Sunday, October 1, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት የምርምር ሥራዎችን እንዲያከናውን ተጨማሪ ተልዕኮ ተሰጠው

ተዛማጅ ፅሁፎች

የግብርና ዘርፍ ማነቆዎችን በሳይንሳዊ መንገድ በማጥናት የመፍትሔ ድጋፎችን ለባለድርሻ አካላት ሲያቀርብ ቆይቷል የሚባለው፣ የግብርና ትራንስፎርሜሽን ኤጀንሲ (ኤቲኤ) ወደ ኢንስቲትዩት (ኤቲአይ) ከተለወጠ በኋላ፣ የምርምር ሥራዎችን ለማከናወን የሚያስችል ተጨማሪ ተልዕኮ እንደተሰጠው ተገለጸ፡፡

ኢንስቲትዩቱ ከዚህ ቀደም ሲቋቋም ታሳቢ የተደረገው ውስን ለሆኑ ጊዜያት፣  በግብርና ዘርፍ ውስጥ ያሉ ተቋማትን ሙሉ አቅማቸውን በመገንባትና ሥርዓት በማበጀት ወደ ዘመናዊ ሥርዓት እንዲሸጋገሩ ማድረግ እንደነበር ይታወሳል፡፡

መንግሥት ተቋሙን ከኤጀንሲ ወደ ኢንስቲትዩት ሲያሳድገው ላለፉት አሥር ዓመታት የተሠሩትን ሥራዎች በመገምገም እንደነበር፣ በዚህም  ከዚህ ቀደም ከነበረው አራት የተልዕኮ ሥራዎች በተጨማሪ በምርምር ሥራዎች ላይ ለመሳተፍ የሚያስችል ሌላ ተጨማሪ ተልዕኮ እንደተሰጠው፣ የኢንስቲትዩቱ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ማንደፍሮ ንጉሤ (ዶ/ር) ተናግረዋል፡፡

ለኢንስቲትዩቱ የተሰጠው የግብርና ምርምር ተግባር፣ የኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት የሚያከናውነው የሰብልና የእንስሳት ምርምር ዓይነት ሳይሆን፣ በግብርና ዘርፍ የተሠሩ የምርምር ሥራዎች የሚሻሻሉበት ሥርዓት ላይ የሚያተኩር መሆኑ ተጠቅሷል፡፡

የግብርና ምርምር ሥርዓትን እንዴት ነው ማሻሻል የሚቻለው? እንዴት ነው ውጤታማ የሚኮነው? የኤክስቴንሽን፣ የገበያ፣ የኢንዱስትሪ ሥርዓት (ሲስተም) የሚባሉትን ጉዳዮች የግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩቱ በተጨማሪ የተልዕኮ ሚናው የሚቃኘው መሆኑን ማንደፍሮ (ዶ/ር) አስታውቀዋል፡፡

የግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት ሐሙስ ሰኔ 23 ቀን 2014 ዓ.ም. በዋና መሥሪያ ቤቱ በአዲሱ መጠሪያ ስሙ የሚተገብረውን ተልዕኮ በይፋ ያስታወቀበትን መርሐ ግብር፣ የግብርና ሚኒስትሩ አቶ ኡመር ሁሴንና የልማት አጋር ኃላፊዎች በተገኙበት አከናውኗል፡፡

አቶ ኡመር በግብርና ሚኒስቴር ሥር ካሉ ዘጠኝ ተጠሪ ተቋማት ውስጥ ኤቲአይ አንዱ ነው ብለዋል፡፡ ተቋሙ ኤጀንሲ በነበረበት ወቅት የተለያዩ ጥናቶችን አጥንቶ ሌላ ፈጻሚ ይጠበቅ እንደነበር ያስታወሱት ሚኒስትሩ፣ በዚህ ወቅት ከጥናት ባሻገር ከግብርና ሚኒስቴር ጋር በመሆን የመፈጸም ሚና ይወጣል ብለዋል፡፡

የግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት አነስተኛ ይዞታ ያላቸውን አርሶ አደሮችን በማዘመን ተጠቃሚ ለማድረግ ከተጀመረና ውጤት ከተገኘበት ፕሮግራም ውስጥ፣ የግብርና ኮሜርሻላይዜሽን ክላስተር ተጠቃሹ መሆኑን በመርሐ ግብሩ ላይ አስታውቋል፡፡

የግብርና ኮሜርሻላይዜሽን ክላስተር ፕሮግራም ከዚህ ቀደም አራቱ ዋና ዋና ክልሎች በተባሉት ከአማራ፣ ከኦሮሚያ፣ ከትግራይና ከደቡብ ክልሎች በተመረጡ 300 ወረዳዎች ተግባራዊ እየተደረገ የሚገኝ ሲሆን፣ የደቡብ ክልል በዚህ ወቅት ወደ ሦስት ክልሎች ከመሸጋገሩ ጋር ተያይዞ በጠቅላላው የፕሮጀክቱ ትግበራ በስድስት ክልሎች እየተከናወነ እንደሚገኝ ማንደፍሮ (ዶ/ር) ገልጸዋል፡፡

ኢንስቲትዩቱ ከቀጣዩ የበጀት ዓመት አንስቶ በይፋ ወደ አዳዲስ ክልሎች በመግባት የክላስተር እርሻ ልማት ሥራውን እንደሚጀመር የተገለጸ ሲሆን፣ ከወዲሁ በሙከራ ደረጃ የተጀመረባቸው ክልሎች እንዳሉም ተመላክቷል፡፡ ይህ ብቻ ሳይሆን ኢንስቲትዩቱ ከዚህ ቀደም ባልገባባቸው የሶማሌ፣ የአፋር፣ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ የሐረርና የጋምቤላ ክልሎች ከሰብል ምርቶች በተጨማሪ በእንስሳት ሀብት፣ በተለይም የዶሮና ወተት ሀብት ልማት ፕሮጀክቶች እንቅስቃሴ መጀመሩ ታውቋል፡፡

በሌላ በኩል ኢንስቲትዩቱ በግብርና እሴት ሰንሰለት ውስጥ ያሉ ተዋንያንን ማገናኘትና ማስተሳሰር አንዱ የተልዕኮው ዓይነት መሆኑ ተገልጾ፣ በዚህም የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ተዋንያንን ከአገሪቱ አርሶ አደሮች ጋር የማስተሳሰር ሚና መወጣቱን አስታውቋል፡፡ ለአብነትም በክላስተር የብቅል ገብስ የሚያመርቱ አርሶ አደሮችን ብቅልን ከሚያቀነባብሩ (ፕሮሰስ) ከሚያደርጉ ኩባያዎች ጋር የማስተሳሰር፣ ዘይት የሚጨምቁ ኢንዱስትሪዎችን አኩሪ አተር አምራች ከሆኑ አርሶ አደሮች ጋር ለማገናኘት መቻሉን የኢንስቲትዩቱ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አስረድተዋል፡፡

እንደ ዋና ሥራ አስፈጻሚው ገለጻ የተለያዩ አገሮች፣ ዓለም አቀፍ ፋውንዴሽኖች፣ ተቋማትና ሌሎች አጋር አካላት የኢንስቲትዩቱን ተልዕኮ በተለያየ መንገድ እየደገፉ ናቸው፡፡ ከእነዚህም ውስጥ ዴንማርክ፣ ኔዘርላንድ፣ ኖርዌይ፣ ፈረንሣይ፣ የቢልና ሚሊንዳ ጌትስ ፋውንዴሽን ተጠቃሾቹ መሆናቸው ተገልጿል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች