የ2014 ዓ.ም. የቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ በቅዱስ ጊዮርጊስ የበላይነት ተጠናቋል። ፈረሰኞቹ በ30ኛው ሳምንት የመጨረሻ ጨዋታቸውን ሰኔ 24 ቀን 2014 ዓ.ም. ከአዲስ አበባ ጋር በባህር ዳር ስታዲየም አድርገው 4ለ0 አሸንፈዋል። ፕሪሚየር ሊጉ በአዲስ መልክ በ1990 ከተጀመረ ወዲህ ይኸኛው ዋንጫ ያነሱበት ድላቸው ለ15ኛ ጊዜ ሆኗል። ለቅዱስ ጊዮርጊስ ኢስማኤል ኦሮ አጎሮ በ17ኛው ደቂቃ እና በ54ኛው ደቂቃ በጨዋታና በፍፁም ቅጣት ምት እንዲሁም አማኑኤል ገብረሚካኤል በ89ኛው እና በ93ኛው ደቂቃዎች ላይ ግቦቹን አስቆጥረዋል። በተመሳሳይ ጊዜ በባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ሜዳ በተካሄደው ጨዋታ ድሬዳዋ ከተማ የዓምናውን ሻምፒዮን ፋሲል ከነማን 3ለ2 በሆነ ውጤት ረትቷል። ድሬዳዋ በማሸነፉ ከመውረድ ሲተርፍ፣ በጊዮርጊስ የተሸነፈው አዲስ አበባ ወደ ከፍተኛ ሊግ መውረዱን አረጋግጧል። ሌሎቹ አስቀድመው መውረዳቸውን ያረጋገጡት ሰበታ ከተማና ጅማ አባ ጅፋር ናቸው። ቅዱስ ጊዮርጊስ ሻምፒዮን የሆነው በ65 ነጥብ ሲሆን በአራት ነጥብ የተበለጠው ፋሲል ከነማ በሁለተኛነት ያጠናቀቀው በ61 ነጥብ ነው።