Monday, December 4, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ልናገርፅንፈኝነት እንዴት ይፈጠራል? ማርከሻውስ ምንድነው? (ክፍል ሁለት)

ፅንፈኝነት እንዴት ይፈጠራል? ማርከሻውስ ምንድነው? (ክፍል ሁለት)

ቀን:

በያሬድ ኃይለ መስቀል

በክፍል አንድ እንደገጽኩት ለእኔ ‹‹ፅንፈኝነት በአጭሩ ሲታይ ከምክንያታዊነትን ሙሉ ለሙሉ የፀዳ፣ በስሜታዊ አዕምሮ ብቻ የሚመራ፣ የራሱን ስሜት እንደ መጨረሻው እውነትና መንገድ የሚወስድና ይህንን በሁሉም ላይ ለመጫን ኃይልን የሚጠቀም ማለት ነው፤›› ፅንፈኝነት ምክንያታዊነት ሳይሆን እምነት ነው ካልን፣ ይህ ፅንፈኝነት እንዴት ይፈጠራል? ፅንፈኝነት በአንድ ቀን የሚፈጠር አይደለም፡፡

ፕሮፌሰር ካሲም አንድ ሰው ፅንፈኛ ለመሆን የብዙ ዓመት የተበዳይነት፣ የተገፊነትና የበታችነት ስሜት ሊሰበከው ይገባል፡፡ በዚህም ቁጭት ውስጡ መቃጠል አለበት፡፡ ይህ ራዲካላይዜሽን የሚባለው ነው ይላሉ፡፡

‹‹ራዲካላይዜሽን›› በፖለቲከኞች ጊዚያዊ ጥቅም ላይ ተመሥርቶ የበታችነት ስሜት በመፍጠር ቁጭት፣ በቀል በመመገብ ፍፁም የማያመዛዝን ጨካኝና አስፈሪ ደጋፊ የመፍጠር የረዥም ጊዜ ፕሮጀክት ነው፡፡ ማመዛዘን የማይችል፣ ከምክንያታዊነት የፀዳና ትልቁን ጭካኔ ፈጽም ሲባል የሚፈጽም፣ ፍፁም ህሊናውን የሳተ ታዛዥ ኃይል መፍጠርና ይኼንን እንደ ተናካሽ ውሻ እያሳዩ ወደ ሥልጣን መውጣት፣ ወይም  ሥልጣን ላይ የመቆየት ፕሮጀክት ውጤት ነው፡፡

ናዚዎች አስፈሪ ኤስኤስ (SS) የሚባል ኃይል ነበራቸው፡፡ የሞሶሎኒ አስፈሪ ጥቁር ሸሚዝ ለባሽ የሚባለው ፅንፈኛ ፈጥሮ ነበር፡፡ ኮሎኔል መንግሥቱ አብዮት ጠባቂ የሚባል ነበራቸው፣ ሕወሓት በድርጅት ውስጥ ድርጅት ያደረገው ባዶ ስድስት ከቶ የሚያሰቃይ የደኅንነት ኃይል ነበረው፡፡

ይህንን ፍፁም ታዛዥና ተናካሽ ኃይል ምንም ዓይነት ምክንያታዊነትን አይቀበልም፡፡ በራስም ማሰብ የተከለከለ ነው፡፡ ዛሬም የኦፒዲኦና የኦነግ ማስፈራሪያ ኦነግ ሸኔ የሚባለው የተለየ የሚመስል ኃይል ነው፡፡ እኛን ካልሰማህና ካልተቀበልክ ኦነግ ሸኔ ያርድሃል ብሎ ማስፈራሪያ ነው፡፡

የሕወሓት ምክንያታዊነትንና በራስ ማሰብን ለማጥፋት መጀመርያ ያደረገው ድርጅቱን በከብት እረኛና በገበሬ ማጥለቅለቅ ነበር፡፡ ከዚያ ገበሬውን ፊደል በቆጠረው ላይ ማንገሥ ነበር፡፡ በአጭሩ መማርና ማሰብን ዋጋ ማሳጣት ነበር፡፡ ከዚያ ገበሬውን በተጠቂነትና የበታችነት ስሜትና ሥነ ልቦና እንዲቃጠል ካረገ በኋላ አባቶች የሞቱላትን ኢትዮጵያ ‹‹ለእኔ ምኔ ናት›› እንዲል ማብቃት ነበር፡፡ ይህ ጉዞ በአማርኛ ስም ያጣሁለት ‹‹ራዲካላይዜሽን›› የሚባለው ነው፡፡ ሰው ራሱን እስኪጠላ ድረስ የበታች እንደሆነና ዋጋ እንደሌለው የሚለውን ስሜትና ቁጭት መፍጠር ነው፡፡ ከዚያ ኤርትራ ትገንጠል፣ ወደብ ምን ያደርጋል? አማራ ጠላትህ ነው የሚለው የረዥም ጊዜ የወሰደ ፕሮጀክት ነበር፡፡ ከዚያ ናዚዎቹ ‹‹ይሁዳዊ ደም ከተገኘብን ወደ እሳት ጣሉን›› እንዳሉት ለእኔና ለእኛ ያልሆነች ኢትዮጵያ ትበታተን የሚል ፅንፍ ማስያዝ ነው፡፡ አልታዘዝ ያለና በራሱ ሊያስብ የሞከረ ደግሞ እኔን ያየ ይቀጣ እስኪል ባዶ ስድስት ተልኮ ይቀጠቀጣል፡፡

የትግራይ ገዥ መደብ በመላው ኢትዮጵያ ‹‹ገዥ፣ ጨቋኝና አስገባሪ›› ሆኖ ለዓመታት የቆየና ለበጎውም ሆነ ለክፉውም ተካፋይ ነበር፡፡ ይሁንና የኢትዮጵያን ባንዲራና ታሪክ ሕዝብ አያሳየኝ የሚል ፅንፈኛ ትውልድ ሕወሓት መፍጠር የቻለው በረዥም ጊዜ ‹‹ራዲካላይዜሽን›› ጥረት ነው፡፡ ትናንት ኤርትራን ለማስገንጠል በናቅፋ ምሽግ ላይ ሂድ ሲባል፣ እንዴ ዶጋሊ ላይ አይደለም እንዴ አሉላ የተዋደቀበት እንዳይል፣ አስመራ እኮ ጣሊያን ሳይሆን አሉላ የቆረቆረው ከተማ አይደለም እንዴ ብሎ የማይጠይቅ መንጋ መፍጠር ነበር፡፡ ዛሬ ደግሞ የባህር በር እናስመልሳለን ሲባል ትናንት ምን ብላችሁን ነበር? ብሎ የማይጠይቅ ከፕሮፌሰር እስከ እረኛ ያለ ከምክንያታዊነት የፀዳ ፅንፈኛ ኃይል ፈጠረ፡፡

ስለዚህ ፅንፈኝነት ዱብ ብሎ የሚወለድ ሳይሆን፣ ትውልድ የሚፈጅ የበታችነትና የበቀል ቅስቀሳ ውጤት ነው፡፡ ሕወሓትና ኦፒዲኦ በጥምር የኦሮሞ ወጣት ከሌላው ጋር ከቆመ ለከፋፍለህ ግዛ አይመችም ብሎ በማሰብ፣ ‹‹ራዲካላይዜሽን›› እንደ አንዱ በሥልጣን መቆያ መንገድ ተጠቅመውበት ነበር፡፡

ክልል የእኛና የእነሱ በሚል ‹‹ራዲካላይዜሽን›› (ቅስቀሳ) ያደረገው ወጣት በመጨረሻው ‹‹ነፍጠኛ›› የተባለው ጠላት ብቻ ሳይሆን፣ ነፃ አወጣሁህና በቋንቋህ እንድትናገር አደረግኩህ ያለውን ሳይቀር ፋብሪካውንና እርሻውን ላይ እሳት ለቀቀበት፡፡ ከሥልጣንም ከከተማም ነቅሎ በወታደር ካምፕ ውስጥ አሰረው፡፡

ይህ አክራሪነት የበታችነት፣ የተጠቂነትና የመዋረድ ትርክት በትምህርት ቤት፣ በሚዲያ፣ በሕገ መንግሥት ታግዞ፣ በተረት፣ በልብ ወለድ፣ በሥልጠና የተሰጠና ለአንድ ትውልድ ተመግቦ ከሰብዓዊነቱ በላይ በልዩነቱ ላይ እንዲያተኩር በመደረጉ ነው፡፡

ፅንፈኞች ከሌላ ዓለም የመጡ አረመኔዎች ወይም ልዩ ፍጡሮች ሳይሆኑ፣ ፖለቲከኞች ለፖለቲካ ትርፍ ብለው በቁጭት ባህር ውስጥ ያጠመቋቸው ከምክንያታዊነትና ከዕውቀት የፀዱ ወጣቶች ማለት ነው፡፡

ፅንፈኝነት የት ያብባል? ያፈራል? እንደ ፕሮፌሰር ካሲም የፅንፈኝነት ዕድገቱ በአምባገነን ሥርዓት ውስጥ ነው፡፡ አምባገነን አገር ማለት የአንድ ትርክት አገር ማለት ነው፡፡ ፅንፈኝነት በአምባገነን ሥርዓት ውስጥ ነው ጉልበት የሚያገኘው፡፡ ምክንያቱም በራዲካላይዜሽኑ ጊዜ ለፅንፈኝነት የታጨውን ወጣት የተሰጠውን የተሳሳተ ትርክት የሚሞግት መረጃ እንጂ ነገር አይፈለግም፡፡

በሶሻሊዝም ጊዜ የሰው ልጅ ዕድገት በመሰላል ዓይነት ነበር የተደረደረው፡፡ የጋርዮሽ፣ የባርያ አሳዳሪ፣ የፊውዳል፣ የካፒታሊስት ወይም በአብዮታዊ ዴሞክራሲ ሶሻሊዝም ገንብቶ ከዚያ ሰው ሁሉ ወደ ኮሙዩኒዝም የሚባል ገነት ይገባል የሚል ነበር፡፡ ይህንን ጥንቆላ የሚመስል ሐሳብ ማርክስ አለው ከተባለ እንደ እግዚአብሔር ቃል ነበር የሚቆጠረው፡፡

አንድ የብአዴን አባል የሆነ ሰው ያጫወተኝን እውነተኛ ታሪክ ላካፍላችሁ፡፡ አቶ ህላዌ ዮሴፍ በትግሉ ጊዜ የብአዴንን ታጋዮችንና ገበሬዎችንን ሰብስቦ ስለኮሙዩኒዝም ያስተምራል፡፡ በኮሙዩኒዝም ሥርዓት ሁሉም እንደ ችሎታው የሚሠራበት፣ ሁሉም እንደ ፍላጎቱ የሚያገኝበት ሥርዓት ነው፡፡ በኮሙዩኒዝም ሥርዓት ሰው የግል ንብረት የለውም፡፡ አንዱ መኪናውን ነድቶ ጉዳዩ ጋ ሲደርስ፣ ሌላ ሰው እንዲጠቀምበት ቁልፏን መኪናው ውስጥ ትቶት ነው የሚሄደው፡፡ ስትደርስ አስነስተህ ወደ ጉዳይህ መንዳት ነው፡፡ የልብስ ሱቅ ገብተህ ምንም ሳትከፍል የፈለግከውን ለብሰህ ትወጣለህ፡፡ ሆቴል ቤት ገብተህ የፈለግከውን በልተህ ምንም ሳትከፍል ትወጣለህ፡፡ በባዶ ሆዳቸው የተሰበሰቡትን ገበሬዎችና ታጋዮች ምራቅ ያስውጣል፡፡

ከዚያ የጥያቄ ሰዓት ሲደርስ አንዱ ታጋይ እጁን ያወጣና ጓድ ህላዌ እርስዎ ከዚህ ከኮሙዩኒስት አገር መጥተው ነው የሚያስተምሩን? ወይስ ከእኛው ጋር ሆነው ነው ሄደው የሚያዩት? ብሎ ጠየቀው፡፡ ለተራቡ ገበሬዎች መኪናው ይቅርና በነፃ ሆቴል ተገብቶ እስኪጠግቡ የሚበላበት ዓለም ምን ያህል አጓጊ እንደሆነ መገመት አይከብድም፡፡ ጓድ ህላዌ ምኞትና እውነተኛው ዓለም ተቀላቅሎበት በህልም ዓለም ሆዳቸውን ማስጮህ እንጂ መልስ አልነበረውም፡፡

የሚገርመው ገበሬው ሳይሆን ኮሙዩኒዝም የሚባል ዓለም ባይኖርስ? ብሎ የጠየቀም፣ የተማረም አልነበረም፡፡ ቢጠይቅም እንደ ፀረ አብዮተኛ ተቆጥሮ ‹‹ኮሙዩኒዝም አለ እስከሚል›› ይቀጠቀጥ ነበር፡፡ እንዲህ ዓይነት ድንቁርና የሚተረክበትና ኮሙዩኒስት አገር ገብቶ እስኪጠግብ የፈለገውን ለመብላት ብዙ ገበሬ በባዶ ሆዱ አገሩን ወጋ፡፡

ማርክስ እንደ ጠነቆለው ወደ ኮሙዩኒዝም መግባቱ ቀርቶ አሻጋሪው ሶሻሊዝምም ተደመሰሰ፡፡ ዓለም የወዝ አደሮች መሆኗ ቀረና ድኅረ ኢንዱስትሪያል (Post industrial Society) ማኅበረሰብ ተፈጠረ፡፡ በካፒታሊስቱ ዓለም ጭራሽ የወዝ አደሩ ቁጥር እየቀነሰ፣ የዕውቀት ሠሪው እየጨመረ፣ ወዝ አደርነት ራሱ የሚጠፋ ማሽንና ሮቦት የሚተካው ሆነ፡፡ ማርክስ በ1850ዎቹ ያለውን የኢንዱስትሪ ዕድገት ተመልክቶ፣ ኢንዱስትሪ እየተስፋፋ የወዝ አደሩ ቁጥር ይጨምራል፡፡ ከዚያም ዓለም የወዝ አደሮች ትሆናለች ብሎ ጠነቆለ፡፡ ማርክስ በ21ኛው ክፍለ ዘመን ተወልዶ ቢሆን ኖሮ ደግሞ፣ ዓለም የሮቦቶችና የአርተፊሻል ኢንተለጀንስ ትሆናለች ይል ይሆናል፡፡ የሚገርመው ማርክስም ኤንግልስም የኢኮኖሚ ፍልስፍና ግምት ጻፉ እንጂ፣ ‹‹የእግዚአብሔር ቃል ነው›› አላሉም ነበር፡፡ ግፋ ቢል የራሱን የማይነበብ ጽሑፍ ሳይንሳዊ ከማለትና ማንቆለጳጰስ አላለፈም፡፡ ይሁንና የርዕዮት ፅንፈኞች ግን የማርክስን ቃል እንደ እውነት መንገድ ቆጥረው፣ ይህንን ቃል የተጠራጠረውን ሁሉ ፈጁ፡፡

ስለዚህ አንድ ትርክት ብቻ በሚነገር አገር የርዕዮተ ዓለም አብዮታዊ ፅንፈኞች ተፈጥረው ተጨራረሱ፡፡ አርበኞችን ማርክስ ስላለ ረሸኑ፣ አባቶቻቸውን ገረፉ፣ ቤተ መቅደስንና መስጊድን አረከሱ፡፡ በድንቁርናቸው ታብየው፣ አንድ ትርክት አምነው፣ ኢትዮጵያን ከፈፍለው፣ የባህር በሯን አስቀምተው እነሱም ፈረጠጡ፡፡

ከዚያም ተከትሎ የመጣው የብሔር ጥያቄ አቀንቃኞች ስታሊንን ሳያነቡ እንደ እግዚአብሔር ቃል ወሰዱ፡፡ የሚገርመው ነገር ስታሊን ‹‹የብሔር ጥያቄ›› የሚለውን ጥንብ እርኩሱን አውጥቶ የብሔር ጥያቄ እንደ ኮሌራ ወረርሽኝ ነው፣ አብዮተኞች በዓለም አቀፋዊ ወዝ አደርነት ሊያወድሙት ይገባል ብሎ በብሔርተኞች ላይ ጦር ያወጀበትን ጽሑፍ በሩሲያኛም ሆነ በጀርመንኛ፣ ወይም በእንግሊዝኛ ትርጓሜ ሳያነቡ እንደ እውነት ቆጥረው እነ አቶ መለስ፣ እነ አቶ ሌንጮና እነ ዋለልኝ በስማ በለው የሰሙትን ይዘው አበዱ፡፡ ከዚህ የስማ በለው ትርክት ውጪ የሚቀርበውን ሁሉ ፀረ ብሔረሰቦች፣ ብሔር ጠሎች፣ ትምክህተኞች፣ ፀረ ሕገ መንግሥት፣ ፀረ ሕዝብና ትምክህተኛ እያሉ ፈጅተው የአንድ ትርክት አገር ፈጠሩ፡፡

ከድንቁርናቸው ጥልቀት የተነሳ ዛሬም ወደ ላይ ወጥተው ስታሊንን በጎግል ፈልገው ለማንበብ ፈቃደኛ አይደሉም፡፡ በዚህም ምክንያት ስታሊን እንዳለው በብሔር ወረርሽኝ የተለከፉ ፅንፈኝነት ፈጠሩ፡፡ እነዚህ የፈጠሩት ፅንፈኝነት፣ ‹‹በእኔ ክልል ምን ትሠራለህ?›› እያሉ ያቋቋሙት ፋብሪካና እርሻ ላይ እሳት እየለኮሱ ወደ መቀሌ አባረሯቸው፡፡ እባካችሁ የብሔር መለያን በመታወቂያ ላይ አትጻፉ፣ ከሩዋንዳ ተማሩ ሲባሉ እንቢ አሉ፡፡ ባይሆን እንኳን አይጻፍብኝ የሚለውን ሰው አታስገደዱ ሲባሉ ብሔሩን መናገር የማይፈልገው ዲቃላው ነው፣ አማራው ነው፣ ስለዚህ በእኔ መቃብር ላይ ብለው ጻፉ፡፡ በመጨረሻው የእነሱ መታወቂያ እየታየ ከሥራ ታገዱ፣ ከአውሮፕላን ጣቢያ እንዳይወጡ ተደረጉ፣ ሀብታሞቹና ወታደራዊ ትምህርት ያላቸው ደግሞ ያለ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ በታጠቅ ጦር ሠፈር፣ በአዋሽ፣ በብላቴና በየፖሊስ ጣቢያው ተለቅመው ታሰሩ፡፡

አማራጭን አለማየት የሚፈጥረው ድንቁርና የሚሰጠው ጭፍን ድፍረት ብቻ ነው፡፡ ፅንፈኛ ሰው አማራጭ ሐተታ መስማት አይፈልግም፡፡ መማር የሚችለው ከሌሎች ሳይሆን ከውድቀቱ ብቻ ነው፡፡  ዛሬም ይህ በድንቁርና የተሞላ አውቃለሁ ባይነት ተጠናክሮ ቀጥሏል፡፡ ይኼው ከሃምሳ ዓመታት በኋላ ስታሊን የጻፈውን መጽሐፍ እንኳን ላንብብና እውነቱን ልረዳ የሚል የለም፡፡ ዛሬም ስታሊን እንዳለው የሚሉ የብሔር አቀንቃኞች አሉ፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ፣ ‹‹ዕውር ዕውርን ቢመራው ተያይዘው ገደል ይገባሉ›› እንደሚለው ነው፡፡ ስታሊን የጻፈውን ሳያነቡ፣ ዋለልኝ ያልጻፈውን ወይም ጻፍኩት ያላለውን ጽሑፍ ዋለልኝ ስለብሔር የጻፈው እያሉ ዛሬም ብዙ ደፋሮች ይሰማሉ፡፡ ዋለልኝ ፈረንጅ ጽፎ የሰጠውን ነው ያነበበው፡፡ የብሔር ጥያቄ ደጋፊ አልነበረም፡፡

ስለዚህ ፕሮፌሰር ካሲም ፅንፈኝነት የሚፋፋውና የሚጎለብተው የገደል ማሚቱ አዳራሽ (Eco Chamber or Epistemic Bubble) ውስጥ ነው የሚለው እውነት ነው፡፡ አንድ ነገር ብቻ እንዲሰማ በተፈረደበት ማኅበረሰብ ውስጥ ነው ፅንፈኝነት የሚያድገው ይላል፡፡ ለዚህ ነው ዛሬ ኢትዮጵያ ማሰብና ማመዛዘን በማይችሉ፣ ለራሳቸው የሚጠቅማቸውን እንኳን ለማዳመጥ የማይፈልጉ፣ በድንቁርናቸው ናላቸው የዞረ ፅንፈኞች አገር የሆነችው፡፡ ያው እንደ ሩዋንዳ ሰው ጨርሰው፣ በመጨረሻ ተሸንፈው ለልጅ ልጆቻቸው የሚተርፍ ኃፍረት እስከሚጎናፀፉ ደረስ ከፅንፈኝነት አስተሳሰባቸው አይላቀቁም፡፡

የሚገርመው እንደ ጋሪ ፈረስ ሕዝብን ለመጋለብ የሚፈጠሩ ፕሮጀክቶች፣ በመጨረሻው ለጋላቢዎችም አጥፊ ሆነው ይገኛሉ፡፡ እንዴት ‹‹ራዲካላይዜሽን››ን መዋጋት ይቻላል?

‹‹ራዲካላይዜሽን›› ፅንፈኞችን የማስፈልፈያ መንገድ ነው እንጂ፣ በራሱ ፅንፈኛ አይደለም፡፡ ስለዚህ መንገዱንና መዳረሻውን መለየት አለብን፡፡ ‹‹ራዲካላይዜሽን››ን ማስቆም ይቻላል ፅንፈኝነት ግን ከመዋጋት ውጪ መፍትሔ የለውም፡፡

ፅንፈኝነትን ማስቆም የሚቻለው ‹‹ራዲካላይዜሽን›› የተባለው የአዕምሮ አጠባ ላይ ጣልቃ በመግባት ብቻ ነው፡፡ የአዕምሮ አጠባ ደግሞ በብዙ አገሮች የመንግሥት ፕሮጀክት ነው፡፡

ካሲም ‹‹Eco-Chamber Of Epistemic Bubble›› የገደል ማሚቱ እልፍኝ ማፍረስና በሩንና መስኮቱን በመክፈት ለወጣቶች የተለያየ ዜማ እንዲሰሙ ማድረግ ነው፡፡ አማራ ነኝ፣ ኦሮሞ ነኝ ሲል፣ ‹‹ለምን ሆንክ? እስኪ ንገረኝ?›› እያሉ ምክንያታዊነትን እንዲያጎለብት እንጂ፣ እንደ ህላዌ ዮሴፍ ያለውን ተረት አድምጦ እንዲያምን አለማድረግ ነው፡፡ የተለያዩ መጻሕፍት እንዲያነቡ፣ በተለይ ደግሞ የእነሱን እምነትን የሚሞግት ሐሳን በካድሬዎች ሳይሆን ነገሩ በገባቸው ሰዎች እንዲነገራቸው ማድረግ ነው፡፡ ሰዎች የራሳቸው ገደል ማሚቱ ብቻ እንጂ የሌሎችን ድምፅ እንዳይሰሙ ሲገደዱ ፅንፈኛ ይሆናሉ፡፡

የተለያየ ሐሳብ በማይገለጥባትና የአንተ ትርክት ትክክል አይደለም ይኼንን መረጃ ተመልከት በማይባልባትና የሐሳብ ነፃነት ባልተፈቀደባት አገር ፅንፈኝነት በቀላሉ ይፈጠራል፡፡ መንግሥት እኔ ብቻ፣ ለእኔ ብቻ፣ ይኼንን ካልተቀበልክ አወድምሃለሁ ካለ መንግሥትም፣ ሕዝብም ፅንፈኞች ይሆኑና በመጨረሻው ፅንፈኛ ሕዝብ ፅንፈኛን መንግሥት ያጠፋና ሌላ ፅንፈኛ ያነግሣል፡፡

ስለዚህ ፅንፈኝነት የባህል ጨዋታ እስከሚመስል ድረስ ነግሧል፡፡ የባህል ጨዋታችን ፈረስ ጉግስ፣ ትግልና ሩጫ መሆኑ ቀርቶ መተራረድ፣ ሰው ሲገደል፣ ሲታረድ፣ በቦምብ ሲበጣጠስ ወይም በእሳት ሲንጨረጨር በቪዲዮ ቀርፆ ማሳየት ሆነ፡፡

ለዚህ ነው ፅንፈኛነታችንን በካሲም በተሰጡት ሦስት መመዘኛዎች መመርመር ያስፈልጋል፡፡ ርዕዮታችንን ካልተቀበሉን እናጠፋቸዋለን የሚል ስሜት በውስጣችን ካለ ፅንፈኞች ነን፡፡

እንዲህ የሚያስቡትን፣ ይህንን የሚመስሉትን ማውደም፣ ማቃጠል፣ ማፈንዳት፣ መጨፍጨፍ ነው የሚል የጭካኔ ስሜት በልባችን ካለ ፅንፈኞች ነን፡፡ መንግሥትም ሆንን ተቃዋሚ ይህ ሐሳብ በልባችን ከመጣ እኛም ፅንፈኞች ነንና ራሳችንን ከጥላቻ ስሜታችን ማፅዳት አለብን፡፡ በሐሳብና በምክንያታዊነት፣ በመረጃ ማሸነፍ እንችላለን ብለን ማሰብ ካልቻልንና በካራ ብቻ ነው ችግራችንን የምንፈታው ካልን ፅንፈኞች ነን፡፡

የእኛ ፖለቲካ፣ የእኛ ቋንቋ፣ የእኛ ብሔር፣ የእኛ ሃይማኖት ብቻ ያለባት ገነት መፍጠር እንችላለን ብለን ካሰብን እኛም ፅንፈኞች ነን፡፡ የተቀላቀለ ዲቃላ ነው የሚል እምነት በውስጣችን ካለ ዕድሉን አላገኘነውም እንጂ እኛም ፅንፈኞች ነን፡፡

ስለዚህ በሁለት ፅንፈኞች መካከል ወርቃማ አማካይ መፈለግ ሞኝነት ነው፡፡ ፅንፈኝነት በእኛ ውስጥ ያለ ምክንያታዊነት ማጣት እንጂ፣ የሁለት ፅንፈኞች አማካይ ውጤት አይደለም፡፡ የምንፈልገውን ነገር በክርክር ሳይሆን በጉልበት እናስፈጽማለን ብለን ካሰብን እኛው ነን ፅንፈኞች፡፡

ስለዚህ ፅንፈኝነትን በውስጣችን እንፈልግ፡፡ የኢትዮጵያም ፅንፈኝነት ምንጭ መንግሥት ነው፡፡ ፅንፈኝነት በትምህርት ቤት፣ በሚዲያ፣ በሥልጠና ‹‹እኛ›› አንድ ሕዝብ እንዳልሆንን፣ ‹‹እነሱ መጥፎ፣ እኛ ጥሩ››፣ ‹‹እነሱ ጨቋኝ፣ እኛ ተጨቋኝ›› በሚል ሰበካ የትምህርትና የፖለቲካ ሥሪት ውስጥ እየዋኘን ፅንፈኝነት ያጠፋናል እንጂ አናጠፋውም፡፡ ዓሳ ሆኖ ውኃን እዋጋለሁ እንደማለት ነው፡፡

 

ፅንፈኛ መንግሥት ነው ፅንፈኛ ሕዝብ የሚፈጥረው፡፡ ሕወሓት በእኛና በእነሱ ትርክት ለ27 ዓመታት አትርፏል፡፡ እባካችሁ ይህ አይጠቅማችሁም፣ ያጠፋችኋል ሲባል አልሰሙም፡፡ መጨረሻው የእኛና የእነሱ መታወቂያ ካርድ ብቻ ሳይሆን፣ እንደ እኔ ያሬድ ኃይለ መስቀል ወልደ ማሪያም ረዣዥም ስምም ያለው ሰው በአውሮፕላን ላይ እንዳይሳፈር መሰናክል ተፈጥሮ ነበር፡፡

በፅንፈኝነት ኮሎኔል መንግሥቱ አላተረፈም፣ ሂትለር መጨረሻ ቤንዚል ሞልቶ አመድ እስክሆን አቃጥላችሁ አመዱን ሽንት ቤት ልቀቁት እስካለባት ጊዜ ድረስ ፅንፈኝነቱን አልቀነሰም፡፡ ዛሬም ፖለቲከኞች አስፈሪና ተናካሽ ፅንፈኛ በመልቀቅ  ‹‹አማካይ ወርቃማ እኔ ነኝ›› የሚል ሙከራ ጅልነትና ስለፅንፈኝነት አለማንበብ ነው፡፡

አሁን ያለንበት ሁሉም ፅንፈኛ ለመሆን የተገደደበት ሰዓት ነው፡፡ የመጨረሻው ዘፈን ‹‹የማን ቤት ጠፍቶ የማን ሊበጅ፣ የአውሬ መፈንጫ ይሆናል እንጂ›› እንዳይሆን እሠጋለሁ፡፡

በክፍል ሦስት ደግሞ እንዴት ከፅንፈኝነት እንላቀቅ፣ ፅንፈኝነትን ምክንያታዊ ማድረግ ባይቻልም ወደ ፅንፈኝነት የሚወስደውን ‹‹ራዲካላይዜሽን›› በማስቆም እሳቱን ማብረድና ማቆም ይቻላል፡፡

ፅንፈኝነት እንዴት ማዳከም ይቻላል?

ከላይ እንደተጠቀሰው ፅንፈኝነት ምክንያታዊነትን ከአዕምሮ አውጥቶ በስሜት ብቻ መመራት ከሆነ፣ ፅንፈኝነትን በምክንያታዊነትና በመረጃ መመለስ አይቻልም፡፡ ስለዚህ አንድ ሰው ፅንፈኝነት ላይ ከደረሰ በኋላ ግን አይመለስም፡፡ ምድር ከፍ ቢል ሰማይ ዝቅ ቢል ሂትለር ይሁዳዎች ይኑሩ አይልም ነበር፡፡ ሽንፈቱ ብቻ ነው ፅንፈኝነትን ያስቆመው፡፡ የሁቱ ሚሊሻዎችም የካጋሜ ጦር ኪጋሌ ከተማን እስከተቆጣጠረ ድረስ ግድያውን አላቆሙም፡፡ የካጋሜ ጦር ባይደርስ ኖሮ፣ ‹‹አረ በቃን 900 ሺሕ ገድለናል›› አይሉም ነበር፡፡ ቱትሲዎችን ሁሉ ከጨረሱ በኋላ ከቱትሲዎች ጋር የተነካኩትን ሁቱዎች ከማጥፈት አይመለሱም ነበር፡፡ ስለዚህ ፅንፈኞች የመግደያ መሣሪያቸውን ከመቀማትና በቀር ማመን አይቻለም፡፡ አንድ ሰው አጥፍቶ ለመጥፋት ካሰበ አውሮፕላን ላይ መጥለፊያ ሥለት ወይም ፈንጂ ይዞ እንዳይሳፈር ማድረግ እንጂ፣ እስኪ ቁጭ ብለን እንነጋገር አይሠራም፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ ይህንን ሲረዳ ፅንፈኝነትን ማስቆም ይችላል፡፡

በሚቀጥለው ጽሑፍ የዘር ማጥፋት (ጄኖሳይድ) ምንድነው? መፍትሔውስ ምንድነው? የሚለውን፣ ‹‹ለምን ሁሉንም አንገላቸውም?›› (Why Not Kill Them All, Daniel Chirot & Clark McCauley, 2006) የሚለው መጽሐፍ ውስጥ ያሉ ቁምነገሮችን አቀርባለሁ፡፡ ከፅንፈኞች ጠብቆ ያቆየን፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊው የዋይኤችኤም የማማከርና የኮሙዩኒኬሽን ኤጀንት ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ማኔጂንግ ዳይሬክተር ሲሆኑ፣ ጽሑፉ የእሳቸውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

ምክንያት አልባው ፅንፈኝነት (ክፍል አንድ)

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

በዓለም አቀፍ ደረጃ ሕይወታቸውን በኤድስ ምክንያት ላጡ ሰዎች 35ኛ ዓመት መታሰቢያ

ያለፍንበትን እያስታወስን በቁርጠኝነት ወደፊት እንጓዝ - በኧርቪን ጄ ማሲንጋ (አምባሳደር) በየዓመቱ...

እዚያ ድሮን… እዚህ ድሮን…

በዳንኤል ካሳሁን (ዶ/ር) ተዓምራዊው የማዕበል ቅልበሳ “በሕግ ማስከበር” ዘመቻው “በቃ የተበተነ...

ለፈርጀ ብዙ የማንነት ንቃተ ህሊናችን የሚጠቅሙ ጥቂት ፍሬ ነገሮች

በበቀለ ሹሜ ከጨቅላነት ጅምሮ ያለ የእያንዳንዳችን የሰብዕና አገነባብ ከቤተሰብ እስከ...