በአዲስ-አዳማ ፍጥነት መንገድ በሁለቱም የመንገድ አቅጣጫዎች 7.5 ኪሎ ሜትር የተዘረጋ የመንገድ አጥር በስርቆት መወሰዱን የፌዴራል ዋና ኦዲተር አስታወቀ፡፡
የክፍያ መንገዶች ኢንተርፕራይዝ በፍጥነት መንገዱ ላይ የሚገኙ የመንገድ ሀብቶችን ለማስጠበቅ ከ 21 ማኅበራት ጋር የጥበቃ ውል ስምምነት በመግባት፣ በየወሩ በአማካይ 380 ሺሕ ብር ወይም በዓመት በአማካይ 4.5 ሚሊዮን ብር በላይ ለጥበቃ ወጪ እያደረገ የሚከፈል ቢሆንም፣ በንብረቱ ላይ ስርቆት እየተፈጸመ መሆኑን የፌዴራል ዋና ኦዲተር ባጠናቀረውና ከሳምንት በፊት ይፋ ባደረገው የ2013 ዓ.ም. የኦዲት ሪፖርት አመላክቷል፡፡
በተጨማሪም በየመንገዱ በሁለቱም አቅጣጫዎች መሀል አካፋይ፣ ዳርና ቀኝ አቅጣጫዎች ብሎናቸው ተፈተው ከእነ ኮንክሪታቸው የተሰረቁ የአደጋ መከላከያ ጋርድሬሎች እንዲሁም ለአደጋ ጊዜ ተብለው በመንገድ አከፋፋይ ላይ የተተከሉ የአደጋ ጊዜ ብረቶች መሰረቃቸው በሪፖርቱ ተገልጿል፡፡
በአዲስ-አዳማ የፍጥነት መንገድ ኢንተርፕራይዝ ባለው የነዳጅ ማዳያ አጠቃቀም ከ2011 እስከ 2013 ዓ.ም. በተመረጡ የናሙና ተሽከርካሪዎች ላይ በተደረገ ኦዲት የሰሌዳ ቁጥራቸውና ኪሎ ሜትራቸው ሳይመዘገብ ነዳጁ ለምን አገልግሎት እንደዋለ የማይታወቅ 1614 ሊትር ነዳጅ መቀዳቱ በሪፖርቱ ተገልጿል፡፡
በሌላ በኩል በመንገድ ሀብቱ ላይ ጉዳት ካደረሱ አካላት በወቅቱ መሰብሰብ የነበረበት ነገር ግን ያልተሰበሰበ 11 ሚሊዮን ብር መኖሩን የኦዲት ሪፖርቱ አረጋግጧል፡፡
በአዲስ አዳማና ድሬዳዋና ደወሌ የክፍያ መንገድ ላይ የሚጓዙ ተሽከርካሪዎች በተፈቀደላቸው የፍጥነት ወሰን መሠረት እንዲጓዙ የሚያስገድድ ሕግ የተቀመጠ ቢሆንም ይህን ለማስፈጸም የሚረዱ ዘመናዊ የፍጥነት ቁጥጥር ሥርዓት ተግባራዊ እየተደረገ አለመሆኑ ተጠቁሟል፡፡
በሌላ በኩል በዚህ መንገድ ከክብደት በላይ ጭነው የሚንቀሳቀሱ ተሽከርካሪዎችን ለመቆጣጠር የሚደረግ ግልጽ መመርያ የለም ተብሏል፡፡
የኦዲት ሪፖርቱ እንደሚያመለክተው በድሬዳዋ ደወሌ ክፍያ መንገድ ሥራ ሲጀመር ወጥ የሆነ የመንገድ ርክክብ ያልተደረገበት በመሆኑ የመንገድ ሀብቱን ማወቅ እንዳልተቻለ፣ እንዲሁም ቆጠራ ያልተደረገ በመሆኑ የመንገድ ክልል ወሰኑ ባለመታወቁ ግለሰቦች የእግረኛ መንገዱን ጠርዝ በመያዝ ግንባታ እያከናወኑ ነው፡፡