Friday, June 9, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ተሟገትለአገራዊ መግባባት ለሰላምና ዕርቅ አንዳንድ ነገሮች

ለአገራዊ መግባባት ለሰላምና ዕርቅ አንዳንድ ነገሮች

ቀን:

በበቀለ ሹሜ

ተቦጫጭቆ፣ ተከፍፋሎና ዕጣዬ በራሴ ብሎ ለየብቻ መሮጥ የአቅመ ቢስነት፣ የድህነትና የአምባገነንነት መጫወቻ እንደሚያደርግ በዓለማችንም በአኅጉራችንም ውስጥ ሲበዛ ታይቷል፡፡ ከኢትዮጵያ ማዕቀፍ በመውጣትም ልምድ ታይቷል፡፡ ዛሬ በኢትዮጵያ ውስጥ ያለን ማኅበረሰቦች ዕጣችን ከእርስ በርሳችን ጋር ብቻ ሳይሆን፣ ከጎረቤቶቻችን ጋር ሁሉ የተሳሰረና አንድ ላይ ተያይዞ መጓዝን የሚጠይቀን መሆኑን፣ ታሪክ በመራራ ልምድ ከማስተማር አልፎ በቀጣናዊና በአኅጉራዊ የመሰባሰብ መርከብ ውስጥ አሳፍሮ እየቀዘፈን ይገኛል፡፡

ይህ የመሰባሰብ ቀዘፋ የአፍሪካ አገሮች የቅኝ ከፋፋይነትን ነቃቅለው ወደ ሙዚየም የሚያስገቡበት ጉዞ ነው፡፡ ጉዞው በተለይ ለአፍሪካ ቀንድ አገሮች ትርጉሙ ልዩ ነው፡፡ ቅኝ ገዥዎች በቅርጫቸው የአንድ አገር ልጆችንና ወጥ ማኅበረሰቦችን ከፋፍለዋል፡፡ አንዱን ሕዝብ በጎረቤቱና በገዛ ወገኑ ላይ እንዲዘምት አድርገዋል፡፡ ቅኝ ስያዝ አልደረስክልኝም/ለቅኝ ገዥ በውል አሳልፈህ ሰጠኸኝ የሚል ቅያሜ ተክለዋል፡፡ ቅኝ ገዥዎች ከፍፋለው እንደገዙ ሁሉ ሲወጡም ከፋፋይ ተንኮል ከመቅበር አልተገቱም፡፡ ሶማሊያን ከጎረቤት ጋር ሲያላትም የኖረው የታላቂቱ ሶማሊያ ግንባታ ከቅኝ ገዥዎች እንደተመዘዘ ሁሉ፣ ሶማሊያ ስትንኮታኮት የገባችውም እዚያው የቅኝ ገዥዎች ፈጥረውት የነበረ ብጥስጣሽነት ውስጥ ነበር፡፡ ብጥስጣሽነትና ሌሎች ቀውሶች የተዛመዱበት የሶማሊያ መከራ ለጎረቤቶቿ እንደተረፈ ሁሉ፣ የጎረቤቶቿም ጣጣ ለሶማሊያ ተርፏል፡፡ የውስጥና የደጅ ሰበዞች ፈትል የሠሩበት መታመስ እስካሁንም አልደረቀም፡፡

      በኢትዮጵያ ላይ የተካሄደውና ረዥም ታሪክ ያለው የውጭ ተስፋፊዎች ከበባ ከቱርክና ከግብፅ ወደ ጣሊያን፣ ፈረንሣይና እንግሊዝ ቅንብር የተሸጋገረ ነበር፡፡ በተለይ ጣሊያን በሰሜን እግሯን ካስገባችበት ጊዜ አንስቶ፣ በመሣሪያና በሥልጣን ጥቅም የኢትዮጵያ ገዥዎችን ከፋፍሎ ሸፍጠኛ ውል በማሰርና በተገኘው ቀዳዳ በኃይል ተንፏቆ የተወሰነ ክፍልን ከመያዝ በላይ፣ መላ አገሪቱን ለመሰልቀጥ ታካሂድ የነበረው ዲፕሎማሲያዊና የግጭት ልፊያ አታካች ነበር፡፡ ሰበባ ሰበቡ አልቆ በተካሄደው የመጀመርያው ታላቁ የዓድዋ ጦርነት ነጭ ቅኝ ገዥን ጥቁር ያንበረከከበት ድል ዓለምን ዕፁብ ያሰኘ ቢሆንም፣ ከኢትዮጵያ ምድር ቅኝ ገዥነትን በማባረር ረገድ ግን ድሉ ግማሽ ድል ከመሆን አልዘለለም ነበር፡፡ በሁለተኛው የጣሊያን ወራራ ላይ የኢትዮ-ኤርትራ አርበኞች ጥቁር ከነጭ ባሳተፈ ዓለም አቀፋዊ ተቆርቋሪነት ታጅበው ከአምስት ዓመታት ተጋድሎ በኋላ የተቀዳጁት ድል በጣሊያን ቅኝ ገዥነት ላይ ሙሉ ድልን የተቀዳጀ ቢሆንም፣ በተጋድሎው አናት የገባችው እንግሊዝና ቢጤዎቿ የኢትዮ-ኤርትራን ዕጣ ለራሳቸው ለባለቤቶቹ አልተውላቸውም፡፡ መሰሪነቱ ተብሎ፣ ተብሎ በመጨረሻ ኢትዮጵያና ኤርትራ በፌዴሬሽን ከተዋሀዱ በኋላ፣ ውሎ አድሮ ደግሞ ንጉሡና ሙሉ አንድነት ፈላጊዎች ፌዴሬሽኑን በማፍረስ የሠሩት ጥፋት ያንን የቅኝ ድንበር መሸሻ ወዳደረገ የነፃነት ትግል ወስዶ፣ ደምና ጥሪት እየበላ 30 ዓመታት አማቀቀ፡፡ ጦርነቱ በድል ተጠናቆ የተገኘው ‹‹ነፃነት›› ያንኑ የቅኝ ገዥዎች የአፈና ይዞታ ከማፅደቅ ያላመለጠና የሁለቱን ሕዝቦች የማይነጣጠል ህልውና ሕግና ሥርዓት በያዘ መተሳሰብ ያልተንከባከበ ነበርና ጦርነት ውስጥ ለመግባት ጊዜ አልወሰደባቸውም፡፡ አሁን የፈካው በቀጣና ደረጃ የመሰባሰብ ዕይታ ይህን ሁሉ የሚቀይር፣ በክፍለ አኅጉራችን ያለውን የቅኝ ግዛት ካቴና የሚያራግፍና የተቆራረጡ ሕዝቦችን የሚያሰባስብ ጉዞ ነው፡፡ ዕይታችን ይህንን መንገድ መልቀቅ የለበትም፡፡

ይህን የታሪክ ጉዞ በዕንቢ ለብቻዬ መቃረን እሳት አማረኝ የማለት ያህል ወፈፌነት ነው፡፡ ዕጣችን የተሳሰረ መሆኑን ከተቀበልን፣ የፖለቲካ ፍላጎቶቻችንን ማቻቻልና ቁርሻ ቁርሾዎችን በዕርቀ ሰላም ማጠብ ከመተላለቅ የማምለጥ ግዳጃችን ነው፡፡ በደቡብ አፍሪካና በትናንቷ ሮዴሺያ የጥቂት ነጮች ግፈኛ ገዥነት ጥቁሮችን ከሀብታቸው ገፍፎ ሲዖል ሲያስቆጥራቸው መኖሩ የቅርብ ልምድ ነው፡፡ ዛሬ የሥርዓቱ የአድልኦ ቅርስ በአግባቡ ታጥቦ በፍትሐዊነት የመሞላቱ ሒደት በጣም ገና ቢሆንም፣ ሁለቱም እንደምንም ተቻችለው እየኖሩ ነው፡፡ በሩዋንዳም በነጭ መሰሪነት የአንድ አገር ልጆች በእርስ በርስ ፍጀት ውስጥ አልፈው፣ ይኼው ዛሬ ከፋም ለማም አንድ ላይ አገር እየገነቡ ነው፡፡

ከ20ኛውና ከ21ኛው ክፍለ ዘመን የፍትሕ እሴቶች ማዕዘን አኳያ ቆመን ልንፈርደው የምንችለው የደቡብ አፍሪካ ዓይነት ዘርና ቀለም (ሬስ) ላይ የተመሠረተ ግፍም ሆነ፣ የሩዋንዳ ዓይነቱ ፍጅት በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ የለም፡፡ የእኛ የአሁን ዕርቀ ሰላም ዋና ዒላማም በግፍ ሥርዓት ላይ ትኩስ ድል ከተቀዳጁ በኋላ፣ ገና ትኩስ የሆነ የግፍ ቁስል ለማከምና ለማጠገግ የሚደረግ አይደለም፡፡ የእኛ ‹‹ድል›› ገና ጅምር ነው፡፡ በአሁኑ ደረጃ ብሔረሰብ በብሔረሰብ ላይ ጥቃት ተፈጸመብኝ ብሎ ለበቀል እንዲነሳ አናዳጅ ጭካኔና ተንኮል በመሥራትም ሆነ ሃይማኖት ተደፈረ የሚያሰኝ ሻጥር በመፍጠር ክርስቲያን በሙስሊም ላይ፣ ሙስሊም በክርስቲያን ላይ የሚዘምትበት፣ አጠቃላይ መተላለቅ ውስጥ እንድንዘፈቅ፣ ከዚህ ትርፍ የሚገኝ የሚመስላቸው ኃይሎች በስውር እያዋከቡን ነው፡፡ እነዚህ ኃይሎች ማንም ሆኑ ማን እነሱ በሚያጠምዱልን ወጥመዶች ውስጥ እንዳንጠመድ ምሁራን ፖለቲከኞች ሁሉ አንድ ላይ ገጥመን በሁነኛ የህልውና ጉዳዮቻችን ላይ አንድ ልብ በመሆን፣ ሕዝቦች ለሸሮች የማይበገር ኅብረት በዕርቀ ሰላም እንዲይዙ፣ የመንግሥትም ሕግን የማስከበርና የሕዝብ ደኅንነትን የመጠበቅ አቅም እንዲጠነክር ማገዝ የሞት ሸረት ሥራችን ነው፡፡ በዚህ ላይ መዘናጋታችን መቆም አለበት፡፡

ታሪክ ያለፉ ክንዋኔዎችንና በታሪክ ውስጥ የታዩ ግለሰብ ተዋንያንን በነበሩበት ዘመን ፍልስፍናና ሥነ ልቦና ውስጥ ገብተን ድክመትና ጥንካሬያቸውን እንድንመዝን ይጠይቀናል፡፡ ይህ ዛሬ አብሮ ለመኖር የምንከፍለው ዋጋ ሳይሆን፣ ወደ እውነት ወደ ሳይንሳዊነት የተጠጋና ለዛሬ ተግባራችን የሚበጅ የታሪክ ዕውቀት ለማግኘት ማድረግ ያለብን ጥቂቱ ነገር ነው፡፡ ሚዛናዊና ፍትሐዊ ውጤት ላይ ለመድረስ ብዙ የተለፋበት የጋራ የታሪክ ፈትል ማበጃጀታችንም የማይቀር ነው፡፡ ለዚህ ዋስትናችን ታሪካችን ከማኅበረሰቦች እስከ መደቦች ድረስ፣ መወራረስና መውጣት መውረድ የሞላበት መሆኑ ነው፡፡

በታሪክ መግባባት ችግር ሆኖ የቆየውና ፊትም እስካሁንም ገዥዎች ራሳቸውን ገድል በገድል እየሞሉና ከመለኮት ጋር ለመዛመድ ሰማይ ድረስ ያወጡትን ገድል ታሪክ እያሉ ህሊና የመግዣ ማገዶ ስላደረጉት፣ ፖለቲከኞች ደግሞ የተበለሻሸ ተጨባጭ እውነታን በምኞት ለማቆንጀት ‹‹ታሪክ››ን ስለተጠቀሙበት፣ ወይም በምኞት የተሞላ ፖለቲካን ‹‹ታሪካዊ›› ካስማ ለመስጠት ስለነገዱበት ነው፡፡ ይህ ሁሉ ሆኖም ፖለቲካ ጠለቀን፣ የሕዝባችን ጥቅም ታወቀን ባዮች በጊዜያት ውስጥ፣ ታሪክን ለውዳሴም ሆነ ደምን ለማምረር መጠቀም፣ ለሕዝብ የሚበጅ ፍሬ እንዳላስገኘ የተረዱበት ደረጃ ላይ ደርሰዋል፡፡ ተባብሮ ኢትዮጵያን ለሁሉም የምትደላ ዴሞክራሲያዊት ፌዴራላዊ አገር አድርጎ የመገንባት ዕድል (ከለውጡና ሽግግሩ መምጣት ጋር) ብቅ ሲል፣ ዕድሊቱ ወደ ጉምነት እንዳትለወጥ ከሞላ ጎደል ወደ መረባረብ፣ እናም ከመማረር ወደ መቀራረብ መምጣትና በታሪክ ግንዛቤ ረገድም የጋራ መገናኛ ለመፍጠር መጣጣር መጀመር አለብን፡፡

የዛሬ እውነታ ሁለት ተግባራትን ደቅኗል፡፡ አንደኛ ፖለቲካን የዱሮ ታሪክ መተሳሰቢያ ወይም በዱሮ ሮሮ ላይ ሙሾ ማውረጃ ከማድረግ ወጥቶ የዛሬን ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮቻችንን መፍቻ ወደ ማድረግ መዞር፣ ሁለተኛ ታሪክን የውዳሴና የኩነና ማርኪያ ከማድረግ ወጥቶ ከእስከ ዛሬው ሙከራ እጅጉን የተዋጡ የታሪክ ሐተታዎችን ከሙያው ሰዎች ወደ መጠየቅ መዞር፣ የተማሩ የታሪክ ግንዛቤዎቻችን ከፖለቲከኞቻችን መማረር ጋር የተሳሰረ አመጣጥ እንዳላቸው ሁሉ፣ የፖለቲከኞች ወደ መለሳለስ መምጣት ለሁለቱ ተግባራት ዕውን መሆን ያመቻል፡፡ ለስላሳ ሁኔታ ከለማ፣ ፖለቲከኞች የዛሬን ታሪክ በመሥራት (የዛሬን ሕይወት በማልማት) ላይ ያተኩራሉ፡፡ የታሪክ ጥናትና ትርጓሜም ከፖለቲከኞች አቡኪነት እየራቀ ወደ ማኅበራዊ ሳይንስ ሠፈር ይገባል፡፡

በአጭሩ ልሂቃን የሚባሉት ወገኖች መቀራረባቸው በእነሱ ተፈትሎና ከርሮ ወደ ሕዝቦች ውስጥ የገባ መሻከርንም የሚያቀል ነው፡፡ በሐሳብ መለያየት መጠማመጃና መጣያ መሆኑ በትምህርት ቀመሶቹ መሀል ከመከነ፣ አገርን በአያሌው የሚያስማማ የታሪክ ልቃቂት ኢትዮጵያ እንደሚኖራት አያጠራጥርም፡፡ ይህ ማለት ግን ድፍን መስማማት ይኖራል ማለት አይደለም፡፡ በተለይ ደግሞ በነገሥታት አቀባበልና ግንዛቤ ላይ ስምምነት ይፈጠራል ብሎ መጠበቅ የዋህነት ነው፡፡ አንደኛ ለዘመናት በደግና በክፉ ተጋንኖ ሰማይ ጥግ የደረሰ የነገሥታትን የውዳሴና የኩነና ስንክሳር፣ በተለያየ ምክንያት የፖለቲካ ትርፍ አገኛለሁ ብሎም ሆነ ማኅተብ የመበጠስ ያህል አልሆንልህ ብሎት የማይለቅ ሰው ይኖራል፡፡ ሁለተኛ ግለሰብ ነገሥታቶቹ/ገዥዎቹ ክፉም ደግም የተግባር ገጽ ያላቸው እንደ መሆኑ፣ አወዛጋቢነታቸው በቶሎ ላይቋረጥ ይችላል፡፡ ቀደምት ታሪክን በተፈጸመበት ዘመን መረዳት ቢቻል እንኳ፣ ሐተታ ታሪኩ የዛሬ ተቀባይ ላይ የሚፈጥረው ስሜት በሁሉም ሰው ላይ አንድ ዓይነት አይሆንም፡፡ በኢትዮጵያ የገዥነት ታሪክ ውስጥ በታየ ‹‹ሰለሞናዊ›› አፄነትና መሳፍንትነት ውስጥ ከልዩ ልዩ ማኅበረሰብ የበቀሉ ሰዎች የገቡበት ሁኔታ ቢኖርም፣ የኢትዮጵያ አፄያዊ አስገባሪነት ማለቂያ ባልነበረው ዘመቻ ሁሉንም አሳረኛ ያደረገ ቢሆንም በዘመቻ፣ በቃጠሎ፣ በባርነት መነዳት፣ የአካል ቆረጣ ቅጣት የሰሜኑንም የደቡቡንም ሕዝብ የላሰ ቢሆንም፣ ዘመቻ ወደ ደቡብ ሲስፋፋ የምኒልክን ጦር ውጊያ የገጠሙ ማኅበረሰቦችና የአካባቢ መንግሥታት የደረሰባቸው (ለሌላውም በሩቁ መቅጣጫ/ማስፈራሪያ የሆነ) ጭካኔ፣ ከዚህም ጋር ተያይዞ የደራው አስደንጋጭ የመሬት ገፈፋና የጭሰኛነት ግንኙነት፣ በኢትዮጵያ ሌላ ክፍል ወደር ያልነበረው ግፍ ነበር፡፡ የምኒልክ ጦር ማኅበረሰባዊ ጥንቅር ምንም ሆነ ምን፣ ይህ የትናንት ግፍ የዛሬን የበስተ ደቡብ ሰው ስሜት አያጉላላም ብሎ ማሰብና መጠበቅ የማይመስል ነው፡፡

እናም ምኒልክን ጀግናዬ ብሎ የሚያወድስ ኦሮምም ሆነ ወላይታ ወይም የከፋና የሐረሪ ሰው ባይበረክት የሚደንቅ አይሆንም፡፡ የዓድዋ ድልን ማድነቅና መኩራት የግድ ምኒልክን ከማወደስ ጋር የተጣበቀ እንዳለመሆኑም ውዳሴ ምኒልክ በመቀነሱ የታሪክ መግባባታችን ላይ ስብራት አይደርስም፡፡ እናም ታሪክ ማለት ነገሥታትን መቁጠር የሚመስላቸውና ግለሰብ አፄዎች ሲነቀፉ የኢትዮጵያ ታሪክ የታረደ እየመሰላቸው የሚንዘረዘሩ ገትጋቶች ዓይናቸውን ቢገልጡ ደግ ነው፡፡ የዓድዋ ተጋድሎ የብዙ ብዙ ጀግኖችና ሕዝቦች የተጋድሎ ሥራ ነው፡፡ ውዳሴ በታሪክ ውስጥ አንድ ሰው ለሠራው ሥራ አክብሮትና ዋጋ ከመስጠት ያልፋልና አወዳሽ አለመሆን ግዴታ ለታሪክ ዋጋ አለመስጠት አይደለም፡፡ ወደፊት እንዲያውም ጭፍን አወዳሽነት እየቀነሰ በታሪክ ሒደት ውስጥ ብዙ የተለቀለቀላቸውን ሰዎችን በጎ ሚና ከእነ ህፀፃቸው በዘመን ውስንነታቸው ውስጥ የሚገነዘቡና የሚበረክቱ መሆናቸው አያጠራጥርም፡፡ የዚህ ጅምርም ዛሬ ኮናኝነትና አወዳሽነት በደራበት ጊዜ ውስጥ እንኳ አለ፡፡

 በተረፈ ረዥሙ የታሪክ ጉዟችን በሚከተሉት አንኳሮች ቢቀመጥ የሚያስማማ ትረካ ላይ ለመድረስ የሚያንደረድረን ይመስለኛል፡፡

ሀ) አገረ ኢትዮጵያ በጎራዴና በጦር ብቻ ሳይሆን የተለያዩ ሕዝቦች ከቦታ ቦታ እየተንቀሳቀሱ በፈጠሩት ማኅበረሰባዊ፣ ባህላዊና ቋንቋዊ መዘማመድ የተገነባች ነች፡፡ በዚህ የግንባታ ታሪክ ውስጥ የሁላችንም ጀግንነትና ወኔ፣ አጥንትና ደም፣ ስቃይና ዕንባ፣ ጉልበትና ላብ እንደ አነባበሮ ተነባብሯል፡፡ ይህ የታሪክ አነባበሮ ቢተረተር ብዙ ቅፅ ሊወጣው ይችላል፡፡

በየትኛውም ለዴሞክራሲና ለእኩልነት ባልደረሰ ኅብረተሰብ እንደሚሆነው፣ የኢትዮጵያ አገረ መንግሥት ግንባታ በጠበበ ማኅበራዊና አካባቢያዊ ግቢ ውስጥ ከተወዛወዘ ጠቅላይ ገዥነት ጋር በአያሌው መቆራኘቱ አልቀረም፡፡ ዋና ገዥዎቹ የበቀሉበት ባህል ሃይማኖትና የመግዣ ቋንቋቸው የኢትዮጵያ መታወቂያም ሊሆን ችሏል፡፡ እናም በኦርቶዶክስ ተዋህዶ ክርስትናና ባህል ሥር ሌሎች እምነቶችና ባህሎች ማደር አይቀሬ ዕጣቸው ነበር፡፡ አማርኛም ብቸኛ የአንድነት መቅረጫ፣ ብቸኛ መደበኛ መግባቢያ (መማሪያ፣ መተዳደሪያ፣ መዳኛ) ሆኖ ነግሦ ነበር፡፡

ይህ እውነታ ባስከተለው ሥነ ልቦናዊ ቀንበር አማርኛ አለመቻልንና አማርኛን በሌላ አፍ ቅላፄ መናገርን ካለመሠልጠን የሚያስቆጥርና ለማሾፊያነት የሚዳርግ አድርጎት ነበር፡፡ እናም ከዚህ ለማምለጥ የአፍ መፍቻ ቅላፄን ለማራገፍ መልፋት፣ አማርኛን በቅጡ የማያውቅ ዘመድን ማሾፊያ እንዳትሆን አትንተባተብ ብሎ መጫን፣ የእናት ቋንቋን በማይጠቁም ጥራት አማርኛን ለመናገር መቻልን እንደ ነፃነትና ኩራት መቁጠር፣ ከአማርኛ ውጪ የሆነ አፍ መፍቻን መደበቅ፣ ‹‹ተናቂ›› የአፍ መፍቻ ቋንቋን የሚጠቁም መጠሪያ ለልጅ አለማውጣት/ከወጣ በኋላም መቀየር የሚካሄድበት ዘመን ውስጥ ተኑሯል፡፡ እነዚህ ሁሉ የጭቆና ግንኙነት ተራ መልኮች ነበሩ፡፡

ያም ሆነ ይህ በጭቆና ኑሮ ውስጥ ጭቆናና ዕንቢ ባይነት በተለያየ መልክ ሲወራጭና ሲገለጽ ቆይቶ፣ በኢትዮጵያ ተማሪዎች እንቅስቃሴ ፈክቶ፣ በ1966 ዓ.ም. አብዮትና ከዚያ በኋላ በመጣ የአመለካከት ለውጥ በብሔረሰብ ማንነትና በአፍ መፍቻ ቋንቋ መሸማቀቅና ማሸማቀቅ ትልቅ መሰልሰል ደርሶበታል፡፡ በተለይ ከ1983 ዓ.ም. ወደዚህ በመጣ የአመለካከት ለውጥ በብሔረሰብ ማንነትና በቋንቋ የመኩራት ንቃተ ህሊና፣ ማንም ላንኳስ ባይ የማይዳፈረው ደረጃ ላይ ደርሷል፡፡

በዚህ ደረጃ ላይ በአነጋገር ቅላፄ ለመቀለድ መሞከር አናዳጅና የፀብ መነሳሻ ሊሆን ይችላል፡፡ ምክንያቱም በአሁኑ ሰዓት የቀላጁ መነሻ ንቀት ይሁን አይሁን መለየት ስለሚከብድ ነው፡፡ የንቀት ስሜት እየተመናመነ መከባበር እየዳበረ፣ ከጊዜ በኋላ ሌላ ቋንቋ ሲለመድ አፍ የፈቱበት ቋንቋ ፀባያት አንደበት ላይ ተፅዕኖ ማሳደራቸው ተፈጥሯዊ (ምንም የሚያስንቅ ነገር የሌለው) መሆኑ ሰፊ ግንዛቤ እያገኘ ሲሄድ በቅላፄ የመቀለድ አናዳጅነትም ይከስማል፡፡ ዛሬ ፈረንጅ አማርኛ ለመናገር ሲሞክር የሚፈጥራቸውን ስህተቶች በመድረክ ቀልድ መከወንን ፈረንጅነትን ከመናቅ/ከመዝለፍ ጋር እንደማናገናኘው ሁሉ በጋሞ፣ በኦሮሞ፣ ወዘተ ቅላፄዎች የአማርኛ ንግግርን ስንከውን ክወናችንን ብሔረሰቦችን ከማሽሟጠጥ ጋር የማናገናኝበት ጊዜም ይመጣል ማለታችን ነው፡፡

ለ) የኢትዮጵያ የለውጥ ትግል በብሔረሰባዊ ንቃትና በኢኮኖሚ ልማት ፈርጅ ከቀድሞ ዘመን ጋር ሲነፃፀር ብዙ ርቀት የሄደ ቢሆንም፣ ዛሬም ዴሞክራሲ ለመገንባት ከመንደፋደፍ ገና አላለፈም፡፡ የዴሞክራሲ ግንባታ ጥረቱን ሊያጨናግፉ የሚችሉ የማንከስ ችግሮች ዛሬም አሉበት፡፡ ችግሮቹ መልካቸው ይለያይ እንጂ አንጀታቸው አንድ ነው፡፡ ከፖለቲካ ልምድና ከጥፋቶች አለመማር፡፡ ከተማሪ ትግል የተወለዱት የድህረ 1966 ዓ.ም. ፖለቲካ ድርጅቶች በተለይ ኅብረ ብሔራዊዎቹ፣ ተመሳሳይ ርዕዮት አለን እያሉና ሁሉም እንሻላለን በሚሉት ዓላማ ሳይራራቁ ተባብሮ በመታገል ፈንታ ተጠማምደው፣ በ‹‹ነጭ›› እና በ‹‹ቀይ ሽብር›› ተበላልተው (ከመበላላት ጥፋታቸው ቶሎ ለመታረም ሳይችሉ) ለወታደራዊ አምባገነንነት ሥልጣን መራዘም እራት ሆነው አለፉ፡፡ ከእነሱ በኋላ የትግል ሜዳውን የተቆጣጠሩት ብሔርተኛ ቡድኖችም ባልንጀሮቻቸውን ካጠፋውና የለውጥ ትግሉን ከጎዳው የመከፋፈል ጥፋት አልተማሩም፡፡ በየብሔር በተነጣጠለ ትግል ውስጥ ተሰማርተው፣ በፖለቲካ ክስርስሩ ከወጣ የቆየው ደርግ በአንድነት ስም እያምታታ ዕድሜውን እንዲያረዝም ዕድል ሰጡት፡፡ በተነጣጠለ ብሔርተኛ ትግላቸው ምክንያት እንወክልሃልን የሚሏቸውን ማኅበረሰቦች በጠባብነት ወይም በገንጣይ/አስገንጣይነት ጥርጣሬ፣ እያሳደደ አስሮ እያሰቃየና እየገደለ እንዲያበራይ የፖለቲካ ፈቃድ ሰጡት፡፡ ነጣጥሎ አስጠቂ ፖለቲካቸው የማሸነፍ (መላ ሕዝብን የማነቃነቅ) አቅም አዳብሮ ሳይሆን፣ ወታደራዊው አምባገነንነት ደኅንነቱ፣ ወታደሩና ፓርቲው ከላይ እስከ ታች እስኪ ከዳውና እስኪለግምበት ድረስ የፖለቲካ መካን ሆኖ ራሱን በራሱ ሲጥልም ከችግሮቻቸው አልተማሩም፡፡

በ1960ዎቹ የተማሪነት ትግላቸው ጊዜ ጀምሮ በአንድ ብሔረሰብ ሞኖፖሊ የተዋጠ ይሉት የነበረውን አገረ መንግሥት፣ ከሞኖፖሊ ይዞታነት ከማውጣትና የኢትዮጵያን መላ ሕዝቦች የሚወክል እንዲሆን ከማድረግ ተግባር ጋር የእግረ መንገድ ያህል እንኳ አልተገናኙም፡፡ ይህ ይቅርና አንድ ላይ ተስማምተው እንኳ ከሥልጣን የሚገኝ ኬክ ገማጮች ሊሆኑ አልቻሉም፡፡ የተደረገው ለውጥ የብሔረሰቦችን መብቶች በማረጋገጥ ሽፋን የኢትዮጵያ ብሔረ ብዙ ኅብረተሰብን የማሞኘት ብልጣ ብልጥነት ነበር፡፡

አወቅን ባዮች የናኙት ጽንሰ ሐሳብና ‹‹ትንታኔ›› ተራ ሕዝብ ህሊና ውስጥ ሲደርስ መሰነጣጠርና መንሻፈፍ ደርሶበት ያልተፈለገ አሉታዊ ትርጓሜ ሊይዝ እንደሚችል ያስተዋለ ጥንቃቄ አልተደረገም፣ ወይም ጥንቃቄ ማድረግ አልተፈለገም፡፡ ነባሮቹ ቅድመ 1983 ዓ.ም. አገዛዞች በአማራነት ላይ አሉታዊ ስሜት እንዲፈጠር ጠንቅ መሆናቸው ሳያንስ፣ ‹‹አማራ ነፍጠኞች … ፣ የአማራ ገዥዎች …፣ የአማራ ትምክህት ›› … ባይነት ዕለት በዕለት እየተራገበ ደም ፍላቱና የበቀል ጥቃቱ በጥይትና በዱላ እስከ ማፈናቀል ድረስ ጦፈ፡፡ በዚህ አየር ውስጥም፣ ዋናው ታጋይም ባለድልም እኔ ነኝ ባዩ ሕወሓት ለተቀናቃኞቹ ሎሌነት የማደር ወይም ጠላት የመሆን ብቻ አማራጭ ሰጥቶ፣ ጭፍራ ብሔርተኛ ቡድኖችን የግንባር/ የአጋርና የፌዴራላዊነት ልብሱ አድርጎ፣ በኢትዮጵያ ኅብረ ብሔራዊ ኅብረተሰብ ላይ በዋና ገዥነት ተቀመጠ፡፡

በዚህም ክንዋኔ አማካይነት በብሔረሰቦች ‹‹ራስን በራስ የማስተዳደር›› እና በ‹‹ፌዴራላዊነት›› ቆዳ ውስጥ፣ ከበፊቶቹ አገዛዞች የባሰ ጥላቻና መሸካከርን ያመረቱ ጠንቆች ተከተሉ፡፡ አማራዎች የተቆጣጠሩት/የተከማቹበት ይባል የነበረው የአፄ/የደርግ አገዛዝ ቢሰረዝም፣ ከተወሰነ ብሔረሰብ ጋር የመንግሥት መዛመድ ታሪክ አልተዘጋም፡፡ እንዲያውም በትግራዊነት ራሱን ለይቶ የተደራጀው ቡድን የኢትዮጵያን የፀጥታ አውታራትና የክልሎች ማጅር ግንድ ተቆጣጣሪ ሆኖ ከላይ ሲዘውር፣ ከሥር የክልል ገዥነትን የሸለማቸው ብሔርተኛ ቡድኖች ደግሞ ክልላዊ ባለቤት በተባሉ ብሔረሰባዊ ጥንቅሮች አገዛዛቸውን ቀረፁ፡፡ እናም የአማራ የበላይ ገዥነት ሄዶ እኩልነት መጣ ቢባልም፣ ከላይ በሕወሓት የበላይ ገዥነት ምክንያት ባለ ሁለት ጥፍር ድቀት ያደቀን ገባ፡፡ በትግራዊ ሕወሓታዊ ሠፈር ውስጥ ‹‹የእኛ መንግሥት/የእኛ ዘመን›› ነውና እንዳሻ ልዘባነን፣ እስከ ዛሬ የተጎዳሁትን/የታገልኩትን ያህል ተሹለክልኬ ሀብት ላካብት ባይ ዝንባሌ ሰዎችን ይፍቃል፡፡ ይህ በምላሹ ከዚያ ግቢ ውጪ የሆነው ኅብረተሰብ በቀጥተኛ ልምድም በወሬም እየበገነ የጥላቻ መጫወቻ እንዲሆን ያደርጋል፡፡ አገር ካካለለ የትግሬ ተብጠልጣይነት በታች ደግሞ ሌላ ጥምር ድቀት፣ የየክልሉን ገዥነት በያዙት ብሔርተኛ ቡድኖች ምክንያት ‹‹ራስን የማስተዳደር›› ስም የተረፋቸው ብሔረሰቦች ‹‹የብሔረሰብ ይዞታዬ/ወሰኔ›› እያሉ በመንቀብቀብና ከእነሱ ውጪ የሆኑ የአገር ልጆችን ባዕድ አድርጎ በሚያይ አሳሳች ግንዛቤ ተወድረዋል፡፡ የ‹ባዕዶቹ/የመጤዎቹ› መብት መቀነስና ከጥቅም መገፋት የእነሱ ጥቅም መሟላት በመሰለ ተላላነት ይላሳሉ፡፡ በብሔርተኛ አስታዋሽነት የዱሮ ቁስልን እያሰቡ የአሁኑን አንጓላይነት ብድር የማወራረድ በጎ ሰንደል ባስመሰለ መጭበርበር ይነዘነዛሉ፡፡ ተንጓላያዎቹ የአገር ልጆች ደግሞ የእኩል ዜግነት ግንዛቤያቸው ተሰልቦ ሥጋት በሚመነጥረው አንገት የደፋ ኑሮ ውስጥ የአድልኦ ትኩስ ቁስልን እያንቆሻበሉ የብግነትና የጠለሸ ስሜት መጫወቻ ይሆናሉ፡፡ በሌላ አነጋገር፣ በገራፊና በአሰቃይ ላይ የደረሰ የሰብዕና ስብራት በተሰቃዩ ላይ ከሚደርሰው ስብራት ሳይበልጥ አይቀርም፡፡ የፖለቲካ ነቃፊን ኑሮ በማመሳቀል ነቀፋን መበቀል የሰብዕና ዕልቀት ነው፡፡ በሌላው ላይ በመደንፋት ወይም ሌላውን በማሸማቀቅ መርካት ድቀት ነው፡፡ በሌላው ላይ የሚካሄድ አድልኦንና አሸማቃቂነትን በተግባር ባይጋሩም፣ በስሜት መጋራት/በዝምታ ማፅደቅ ደረጃው ይለይ እንጂ የድቀት ፈርጅ ነው፡፡ በተሸማቃቂነት/በተጠቂነት ቁጭት ተገንዞ መመዝመዝም የድቀት ገጽ ነው፡፡ በሁለቱም ሠፈሮች ውስጥ የጥላቻ ስሜት አለ፣ ሁለቱም ክስረቶች ናቸው፡፡ እነዚህን በሁለት በኩል የደረሱ የኅብረተሰባችንን ጉዳቶች ለማየት መቻል በዕርቅ ለመቀራረብ በጣም ጠቃሚ ነው፡፡

ከላይ ባየነው የድቀት ጉዟችን ውስጥ ለውጥ ‹‹ፈላጊ›› ፖለቲካችንም ያገኘውን ጉስቁልና ጨረፍ ማድረግ ይበጃል፡፡ ‹‹ብሔራቸውን የካዱና ከትምክህተኞች ጋር የተደረቡ፣ ጠባቦች/አሸባሪዎች›› የሚል ስም የተለጠፈባቸው (ከገዥዎቹ ቡድኖች ጋር በብሔረሰብ ምንጭ አንድ የሆኑ) ተቃዋሚዎች፣ እነሱ ሥልጣን ሲይዙ ክልላቸው ከተለጣፊ ገዥነት እንደሚላቀቅ ከማሰብ ተሻግረው የአገሪቱና የሕዝባቸው መፍትሔ ከብሔርተኛ ክፍልፋይነት መውጣትን እንደሚጠይቅ ማስተዋል በአያሌው ተሰውሯቸው ቆይተዋል፡፡ የኢትዮጵያ አንድነት ፖለቲካ አራማጆች ነን ከሚሉት ውስጥ ገሚሶቹ ወደ ክፍልፋይነት እየተምዘገዘጉ ጠለቁ፡፡ በአጠላለቃቸው አንዳንዶቹ ገለፈታቸውን በደንብ ገፈው ማኅበረሰባዊ ጎጇቸው ውስጥ ገብተዋል፡፡ አንዳንዶቹ ደግሞ ‹‹የኢትዮጵያ…›› የሚል የስም ገለፈት እንደያዙ የስብስብ ክምችታቸውና ጩኸታቸው ጠቧል፡፡ ገሚሶቹ ደግሞ በዚያው ‹‹አንድነት›› ላይ በደረቀና ለአገሪቱ ዕውናዊ ችግሮች ዕውናዊ መልስ በሌለው ባዶ ቀፎ ውስጥ ራሳቸውን ቀብረው፣ የብሔረሰብ መብት ጉዳይ በሽሽት የማይመለጥ የኢትዮጵያ እውነታ መሆኑን ሳይገነዘቡ ቀሩ፡፡

ስለፖለቲከኞቻችን ያልነውን ስለኅብረተሰባችን ከተናገርነው ጋር አንድ ላይ ብንፈትለው፣ የኢትዮጵያ ኅብረተሰብ በጥቅሉ ድርብርብ በሆኑ የመሸካከር ድቀቶችና የፖለቲካ ድህነት ተጠፍሮ መቆየቱን እንረዳለን፡፡ ሁሉም ወገን ከተራ ሰው እስከ ፖለቲካ ቡድን ተከፋፍሎ በመገዛት ካቴና መያዙን በቅጡ ለማስተዋልና ከዚያ ለመውጣት የሚያስችል መላ ለማበጀት አቅም ሳይጎለምስ ቆየ ብንል ሐሰት አይሆንብንም፡፡ ዛሬ የለውጥ ብርሃን ከታየም በኋላ፣ ሁሉንም ብሔረሰቦች አዳርሶ ለስቃይ እየዳረገ አልገባደድ ያለው የጥላቻ ስሜት፣ የበቀል ጥቃትና ማፈናቀል፣ የኖርንበትን የድቀት ካቴና ጥንካሬ የሚጠቁም ነውና፡፡

ይህንን አገራዊ መግባባት፣ ዕርቅና ሰላም የሚፈልገውን መሠረታዊ ችግራችንን ኃላፊነት የጎደለው ፖለቲካ፣ በማኅበራዊ ሚዲያ የሚለቀቀው ብሽሽቅና አሉታዊ ፕሮፓጋንዳው፣ እንዲሁም መሬት ላይ የሚከሰተው በካራ፣ በእሳትና በባሩድ የሚፋፋም ቀውስ ዕልቂታችንና መጨራረሳችንን እየደገሰልን ነው፡፡ ይህን ችግርና የህልውና አደጋ በመጋፈጥ በዚህ ትግል ውስጥ ተቀዳሚ የአስተዋይነት ተግባር የኃይል ሚዛንን፣ ነባራዊና ህሊናዊ ሁኔታዎችን በቅጡ መረዳት ነው፡፡ የሚፈታተነን ችግር ብቻውን አይደለም፡፡ የኢትዮጵያን የውኃ በተለይም የዓባይ ውኃ የመጠቀም መብት ሰንካላ የማድረግ፣ የግብፅና የሱዳን ፍላጎት በግርግርና በአጋጣሚ መሬት ከመቦጨቅ የሱዳን ፍላጎት ጋር ተሸራርቦ ተገናኝቷል፡፡ የኢትዮጵያን ልማትና መጠንከር ከሥጋት የሚቆጥሩ፣ የውኃ ልማትሽ የህልውናችን አደጋ ነው የሚሉ የነገረኛ ጎረቤቶቻችን ፍላጎት፣ ኢትዮጵያ ላይ ቀጥተኛ ጦርነት ከመክፈት አንስቶ በእጅ አዙር በታጠቁ የውስጥ ‹‹ትግሎች›› ሽፋን እስከማመስ ተግባራዊ ፈርጅ አበጅቷል፡፡ ምዕራባዊ ጫናና ሚናም በውስብስቦሹ ውስጥ አለበት፡፡ የምዕራባዊው ጫና በኃይል ሚዛን ላይ የሚያሳድረው ተፅዕኖ ኢትዮጵያ ውስጥ ሥውር እጅ የመስደድ፣ በማዕቀብ የማፈንና የማሰናከል፣ ተጨማሪ የጎረቤት ባላገር በጉርሻ የመግዛትና የማሠለፍ፣ እንዲሁም አበሳ የማባዛት ገጽታና መልክ ሁሉ ሊኖረው እንደሚችል ውስጡ ገብተንበት እያየነው ነው፡፡ አገርን የማዳኑ ትግል አዲስ ቅራኔዎች ከውስጥም ከውጭም እንዳይፈለፈሉ ተጠንቅቆ በሚቻለው ሁሉ በአርበኝነት መቆም የሚችለውን የውስጥ ኃይል ሁሉ አንድ ላይ የማገናኘት፣ ከኢትዮጵያ ጎን የሚቆመውን የውጭ ድጋፍም እያበረከቱ፣ ከውስጥ ጣጣ ጋር የተጠላለፈውን ውጫዊ የኃይል ጉድኝት የማለዘብ/የመብተን ሥራ ላይ የመጠበብ ጉዳይና ግዳጅ አለበት፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ