የሰሜን ኢትዮጵያ ጂኦ ፖለቲካና የግጭት አፈታት ሒደት (Conflict Resolution in Northern Ethiopia and Geopolitics) የሚል የጥናት ጽሑፍ እ.ኤ.አ. ዲሴምበር 27 ቀን 2020 ያቀረቡት ማቲያስ ሌትነር፣ የትግራይ ግጭትና የሰላም ዕድሎችን በጥልቀት ዳሰዋል፡፡ ከሁለተኛው ዙር ግጭት ወይም ሕወሓት በአማራና በአፋር ክፍሎች ላይ ጥቃት ከመሰንዘሩ በፊት ስለነበረው የግጭት ሁኔታና የሰላም ጥረቶች ለማስታወስ የሚረዱ ጠቃሚ ነጥቦች በእሳቸው ጥናት ተዘርዝረዋል፡፡
‹‹ከግጭቱ መጀመር አስቀድሞ የነበሩ ግጭቱን ለማስቀረት ወሳኝ የነበሩ የሰላም ጥረቶችን ሳናነሳ፣ ወደ ግጭቱ ከተገባ በኋላ እየመጡ ስላሉ የሰላም ጥረቶች ማንሳት አይቻልም፤›› ነበር ያሉት ሌትነር በዚህ ጥናታቸው፡፡ የጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) መንግሥት ጦርነቱ ከመከሰቱ በፊት ለሰላም እጁን ዘርግቶ ብዙ ርቀት መጓዙን በዘገባቸው አስታውሰዋል፡፡ ሕወሓት ለሰላም እንቢተኝነት በማሳየቱ የተነሳ ሕወሓትን ከማስወገድ ውጪ ችግሩ በድርድር ይፈታል የሚለው የመንግሥት እምነቱ እየተሸረሸረ መምጣቱን ጸሐፊው አስገንዝበው ነበር፡፡
ጦርነቱ ተፋፍሞ በቀጠለበት ወቅት ግን በተለይ በዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ጫና መግፋት ሳቢያ፣ አንዳንድ የሰላም ጥረቶች መጀመራቸውን ነው ጥናቱ የሚጠቃቅሰው፡፡ እ.ኤ.አ. ዲሴምበር 21 ቀን 2020 በወቅቱ የአፍሪካ ኅብረት ሊቀመንበር በደቡብ አፍሪካው ፕሬዚዳንት ሲሪል ራማፎሳ አነሳሽነት፣ የአፍሪካ ኅብረት ከፍተኛ የአደራዳሪዎች ፓናል (High Level Mediation Panel) ተመሠረተ፡፡ የላይቤሪያ፣ የደቡብ አፍሪካና የሞዛምቢክ የቀድሞ መሪዎች ፓናሉን ወክለው ወደ አዲስ አበባ መጓዛቸውና ከዓብይ (ዶ/ር) ጋር መነጋገራቸው ተመልክቷል፡፡
ሌላው የሰላም ጥረት የምሥራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግሥታት ድርጅት (IGAD) የጀመረው ሲሆን፣ የወቅቱ የድርጅቱ ሊቀመንበር የሱዳን ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሃምዶክ እ.ኤ.አ. ዲሴምበር 13 ቀን 2020 ጀምሮ ወደ ኢትዮጵያ መመላለሳቸውን ጥናቱ መልሶ ያስታውሳል፡፡ ኢጋድ ዲሴምበር 20 በጂቡቲ ልዩ ስብሰባ በጠራ ወቅትም ቢሆን የትግራይ ጦርነት ከአጀንዳዎቹ አንዱ ነበር ይላል፡፡ በዚህ ስብሰባውም ከአንድ ወር አስቀድሞ በኖቬምበር 29 የደረሰውን የሰብዓዊ ረድኤት ያለ ቅድመ ሁኔታና ያለ ክልከላ ወደ ትግራይ እንዲገባ የመፍቀድ ስምምነት እንዲከበር፣ አገሮቹ በሐሳብ ተስማምተው ነበር የተለያዩት፡፡
ማቲያስ ሌትነር በዚህ ጽሑፋቸው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፀጥታው ጥበቃ ምክር ቤትን ደጃፍ የትግራይ ጉዳይ የረገጠው እ.ኤ.አ. በዲሴምበር 14 ቀን 2020 እንደነበር ያስታውሳሉ፡፡ የአውሮፓ ኅብረትና የአሜሪካ ባለሥልጣናት የጀመሯቸውን አንዳንድ የሰላም ተነሳሽነቶች የሚጠቃቅሱት ጸሐፊው፣ የትግራይ ጦርነት እንዴት ባሉ የግጭት አፈታት ሒደቶች እንዳለፈ ከመነሻው ያለውን ሁኔታ አስቀምጠውታል፡፡
ይህ ጽሑፍ ከቀረበ በኋላ የትግራይ ጦርነት እግጅ አስፈሪ የግጭት ምዕራፎችን ተሻግሯል፡፡ ጦርነቱ ከትግራይ ክልል ወጥቶ አማራና አፋር ክልሎችን አዳርሷል፡፡ ለአንድ ዓመት ከስምንት ወራት የዘለቀው የትግራይ ግጭት አድማሱም ቢሆን የዕልቂት መጠኑ በአሳሳቢ ሁኔታ ሰፍቷል፡፡ ፍሬ ባላፈሩ የሰላም ጥረቶች ውስጥ አንዴ በረድ ሌላ ጊዜ ጋል እያለ የቀጠለው ይህ ግጭት፣ ከሰሞኑ ከፍ ያለ ግምት የተሰጠው የድርድር ጅማሮ መፍትሔ ያገኘ ይመስላል፡፡
ቀደም ሲል ይነሳ የነበረው የድርድር ማድረግ አስፈላጊነት ጥያቄ ታልፎ፣ እነሆ ስለ ትግራይ ጦርነት የድርድር መፍትሔ በይፋ የሚወራበት ምዕራፍ ላይ ጉዳዩ ይገኛል፡፡ ድርድር ማካሄዱና ሰላማዊ የችግር መፍቻ መንገድ ለግጭቱ ማፈላለጉ በብዙዎች ዘንድ በበጎ የታየ ቢሆንም፣ ነገር ግን ድርድሩ የሚካሄደው እንዴት ነው? የድርድር አጀንዳዎቹ ምንድናቸው? አደራዳሪዎቹና ተደራዳሪ ሆነው የሚቀርቡት እነማን ናቸው? የሚሉ መሠረታዊ ጥያቄዎች በመነሳት ላይ ናቸው፡፡
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሕግ ትምህርት ቤት መምህር ዮናስ ዲርመታ (ረዳት ፕሮፌሰር) ከሰሞኑ የድርድር አጀንዳ ጎልቶ መነሳቱ አስፈላጊና በጎ መሆኑን ይናገራሉ፡፡ ሆኖም ወደ ድርድሩ ጠረጴዛ ተደራዳሪዎቹ ሲመጡ፣ ‹‹ከሕገ መንግሥቱ ጋር የሚጣጣሙ፣ ብሔራዊ ጥቅም ያማከሉ የመደራደሪያ ነጥቦችን ይዘው መምጣት አለባቸው፤›› ሲሉ ያስረዳሉ፡፡ አሁን ይደረጋል ተብሎ የሚጠበቀው ድርድር፣ ‹‹እንደ ከዚህ ቀደም ድርድሮች የኢዮጵያን ብሔራዊ ጥቅሞች አሳልፎ የሚሰጥ መሆን የለበትም፤›› በማለት ነው የድርድሩ ዋና ማጠንጠኛ ሊዘል የማይገባውን ጉዳይ ዮናስ (ረዳት ፕሮፌሰር) የተናገሩት፡፡
በሰሞነኛው የድርድር አጀንዳ መጉላት ላይ ሐሳባቸውን የተጠየቁት በአዲስ አበባ የወልቃይት ጠገዴ አማራ የሰላምና የልማት ማኅበር ፕሬዚዳንት አሰፋ አዳነ (ዶ/ር)፣ ሁለቱ የግጭቱ ዋና ተዋንያን ድርድሩን በተጨባጭ ፈልገውታል የሚለውን መሠረታዊ ነጥብ እንደሚጠራጠሩት ይናገራሉ፡፡
‹‹ድርድር ያለ ቅድመ ሁኔታና በተደራዳሪዎች ፅኑ ፍላጎት የሚካሄድ ከሆነ፣ ከድርድሩ በጎ ውጤት ለማግኘት የተሻለ ተስፋ ይሰጣል፤›› ብለው፣ በመንግሥትና በሕወሓት በኩል ይህ መጓደሉ እንደሚሰማቸው ጠቁመዋል፡፡ ‹‹ዓለም አቀፉ የድርድር ጫና ስለበረታ እንጂ፣ በሁለቱም ወገን የድርድር ዝግጁነት ኖሮ አልያም ምቹ ሁኔታ ፈጥረው፤›› አይደለም ይላሉ፡፡
የድርድር ጉዳይ ወደ አደባባይ መምጣቱ በአንድ ወገን በጎ ስሜትና ተስፋ ቢያሳድርም፣ ጉዳዩ በቀቢፀ ተስፋ መታየቱም አልቀረም፡፡ ሕወሓትም ሆነ መንግሥት ቀጥተኛ ያልሆነ ድርድር ለመጀመር ያላቸውን ዝግጁነት አረጋግጠዋል፡፡ በሁለቱም ወገን በኩል የድርድር ቅድመ ሁኔታ በሚል የተለያዩ መሠረታዊ ነጥቦች ተቀምጠዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ (ዶ/ር) በቅርቡ ለፓርላማ በሰጡት ማብራሪያ፣ በመንግሥት ወገን የሰላም ዝግጁነት መኖሩን ካረጋገጡና ድርድሩን የሚከታተል ብሔራዊ ኮሚቴ መዋቀሩን ከተናገሩ ወዲህ የድርድር ጉዳይ ዳግም አጀንዳ ሆኗል፡፡ ባለፈው ሳምንት ገዥው የብልፅግና ፓርቲ የማዕከላዊ ኮሚቴ ስብሰባ ማድረጉን ተከትሎ፣ አስቀመጥኳቸው ካላቸው ‹‹አቅጣጫዎች›› አንዱ ይኸው የድርድር ጉዳይ ነበር፡፡
ከስብሰባው በኋላ በፓርቲው ማዕከላዊ ኮሚቴ አባልና በፍትሕ ሚኒስትሩ ጌዲዎን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር) አማካይነት ሰባት የድርድር ቡድን አባላት ስም ይፋ ሆኗል፡፡ የፍትሕ ሚኒስትሩ በመግለጫው ፓርቲው ይከተለዋል ብለው ያስቀመጡት የሰላም አማራጭ፣ ሕገ መንግሥታዊነትን ያከበረና አገራዊ ጥቅም ያረጋገጠ መሆኑንም አመልክተዋል፡፡
የሕወሓት ቃል አቀባይ አቶ ጌታቸው ረዳ የሰላም ጥረቱ የትግራይን ሕዝብ ጥቅም ባልተሸራረፈ ሁኔታ የሚያረጋግጥ መሆን እንዳለበት ከሰሞኑ በሰጡት መግለጫ ተናግረዋል፡፡ ‹‹የሰላም አማራጭን አሟጠን መጠቀም ስለሚኖርብን፣ በዚያኛው ወገን ፍላጎት ኖረም አልኖረም የሰላማዊ መፍትሔን ጉዳይ ወደ ጎን አንለውም፤›› ብለው ነበር፡፡
‹‹የትግራይ ሠራዊት›› በመባል የሚጠራው የሕወሓት ኃይል አዛዥ የሆኑት ታደሰ ወረደ (ሜጄር ጄኔራል) እንደተናገሩት ከሆነ ደግሞ፣ ሰላምም ሆነ ጦርነት በሕወሓት ጠረጴዛ ላይ እንደተቀመጠ ነው፡፡ ‹‹የትግራይ ሕዝብ በሰላምም ካልተቻለ በጦርነትም የራሱን ጥቅም በአስተማማኝ ሁኔታ የሚያስጠብቅበት ደረጃ ላይ መገኘት አለብን፤›› ሲሉ ከሰሞኑ በሰጡት መግለጫ ገልጸው፣ ሁለቱንም አማራጮች ሕወሓት እንደሚከተል ነው በይፋ የተናገሩት፡፡
ስለ ድርድሩ አጀንዳ ሆኖ በቅርብ ሰሞን በመነሳቱ ብዙዎች ተስፋ ቢሰንቁም፣ ሁለቱ የጦርነቱ ዋና ተዋንያን የድርድሩ ሜዳ የሚገቡት ምን ዓይነት ፖለቲካዊ ተክለ ቁመና ይዘው ነው? የሚለው ሥጋት ግን በብዙዎች ዘንድ እየተነሳ ነው፡፡
የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲው የሕግ ምሁር ዮናስ (ረዳት ፕሮፌሰር)፣ ከሁለቱ ተደራዳሪዎች በዋናነት ሕወሓት ይዟቸው የቀረበው የፖለቲካ አጀንዳዎች ለድርድሩ መስመር ፈተና እንደሆኑ ይናገራሉ፡፡ ‹‹በኢትዮጵያ የድርድር ታሪኮች ከዚህ ቀደም የተሠሩ ስህተቶች መደገም የለባቸውም፡፡ ከሕወሓት ወገን ሕገ መንግሥቱንና ብሔራዊ ጥቅምን ያላማከሉ ጥያቄዎች እየቀረቡ ነው፡፡ በድርድር ወቅት አንዳንድ ጊዜ ድርድር ሲደረግ ፈታኝ ከሆኑ ነገሮች አንዱ ተደራዳሪዎች የተለየ የመደራደር አቅም ያለው ወገን ራሳቸውን አድርገው ለማቅረብ መሞከራቸው ነው፤›› በማለትም የድርድሩን ፈተና ያስረዳሉ፡፡ ይህ ሁኔታ ግን ወደ ድርድሩ ሲገባ በሒደት ሊቀየር እንደሚችል ግምታቸውን ያጋራሉ፡፡
‹‹የትግራይ ሕዝበ ውሳኔ ጥያቄ ጉዳይ በሕገ መንግሥቱ ማዕቀፍ ለመመለስ የማይመች ነው፡፡ ድርድሩ እንደ አንድ ሉዓላዊ አገር ነው መካሄድ ያለበት፡፡ ሉዓላዊነትን የሚጋፉ ጥያቄዎች መቅረብ የለባቸውም፤›› ሲሉ ነው ዮናስ (ረዳት ፕሮፌሰር) ምልከታቸውን የተናገሩት፡፡
ሌላኛው አስተያየት ሰጪ አሰፋ አዳነ (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ ሁለቱም ኃይሎች በአገር ውስጥም ሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ እየጨመረ የመጣውን ሰላም ፍጠሩ የሚል ግፊት ለማብረድ በማሰብ ወደ ድርድር ሜዳው እንደመጡ ነው የሚገምቱት፡፡
‹‹በሕወሓት በኩል ድርድር ብለው ካቀረቧቸው ቅድመ ሁኔታ ውስጥ አንዱ፣ የትግራይ ሉዓላዊነት ወይም ሕዝበ ውሳኔ ማድረግ የሚል ነጥብ አለ፡፡ በሌላ በኩል የትግራይ መከላከያ የሚሉት የታጠቀ ኃይል ሳይነካ ባለበት እንዲቀጥልም ፍላጎት አላቸው፡፡ በትግራይ ጭፍጨፋ የፈጸሙ ለሕግ ይቀርባሉ የሚል ነጥብም አላቸው፡፡ የወልቀይትና የራያ ጥያቄም ቢሆን በሕገ መንግሥቱ መሠረት የትግራይ ናቸው የሚል አቋም አስቀምጠዋል፡፡ እነዚህ ሁሉ ቅድመ ሁኔታዎች ለድርድር ዝግጁ እንዳልሆኑ የሚያመለክቱ ናቸው፤›› ሲሉ የተናገሩት አሰፋ (ዶ/ር)፣ ከድርድሩ ብዙም ውጤት እንደማይጠብቁ ነው የተናገሩት፡፡
አሰፋ (ዶ/ር) ሐሳባቸውን ሲቀጥሉም፣ ‹‹በአገር ላይ አንዳችም ጉዳት ሳያደርስ በራሱ በመንግሥት ጥሪ አገር ለመከላከል የመጣውን የፋኖ ኃይል ኢመደበኛ አደረጃጀት በሚል በሕግ ማስከበር ዘመቻ ስም ጠንካራ የማፍረስ ዕርምጃ መንግሥት እየወሰደበት ይገኛል፡፡ ለፋኖ ያልተመለሰ መንግሥት ራሱን የትግራይ መከላከያ ኃይል ብሎ የታጠቀ ጠንካራ ኃይልን ወደ ውድድር ሲገባ አይነኬ መሆን አለበት ሲባል ዝም ካለ ለድርድሩ አሥጊ ነው፤›› በማለት ነው ከድርድሩ ፈተናዎች አንዱ ብለው የሚያቀርቡት፡፡
ሁለቱ ተፋላሚዎች ወደ ድርድሩ ምን ዓይነት ተክለ ቁመና ይዘው ይገባሉ? ወይም ከድርድሩ ምን ይጠበቃል? የሚለው ጉዳይ ብቻ ሳይሆን፣ ድርድሩ በማን አደራዳሪነት ይደረጋል? የሚለው ጉዳይም ብዙ እያነጋገረ ይገኛል፡፡
በናይጄሪያ የቀድሞ ፕሬዚዳንት በኦሊሴጉን ኦባሳንጆ ይወከላል ሲባል የቆየው የአፍሪካ ኅብረት አደራዳሪነት ሚና በሕወሓት በኩል የሚፈለግ አይመስልም፡፡ ‹‹ኦባሳንጆ ለሰባት ጊዜ ተመላልሰዋል፣ ነገር ግን በተደራጀ መንገድ የድርድሩን ሒደት እንዲያቀርቡ እንፈልጋለን፤›› በማለት የተናገሩት የሕወሓት ቃል አቀባይ አቶ ጌታቸው፣ ተጠናክረው ከቀጠሉ የሰላም ጥረቶች ለመጠቀም ዝግጁ መሆናቸውን አመልክተዋል፡፡ ‹‹የኦባሳንጆ ጥረት ለአንድ ወገን ያላደላ መሆን አለበት፤›› ብለው አሜሪካ፣ ኬንያና የተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ የመሳሰሉ አገሮችም ተመሳሳይ የሰላም ጥረት መጀመራቸውን ተናግረው ነበር፡፡
ባለፈው ሳምንት ሐሙስ በእነ ኬንያ ስለተጀመረው የሰላም ጥረት የተጠየቁት የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ፕሬስ ሴክሬታሪያት የውጭ ቋንቋዎችና የዲጂታል ሚዲያ ኃላፊ ቢልለኔ ሥዩም ግን ስለጉዳዩ አስተባብለዋል፡፡ ‹‹ስለድርድሩ አስቀድሞ የተደረሰ አንዳችም ስምምነት የለም፡፡ የኬንያው መሪ ራሳቸው የአፍሪካ ኅብረትን አደራዳሪነት ሚና ይደግፋሉ፤›› በማለት የተናገሩት ቢልለኔ፣ ከዚህ ውጪ ስለሰላም ሒደቱ ማብራሪያ ለመስጠት እንደሚቸገሩ ነበር ያስረዱት፡፡
ስለዚሁ የአደራዳሪዎች ጉዳይ የተጠየቁት ዮናስ (ረዳት ፕሮፌሰር) በበኩላቸው፣ ድርድሩን የአፍሪካ ኅብረት ይምራው መባሉን ትክክለኛ ውሳኔ ብለውታል፡፡ ‹‹የተለያዩ ፍላጎቶችና ጥቅሞች ያላቸው ወገኖች ወደ ማደራደሩ ካልገቡ የሚለው ተገቢነት የለውም፡፡ መንግሥት በብዙ መንገዶች ገለልተኝነቱ የተረጋገጠው የአፍሪካ ኅብረት ያደራድረን ማለቱ ትክክለኛ ውሳኔ ነው፤›› ሲሉ አክለዋል፡፡
አስፋው (ዶ/ር) በዚህ ጉዳይ ላይ፣ ‹‹ሕወሓት ጥቅሙን የበለጠ የሚያስጠብቅበት ሁኔታ ካልተመለከተ በስተቀር ወደ ድርድሩ አይገባም፤›› ይላሉ፡፡ ‹‹ሕወሓቶች የአፍሪካ ኅብረት ብቻ ሳይሆን የተባበሩት የዓረብ ኤምሬት፣ ኬንያና አሜሪካ ወደ አደራዳሪነት ካልገቡ የሚሉት የሚያገኙትን ጥቅም ከወዲሁ አሥልተው ነው፤›› ብለዋል፡፡ ወደ ድርድሩ ሜዳ እንዴት ይገባና በአደራዳሪነቱ ማንም ይሰየም ከሚለው ጋር ድርድሩ የብዙ ወገኖችን ፍላጎት ያከበረ መሆን እንዳለበት አስምረውበታል፡፡ በተለይ ከወልቃይት ጠገዴና ከራያ ማንነት፣ እንዲሁም ከአፋር ክልል ጥያቄዎች ጋር በተያያዘ መንግሥት ጥንቃቄ የተሞላው መንገድ መከተል እንዳለበት ነው የጠቆሙት፡፡