል ይህ ጽሑፍ ተዋናዮችን በሁለት መደብ በፖለቲካዊና በልማት ደጋፊ የውጭ ኃይሎች ይከፍላቸዋል፡፡ በዚህ አግባብ በመለየትም የበርካታ ተዋናዮችን ስብጥር ይመለከታል። የፖለቲካ ተዋንያን የምንላቸው ዓለም አቀፋዊና ክልላዊ ባለ ብዙ ወገን ድርጅቶችን፣ የጎረቤትና የሩቅ አገረ መንግሥታትና ርዕዮተ ዓለማዊ ድጋፍ ያላቸው መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችን፣ ወዘተ. በስፋት ያጠቃልላሉ። በተጨማሪም የሃይማኖት መሪዎች፣ የአካዳሚክ ተቋማት፣ የዳያስፖራ ቡድኖች፣ የንግዱ ዘርፍና ተፅዕኖ ፈጣሪ ግለሰቦችን ያቀፉ ናቸው።
እነዚህ የፖለቲካ ተዋናዮች አብዛኛውን ጊዜ ብቻቸውን በተናጠል ሲሳተፉ፣ በሌላ ጊዜ ደግሞ እንደ የአጋር ቡድኖች ስብስብ ወይም የዕውቂያ ቡድኖች ያሉ ብሔራዊ ውይይትን ለመደገፍ የተፈጠሩ ጥምረቶች አካል ሊሆኑ ይችላሉ። ሌላው የውጫዊ ደጋፊ አካላት ምድብ የልማት ተዋናዮችና ደጋፊዎች ናቸው፡፡ እነዚህ ቡድኖች ለብሔራዊ ውይይት የሚያበረክቱት አስተዋጽኦ በበቂ መጠን ዕውቅና ያልተሰጠውና ብዙውን ጊዜም በይፋ ተቀባይነት የሌለው ብሎም ሌሎች አካላት በሚገባው ልክ ያልተረዱት ነው፡፡ እነዚህ የልማት ደጋፊዎች የሚባሉት አካላት በዋናነት እንደ አይኤምኤፍና የዓለም ባንክ ያሉ የፋይናንስ ተቋማት ሲሆኑ፣ በተጨማሪም የብሔራዊ ልማት ፈንዶችና የረድኤት ኤጀንሲዎች፣ እንዲሁም መንግሥታዊ ያልሆኑ የልማት ድርጅቶች ይገኙባቸዋል። ብዙውን ጊዜ የልማት ተዋናዮች የምንላቸው ኃይሎች በተለምዶ የተዳከመ አገረ መንግሥት በሚባለውና ግጭት ደጋግሞ በሚከሰትበት አገራዊ ዓውድ ውስጥ የድጋፍና ልማት ተግባራቸውን ለማከናወን ሲቸገሩ ይታያሉ፡፡
በዚህ ልክ እየተቸገሩም ቢሆን የልማት ሥራቸውን የሚያከናውኑባቸውን አገሮች የፖለቲካዊ ባህሪ በአግባቡ ለመገንዘብ ሲያቅማሙ ቆይተዋል፡፡ ሆኖም በግጭቶች ከዕለት ወደ ዕለት መባባስ ከእንቅስቃሴ መገደብ፣ ቀውስ በገነቧቸው የልማት ተቋማት ላይ የሚያደርሰው ይህ ቀረሽ የማይባል ውድመትና የፖለቲካዊ ምኅዳር መቀንጨር በልማት ሥራ ላይ የሚያሳድረው ቀጥተኛና ጉልህ ተፅዕኖ ብሔራዊ ውይይትን ጨምሮ ለሌሎች ፖለቲካዊ የመፍትሔ ሒደቶች መተግበር ያላቸውን ፍላጎት በአትኩሮት እንዲያሳዩ አድርጓቸዋል። በተጨማሪም ይህ መሰሉ አዙሪታዊ ሁነት በግጭት ቅድመ መከላከል ላይ አፅንኦት ሰጥተው እንዲሠሩ አድርጓቸዋል፡፡ በዚህም እ.ኤ.አ. በ2015 በተካሄደው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰላም ግንባታ ንድፈ ሐሳብ መዋቅር ግምገማ ላይ፣ የልማት ተዋናዮች በሰላም ግንባታና ግጭትን በመከላከል ረገድ ያላቸው ሚና ተቀባይነት አግኝቷል። በአጭር አነጋገር የልማት ተዋናዮች የሚያደርጓቸው የሰላም ሒደቶች ድጋፍ የበለጠ ጉልህና የተቀናጀ እየሆነ መጥቷል። (ክፍል ሁለት ሳምንት ይቀጥላል)
ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል [email protected] አድራሻቸው ማግኘት ይቻላል፡፡