Friday, December 1, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

በተሽከርካሪዎችና የመሸጋገሪያ ድልድይ ምሰሶዎች ላይ ማስታወቂያዎችን መለጠፍ ተከለከለ

ተዛማጅ ፅሁፎች

የውጭ ማስታወቂያ ፈቃድ ሥርዓትን ለመቆጣጠር የሚያስችል ስታንዳርድ የማውጣት ኃላፊነት የተሰጠው የአዲስ አበባ ከተማ የግንባታ ፈቃድና ቁጥጥር ባለሥልጣን፣ በተሽከርካሪዎችና የመሸጋገሪያ ድልድይ ምሰሶዎች ላይ የውጭ ማስታወቂያዎችን ማስተዋወቅ ከለከለ፡፡

በባለሥልጣኑ የተዘጋጀው ስታንዳርድ ካካተታቸው አጠቃላይ ዋና ዋና መሥፈርቶች ውስጥ በመኪና፣ በባቡርና በእግረኛ መሸጋገሪያ ድልድይ ምሰሶዎች ላይ ምንም ዓይነት የውጭ ማስታወቂያዎች መስቀል የከለከለ ሲሆን፣ በአንፃሩ በድልድዮች ላይ መስቀል እንደሚቻል ያመለክታል፡፡

ከዚህ ቀደም ማንኛውም ግለሰብም ሆነ ድርጅት በመንግሥታዊ ተቋማት ተሽከርካሪዎች ጭምር ያለ ማንም ከልካይ ማስታወቂያዎችን በክፍያም ሆነ በግል ፈቃድ ሲለጥፍ መቆየቱን ያስረዱት የአዲስ አበባ ከተማ የግንባታ ፈቃድና ቁጥጥር ባለሥልጣን የኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ አረጋዊ ማሩ፣ እስካሁን ድረስ በአሠራር የሚከለክል ነገር ስላልነበር ሲሠራበት መቆየቱን ገልጸው፣ በዚህ ወቅት የተዘጋጀው ስታንዳርድ እነዚህን ጉዳዮች የሚከለክል መሆኑን ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

በአዲስ አበባ የኮድ 1 ታክሲዎችን ጨምሮ የብዙኃን ትራንስፖርት በሚባሉት የአንበሳና ሃይገር አውቶቡሶች ላይ የተለያዩ ተቋማት ምርቶቻቸውን ሲያስተዋውቁ የሚስተዋል ሲሆን፣ ከዚህ ባሻገር በከተማዋ ትልልቅ አደባባዮች ሥር በሚገኙ ድልድይ ምሰሶዎች ላይ ማስታወቂያ ህትመት የተለመደ መሆኑ ይታወቃል፡፡

አቶ አረጋዊ እንዳስታወቁት፣ አሁንም በከተማዋ በተለያዩ መልኩ በማስታወቂያ ሥራ ላይ የተሰማሩ አካላት እንደፈለጉ በአደባባይ፣ በእግረኛ መንገድ ላይ ባነር ሲሰቅሉና ሲለጥፉ የሚስተዋሉ ሲሆን፣ ይህ መሆኑ ለአካል ጉዳተኞችም ሆነ ለሌላው አካል እንደልብ እንዳይንቀሳቀስ እንቅፋት ሆኗል ብለዋል፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ የውጭ ማስታወቂያ ሥራ በአግባቡና ወጥነት ባለው መንገድ ባለመተግበሩ ዘርፉ ላይ ከፍተኛ ችግሮች መታየቱን ያስታወቀው ባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ፣ በውጭ ማስታወቂያዎች ዙሪያ የወጡና የተቀመጡ ሕጎች፣ ደንቦችና መመርያዎች በዘርፉ ባሉ ባለድርሻ አካላት እንዲሁም በኅብረተሰቡ በተገቢው መልኩ አለመታወቃቸውና አለመተግበራቸውን በማሳያነት ጠቅሷል፡፡

በመንገድ ዳር በሚገኙ ምሰሶዎች፣ ግድግዳዎችና የድጋፍ ግንቦች ላይ ሥርዓት አልባ በሆነ መልኩ ሕገወጥ ማስታወቂያዎችን በብዛት የመለጠፍ ልምድ ማደጉ የከተማዋን የውበት ደረጃ በከፍተኛ መጠን ከመቀነሱ ባሻገር፣ የሕገወጥ ማስታወቂያ መበራከትና እንደ ሕጋዊነት መቆጠር ከተማዋ ልታገኘው የሚገባትን ከፍተኛ ኢኮኖሚያዊ ገቢ አስቀርቷል ተብሏል፡፡

በተዘጋጀው ስታንዳርድ መሠረት የውጭ ማስታወቂያን በትምህርት፣ በጤና፣ በሃይማኖትና በመንግሥታዊ ተቋማት፣ በኤምባሲዎች፣ በዓለም አቀፍ ድርጅቶች፣ በቤተመንግሥትና በመሳሰሉት ተቋማት አካባቢ መለጠፍ፣ መስቀልና ማንጠልጠል እንደማይቻል ተመላክቷል፡፡ 

ከዚህ ባሻገር በሕንፃ የውጭ መስታወት በር፣ መስኮትና የግንባታ ማጠናቀቂያ ቁሶች ላይ ምንም ዓይነት የውጭ ማስታወቂያ ማስተላለፍ የማይቻል ሲሆን፣ ነገር ግን በሕንፃ ውስጥ ባሉ የፓርቲሽን መስታወት በር፣ መስኮትና የግንባታ ማጠናቀቂያ ቁሶች ላይ በአከፋፈል ደንብ ቁጥር 117/2013 መሠረት በማስከፈል ፈቃድ ማግኘት እንደሚቻል ተቀምጧል፡፡

በዋና ዋና አደባባዮች የሚደረጉ ማስታወቂያዎች ደጂታል እንዲሆኑ፣ በዋና ዋና መንገዶች ደግሞ የሚሰቀሉት የማስታወቂያ ሰሌዳዎች ተገቢውን የልኬት አማራጮች በመውሰድ በሜትር ርቀት ውስጥ የሚተከሉ ይሆናል ሲሉ አቶ አረጋዊ ገልጸዋል፡፡

ስታንዳርዱን ከአዲሱ የበጀት ዓመት አንስቶ ተግባራዊ ለማድረግ እንቅስቃሴ እየተደረገ እንደሚገኝ የተገለጸ ሲሆን፣ እስከ ወረዳ ድረስ በሚዘልቁት የባለሥልጣን ቅርንጫፎች ሥራውን በማውረድ በስታንዳርዱ መሠረት ተገቢውን የማስታወቂያ ምዝገባ በማድረግ ተገቢውን ክፍያ ተፈጻሚ የማድረግ ሥራ እንደሚጀመር ተነግሯል፡፡

ባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ የወጣውን ስታንዳርድ ብቻውን የሚፈጽም ተቋም እንዳልሆነ ያስታወሱት የኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተሩ፣ የከተማው የኮሙዩኒኬሽን ቢሮ የሚተከሉ ማስታወቂያዎች ይዘታቸው ከማኅበረሰቡ ባህልና ወግ ጋር የሚጣጣሙ መሆኑን በመከታተል፣ የመንገዶች ባለሥልጣን፣ በመንገዶች ዳርቻና ድልድዮች ላይ የሚሰጡ የማስታወቂያ  ቦታዎችን በተመለከተ በመገምገም እንዲሁም ሌሎች ተቋማት በተሰጣቸው ሚና ልክ ለተግባራዊነቱ ያልተቋረጠ ድጋፍና ቅንጅት ማድረግ ይገባቸዋል ብለዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች