Sunday, September 24, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ስፖርትየሁሉንም ተጠያቂነት የሚሻው የኢትዮጵያ እግር ኳስ

የሁሉንም ተጠያቂነት የሚሻው የኢትዮጵያ እግር ኳስ

ቀን:

በ‹‹ጨዋታ ማጭበርበር›› ንፁህ ማን ነው?

ለኢትዮጵያ እግር ኳስ ሁሉን አቀፍ ዕድገት እንዲያሳካ ከተደቀኑበት ተግዳሮቶች መካከል፣ የበቁ ባለሙያዎች እጥረትና ለዘርፉ የሚመጥን ዕውቀት አንዱ እንደሆነ ብዙዎች ይስማማሉ፡፡ እግር ኳስ ሁሉም የሚስማማበት ሕግና ሥርዓት ያለው ከመሆኑ ባሻገር፣ በተለይም በአሁኑ ወቅት አገራዊ መግባባትን በመፍጠር፣ ብሎም የአገሮችን መልካም ገጽታ በማስተዋወቅ እንዲሁም ምክንያታዊ ገቢ በማስገኘት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑም ይታመናል፡፡

ይህን የእግር ኳስ ጨዋታን መሠረታዊ ዕሳቤ ወደ ጎን በማለት በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ‹‹ቡድኖች ይለቃሉ›› የሚለው ወሬ ሰሞነኛ መነጋገሪያ ሆኗል፡፡ በአንጋፋው ቅዱስ ጊዮርጊስ አሸናፊነት የተጠናቀቀው የዘንድሮ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ከጨዋታ ማጭበርበር ጋር ተያይዞ ብዙ እያነጋገረ ይገኛል፡፡

ሰሞነኛው መነጋገሪያ ሆኖ እየተደመጠ የሚገኘው ክስተት ከወትሮ በተለየ በዚህኛው የውድድር ዓመት ጎልቶ እንዲህ አቧራ ያስነሳበት ምክንያት ባይታወቅም፣ ሲወርድ ሲዋረድ የመጣ የአደባባይ ሚስጥር መሆኑ ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡

ባለፈው ቅዳሜ ሰኔ 25 ቀን 2014 ዓ.ም. ፍፃሜውን ያገኘው የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ፣ ጅማ አባ ጅፋር፣ ሰበታ ከተማና አዲስ አበባ ከተማን ወደ ከፍተኛው ሊግ በማውረድ መጠናቀቁ ይታወሳል፡፡

በሊጉ እስከ መጨረሻው በመውረድና ባለመውረድ ሥጋት ውስጥ ገብቶ የቆየው አዲስ አበባ ከተማ፣ ‹‹እንድወርድ የተደረገው እግር ኳሳዊ ባልሆነ የእግር ኳስ ፕሮፌሽናሊዝምን ባልጠበቀ የጨዋታ ማጭበርበር ነው፤›› በማለት ድርጊቱ በብሔራዊ ፌዴሬሽኑ አሊያም ሌሎች በሚመለከታቸው አካላት ታይቶና ተመርምሮ ውሳኔ የማይሰጠው ከሆነ ጉዳዩን ወደ ዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ግልግል ፍርድ ቤት (ካስ) እንደሚወስደው አስጠንቅቋል፡፡

በሌላ በኩል በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ በተለይም ከጨዋታ ማጭበርበር ጋር ተያይዞ የሚታየውን አካሄድና ድርጊት ባይደግፉትም፣ ነገር ግን ደግሞ በሊጉ አሸናፊ ቅዱስ ጊዮርጊስ 4 ለ 0 ተሸንፎ ወደ ከፍተኛው ሊግ የወረደው የአዲስ አበባ እግር ኳስ ክለብ፣ በጨዋታው የራሱን ዕድል በራሱ መወሰን እየቻለ ለምን ቀጣይ ዕጣ ፈንታውን በሌሎች ቡድኖች ጥንካሬና ድክመት ላይ እንዲወሰን አደረገ? በማለት ክለቡ የሚጠይቀውን የፍትሐዊነት ጥያቄ የሚያጣጥሉ አልጠፉም፡፡

በአሁኑ ወቅት ‹‹ከጨዋታ ማጭበርበር›› ጋር ተያይዞ ከፍተኛ የሆነ ወቀሳና ትችት እየቀረበባቸው ከሚገኙ ቡድኖች መካከል፣ ለአሸናፊነት ሲጠበቅ በመጨረሻ በድሬዳዋ 3 ለ 2 የተሸነፈው ፋሲል ከነማ ይጠቀሳል፡፡ የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ በሚካሄድበት ዕለት በተመሳሳይ ሰዓት፣ ቅዱስ ጊዮርጊስ ከአዲስ አበባ እንዲሁም ሌላው የመውረድ ሥጋት የነበረበት አዳማ ከተማ ከሐዋሳ ከተማ ጋር መጫወታቸው አይዘነጋም፡፡

አዳማ ከተማ የሐዋሳ አቻውን 3 ለ 2 በማሸነፍ የፕሪሚየር ሊግ ቆይታውን ቢያረጋግጥም፣ ውጤቱ ከስፖርታዊ ጨዋነት አንፃር ‹‹ምን ያህል ተዓማኒ ነበር?›› ሲሉ የሚጠይቁ አሉ፡፡ ለዚህ በተለይም ከጨዋታ ማጭበርበር ጋር ተያይዞ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ አመራሮች ከሰሞኑ የሰጡትን መግለጫ መመልከት ግድ ይላል፡፡

‹‹በእኛ ግምገማ በመጨረሻው ጨዋታ በርካታ ክለቦች በጨዋታ ማጭበርበሩ ተሳትፈዋል፡፡ የሐዋሳና የአዳማ ጨዋታም የዚሁ ጨዋታ ማጭበርበር አካል ነው፤›› በማለት የተናገሩት የቢሮው ምክትል ኃላፊ አቶ ዳዊት ትርፉ መሆናቸው ልብ ይሏል፡፡

በዚህ ዓመት ‹‹ተደርጓል›› ተብሎ የሚታመነው የጨዋታ ማጭበርበር፣ ከወትሮ የሚለየው ሁሉም ጨዋታዎች በዲኤስ ቲቪ አማካይነት በቀጥታ ሥርጭት ለስፖርት ቤተሰቡ ተደራሽ መሆናቸው ካልሆነ፣ ቀደም ባሉት የውድድር ዓመታት ከስፖርታዊ ጨዋነት ውጪ በሆነ መንገድ ውጤት ያላስቀየረ ‹‹ከደሙ ንፁህ ነኝ›› የሚል ክለብ እንደሌለ የሚናገሩ አሉ፡፡

ሪፖርተር በዚህ ጉዳይ እንዳነጋገራቸው አሠልጣኞችና የፌዴሬሽን አመራሮች ከሆነ፣ ‹‹የኢትዮጵያን ፕሪሚየር ሊግ ጨምሮ በየደረጃው የሚገኙ ቡድኖች የተቃራኒ ቡድን ተጫዋቾችን በገንዘብ በማማለል ወይም በቀጣዩ የውድድር ዓመት ለእኔ ክለብ በጥሩ ወርኃዊ ክፍያ ትጫወታለህ፤›› በሚል መደለያ ጨዋታ በማጭበርበር ስማቸውና ማንነታቸው ጭምር የሚጠቀሱ አሉ፡፡ ከዚህም ባለፈ ለአመራሮችና የውድድር መሪዎች ገንዘብ በመመደብ፣ የጨዋታ ዳኞች እንዲቀየሩ መመርያ የሚሰጡ እንዳሉም የሚያነሱ አሉ፡፡ ተቀባይነት በሌለው በዚህ ድርጊት በተከናወኑ የጨዋታ ማጭበርበር የፈረሱ በርካታ ክለቦች አሉ በማለት ድርጊቱ ሲወርድ ሲዋረድ ዛሬ ላይ ስለመድረሱ ጭምር ይናገራሉ፡፡

የእነዚህ ዓይነት ድርጊቶች የተደራጀ ምርመራ የሚፈልጉ መሆናቸው እንደተጠበቀ ሆኖ፣ በጨዋታ ማጭበርበር ከመላቀቅ ጋር ተያይዞ ከዚህ ቀደም የተደረጉ ትክክለኛ ማስረጃ ሊቀርብባቸው የሚችሉ ክስተቶች የተስተዋሉባቸው ጊዜያት ከመኖራቸውም በላይ፣ በችግሩ ምክንያት እንዲፈርሱ የተደረጉ ቡድኖች በርካታ ስለመሆናቸው ጭምር እነዚሁ አሠልጣኞችና የፌዴሬሽን አመራሮች ያስረዳሉ፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የቤት ባለንብረቶች የሚከፍሉትን ዓመታዊ የንብረት ታክስ የሚተምን ረቂቅ አዋጅ ተዘጋጀ

በአዋጁ መሥፈርት መሠረት የክልልና የከተማ አስተዳደሮች የንብረት ታክስ መጠን...

እንደ ንብረት ታክስ ያሉ ወጪን የሚያስከትሉ አዋጆች ከማኅበረሰብ ጋር ምክክርን ይሻሉ!

የመንግሥትን ገቢ በማሳደግ ረገድ አስተዋጽኦ እንዳላቸው የሚታመኑት የተጨማሪ እሴት...

ለዓለምም ለኢትዮጵያም ሰላም እንታገል

በበቀለ ሹሜ ያለፉት ሁለት የዓለም ጦርነቶች በአያሌው የኃያል ነን ባይ...