በመቶዎች የሚቆጠሩ ዜጎችን ሕይወት የቀጠፈው የምዕራብ ወለጋ ጭፍጨፋ በተፈጸመ በሁለት ሳምንት ጊዜ ውስጥ፣ በቄለም ወለጋ ዞን ሀዋ ገላን ወረዳ በድጋሚ በመቶዎች የሚቆጠሩ ንፁኃን መጨፍጨፋቸውን የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) አስታወቀ፡፡
ኢሰመኮ ሰኞ ሰኔ 27 ቀን 2014 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ ጭፍጨፋውን፣ ‹‹በብሔር ላይ ያነጣጠረ የሚመስል ግድያ›› ሲል የገለጸው ሲሆን፣ የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት በበኩሉ ጥቃቱ ‹‹በአንድ አካል ላይ ያነጣጠረ አይደለም፤›› ብሏል፡፡
ጭፍጨፋው የደረሰው በቄለም ወለጋ ዞን ሀዋ ገላን ወረዳ በሚገኙት መንደር 20 እና መንደር 21 በተባሉት አካባቢዎች እንደሆነ የጠቀሰው የኢሰመኮ መግለጫ፣ ድርጊቱ ሰኞ ሰኔ 27 ቀን 2014 ዓ.ም. ጠዋት ላይ እንደተጀመረ ገልጿል፡፡ ኢሰመኮ እነዚህ መንደሮች በዋነኝነት የአማራ ተወላጅ ነዋሪዎች የሚኖሩባቸው እንደሆኑ መረዳቱን በመግለጫው አስታውቋል፡፡
‹‹ድርጊቱን የፈጸሙት የኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት (ሸኔ በመባል የሚታወቀው) አባላት መሆናቸውን ምንጮች ጠቁመዋል፤›› ያለው ኮሚሽኑ፣ በጭፍጨፋው ሕይወታቸው ያለፉ ሰዎች ብዛት ምን ያህል እንደሆነ እንዳልተረጋገጠ አስታውቋል፡፡
በመንግሥት በኩልም እስካሁን ድረስ ምን ያህል ሰዎች እንደተገደሉ ይፋ ያልተደረገ ሲሆን፣ የአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን ሰኞ ምሽት ባሠራጨው ዘገባ ያቀረባቸው ‹‹የጥቃቱ ሰለባዎች›› የ320 ሰዎች አስከሬን መሰብሰቡን ተናግረዋል፡፡
የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ለገሰ ቱሉ (ዶ/ር)፣ ‹‹የሚባሉ ቁጥሮች ዓይነት አይደለም፡፡ ጉዳት ግን ደርሷል፡፡ በሚመለከታቸው አካላት ተጣርቶ ይፋ ይደርጋል፤›› ሲሉ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡
እንደ ለገሰ (ዶ/ር) ገለጻ ጭፍጨፋው የተፈጸመበት ሀዋ ገላን ወረዳ የመከላከያ ሠራዊት ከሚገኝበት ‹‹ራቅ ያለ ቦታ›› ላይ የሚገኝ ነው፡፡ የኦሮሚያ ልዩ ኃይልም ትኩረቱ ሥጋት በነበረባቸው ሌሎች አካባቢዎች ላይ ነበር ብለዋል፡፡ ታጣቂዎቹ ይኼንን አጋጣሚ እንደተጠቀሙ የሚናገሩት ሚኒስትሩ፣ ‹‹[ታጣቂዎቹ] መኖራቸውን ለማረጋገጥ የኅብረሰተሰቡን ትኩረት ለመሳብና ይኼ ጉዳይ በተለይም የኦሮሞ ማኅበረሰብን ከሌላ ማኅበረሰብ ያጋጫል የሚል ሐሳብ ስላላቸው›› ጭፍጨፋውን መፈጸማቸውን ተናግረዋል፡፡
‹‹ተሰባጥረው የሚኖር ማኅበሰረብ ነው እዚያ ያለው፣ ያገኙትን ነው የጨፈጨፉት፤›› ያሉት ለገሰ (ዶ/ር)፣ በጭፍጨፋው የወረዳና የቀበሌ አመራሮችም መገደላቸውን አስታውቀዋል፡፡ ‹‹እዚያ መንደር ውስጥ የሐረርጌ ኦሮሞዎችም አሉ፡፡ በ1977 ዓ.ም. ከአማራም ከደቡብም የሠፈሩ አሉ፣ [ታጣቂዎቹ] ያገኙትን ነው [የገደሉት]፡፡ መለያ ጊዜ መቼ ይኖራቸዋል? ወቅቱ አይፈቅድላቸውም፤›› በማለት ታጣቂዎቹ አሁን ያሉበት ሁኔታ ማንነት ለይቶ ጥቃት ለመፈጸም እንደማይፈቅድ ገልጸዋል፡፡ አሁን በአካባቢው የመንግሥት ኃይሎች መሰማራታቸውን አክለዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ሰኞ ሰኔ 27 ቀን 2014 ዓ.ም. በፌስቡክ ገጻቸው ባጋሩት ጽሑፍ፣ ‹‹በኦሮሚያ ክልል፣ ቄለም ወለጋ ዞን ውስጥ የሚገኙ ዜጎች ጭፍጨፋ ተፈጽሞባቸዋል፤›› ብለዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ‹‹የሸኔ ቡድን›› ጭፍጨፋውን የፈጸመው የፀጥታ አካላት ‹‹የሚያደርሱበትን ዱላ›› በመሸሽ ላይ እያለ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ዓብይ (ዶ/ር) አክለውም፣ ‹‹በዜጎቻችን ላይ በደረሰው መከራ እያዘንን፣ ይኼንን አሸባሪ ቡድን እስከ መጨረሻው ተከታትለን ከሕዝባችን ጋር እናስወግደዋለን፤›› ብለዋል፡፡
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን በተመሳሳይ ትናንት ማክሰኞ ባጋሩት ጽሑፍ፣ ‹‹የሸኔ ቡድን በንፁኃን ወገኖቻችን ላይ አሳዛኝ ጭፍጨፋ አካሂዷል፡፡ ጥቃቱ የአማራ ብሔር ተወላጆችን ዒላማ ያደረገና ተጠቂዎችን ለመከላከል ሙከራ ባደረጉ የኦሮሞ ተወላጆች ላይ ጭምር ያነጣጠረ ነው፤›› ብለዋል፡፡
የኮሙዩኒኬሽን ሚኒስትሩ ለገሰ (ዶ/ር)፣ ታጣቂዎቹ ከዚህ ቀደም ‹‹የተወሰኑ›› ወረዳዎችና ቀበሌዎች ተቆጣጥረተው የነበረ ቢሆንም፣ ካለፉት ሁለት ወራት ወዲህ ግን ‹‹በብዙ ካምፖች፣ ማዘዣና ማሠልጠኛ ጣቢያዎች›› ላይ በተወሰደው ዕርምጃ ይኼ አካሄድ እንደተቀየረ ተናግረዋል፡፡ አሁን ጭፍጨፋ በተፈጸመበት ቄለም ወለጋ ዞንም ሆነ በሌሎች አካባቢዎች ታጣቂዎቹ ጫካ ውስጥ ተበትነው እንደሚገኙና ራሳቸውን ቀይረው ነዋሪ ሆነው እንደሚቀመጡ አብራርተዋል፡፡
‹‹ከኦሮሚያ ልዩ ኃይልም ሆነ ከመከላከያ ጋር በመዋጋት አይደለም ይኼንን ጥቃት እያደረሰ ያለው፤›› ያሉት ለገሰ (ዶ/ር)፣ እንዲህ ዓይነት ‹‹የሽብር ጥቃቶች›› የፀጥታ አካላት በሚያደርጉት ቁጥጥር ብቻ መግታት እንደማይቻል ገልጸዋል፡፡ አክለውም፣ ‹‹የአካባቢው ኅብረተሰብ በደንብ በንቃት እነዚህን ዓይነት እንቅስቃሴዎች መጠበቅ አለበት፣ ራሱን ማደራጀት አለበት፣ ወዲያውኑ ምልክቶችን ካየ፣ ከሰማና ካስተዋለ ለፀጥታ አካል መግለጽ አለበት፤›› ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ዋና ኮሚሽነር ዳንኤል በቀለ (ዶ/ር) በበኩላቸው ተጨማሪ ንፁኃን እንዳይገደሉ ሲባል በአስቸኳይ የመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች እንዲሰማሩ በኮሚሽኑ መግለጫ ላይ ጠይቀዋል፡፡ ‹‹በአካባቢው የቀጠለው የፀጥታ ችግርና ብሔርን መሠረት ያደረገ የሚመስለው በነዋሪዎች ላይ የሚፈጸም ግድያ በአስቸኳይ መቆም አለበት፤›› ብለዋል፡፡
ኢሰመኮ፣ ሰኔ 11 ቀን 2014 ዓ.ም. በምዕራብ ወለጋ ዞን ጊምቢ ወረዳ ቶሌ ቀበሌ የተፈጸመውን ጭፍጨፋ አስመልክቶ ባወጣው መግለጫም፣ በተመሳሳይ ተጨማሪ ግድያ እንዳይፈጸም መንግሥት አስፈላጊ የሆኑ የመከላከል ዕርምጃዎችን እንዲወስድ አሳስቦ ነበር፡፡
መንግሥት ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ባወጣው ቁጥር በጊምቢ ወረዳ ጭፍጨፋ 338 ሰዎች መገደላቸውን አስታውቋል፡፡ ሪፖርተር በአካባቢው ያነጋገራቸው ሰዎች በበኩላቸው የተገደሉ ሰዎች ቁጥር ከ400 እንደሚልቅ ሲናገሩ፣ በጥቃቱ የተገደሉ ሰዎችን በመቅበር ላይ እንደተሰማሩ የተናገሩ አንድ ነዋሪ የተቀበሩ ሰዎች ቁጥር ቢያንስ 582 እንደሚደርስ ገልጸዋል፡፡
የአማራ ማኅበር በአሜሪካ የተባለና መሠረቱን በውጭ ያደረገ ማኅበር የጊምቢውን ጭፍጨፋ አስመልክቶ ባወጣው ባለ 33 ገጽ ሪፖርት፣ በጭፍጨፋው ሕይወታቸው ያለፈ የ455 ነዋሪዎችን ስም፣ ፆታ፣ ዕድሜና መኖሪያ መንደር ይፋ አድርጓል፡፡