በግብይት ሥርዓት ውስጥ ከተጣባን እጅግ ክፉ ምግባሮች መካከል አንዳንድ አጋጣሚዎችን ላልተገባ ተግባር መጠቀም ተጠቃሽ ነው፡፡ አጋጣሚ ተገኘ ተብሎ የሚፈጸም ሕገወጥ ድርጊት እየተበራከተ መጥቷል ብቻ ሳይሆን እየተስፋፋ ነው፡፡ ስለአገርና ስለሕዝብ ከማሰብ ይልቅ የራስን ጥቅም በማስቀደም የሚፈጸሙ ሸፍጦች የብዙዎች እየሆነ መምጣቱ አሳሳቢ ደረጃ ላይ ደርሷል፡፡ ያሉብንን ችግሮች ተሰባስቦና ተማክሮ ከማለፍ ይልቅ፣ ችግሮችን በሚያባብሱ ተግባራት ላይ የሚጠመዱ መብዛታቸው እንደ አገር ዋጋ እያስከፈለን ነው፡፡ ይህ አደገኛ ልምድ ሕዝብን ለምሬት እየዳረገ የግብይት ሥርዓቱንም የበለጠ እያበለሻሸው ነው፡፡ ችግሩን ዓይቶ ሃይ የሚል አካል መጥፋቱም ነገሩን አብሶታል፡፡
በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ውስጥ የሚታየው የዋጋ ንረትና የተበለሻሸ የግብይት ሥርዓት ብዙ ምክንያቶች ያሉት ቢሆንም፣ እንደ ዜጋ እያንዳንዳችን ያለብንን ኃላፊነት በአግባቡ ካለመወጣት ጋር የተያያዘ ጭምር መሆኑን መገንዘብ አለብን፡፡ በኃላፊነት ይሠራሉ የተባሉ አገልግሎት ሰጪ ተቋማትና ግለሰቦች በራስ ወዳድነት የሚፈጽሙብን አንዳንድ ተግባራት ብዙዎች እንዲጎዱ ምክንያት ሆኗል፡፡ በሕግና በሥርዓት ሊሠሩ የሚገቡ ሥራዎች እንቅፋት እንዲገጥማቸው እያደረገ ነው፡፡ የአንድ ምርት እጥረት ተፈጠረ ሲባል ባልተገባ ዋጋ ገበያው ላይ ያለውን ምርት በመሰብሰብ፣ ችግሩን የብዙዎች የማድረግና ፍፁም የተጋነነ ዋጋ ተተክሎ እንዲቀር እያደረጉ ነው፡፡ በስግብግብነት የሚፈጸሙ ሸፍጦች በተለያዩ ምርቶች ላይ ወቅት እየጠበቀ የሚከሰት ሲሆን፣ በነዳጅ ሥርጭትና ግብይት ውስጥም ይህ ሕገወጥ ተግባር በተደጋጋሚ ይከሰታል፡፡ በቂ ነዳጅ እያለ እንኳን ‹‹እጥረት ሊፈጠር ነው›› በሚል ባለው በሌለው ገንዘብ ነዳጅ እየሸመተ በአግባቡ መስተናገድ ያለበትን የነዳጅ ሥርጭት በማስተጓጉል የሚፈጠሩ ውጥረቶች ብዙ ጉዳት ሲያደርሱ ዓይተናል፡፡ ስለዚህ አንዳንዴ ያሉብንን ችግሮች የምናባብሰውና በራሳችን ላይ ችግር የምንከምረው እኛው በመሆናችን የግብይት ባህላችን ተጎጂዎች እያደረገን ነው፡፡
ከዚሁ ነዳጅ ጉዳይ ጋር ተያይዞ ሰሞኑን እያየንና እየተመለከትን ያለነው ነገር ያማል፡፡ ከሳምንት በኋላ ይተገበራል ተብሎ የሚጠበቀውን አዲሱን የነዳጅ ሥርጭት ሥርዓትና የዋጋ ለውጥ እንደ አጋጣሚ በመጠቀም እየተፈጸሙ ያሉ ሸፍጦች እጅግ አሳፋሪ ናቸው፡፡ ሰው ላልተገባ ጥቅም ብሎ አገርና ሕዝብን የሚጎዳ ተግባር ላይ ሆን ብሎ ከመሰማራት በላይ ምን ክፋት አለ?
ገና ለገና ነዳጅ ስለሚጨምር በዚህ ጭማሪ ተጠቃሚ ለመሆን በመፈለግ በእጅ ያለን ነዳጅ መሸሸግና እጥረት መፍጠር እጅግ አሳዛኝ ተግባር ብቻ ሳይሆን ከፍተኛ ወንጀል ነው፡፡ በስንት መስዋዕትነት ተቃርኖ ጭምር በሚገኝ የውጭ ምንዛሪ የሚመጣ ነዳጅ በአግባቡ እንዲያሠራጩ ኃላፊነት በተሰጣቸው አካላት ኪሳቸውን ባልተገባ መንገድ ለመሙላት እንዲጠቀሙበት መፍቀድ አይገባም፡፡
የነዳጅ ዋጋ ሊጨምር ስለሚችል ተብሎ ሸፍጡ ነዳጅ የጫኑ ተሽከርካሪዎች ወደ መሀል አገር እንዳይገቡ እስከ ማድረግ የደረሰ መሆኑ ሲታሰብ ስግብግብነታችንና ደንታ ቢስነታችን ልክ ያጣ መሆኑን ፍንትው አድርጎ የሚያሳይ ነው፡፡
ነዳጅ የጫነ ተሽከርካሪ በቀጥታ በነዳጅ ማደያዎች ነዳጁን ማራገፍ ሲጠበቅበት የዋጋ ማስተካከያ እስኪታወጅ በየቋጥኙ ተሸሽጎ እንዲጠበቅ የሚያደርጉ የአንዳንድ ነጋዴዎች ድፍረት ከአገልጋይነት መንፈስ ያፈነገጠ፣ በድርጊታቸው ለሚደርሰው ጉዳትና ጥፋት ደንታ የሌላቸው እንደሆኑ ያሳያል፡፡ ጉዳዩን የበለጠ አሳዛኝ የሚያደርገው አንዳንድ የነዳጅ ጫኝ ተሽከርካሪ ባለቤቶች ነዳጅ ጭነው እየመጡ ያሉ ተሽከርካሪዎችን ባሉበት እንዲቆዩ ለሾፌርና ለረዳት አበል እስከመክፈል ጭምር ደርሰዋል መባሉ ነው፡፡
ይህ ዕርምጃቸው ምን ያህል ጥቅም እንደሚያገኙበት አሥልተው የሚፈጽሙት ሕገወጥ ተግባር ግን እንዲህ እንደዋዛ መታለፍ የሌለበት መሆኑም ሊሰመርበት ይገባል፡፡ እንዲህ ባለ ስግብግብ ተግባራቸው የተነሳ ሰሞኑን በአዲስ አበባ ከተማ የነዳጅ እጥረትና መጨናነቅ ተፈጥሮ እየተመለከትን ነው፡፡ ጥቂቶች እየፈጠሩት ያሉት ቀውስ ለአገር ኢኮኖሚ ቀውስ ሆኗል፡፡ ብዙዎችን እያጉላላም ነው፡፡ ሕዝብ ሲንከራተትና ሲማረርም እየታየ ነው፡፡ ወትሮም በዋጋ ንረትና የኑሮ ውድነት እየተማረረ ያለው ሕዝብ እንደገና ይህ ሲጨመርበት የሚፈጥረው ሥነ ልቦናዊ ጉዳት ሊታወቅ ይገባል፡፡ በእጥረቱና በሥጋቱ ምክንያት ገበያው ውስጥ የሚያስከትለው የዋጋ ለውጥ ቀላል ባለመሆኑ ሆን ብለው አጋጣሚውን በሕገወጥ መንገድ የተጠቀሙትን በሙሉ ተጠያቂ ማድረግ ይገባል፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ መንግሥት ‹‹ዕርምጃ እወስዳለሁ›› ከሚለው የተለመደ ፉከራው ወጥቶ አስተማሪ ዕርምጃ ካልወሰደ ነገም መደገሙ አይቀርም፡፡
ስለዚህ በኢኮኖሚያዊ ሸፍጦችና በተለይም ዋጋን ከማናር ጋር በተያያዘ እየተፈጠረ ያለውን ፍፁም ክፋት የተሞላበት ተግባር በሕጋዊ መንገድ መቀልበስ ተገቢ ብቻ ሳይሆን የመንግሥት ግዴታ ተደርጎ መወሰድ አለበት፡፡
የሕዝብ ሀብት በሌቦች እየተሸሸገና እየተዘረፈ መልሶ የሕዝብ መሰቃያ መሆን የለበትም፡፡ በዚህ ወቅት ሕዝብን የሚያማርሩ ተግባራት እንዲሁ ዜና እየተነገረላቸው ብቻ ሊቀጥሉ እንደማይገባ፣ በተግባር ማሳየትና ኅብረተሰቡን ከሥጋት መታደግ ያስፈልጋል፡፡ ለዚህ ደግሞ ሌባን በአግበቡ በመቅጣትና ሕግን በማስከበር የመንግሥት ተቀዳሚ ተግባር መሆን ይገባዋል፡፡ በሰሞኑ በአንዳንድ ስግብግቦች የተፈጸመውን ተግባር ከመኮነን ባለፈ የሚወሰደው ዕርምጃ የሚጠበቀው አዲሱ የነዳጅ ሥርጭትና ታሪፍ ተግባራዊ ሲሆን፣ በተመሳሳይ ድርጊት የሚሰማሩትን ለማስተማር ስለሚችል ነው፡፡ ገና አሠራሩ ሳይተገበር ክፍተቱን በመጠቀም እንዲህ ከተደረገ፣ ከትግበራው በኋላ በተገኘው ክፍተት ሁሉ በለመደ እጃቸው ችግሮች ሊፈጥሩ የሚችሉ መሆኑን ከወዲሁ በማሰብ፣ መንግሥት ይህንን ለመከላከል የሚያስችለውን አቅም ማጎልበት ያስፈልጋል፡፡ በጥቅል ሲታይ ሕገወጦችን ለመቆጣጠር ተከታትሎም ዕርምጃ ለመውሰድ ከተፈለገ የመንግሥት ቁርጠኝነት ቀዳሚ ሥፍራ ስለሚሰጠው በኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ዙሪያ ያሉ ሸፍጦችን ይከላከልልን፣ ሕግን ያስከብርልን፡፡