Friday, September 22, 2023
- Advertisment -
- Advertisment -

የኢትዮጵያዊነት ትልቁ ምሥል ላይ ይተኮር!

የአገር ህልውና ፀንቶ መቀጠል የሚችለው ስለኢትዮጵያዊነት ትልቁ ምሥል የጋራ ግንዛቤ ሲኖር ነው፡፡ የአገር ህልውና ጉዳይ ሲነሳ በቀጥታ የሚመለከተው ከ115 ሚሊዮን በላይ ኢትዮጵያዊያንን ነው፡፡ በአገሪቱ አራቱም ማዕዘናት ውስጥ የሚኖሩና በውጭ የሚገኙ ኢትዮጵያዊያን ከአያት ከቅድመ አያቶቻቸው የወረሱት ጥልቅ የሆነ የአገር ፍቅርን ነው፡፡ ይህ ወደር የሌለው ፍቅር በመስዋዕትነት ጭምር የተጠናከረ በመሆኑ፣ የእናት አገር ህልውና ጉዳይ ከምንም ነገር በላይ ያሳስባል፡፡ ይህ የተከበረ፣ ጨዋና አስተዋይ ሕዝብ የአገሩ ጉዳይ ዛሬም ያሳስበዋል፡፡ በአገር ጉዳይ ላይ መነጋገሪያ የሚሆኑ ጉዳዮች የሕዝብን ፍላጎት ማዕከል ማድረግ ይኖርባቸዋል፡፡ የፖለቲካ ፓርቲዎችም ሆኑ ማኅበራት ወይም ግለሰቦች የአገርን ጉዳይ ከጠባብ ፍላጎት አኳያ ሲቃኙ ጠባቸው ከሕዝብ ጋር ነው፡፡ የአገርና የሕዝብ ቁርኝት ይኼንን ያህል መሆኑ ከታወቀ በብሔር፣ በእምነት፣ በፖለቲካ አመለካከትም ሆነ በሌሎች ጉዳዮች ላይ የሚደረጉ ዲስኩሮችም ሆኑ መልዕክቶች ጥንቃቄ ያሻቸዋል፡፡ ኅብረ ብሔራዊ በሆነች አገር ውስጥ ከአንድነት ይልቅ ልዩነት ከመጠን በላይ በመሰበኩ በርካታ ጉዳቶች አጋጥመዋል፡፡

በአሁኑ ጊዜ በድህነትና በኋላቀርነት በምትማቅቅ አገር ውስጥ እናውቃለን ባዮች ማገናዘብ አቅቷቸዋል፡፡ ኢትዮጵያን ከገባችበት ማጥ ውስጥ ለማውጣት መረባረብ ሲያዋጣ፣ ከሥልጣን በፊት አገርና ሕዝብ ማስቀደም ያቃታቸው በገሃዱ ዓለም የሚቃዡ ፖለቲከኛ ተብዬዎች እንደ እንጉዳይ ፈልተዋል፡፡ ኢትዮጵያ እጀግ በጣም ሰፊ ለም መሬት፣ አመቺ የሆነ የአየር ንብረትና ጠንካራ ወጣት የሰው ኃይል ይዛ ትራባለች፡፡ የአፍሪካ የውኃ ማማ እየተባለች ትጠማለች፡፡ የገዘፈ ታሪክ ባለቤት ሆና የአገሮች ጭራ ናት፡፡ አሁንም በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሕፃናት ተመጣጣኝ ምግብ ስለማያገኙ ይቀነጭራሉ ወይም ይሞታሉ፡፡ ከድህነት ወለል በታች የሚኖሩ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያዊያን ካሉት በታች፣ ከሞቱት በላይ ሆነው ከአንገፍጋፊው ድህነት ጋር ይታገላሉ፡፡ ሚሊዮኖች መጠለያ አልባ ናቸው፡፡ በከተሞች በሚያሳዝን ሁኔታ የከተማ ነዋሪዎች ከምግብና ከመጠለያ ችግር በተጨማሪ የትራንስፖርት፣ የውኃ፣ የኤሌክትሪክና የማዘጋጃ ቤት አገልግሎቶችን የሚያገኙት በኋላቀር አሠራሮች ነው፡፡ ድህነት ያመሰቃቀላት አገር ታቅፎ እንደ ደላቸው አገሮች እዚህ ግቡ በማይባሉ ጉዳዮች መተራመስ ትዝብት ላይ ይጥላል፡፡ ከመጠን ያለፈ ድህነት ሕዝቡ አናት ላይ እያናጠረ በከንቱ ግብዝ መሆን አያዋጣም፡፡ ለግል ሥልጣንና ጥቅማ ጥቅም ሲባል በአገር ላይ መዶለት ነውር ነው፡፡ ለሺዎች ዓመታት በሞፈርና በቀንበር የሚከናወነውን እርሻ ለማዘመን የረባ ፖሊሲ የማያወጡ የሥልጣን ጥመኞች፣ አገርን ለመበታተን የአጥፍቶ ጠፊ ጎዳና ሲይዙ ዝም መባል የለበትም፡፡

የወቅቱን የኢትዮጵያ ሁኔታ በአንክሮ የሚከታተሉ አገር ወዳድ ኢትዮጵያውያንም ሆኑ የውጭ ሰዎች፣ ኢትዮጵያ በአፍሪካ ተስፋ ከሚጣልባቸው አገሮች አንዷ መሆኗን ቢያምኑም ሥጋት ግን አላቸው፡፡ ኢትዮጵያ ልጆቿ ተባብረው ጠንክረው ከሠሩ ትንሳዔዋ ቅርብ መሆኑን የሚናገሩትን ያህል፣ ወጥረው የያዙዋት ችግሮች ደግሞ ለህልውናዋ ጭምር አሥጊ መሆናቸውን ያሳስባሉ፡፡ እንደ ምሳሌ ከሚነሱ መሠረታዊ ጉዳዮች መካከል በአገሪቱ የተለያዩ ሥፍራዎች የሚከሰቱ ግጭቶች አለመቆማቸው፣ ማንነትን መሠረት ያደረጉ ግድያዎች መቀጠላቸውና የተዳከመው ኢኮኖሚ ዋነኞቹ ናቸው፡፡ ግጭትን በተባበረ ጥረት ማስቆም ከተቻለ እኮ ሌላው ዕዳው ገብስ ነበር፡፡ ፖለቲከኞችም ሆኑ በዙሪያቸው ያሉ አክቲቪስቶችና ደጋፊዎች ግጭት እየቀፈቀፉ አገር ከሚያምሱ ለአገር ውለታ ይዋሉ፡፡ መተባበር ሲቻል ኢትዮጵያን የፍትሕና የዴሞክራሲ አገር በማድረግ ታሪክ መሥራት ይቻላል፡፡ የተዳከመው ኢኮኖሚ ተነቃቅቶ ለሚሊዮኖች ሥራ በመፍጠር ተዓምር መፍጠር ይቻላል፡፡ በሠለጠነ ንግግር፣ ውይይትና ድርድር የፖለቲካ ምኅዳሩ ክፍት ሲሆን፣ ሰላማዊና ሕጋዊ የፖለቲካ ፉክክር ባህል ይሆናል፡፡ ይኼንን ለማድረግ ግን የአገር ፍቅርን በስሜት ብቻ ሳይሆን በተግባር ማሳየት ይገባል፡፡ ኢትዮጵያ የምትፈልገውም ለሰላምና ለልማት የሚሠለፉላትን ብቻ ነው፡፡

ለአንድ አገር ከሚያስፈልጉ መሠረታዊ ጉዳዮች መካከል አንዱ ፍትሕ ነው፡፡ ፍትሕ ሊሰፍን የሚችለው የሕግ የበላይነት በተረጋገጠበት አገር ውስጥ ብቻ ነው፡፡ የሕግ የበላይነት በመጥፋቱ ግን ኢትዮጵያዊያን በገዛ አገራቸው ሹማምንትን ይለማመጣሉ፡፡ የተጻፈ ሕግ ባለበት አገር ውስጥ ያልተጻፈ ሕግ የበላይ ይሆናል፡፡ ሕግ የዜጎች መብትና ጥቅም ማስከበሪያ መሆን ሲገባው፣ ማጥቂያ መሣሪያ እየሆነ ብዙዎችን አሳር አሳይቷል፡፡ ኢትዮጵያዊያን በሕግ ፊት እኩልነታቸው መረጋገጡ በሕገ መንግሥቱ ቢሰፍርም፣ መብታቸው እየተጣሰ በርካታ በደሎች ደርሰዋል፡፡ ፍትሕ እንደ ሸቀጥ በገንዘብ እየተሸጠ ንፋስ አመጣሽ ባለሀብት ደሃውን ቀልዶበታል፡፡ ባለጉልበቱ አቅመ ደካማውን አጥቅቶበታል፡፡ መብቴ ይከበርልኝ ያለው ሰንሰለት ጠልቆለታል፡፡ ይህ ዓይነቱ የታሪክ ምዕራፍ ተዘግቶ ኢትዮጵያውያን በሕግ ፊት እኩልነታቸው ሊረጋገጥ የግድ ይላል፡፡ ባለሀብቱ በገንዘቡና በሚመካበት ባለሥልጣን ተማምኖ እንዳሻው የሚሆንባት አገር ቅራኔን በማባባስ የበለጠ አመፅ ትጋብዛለች፡፡ በብሔርና በእምነት እየተቧደኑ ፍትሕን መናድ ካልቆመ ለአገር ሰላም አደገኛ ነው፡፡ ለአገር የማይጠቅሙ ድርጊቶች ይቁሙ፡፡

ሁሉም ኢትዮጵያዊያን በፈለጉበት ሥፍራ የመዘዋወር፣ የመኖርና ሠርተው ሀብት የማፍራት መብታቸው በሕግ የተረጋገጠ ቢሆንም አሁንም ችግሮች አሉ፡፡ የገዛ ወገናቸውን እንደ ባዕድ ወራሪ ኃይል የሚመለከቱና በጭካኔ የሚያፈናቅሉ፣ የአገር አንድነትና ኢትዮጵያዊ ማንነት ምንም የማይመስላቸው፣ ራሳቸውን በክልል ማንነት አጥረው ሰፋ አድርገው ማገናዘብ የቸገራቸው በአገርና በሕዝብ ላይ ጉዳት እያደረሱ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ በታሪኩ ዓይቶት የማያውቀው ጥላቻ በዚህ ዘመን ሲቀነቀን መስማት ያሳፍራል፡፡ ከልዩነት ይልቅ ለአንድነት ትልቅ ቦታ ሰጥቶ አገሩን ከአውሮፓ ቅኝ ገዥዎች በመከላከል ደማቅ ታሪክ ያለው አስተዋይና ጀግና ሕዝብ በበቀለባት ኢትዮጵያ፣ ሕዝብን በብሔርና በእምነት በመከፋፈል በርካታ ግፎች ተፈጽመዋል፡፡ አሁንም የገዛ ወገናቸውን የብሔሬ አባል አይደለህም በማለት ከኖረበት ቀዬ እየገደሉና እየዘረፉ የሚያፈናቅሉ አሉ፡፡ ለ21ኛው ክፍለ ዘመን የማይመጥን አሳፋሪ ድርጊት ሲፈጸም፣ ክልሎችን ከሚመሩ ጀምሮ እስከ ፌዴራል መንግሥት ድረስ እንዳላየና እንዳልሰማ ሲታለፍ ያስገርማል፡፡ ይህ ዓይነቱ የአውሬ ድርጊት ለታሪካዊቷ አገር ኢትዮጵያና ለአስተዋዮቹ ኢትዮጵያዊያን አይመጥንም፡፡

ሌላ ፈጣን ዕርምጃ የሚያስፈልገው ጉዳይ አለ፡፡ በሐምሌ ወር በሚጀምረው በአዲሱ በጀት ዓመት የነዳጅ ድጎማ እንደሚነሳ መንግሥት ማስታወቁ ይታወሳል፡፡ የሐምሌ ወር መግቢያ ሲቃረብ አጋጣሚውን በመጠቀም ትርፍ ለመዛቅ ያሰፈሰፉ ደግሞ፣ ነዳጅ በመደበቅና ከውጭ በመግባት ላይ የሚገኝ ነዳጅ ጉዞ በማስተጓጎል እጥረት ፈጥረዋል፡፡ በተለይ ናፍጣ በመደበቅ በአዲስ አበባና በተለያዩ የአገሪቱ ክልሎች ብዙዎችን ለሠልፍ ዳርገዋል፡፡ ናፍጣ እንደሚታወቀው የምግብ ምርቶችን፣ የግንባታ ቁሳቁሶችን፣ ለሕይወት አድን ዕርዳታ የሚያስፈልጉ መድኃኒቶችን፣ ለድንገተኛ አደጋዎች ምላሽ ለመስጠት፣ በአጠቃላይ ለሕዝብና ለተለያዩ ጭነቶች የትራንስፖርት አገልግሎቶችን ለማቀላጠፍ የሚረዳ ስትራቴጂካዊ ግብዓት ነው፡፡ ጥቂት አልጠግብ ባዮች በማናለብኝነት በሚሊዮኖች ሕይወት ላይ ሲቀልዱ መንግሥት ዝም ማለት የለበትም፡፡ የመንግሥት ሕግ የማስከበር አቅም የሚፈተነው በዚህ ጭምር ስለሆነ፣ ይህንን በግላጭ እየተፈጸመ ያለ ውንብድና አደብ ማስገዛት የግድ ይሆናል፡፡ መንግሥት አፍንጫ ሥር እንዲህ ዓይነቱ ወረበላነት ሲፈነጭ ማየት ያማል፡፡ ወረበላነትን ከመንግሥት ትልቅ ቢሮ ጀምሮ እስከ ታች ቀበሌ ድረስ በጋራ መታገል ይገባል፡፡ በአጠቃላይ ለህልውና ሲባል ለትልቁ ኢትዮጵያዊነት ምሥል ትኩረት ይደረግ!

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

የዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ባለሙያዎች ኮሚሽን ሪፖርት ምን ይዟል?

ለአሜሪካ ድምፅ አማርኛ ዝግጅት የስልክ አስተያየት የሰጡ አንድ የደንበጫ...

መንግሥት በአማራ ክልል ለወደሙ የአበባ እርሻዎች ድጋፍ እንዲያደርግ ተጠየቀ

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአማራ ክልል የተፈጠረው ግጭትና አለመረጋጋት በቢዝነስ...

አምናና ዘንድሮ!

እነሆ መስከረም ጠብቶ በአዲስ መንፈስ ተሞልተን መንገድ ጀምረናል። ‹‹አዲስ...

በሰጥቶ መቀበል መርህ መደራደርና ሰላም ማስፈን ለምን ያቅታል?

በያሲን ባህሩ አገር ግንባታ የትውልድን ትልቅና ታሪካዊ ኃላፊነት የሚጠይቅ ተግባር...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

የትምህርት ጥራት የሚረጋገጠው የፖለቲካ ጣልቃ ገብነት ሲወገድ ነው!

ወጣቶቻችን የክረምቱን ወቅት በእረፍት፣ በማጠናከሪያ ትምህርት፣ በበጎ ፈቃድ ሰብዓዊ አገልግሎትና በልዩ ልዩ ክንውኖች አሳልፈው ወደ ትምህርት ገበታቸው እየተመለሱ ነው፡፡ በአዲስ አበባ ከተማ ሰኞ መስከረም...

ዘመኑን የሚመጥን ሐሳብና ተግባር ላይ ይተኮር!

ኢትዮጵያ በአዲሱ ዓመት ዋዜማ ሁለት ታላላቅ ክስተቶች ተስተናግደውባት ነበር፡፡ አንደኛው የታላቁ ህዳሴ ግድብ አራተኛ የውኃ ሙሌት ሲሆን፣ ሁለተኛው ኢትዮ ቴሌኮም በአዲስ አበባ ከተማ ያስጀመረው...

ለሕዝብና ለአገር ክብር የማይመጥኑ ድርጊቶች ገለል ይደረጉ!

የአዲሱ ዓመት ጉዞ በቀናት ዕርምጃ ሲጀመር የሕዝብና የአገር ጉዳይን በየቀኑ ማስታወስ ግድ ይላል፡፡ በአሁኑ ጊዜ ለኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም፣ ዴሞክራሲ፣ ልማትና ዕድገት ያስፈልጋሉ ከሚባሉ ግብዓቶች...