የኢትዮጵያ መገናኛ ብዘኃን ባለሥልጣን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ አንዳንድ የሃይማኖት መገናኛ ብዙኃን ከአብሮነት ይልቅ ለጥላቻ መልዕክት ማስተላለፊያ ሆነው መታዘቡን በመግለጽ፣ ከንግድና የመታገያ መድረክ ከመሆን እንዲቆጠቡ ጠየቀ፡፡
ከብዙ ጊዜ ጥበቃ በኋላ በቅርቡ የሃይማኖት መገናኛ ብዙኃን ምዝገባ የጀመረው ባለሥልጣኑ፣ አንዳንዶቹ የሃይማኖች መገናኛ ብዙኃን ለማሳሳቻና ለማጭበርበሪያ መልዕክቶች የተጋለጡ መሆናቸውን ገልጿል፡፡
የባለሥልጣኑ ዋና ዳይሬክተር አቶ መሐመድ እድሪስ ይህንን የተናገሩት በሳምንቱ አጋማሽ መሥሪያ ቤታቸው የጥላቻ ንግግርና ሐሰተኛ መረጃን አስመልክቶ ባዘጋጀው የውይይት መድረክ ላይ ነው፡፡ ዋና ዳይሬክተሩ፣ ‹‹ወዲህ አንዳንድ የሃይማኖት ሚዲያዎችን በምንመለከትበት ጊዜ ሚዛኑን ባልጠበቀ መልኩ ከራስ ባለፈ፣ ክብርን ዝቅ ያደረገ፣ ከአብሮነት ይልቅ ለጥላቻ መልዕክት፣ እንዲሁም አልፎ አልፎ ደግሞ ለማሳሳቻና ለማጭበርበሪያ መልዕክቶች የተጋለጡ [ሆነዋል]፤›› በማለት ተናግረዋል፡፡
ለሃይማኖት መገናኛ ብዙኃን የሕግ ማዕቀፍ መዘጋጀቱን የገለጹ አቶ መሐመድ፣ የሃይማኖት መገናኛ ብዙኃን ‹‹የኮሜርሻል ቅርፅ ወይም የተለየ የመታገያ ቅርፅ ወይም የመግፊያ ቅርፅ እየያዙ የመጡ የሃይማኖት ሚድያዎች ይሄኛው መንገድ ለእናንተ የተፈቀደ አይደለም፤›› ብለዋል፡፡ አክለውም ሲጀምሩ ወደ ተቋቋሙበት ዓላማ እንዲመለሱ ጠይቀዋል፡፡ በራሳቸው አስተምህሮ ላይ አተኩረው ሌሎችን ሃይማኖቶች አክብረውና አብሮነትን በሚያጠናክር መልኩ መንቀሳቀስ እንዳለባቸውም አሳስበዋል፡፡
ምክንያቶቹ የተለያዩ ቢሆኑም የሐሰተኛ መረጃና ጥላቻ ንግግር ሥርጭትና በዓይነቱ እየሰፋ መሆኑን የተናገሩት ዋና ዳይሬክተሩ፣ ውጤቱን በየጊዜው እየታየ መሆኑን አንስተዋል፡፡ በአገሪቱ ውስጥ የተለያዩ ሁነቶች ሲከሰቱ ለአፀፋዊ ዕርምጃ የሚያነሳሱ መረጃዎች እንደሚሠራጩና ለሌሎች ችግሮች ምንጭ እየሆኑ መምጣታቸውን አስረድተዋል፡፡
ዋና ዳይሬክተሩ ‹‹[የጥላቻ ንግግር] ከአደጋ ራሳቸውን መከላከል የማይችሉ ዜጎችን በጥላቻና በጽንፈኝነት በመነሳት ለአደጋ እያጋለጠ ነው፤›› በማለት ይሄንን አይነቱን ጉዳይ በመመካከር ማስቆም እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡
በ2012 ዓ.ም. የጥላቻ ንግግርና የሐሰተኛ መረጃ ሥርጫትን ለመከላከልና ለመቆጣጠር በሚል በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አዋጅ ቢወጣም፣ አዋጁ በሚገባው ሁኔታ ተፈጻሚ አለመሆኑን የባለሥልጣኑ ምክትል ዳይሬክተር አቶ ዮናታን ተስፋዬ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡ ይሄም ከቅጣት ይልቅ ለማስተማር ቅድሚያ በመሰጠቱ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
አቶ መሐመድ በውይይቱ ላይ ባደረጉት ንግግር የጥላቻ ንግግር ወይም ሐሰተኛ መረጃ ለመግታት የሚያስችሉ የሕግ ማዕቀፎች መኖራቸውን ጠቅሰው ‹‹በዚህ የሕግ ማዕቀፍ ዙሪያ ግንዛቤ መፍጠርና ተጠያቂነትን ማረጋገጥ ያስፈልጋል፤›› በማለት የአዋጁ ተግባራዊነት አስፈላጊ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
ባለሥልጣኑ ባዘጋጀው የውይይት መድረክ መነሻ ሐሳብ ያቀረቡት የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች ማኅበር ፕሬዚዳንት አቶ ጥበቡ በለጠ የጥላቻ ንግግርን ያቀርባሉ ተብለው እየተወቀሱ ያሉት መገናኛ ብዙኃን ከአገሪቱ ሁኔታ ተነጥለው እዚህ አለመድረሳቸውም የሚጠቁም መከራከሪያ አቅርበዋል፡፡ አቶ ጥበቡ እንደሚያስረዱት 1984 ዓ.ም. በኋላ የግል መገናኛ ብዙኃን ወደ መድረኩ ሲመጡ አብዛኛዎቹ የቀረቡት የመታገያ ሜዳ ሆነው ነበር፡፡
በተለያዩ መልኮች ወገኝተኝነትን ይዘው የተፈጠሩ መገናኛ ብዙኃን ብዙ መሆናቸውን የጠቀሱት አቶ ጥበቡ፣ በዚህም የተነሳ በአገሪቱ ያለው የፖለቲካ ጡዘት የሚያንቀሳቅሳቸው ሆነው መክረማቸውን ጠቅሰዋል፡፡
ከዚህም ባሻገር ግን ጋዜጠኞች ለዘገባ በሚሄዱባቸው ሁነቶች ላይ የሚነገሩ የጥላቻ ንግግሮች እንደሚጠለፉ ተናግረዋል፡፡
መገናኛ ብዙኃን የፖለቲካ ሥሪቱ ውጤት ናቸው የሚለው ሐሳብ ከተሳታፊዎችም ተነስቷል፡፡ የድሬ ትዩብ ዋና አዘጋጅ አቶ ፍሬው አበበ ‹‹ሚድያው ለብቻው ሸምጥጦ አላመጣውም፣ የፖለቲካ ሥርዓቱ ብልሽት ነው፤›› በማለት ሐሳቡን ተጋርተዋል፡፡ በመንግሥት ሥር ያሉ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣናትን በሚያቀርቡበት ጊዜ የሚቀርበው ንግግር የጥላቻ ንግግር ቢሆን እንኳን ለማስቆም ዕድሉ እንደማይኖራቸው በመግለጽ መገናኛ ብዙኃን ያለባቸው ተፅዕኖ አንድ ምክንያት መሆኑን ተናግረዋል፡፡