- ምን ሆነሻል ዛሬ?
- ምንም አልሆንኩም፣ ይልቅ አረፍ በል የደከመህ ትመስላለህ።
- አዎ፣ ቀኑን ሙሉ ጉብኝት ላይ ነበር የዋልኩት።
- ምን ስትጎበኝ?
- በዘመናዊ ውስብስብ ቴክኖሎጂዎች እንዲደራጁ የተደረጉትን ተቋማት ስንጎበኝ ነበር ዛሬ።
- አይ…
- ምነው? እንዴት ያለ የለውጥ ሥራ መሰለሽ የተመለከትነው፣ በነገራችን ላይ…
- እ…
- እነዚህን ተቋማት የምንገነባው ኢትዮጵያን ሊያፈርሱ ከሚፈልጉ ኃይሎች ለመከላከል ነው።
- ምን ዋጋ አለው?
- እንዴት?
- እየሆነ ያለው ተቃራኒው ነዋ፡፡
- እመኚኝ እየለፋን ያለነው አገራችንን በሰላም ለማቆየት ብቻ አይደለም።
- እ… ሌላ ለምንድነው?
- የበለፀገችና ሰላማዊት ኢትዮጵያን ለልጆቻችን ለማውረስ ነው።
- ስለየትኛው አገር ነው የምታወራው?
- ስለእኛ ነዋ?
- ጨቅላ ሕፃናት እኮ በጥይት እየተገደሉ ነው፡፡
- እሱ ያሳዝናል፣ ለቤተሰቦቻቸው መፅናናትን ይስጣቸው።
- ቤተሰቦቻቸው? በአንድ ሌሊት ሙሉ ቤተሰብ እያለቀ እኮ ነው፡፡
- እመኚኝ፡፡
- ምኑን ልመንህ?
- እመኚኝ፣ ይህ መከራ ሊያበረታን ነው የመጣው፡፡
- ምነው እቴ? አሁንስ አበዛኸው፡፡
- እንዴት?
- ይሁን ብዬ ብሰማህ ሊያበረታን ነው የመጣው ትላለህ ጭራሽ?
- እመኚኝ ስልሽ?
- ለምን ብዬ ነው የማምንህ? እውነታውን እያየሁት?
- ምንድነው እውነታው?
- እውነታውማ አንተ ከምትለው ተቃራኒ ነው።
- ተቃራኒ ማለት?
- መከራው እያበረታችሁ አይደለም፡፡
- እ…?
- እየበረታባችሁ ነው፡፡
- ምን…?
- ከመበርታትም አልፎ…
- እ…
- እያርበተበታችሁ ነው።
- እንዴት?
- የማኅበረሰቡን ሥቃይ ሊያበረታን ነው ከማለት የበለጠ ምን መርበትበት አለ?
[ክቡር ሚኒስትሩ ወደ ቢሯቸው ሲገቡ ጸሐፊያቸው ሞባይሏን እየተመለከተች ሰትስቅ አገኟት]
- በጠዋት ምን የሚያስቅ ነገር አግኝተሽ ነው?
- ውይ ገብተዋል እንዴ ክቡር ሚኒስትር?
- ምንድነው እንደዚያ ሲያፍለቀልቅሽ የነበረው?
- ወድጄ አይደለም ክቡር ሚኒስትር።
- እንዴት?
- ወደው አይስቁ ሆኖብኝ ነው።
- በምን ምክንያት?
- ፌስቡክ ላይ የሚቀለደውን አይቼ ነው ክቡር ሚኒስትር።
- ስለምንድነው የሚቀለደው?
- አይ… ይቅርብዎት ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ለምን?
- ግዴለዎትም ይቅርብዎት ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ለምን? ጉዳዩ እኔን የሚመለከት ነው እንዴ?
- ምን በወጣዎት፣ ቢሆንም ግን…
- ቢሆንም ምን?
- ብዙ አይርቅም፡፡
- ማለት?
- ስለአማካሪዎት ነው እየተቀለደ ያለው፡፡
- እንዴት? በምን ምክንያት?
- ለሚዲያ በሰጡት ኢንተርቪው ነው ክቡር ሚኒስትር።
- ምን ብሎ ነው?
- ለገጠመን የኑሮ ውድነት ችግር የመፍትሔ ሐሳብ አቅርበው ነው።
- ምን እንዳለ ለምን አትነግሪኝም?
- ክቡር ሚኒስትር እንዲያው ቢቀርብዎት ይሻላል ብዬ እኮ ነው፡፡
- ለኑሮ ውድነቱ ምን ዓይነት መፍትሔ አቀረበ? ለምን አትነግሪኝም?
- ሸማቹ ከጠባቂነት ተላቆ የተወደደበትን ምርት ሊያመርት ይገባል የሚል መፍትሔ ነው የሰጡት።
- እ…
- ይቅርብዎት ያልኩት እኮ ለዚህ ነበር ክቡር ሚኒስትር?
- ሌላ የተናገረው ነገር አለ?
- ሸማቹ መንግሥት ዋጋ እንዲያረጋጋለት ከመጠበቅ ይልቅ፣ የተወደደበትን ምርት ራሱ ማምረትና የመፍትሔው አካል መሆን አለበት ብለዋል።
- ታዲያ አንቺን ያሳቀሽ ምንድነው?
- እ…
- መንግሥትም የሚያምነበት መፍትሔ እኮ ነው፡፡
- መንግሥት ያመነበት ነው?!
- በትክክል፡፡
- አይ… ሳቅ ከንቱ፡፡
- ምን አልሽ?
- አሁን ነዋ ማዘን፡፡
- ለምን?
- እንዴት ለምን ይባላል ክቡር ሚኒስትር?
- እንዴ… ለምን አይባልም?
- እንዴት ሆኖ ነው ሸማቹ የተወደደበትን የሚያመርተው? ስንቱን ነው የሚያመርተው? ምን ላይ ነው የሚያመርተው?
- በመንግሥት ደረጃ የጀመርነው የጓሮ አትክልት ምርት ውጤት ብትመለከቺ እንደዚህ አትይም ነበር።
- እሱማ በመንግሥት ጓሮ ነው።
- ማኅበረሰቡም በየጓሮው፣ በየደጃፉ ይህንን ቢያደርግ ችግሩን በቀላሉ መፍታት ይቻላል።
- የአዲስ አበባ ነዋሪ ምን ደጃፍ አለው? የምን ጓሮ አለው?
- እህ… እሱም አለ ለካ? አየሽ እሱን አላሰብንበትም።
- ለነገሩ ማኅበረሰቡም የዋዛ አይደለም ክቡር ሚኒስትር።
- እንዴት?
- ደጃፍ የሌላቸውም ማምረት አለባቸው እያለ ነው ማኅበረሰቡ።
- ምን?
- ደጃፍ!