Monday, September 26, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -
  ማኅበራዊየማሰቃየት ተግባር ሰለባዎች ሲታሰቡ

  የማሰቃየት ተግባር ሰለባዎች ሲታሰቡ

  ቀን:

  በዓለም አቀፍ ደረጃ የተጠረጠሩ ግለሰቦች ወንጀል መፈጸማቸው እንዲያምኑ ብዙ የማወጣጫ ዘዴዎች ይተገብራቸዋል፡፡ በአብዛኛዎቹ ላይ ከፍተኛ ሥነ ልቦናና አካላዊ ጉዳት እንደሚያሳድርባቸው መረጃዎች ያመላክታሉ፡፡

  በኢትዮጵያ በርካታ የወንጀል ማወጣጫ ዘዴዎች እንደሚተገበሩ ይገለጻል፡፡ በቀደሙት ዘመናት  ወንጀለኛን የሚያስገኝ ተብሎ የሚታመንበት ‹‹ሌባ ሻይ›› የሚባል ዘዴ ይተገበር እንደነበር ታሪክ ያስረዳል፡፡

  ‹‹ሌባ ሻይ›› የሌባ መጠቆሚያ ዘዴ ነው፡፡ ከቅጠል የተዘጋጀ መድኃኒት አንድን ወጣት  በማጋት/ማሽተት ከተሰበሰበው ሰው መካከል ሌባውን እንዲጠቁም የሚደረግበት ዘዴ እንደነበር ይታወቃል፡፡ የዚህ የሌባ አሰሳ ትክክለኛነት ባይኖረውም ብዙዎች ሲጠቀሙበት እንደነበር በታሪክ ተቀምጧል፡፡

  ዘመናዊ ተብሎ በሚታሰበው የመንግሥት አስተዳደር ደግሞ በወንጀል የተጠረጠሩ ሰዎች ላይ መረጃ የማውጣጫ ልዩ ልዩ ዘዴዎች በየሥርዓቱ ይተገበራሉ፡፡ ይሁን እንጂ ከሥርዓታዊው መንገድ ባለፈና ባፈነገጠ መልኩ ኢሰብዓዊ ድርጊቶች ከዛቻና ማስፈራሪያ በዘለለ በተለያዩ መንገዶች ድብደባ መፈጸማቸው አልቀረም፡፡

  በሥራ ላይ ያለው የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት በአንቀጽ 18 ኢሰብአዊ አያያዝ ስለመከልከሉ በሚል ንዑስ ርዕስ ሥር ማንኛውም ሰው ጭካኔ ከተሞላበት፣ ኢሰብዓዊ ከሆነ ወይም ክብሩን ከሚያዋርድ አያያዝ ወይም ቅጣት የመጠበቅ መብት አለው ሲል፣ በአንቀጽ 19 ደግሞ የተያዙ ሰዎች መብት በሚለው ሥር ደግሞ በአምስተኛው ረድፍ የተያዙ ሰዎች በራሳቸው ላይ በማስረጃነት ሊቀርብ የሚችል የእምነት ቃል እንዲሰጡ ወይም ማናቸውንም ማስረጃ እንዲያምኑ አይገደዱም። በማስገደድ የተገኘ ማስረጃ ተቀባይነት አይኖረውም ይላል፡፡

  በዓለም አቀፍ ደረጃም ስምምነቶች እንዳሉ ይታወቃል፡፡ የተባበሩት መንግሥታት ጠቅላላ ጉባዔ  ሰኔ 19ን (ጁን 26)  የማሰቃየት ተግባር ሰለባ የሆኑ ተጎጂዎችን የመደገፍ ዓለም አቀፍ ቀን እንዲሆን ባወጀው መሠረት በተለያዩ አገሮች በተለያዩ ዝግጅቶች ሲከበር ቆይቷል፡፡ 

  የማሰቃየት ተግባር ሰለባ የሆኑ ተጎጂዎችን የመደገፍ የዓለም አቀፍ ቀንን አስመልክቶ የኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን (ኢሰመኮ)  ሰኔ 21 ቀን 2014 ዓ.ም. ባዘጋጀው ዓውደ ጥናት  የተለያዩ ባለድርሻ አካላት፣ መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ የሲቪክ ማኅበራት እንዲሁም የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተሳትፈውበታል፡፡

  በመድረኩ እንደተገለጸው የማሰቃየት፣ ኢሰብዓዊ ከሆነ ወይም ክብሩን ከሚያዋርድ አያያዝ ወይም ቅጣት ድርጊት የሚከለክል ጠንካራ ዓለም አቀፍ ተቋማትና የሕግ ማዕቀፍ ቢኖርም ሰዎች ለዚህ ዓይነት ድርጊት ሰለባ ሲሆኑ ይታያል፡፡

  በሰሜን ኢትዮጵያ ከተካሄደው ጦርነት ጋር ተያይዞ ኢሰመኮ ባወጣቸው ሪፖርቶች እንደተመለከተው በጦርነቱ ዓውድ በሲቪል ሰዎች እንዲሁም በተሳታፊ ወገኖች አባላት ላይ የጭካኔና የማሰቃየት ተግባር የተሞላበት ጥቃት እንደደረሰባቸው ተመላክቷል፡፡

  በመድረኩም በዝግጅቱ ሰለባ ለሆኑ ተጎጂዎች ፍትሐዊና በቂ የሆነ ካሳ የማግኘት መብት እንዳላቸው፣ መንግሥት ይሄንን መብት የማስጠበቅ ግዴታ እንዳለበትና የድርጊቱ ሰለባ ተጎጂዎቹ ብቻ ሳይሆኑ ተጽዕኖው በቤተሰቦቻቸውና በማኅበረሰቡም ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ እንደሚያሳርፍ ተገልጿል።

  በዕለቱ ለውይይት መነሻ ጽሑፍ ያቀረቡት በተባበሩት መንግሥታት ውስጥ ለስቃይ ሰለባዎች ድጋፍ ለማድረግ የቆመው ተቋም (UN Voluntary Fund for Victims of Torture) የባለ አደራ ቦርድ ሰብሳቢው ሎረንስ ሙሩጉ ሙቴ ናቸው፡፡

  የቦርድ ሰብሳቢው ከዓለም አቀፍ መስፈርቶች አንፃር በመነሳት ጭካኔ የተሞላበት ኢሰብዓዊ ድርጊት ተጎጂ የሆኑት ፍትሕዊና በቂ ካሳ አግኝተው በተቻለ መጠን ከጉዳቱ ሙሉ በሙሉ የሚያገግሙበትን ሁኔታ የሚፈጥር ሕጋዊ ሥርዓት መዘርጋት ያስፈልጋል ብለዋል፡፡

  የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ወ/ሮ ራኬብ መሰለ እንደተናገሩት፣ የማሰቃየት ተግባር ሰለባ መሆን፣ ከግለሰቦች በተጨማሪ ለቤተሰብና ለአገር ጠንቅ ነው፡፡

  የማሰቃየት ተግባሮች ከታሪክ የሚወረሱ ድርጊቶች መሆናቸውን፣ እንደ ሥልታዊ መንገድ እንደ ተወሰዱ፣ የሕግ አስከባሪዎችም እንደሚጠቀሙት ገልጸዋል፡፡ የነበረውና አሁን ያለውን አሠራር በግንዛቤና በትምህርት ማስቀረት እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡

  በተለይም የሕግ አካላት ቃል ለመውሰድም በኃይልና በማሰቃየት ሳይሆን ሌሎች መንገዶች በመጠቀም ማስቀረት እንደሚችሉ ገልጸዋል፡፡

  የማሰቃየት ተግባር በሠለጠኑ በሚባሉ አገሮችም የሚፈጸም መሆኑን የገለጹት ወ/ሮ ራኬብ፣ ሙሉ በሙሉ ማስቀረት ባይቻል እንኳን በተወሰነ መልኩ መቀነስ እንደሚቻል አመልክተዋል፡፡ አሁን ላይ በምርመራ ክፍሎች ካሜራ በማድረግ፣ ባለሙያው ኃይልና የማሰቃየት ተግባር እንዳይጠቀም ለማድረግ እንደሚቻል ተናግረዋል፡፡

  ኢሰመኮና የተመድ አካል በሠሩት ጥናት በሰሜኑ የአገሪቱ አካባቢዎች ብዙ የማሰቃየት ተግባሮች መታየታቸውን፣ በተለይም የግጭት ቀጣናዎች ላይ የሚደረጉ የማሰቃየት ተግባሮች በፖለቲካ መፍትሔ የሚስተካከሉ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

  ኢትዮጵያ በተባበሩት መንግሥታት የወጣውን ሕግ ካፀደቁት አገሮች አንዷ መሆኗን የጠቀሱት፣ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን የሲቪልና ፖለቲካ መብቶች ኮሚሽነር አብዲ ጂብሪል (ዶ/ር)፣  በሕገ መንግሥቱ አንቀፅ 18 የማሰቃየት ድርጊትን የሚከለክል መሆኑን፣ በኢትዮጵያ ወንጀል ሕግ የማሰቃየት ተግባር የሚፈጽሙ የመንግሥት አካላት በወንጀል ተጠያቂ እንደሚሆኑ ይገልጻል ብለዋል፡፡

  በዓውደ ጥናቱ ማጠቃለያ ላይ የአገር ውስጥና የውጭ ግብረ ሠናይ ድርጅቶች የማሰቃየት ተግባር ሰለባ የሆኑ ወገኖችን በሥነ ልቦና እና በልዩ ልዩ መንገዶች እንዲያግዙ ጥሪ ቀርቦላቸዋል፡፡

  የሰኔ 19ን (ጁን 26)  የማሰቃየት ተግባር ሰለባ የሆኑ ተጎጂዎችን የመደገፍ ዓለም አቀፍ ቀን አስመልክቶ በዓውደ ጥናቱ ማብቂያ ላይ የማሰቃየት ተግባር ሰለባ የሆኑ ተጎጂዎችን የሚደርስባቸውን አካላዊና ሥነልቦናዊ ጉዳት የሚያሳይ አጭር ታዋቂና አንጋፋ ከያንያን የተሳተፉበት ‹‹ሰማይ›› የተሰኘ ፊልም ለስብሰባው ተሳታፊዎች  ቀርቧል፡፡

   በተጨማሪም የጭካኔ ተግባራት ላይ ያተኮረና ለቀናት የሚቆይ የሥዕል ዓውደ ርዕይ በኢሰመኮ ዋና መሥሪያ ቤት መግቢያ  ለዕይታ በቅቷል፡፡

  - Advertisement -

  ይመዝገቡ

  spot_img
  spot_img

  ተዛማጅ ጽሑፎች
  ተዛማጅ

  በኢትዮጵያ ላይ የቀጠለው የምዕራባውያን ጣልቃ ገብነት

  ምዕራባውያን አገሮች በኢትዮጵያ ላይ ጠንካራ ጫና ማሳደራቸውን ቀጥለዋል፡፡ በዲፕሎማሲም...

  የመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች የድጎማ በጀት ለፖለቲካ ሥራ ማስፈጸሚያ እንደሚውል የሚያሳይ ሪፖርት ቀረበ

  ለመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች የሚደረግ የበጀት ድጎማ ከመደበኛው ሥራ ይልቅ ከዋናው...

  መንግሥት የሥራ ግብር ምጣኔን እንዲቀንስ ተጠየቀ

  የኢትዮጵያ ሠራተኛ ማኅበራት ኮንፌዴሬሽን (ኢሠማኮ) መንግሥት የሠራተኛውን የኑሮ ጫና...

  የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የአመራሮች ምርጫና ቀጣይ ዕቅዶቹ

  የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ሲጠበቅ የነበረውን...