ኢትዮጵያ የዓለም ባንክን መዋቅራዊ ማስተካከያ (ስትራክቸራል አጀስትመንት) ፕሮግራም ተቀብላ እየተገበረች እንደሆነና የአገሪቱን የታክስ መሠረት ያሰፋሉ ተብለው እየተተገበሩ የሚገኙ አዳዲስ የታክስ ዓይነቶችም የዓለም ባንክ ለኢትዮጵያ ያዘዛቸው የፖሊሲ አቅጣጫዎች ውስጥ የሚመደቡ መሆኑ ተጠቆመ፡፡
የኢንቨስትመንት አማካሪው አቶ ያሬድ ኃይለ መስቀል የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ባዘጋጀው የውይይት መድረክ ላይ ተገኝተው ለንግዱ ማኅበረሰብ ተወካዮች ባደረጉት ገለጻ የዓለም አገሮች የግሎባላይዜሽን ተፅዕኖዎችን ተገደው እንደሚቀበሉና ኢትዮጵያም ከዚህ መውጣት እንደማትችል አስረድተዋል። ኢትዮጵያ እንደሌሎቹ ተፅዕኖ የሚያርፍባቸው አገሮች ሁሉ ከዓለም አቀፍ ተፅዕኖዎቹ ማምለጥ እንዳልቻለች፣ በዚህም የተነሳ በተለይም የዓለም ባንክ ያዘዘላትን ስትራክቸራል አጀስትመንትን (የፖሊሲ ምክረ ሐሳብ) ተቀብላ እየተገበረች እንደምትገኝ አስረድተዋል።
በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያ የገንዘብ ሚኒስቴርም ሆነ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የአገሪቱን ኢኮኖሚ ቴክኒካሊ ነው የሚመሩት ብለው እንደሚያምኑ የገለጹት አቶ ያሬድ፣ የዓለም ባንክ ኢትዮጵያ የውጭ ምንዛሪ ችግሯን መቅረፍ ባመለመቻሏ እንዲሁም በኢኮኖሚው ውስጥ ያለውን ግዙፍ የመንግሥት ሚና ወደ ግሉ ዘርፍ ማሻጋገር ባለመቻሏ የዓለም ባንክ ፈጣን ስትራክቸራል አጀስትመንት እንድትተገብር ማዘዙን፣ ይህንንም የኢትዮጵያ መንግሥት ተቀብሎ በመተግበር ላይ እንደሚገኝ አስረድተዋል።
የስትራክቸራል አጀስትመንት ግዴታዎች አምስት መሆናቸውን የጠቀሱት አቶ ያሬድ እነዚህም ዲቫሉዌሽን (የብርን የመግዛት አቅም ማዳከም)፣ መንግሥት የሚያደርገውን ኢኮኖሚያዊ ድጎማ ማቆም፣ የታክስ መሠረቱን ማስፋት፣ ሊብራላይዜሽን (ኢኮኖሚውን ክፍት ማድረግ) እና የመንግሥትን ወጪ መቀነስ ናቸው፡፡
አስገዳጅ የሆኑት እነዚህ የዓለም ባንክ የፖሊሲ ምክረ ሐሳቦችን መተግበር በኢኮኖሚ ውስጥ የሚያስከትለውን ተፅዕኖ አስመልክቶ በሰጡት ማብራሪያም ዲቫሉዌሽን በአገር ሀብት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እንደሚኖረውና በኢኮኖሚው ውስጥም ከፍተኛ የዋጋ ግሽበትን የሚያስከትል ተናግረዋል። ሌላው የፖሊሲ ምክረ ሐሳብ መንግሥት የሚያደርጋቸውን ድጎማዎች እንዲያቆም የሚያስገድድ ሲሆን፣ ይህ ምክረ ሐሳብም በአሁኑ ወቅት መተግበር መጀመሩን፣ ለዚህም ምሳሌ የሚሆነው መንግሥት በነዳጅ የመሸጫ ዋጋ ላይ ያደርግ የነበረው ድጎማ አሁን እየቆመ መሆኑን አቶ ያሬድ ገልጸዋል።
የአገሪቱን የታክስ መሠረት ማስፋት የሚለውን የፖሊሲ ምክረ ሐሳብም መንግሥት ተቀብሎ አዳዲስ የታክስ ዓይነቶችን ተግባራዊ ለማድረግ ዝግጅት ላይ መሆኑን የአቶ ያሬድ ማብራሪያ ያመለክታል፡፡ በቅርቡ ይጣላሉ ተብለው ከሚጠበቁት የታክስ ዓይነቶች መካከል አንዱ የንብረት ታክስ (ፕሮፐርቲ ታክስ) ሲሆን፣ ሌሎች ታክስ ዓይነቶችን ለመተግበርም ዝግጅት መኖሩን አስረድተዋል፡፡ በቅርቡ ይጣላል ተብሎ የሚጠበቀው የንብረት ታክስ (ፕሮፐርቲ ታክስ) ከትልልቅ ቪላ ቤቶች አንስቶ እስከ ኮንዶሚኒየም ድረስ ያሉ ቤቶችና ሕንፃዎች ባለቤቶች ታክስ መክፈል እንደሚገደዱ፣ እንደንብረቱ ይዞታና መጠን የታክስ ክፍያው ልዩነት ሊኖረው የሚችል ቢሆንም የፕሮፐርቲ ታክስ የሚከፍልበት አሠራር እየመጣ ስለመሆኑ ከሰጡት ማብራሪያ ለመገንዘብ ተችሏል፡፡
ሊብራላይዜሽንም በዚህ ፕሮግራም ግዴታ እንደሆነና ይህንንም መንግሥት እየተገበረው እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡ ለዚህም የኢትዮ ቴሌኮምን ድርሻ ለመሸጥ የተያዘው ዕቅድና የቴሌኮም ዘርፉን ክፍት በማድረግ ለውጭ ኩባንያዎች ፈቃድ መስጠት መጀመሩን በማሳያነት ጠቅሰዋል። ከቴሌ ኮሙዩኒኬሽን ዘርፍ በተጨማሪ በሌሎች ዘርፎች ያሉ ተቋማትም ሊሸጡ እንደሚችሉ ጠቁመዋል።
ሌላው የዓለም ባንክ ስትራክቸራል አጀስትመንት በሊብራላይዜሽን ፕሮግራም ሥር እንዲፈጸም የሚጠይቀው ለውጭ ኩባንያዎች ዝግ የነበሩ ዘርፎች ተከፍተው የውጭ ተወዳዳሪ ኩባንያዎች እንዲመጡ የሚያስገድድ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የመንግሥት ወጪ መቀነስም በተመሳሳይ የሚታይ ሲሆን፣ ታክስም የግድ ማደግ ስላለበት ይህንን ሊያሳድግ የሚችል ሥራ ተጠባቂ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ ‹‹የታክስ ቤዙ የግድ ማደግ አለበት›› ያሉ አቶ ያሬድ፣ ይህ ደግሞ ነጋዴው ላይ የሚመጣው ብዙ ጫና እንደሚኖርና በዚህም ምክንያት የንግዱ ማኅበረሰብ ከፊቱ ትልቅ ፈተና እንደሚገጥመው እምነታቸውን አንፀባርቀዋል፡፡
ከሊብራላይዜሽን ጋር በተገናኘ ሊከሰቱ ከሚችሉት ጉዳዮች አንዱ የፋይናንስ ዘርፉን ክፍት በማድረግ የውጭ ካንያዎች ወደ ኢትዮጵያ እንዲገቡ ማድረግ በመሆኑ የአገር ውስጥ ባንኮችና ኢንሹራንሶች ከፍተኛ ውድድር እንደሚጠብቃቸው ተናግረዋል፡፡
በጥቅሉ የሚታየው እውነታ የአገሪቱ ማክሮ ኢኮኖሚ እየተቀየረ መሆኑ ነው፣ ይህ ለውጥ መልካም ውጤቶች ሊኖሩት ቢችልም ትልቅ ተግዳሮት ግን ይዞ መምጣቱ እንደማይቀር የተጠቆሙት አቶ ያሬድ ‹‹ዋኝተን ማለፍ አለብን ወይም እንሰምጣለን›› በሚል ሐሳባቸውን ቋጭተዋል፡፡