ወታደራዊ ሚስጥሮችን ላልተፈቀደለት ሰው ወይም ሕዝብ በመግለጽ፣ የሚያደናግር መረጃ በማሠራጨት፣ በመገፋፋትና ግዙፍ ያልሆነ ማሰናዳት ተግባር ወንጀሎች ሦስት ክሶች የተመሠረተበት የፍትሕ መጽሔት ማኔጂንግ ዳይሬክተር ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ የዋስትና መብት ላይ ብይን ለመስጠት፣ ለሰኞ ሰኔ 27 ቀን 2014 ዓ.ም. ቀጠሮ ተሰጠ፡፡
ቀጠሮውን የሰጠው የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ አንደኛ የፀረ ሽብርና ሕገ መንግሥታዊ ጉዳዮች ወንጀሎች ችሎት ዓርብ ሰኔ 24 ቀን 2014 ዓ.ም. ሲሆን፣ በዕለቱ ዳኞች ባለመሟላታቸው ብይኑን ለመስጠት ባለመቻሉ ነው፡፡
በጋዜጠኛ ተመስገን ላይ የፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ሰኔ 21 ቀን 2014 ዓ.ም. የመሠረተው ክስ እንደሚያስረዳው፣ ተከሳሽ ጋዜጠኛ ተመስገን በፍትሕ መጽሔት አንደኛ ዓመት ቁጥር 18 ከመጋቢት 2011 ዓ.ም. ጀምሮ በተለያዩ ኅትመቶች ላይ ወታደራዊ ሚስጥሮችን ለሕዝብ አሳውቋል፡፡
ወታደራዊ ሚስጥራቱ ከፍተኛ ቁምነገር በመያዛቸው ለሕዝብም መገለጽ የሌለባቸው ቢሆኑም፣ ‹‹ሪፎርም ወይስ ፈረቃ፣ ወታደራዊ አመፅ ያሠጋል፣ ክልል ወይስ አገር፣ የጄኔራሉ ሚስጥሮች፣ መከላከያ ሠራዊትና የሹም ዘብ፣ ወታደራዊ ጉዳዮች፣ መከላከያ ተቋማዊ ወይስ ኔት ወርክ›› በሚሉ ርዕሶች መገለጻቸውን ክሱ በዝርዝር ያስረዳል፡፡
ተከሳሹ የተጠቀሱትን የወንጀል ድርጊቶች የፈጸመው፣ የወንጀል ሕግ አንቀጽ 44(1፣2) እና አንቀጽ 336(1)፣ 337 እና 257 (ሠ) ድንጋጌዎችን በመተላለፍ መሆኑን ዓቃቤ ሕግ በክሱ አስፍሯል፡፡
ክፍለ ጦሮችን ከሌሎች አገሮች ወታደራዊ አቋም ጋር በማነፃፀር፣ ከወታደራዊ የተገኘ ሰነድ (ቢገኝም እንኳን) መሆኑን በመጥቀስ፣ የወታደራዊ ቁመናንና ይዘትን በመግለጽ፣ መከላከያ ያለውን መሣሪያና ብዛት በመግለጽ፣ ወታደራዊ አመራሮች የተለዋወጡትን የመጃ ሚስጥር በመግለጽ፣ በፍትሕ መጽሔት በተለያዩ ጊዜያት መታተማቸውን ዓቃቤ ሕግ በክሱ አብራርቷል፡፡ የወታደራዊ ሹመቶችንና ሽልማቶችን በሚመለከትም፣ በጦርነት ግንባር ደርሰው ለማያውቁና በውጭ አገር የሰላም አስከባሪ ለነበሩ የአንድ ብሔር ተወላጆች ብቻ እንደተሰጠ አስመስሎ መታተሙንም ዓቃቤ ሕግ በክሱ ገልጿል፡፡
በአጠቃላይ በጋዜጠኛ ተመስገን ላይ የተመሠረቱ ሦስት ክሶች በፍትሕ መጽሔት ላይ የአገር መከላከያንና ሠራዊቱን በሚመለከቱ ሪፖርት ከተደረጉ መጣጥፎች ጋር የተገኛኙ ሲሆን፣ በጠበቃው በኩል በተደረገ ክርክር የዋስትና መብት ሊፈቀድለት ‹‹ይገባል ወይስ አይገባም›› በሚለው ላይ ነገ ሰኔ 27 ቀን 2014 ዓ.ም. ብይን ለመስጠት ቀጠሮ ተይዟል፡፡