‹‹ክብር ለጥበብ›› በሚል መጠርያ ዓምና የኪነ ጥበብ ባለሙያዎችን በውድድር የሸለመው የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር ለሁለተኛ ጊዜ ያዘጋጀውና ዛሬ ሰኔ 29 ቀን 2014 ዓ.ም. በሸራተን አዲስ በሚያካሂደው የሽልማት ሥነ ሥርዓት፣ ለ45 አንጋፋና ወጣት ኪነ ጠቢባን ዕውቅና እንደሚሰጥ አስታውቋል፡፡
ባለፈው ሳምንት ማብቂያ ላይ ሚኒስቴሩ ከጥበባት ማኅበራት ጋር በመተባበር የሚያካሂደውን መርሐ ግብር አስመልክቶ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ፣ ባለሙያዎችን በሕይወት ሳሉ ማመስገንና የዕውቅና ሽልማት መስጠት ተተኪ ወጣቶችን እንደሚያበረታታ ገልጾ፣ የዘንድሮው ሽልማት ለየት የሚያደርገው የክልሎችን የኪነ ጥበብ ባለሞያዎች የሚያካትት መሆኑ ነው ብሏል፡፡
የዕውቅና ዝግጅቱ አንጋፋ ባለሙያዎች ሕያው በሆኑ ሥራዎቻቸው እንዲዘከሩ ማድረግና ተተኪዎችን ለማፍራት ያለመ እንደሆነ የተናገሩት የኪነ ጥበብ፣ ሥነ ጥበብና ፈጠራ ሚኒስትር ዴኤታ ወ/ሮ ነፊሳ አልመሃዲ ናቸው፡፡
በ2013 ዓ.ም. የተካሄደው የመጀመርያው የዕውቅናና ሽልማት መርሐ ግብር ውድድር ተደርጎ ከተወዳዳሪዎች መካከል ላሸነፉት የተሰጠ እንደነበርም አስታውሰው፣ ዘንድሮ ግን ባለሙያዎች ለአገራቸው ላበረከቱት አስተዋጽኦ መስፈርቶችን በማስቀመጥ ዕውቅናው እንደሚሰጥም አስረድተዋል።
ከዕውቅና ማወዳደሪያ መስፈርቶች መካከል በሙያው ረዥም ዓመታት በትጋት የቆዩ፣ ሙያቸውን ተጠቅመው አገራዊ የቋንቋና የባህል እሴቶችን ማስተዋወቅ የሚሉት ይገኙበታል።
የሽልማት ምልመላና መረጣ ኮሚቴ ሰብሳቢው የኢትዮጵያ ሙዚቀኞች ማኅበር ፕሬዚዳንት ዳዊት ይፍሩ፣ የዕውቅና አመራረጥ ሒደቱንና ያብራሩ ሲሆን ሽልማትና ዕውቅና የሚሰጥባቸው ዘርፎች አሥር መሆናቸውን አመልክተዋል፡፡ እነሱም ሥነ ጽሑፍ፣ ሙዚቃ፣ ቴአትር፣ሥዕል፣ ውዝዋዜ፣ ሰርከስ፣ ሲኒማ፣ ኮሜዲ፣ ፋሽን እና ዕደ ጥበብ ናቸው፡፡