Monday, December 4, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

ከ85 በመቶ በላይ ሴት ሠራተኞች የተሰማሩበት የሽርሽር አዲስ አበርክቶ

በአዲስ አበባ በትራንስፖርት አገልግሎት ዙሪያ ከፍተኛ ችግር እየታየ ይገኛል፡፡ በተለይም በሥራ መውጫያና መግቢያ ሰዓት ላይ ረዣዥም ሠልፎች ማየት የተለመደ ሆኗል፡፡ ከሁሉም በላይ ደግሞ የትራንስፖርት ተገልጋዮች ቁጥርና በከተማዋ ያሉ የሕዝብ ተሽከርካሪዎች ቁጥር አለመመጣጠን ችግሩ እንዲጎላ አድርጓል፡፡ ይሁን እንጂ ይህንን ችግር ለመግታት መንግሥትም ሆነ የተለያዩ ድርጅቶች የበኩላቸውን እያደረጉ ይገኛሉ፡፡ ከእነዚህም መካከል በግል ዘርፉ የተሰማራው ሽርሽር አዲስ ትሬዲንግ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ይጠቀሳል፡፡ ድርጅቱ ከትራንስፖርት አገልግሎት አሰጣጥ ውጪ የተለያዩ ምርቶችን ኤክስፖርት በማድረግና በግብርና ዘርፉ ላይ በመሳተፍ ይታወቃል፡፡ ወ/ሮ ቃልኪዳን ኢሳያስ የድርጅቱ ሥራ አስኪያጅ ናቸው፡፡ የድርጅቱን ሥራ በተመለከተ ተመስገን ተጋፋው አነጋግሯቸዋል፡፡

ሪፖርተር፡- ሽርሽር አዲስ ትሬዲንግ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር መቼ ተመሠረተ?

ወ/ሮ ቃልኪዳን፡- ማኅበሩ ከተመሠረተ ሦስት ዓመት ገደማ አስቆጥሯል፡፡ በ2011 ዓ.ም. ከተመሠረተ ጊዜ አንስቶ የተለያዩ አገልግሎቶችን እየሰጠ ይገኛል፡፡ ሽርሽር አዲስ በአዲስ አበባ ከተማ ላይ የሚታየውን የትራንስፖርት ችግር ለመቅረፍ ዘርፈ ብዙ ሥራዎችን እየሠራ ነው ማለት ይቻላል፡፡ በተለይም በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ለሚገኙ ባለ ላዳ ታክሲዎች ከባንኮች ጋር ስምምነት በማድረግ የዘመናዊ መኪኖች ባለቤቶች እንዲሆኑ አማራጮችን እያቀረበ ይገኛል፡፡ ይህ ለከተማዋ ውበት ከመስጠት ባለፈ የትራንስፖርት ዘርፉ ላይ የሚነሱ ጥያቄዎችን የሚፈታ ይሆናል፡፡ በተለይም በአሁኑ ወቅት የመኪና ባለቤት መሆን ትንሽ ከባድ ነው፡፡ ከአገሪቱ ወቅታዊ ሁኔታ አንፃርም ሆነ ከዶላር ምንዛሪ ጋር ተያይዞ  በሚነሱ ችግሮች ምክንያት አብዛኛው የዘርፉ ተዋናዮች ላይ ክፍተት ተፈጥሯል፡፡ ሽርሽር አዲስ በአሁኑ ሰዓት አዲስ አበባ ላይ ብቻ ይሥራ እንጂ በቀጣይ የተለያዩ የክልል ከተሞች ላይ ለመሥራት ቅድመ ዝግጅቱን አጠናቋል፡፡ በደብረ ብርሃን ከተማም በ4.6 ሔክታር መሬት ላይ የሚያርፍ የመኪና መገጣጠሚያ ለመገንባት ዝግጅቱን አጠናቋል፡፡ ከመኪና ወይም ከተሽከርካሪዎች ውጪም የሰሊጥና የማሾ የቅባት እህሎችን በማምረት ኤክስፖርት እያደረግን እንገኛለን፡፡ የቅባት እህሎችን ለማምረትም በጋምቤላ ክልል ላይ 1000 ሔክታር መሬት አግኝተናል፡፡ ከግብርና ውጪም ማር በማምረት አገር ውስጥም ሆነ ወደ ውጪ አገር በመላክ እንገኛለን፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ትልልቅ ጨረታዎች ላይ በመሳተፍ የፀጥታ አስከባሪዎችን የደንብ ልብስም ሆነ ጫማዎችን ለገበያ ማቅረብ ችለናል፡፡ ወደፊትም ይህንን አጠናክረን በመቀጠል የተለያዩ ምርቶችን የምናቀርብ ይሆናል፡፡

ሪፖርተር፡- ድርጅቱ በጋምቤላ ክልል በ1000 ሔክታር መሬት ላይ የሰሊጥና የማሾ የቅባት እህሎችን በማምረት ኤክስፖርት እያደረገ ይገኛል፡፡ ከዚህ ውጪ በክልሉ ውስጥ ምን ዓይነት አገልግሎትን ይሰጣል?

ወ/ሮ ቃልኪዳን፡- ድርጅታችን በክልሉ ውስጥ እህት ኩባንያ አለው፡፡ ኩባንያው ቻማ አዶት የሚባል ሲሆን፣ ይኼም በአኝዋክኛ ቋንቋ የተሰየመ ነው፡፡ ኢንቨስት ከማድረጋችን በፊት ወደ ማኅበረሰቡ በመግባት ባህሉን፣ ቋንቋውንና አኗኗሩን አጥንተናል፡፡ በዚህም የተነሳ አብዛኛው የድርጅታችን ሠራተኞች ቋንቋውን በቀላሉ ሊያውቁ ችለዋል፡፡ ይኼም ለሥራችን ትልቅ ድልድይ ሆኗል ማለት ይቻላል፡፡ በክልሉ ከ400 የሚበልጡ ዜጎች የሥራ ዕድል አግኝተዋል፡፡ ለሠራተኞች ከሕክምና ጀምሮ የተለያዩ አገልግሎቶችን እንዲያገኙ እያደረግን ነው፡፡ ከሁሉም በላይ ደግሞ መንገዶችን በማስተካከል ለክልሉ ነዋሪዎች እፎይታን ሰጥተናል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ በአጨዳ ወቅትም ሆነ በሌሎች ጉዳዮች ላይ  ዘመናዊ ማሽኖችን በኪራይ መልክም ሆነ በውሰት በመስጠት አማራጮችን አቅርበናል፡፡ እነዚህንም ማሽነሪዎች እንዴት መጠቀም እንዳለባቸው እንዲያውቁ ሥልጠናዎችን ሰጥተናል፡፡ በአሁኑ ወቅት ሥልጠናውን ተግባራዊ ያደረጉ የክልሉ ተወላጆች ለድርጅታችን አገልግሎት እየሰጡ ይገኛሉ፡፡ ለክልሉ የኢንቨስትመንት ቢሮም መዋዕለ ንዋይ በማፍሰስ ተጠቃሚ እንዲሆኑ  አድርገናል፡፡ ለነዋሪዎችም ሆነ ለክልሉ ትልቅ አማራጭን ይዘን መጥተናል ማለት ይቻላል፡፡

ሪፖርተር፡- የግብርናው ዘርፍ በዘመናዊ አሠራር ለማጎልበት በርካታ መዋዕለ ነዋይ አፍሰናል ብላችኋል፡፡ ይህ በዘርፉ ላይ ምን ዓይነት ለውጦችን አምጥቷል? በቀጣይስ ምን ለመሥራት አስባችኋል?

ወ/ሮ ቃልኪዳን፡- በግብርና ዘርፉ ላይ ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችን መጠቀም መቻል በራሱ ትልቅ ለውጥ ነው፡፡ በጋምቤላ ክልል ቲኝኬው ወረዳ ላይ ያገኘነውን መሬት በመጠቀም ሰሊጥ እና ማሾ በዓመት ሁለት ጊዜ እያመረትን ነው፡፡ ምርቱን ቀድመን ስለምንዘራ ሰብላችን ከሌሎች አርሶ አደሮች ቀድሞ ይደርሳል፡፡ ለአጨዳ ዘመናዊ ማሽነሪዎችን ስለምንጠቀም ምርቶቻችን በፍጥነት ይሰበሰባል፡፡ በመሆኑም ማሽነሪዎቻችንን ለክልሉ አርሶ አደሮች በውሰትም ሆነ በኪራይ እየሰጠን  የአገልግሎቱ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ማድረግ ችለናል፡፡ ባለን መሬት ላይ ሽንኩርት፣ ቲማቲምና ሌሎች ምርቶችን ለማምረት ዕቅድ ይዘናል፡፡ ቲማቲም፣ ሽንኩርትና ሌሎች ምርቶች ወደ ክልሉ የሚገቡት ከሌሎች ቦታዎች ነው፡፡ ይኼም የሆነበት ዋነኛ ምክንያት የክልሉ ነዋሪዎችም ሆነ የመንግሥት አመራሮች ሌሎች ምርቶች ላይ ትኩረት ባለመስጠታቸው ነው፡፡ ድርጅታችንም በቀጣይ ይኼንን ጥናት በማድረግ በቂ የሆኑ ምርቶችን ለማምረት ቅድመ ዝግጅት እያደረገ ይገኛል፡፡ በክልሉ የሚገኙ አርሶ አደሮች የእኛን ተሞክሮ በመውሰድ የተለያዩ ምርቶችን እንዲያመርቱ ግንዛቤ የምንሰጥ ይሆናል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ የሰሊጥ ምርታችንን የበለጠ ለማጎልበት እስራኤል አገር ከሚገኙ የግብርና ባለሙያዎች ጋር በመነጋገር ስምምነት ለመፈጸም ዕቅድ ይዘናል፡፡ በቀጣይም በአርባ ምንጭ፣ በባህር ዳር፣ በጎንደርና በደቡብ ክልሎች ላይ በመዘዋወር የተለያዩ ሥራዎችን ለመሥራት አቅደናል፡፡ የአፋር ክልልም ሥራዎችን እንድንሠራ ዕድሉን ሰጥቶናል፡፡ ጋምቤላ ክልል ላይ ዘመናዊ የሆኑ አሠራሮችን በመዘርጋት የተለያዩ ምርቶችን ለማምረት ከወዲሁ መሰናዶአችንን አጠናቀናል፡፡ ከዚህ ጎን ለጎን በዚያው በጋምቤላ ክልል ትልቅ መጋዘን ለመገንባት ዝግጅታችንን ጨርሰናል፡፡ መጋዘኑም ከተገነባ በኋላ የሰሊጥና የማሾ ምርቶችን እዚያው በማበጠር ምርቶቻችንን ኤክስፖርት የምናደርግ ይሆናል፡፡ በክልሉ ያሉት አብዛኛው መጋዘኖች ኋላቀር ናቸው፡፡ በተለይም ከባድ ዝናብ በሚዘንብ ወቅት አብዛኛው ጊዜ  ምርቶች ሲበላሹ ለማየት ችያለሁ፡፡ ይኼንንም ለመቅረፍ ድርጅታችን ዘመናዊ የሆነ መጋዘን ለማቋቋም ዲዛይኑን አጠናቋል፡፡

ሪፖርተር፡- በደብረብርሃን በ4.6 ሔክታር መሬት ላይ የሚያርፍ የመኪና መገጣጠሚያ ለመገንባት ዝግጅት ጨርሳችኋል፡፡ ምን ያህል ወጪ አድርጋችኋል? ለከተማዋ ነዋሪዎችስ ምን ዓይነት ጥቅም ይሰጣል?

Kaldian-Issayas---Interview-with-Ethiopian-Reporet

ወ/ሮ ቃልኪዳን፡- የመኪና መገጣጠሚያ ቦታውን ለማግኘት ከፍተኛ የሆነ ዋጋ ከፍለናል ማለት ይቻላል፡፡ የቦታውን ይዞታም ስናገኝም ለአርሶ አደሮች የሚያስፈልገውን ካሳ መክፈል ችለናል፡፡ ግንባታውም ከተጠናቀቀ በኋላ ከደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ ጋር በጋራ በመሆን በክልሉ የሚገኙ የቴክኒክ ሙያ ባለሙያዎችን ወደ ሥራው እንዲገቡ የሚደረግ ይሆናል፡፡ ሥራው ለቴክኒክና ሙያ ባለሙያዎች መልካም አጋጣሚ  ይፈጥራል፡፡ ከ200 በላይ የሚሆኑ ዜጎች የሥራ ዕድል የሚያገኙ ይሆናል፡፡ ባለሙያዎች ወደ ሥራ ከመግባታቸው በፊት በቂ የሆነ ሥልጠና ይሰጣቸዋል፡፡ ይኼም የዘርፉ ተዋናይ ለሆኑ ዜጎች ትልቅ አማራጭ ይፈጥራል፡፡

ሪፖርተር፡- በሥራችሁ ላይ ምን ዓይነት ተግዳሮቶች ገጥሟችኋል?

ወ/ሮ ቃልኪዳን፡- ትልቁ ተግዳሮት ብዬ የማነሳው የድርጅታችን 85 በመቶ ያህል ሴቶች በመሆናችን ከመንግሥትም ሆነ ከግል ድርጅቶች ይህንን ሥራ አይሠሩም የሚል ተግዳሮት ገጥሞናል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ የፋይናንስም ችግር አጋጥሞናል፡፡ ይሁን እንጂ ይህንን ሁሉ ችግር በማለፍና በድርጅቱ በኩል የተሠሩ ሥራዎችን በማሳየት እዚህ ደረጃ ልንደርስ ችለናል፡፡ በተለይም ደግሞ ሥራን የሚወድ ትውልድ ማግኘት በጣም ከባድ ሆኖብን ነበር፡፡ አብዛኛው ወጣት የግብርናም ሆነ ሌሎች ቴክኖሎጂን ተቅሞ አለመሥራቱ ለአገሪቱም ሆነ ለእኛ ጉዳት አሳድሮብናል፡፡ ለዚህ ዋነኛ ምክንያት በአሁኑ ወቅት ላይ የሚገኘው ትውልድ ሥራ ከመሥራት ይልቅ የሶሻል ሚዲያ ተጠቂ በመሆኑ ነው፡፡ ይህ ሥራችን ላይ በመጠኑም ቢሆን ተግዳሮት ሆኖብናል፡፡ ከዩኒቨርሲቲም የተመረቁ ወጣቶች የሥራ ዕድል ከመፍጠር ይልቅ ሌላ ነገር ውስጥ ስለተዘፈቁ ሥራችን ላይ እንቅፋት ሆኖብናል፡፡

ሪፖርተር፡- መንግሥት ምን ዓይነት ድጋፍ አድርጎላችኋል?

ወ/ሮ ቃልኪዳን፡- መንግሥት ለድርጅታችን ብዙ ድጋፎችን አድርጎልናል፡፡ ለዚህም ምሥጋና እናቀርባለን፡፡ ከመንግሥት ውጪም ባንኮች ከጎናችን በመሆን የተለያዩ ሥራዎችን እንድንሠራ ጉልህ ሚና ተጫውተዋል፡፡ የትራንስፖርት ሚኒስቴርም ትልቅ ድጋፍ አድርጎልናል፡፡ በተለይም በአዲስ አበባ በሥራ መግቢያና መውጫ ሰዓት ላይ ከፍተኛ የሆነ የትራንስፖርት ችግር ስላለ ይኼንን ዕድል ተጠቅመን ተግዳሮቶችን እንድንፈታ ረድቶናል፡፡

ሪፖርተር፡- በትራንስፖርት ዘርፍ ላይ የሚታየውን ችግር ለመቅረፍና መኪኖችን (ተሽከርካሪዎችን) ወደ ገበያ ለማቅረብ ከአቢሲኒያ ባንክ ጋር ስምምነት አድርጋችኋል፡፡ ስምምነቱ ምንድነው?

ወ/ሮ ቃልኪዳን፡- ከአቢሲኒያ ባንክ ጋር ያደረግነው ስምምነት በአምስት ዓመት ጊዜ ውስጥ በሚጠናቀቅ ብድር 100 ተሽከርካሪዎችን ለገበያ ለማቅረብ የታሰበ ነው፡፡ በስምምነቱ መሠረት 65 በመቶ የሚሆነውን ወጪ የአቢሲኒያ ባንክ ይሸፍናል፡፡ ባለ ላዳ ታክሲዎችም ሆኑ ሌሎች የማኅበረሰብ ክፍሎች አስፈላጊውን ቅድመ ሁኔታ በማሟላትና 35 በመቶ ቅድመ ክፍያ በመክፈል ዘመናዊ መኪና እንዲያኙ አማራጭ ይዘን መጥተናል፡፡ 35 በመቶውን ከከፈሉ በኋላ በየወሩ የተወሰነ ገንዘብ በመክፈል በአምስት ዓመታት ጊዜ ውስጥ እንዲያጠናቅቁ የሚደረግ ይሆናል፡፡ ከዚህ በፊትም 100 ተሽከርካሪዎችን ለተጠቃሚዎች ማድረስ ችለናል፡፡ እነዚህም ተጠቃሚዎች በአሁኑ ወቅት የሁለት ዓመት የሆናቸው ሲሆን፣ በየዓመቱም ክፍያቸውን በአግባቡ እየከፈሉ ይገኛል፡፡ በአጋጣሚም ሆነ በተለያዩ ምክንያቶች መክፈል ላልቻሉ አሽከርካሪዎች ድርጀቱ ከባንኩ ጋር በመነጋገር ተጨማሪ ጊዜ እንዲፈጠርላቸው የሚያደርግ ይሆናል፡፡ ይኼም ለተጠቃሚዎችም ሆነ ዘርፉ ላይ ያለውን ችግር በተወሰነ መልኩ የሚቀርፍ ይሆናል፡፡

ሪፖርተር፡- በቀጣይ ምን ለመሥራት አስባችኋል?

ወ/ሮ ቃልኪዳን፡- በቀጣይ ትልቁ ህልማችን ከመኪና መገጣጠም አልፎ ለማምረት ዕቅድ ይዘናል፡፡ ሌላው ደግሞ ከአዲስ አበባ ውጪ በተለያዩ ክልሎች የሚገኙ ኤርፖርቶች ውስጥ ለመሥራት ሁኔታዎችን እያመቻቸን እንገኛለን፡፡ ይህንንም ሥራ ከዛይራይድ ጋር የምንሠራ ይሆናል፡፡

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

ተዛማጅ ፅሁፎች

‹‹የውጭ ምንዛሪ እጥረት ሥራችን ላይ እንቅፋት ፈጥሮብናል›› አቶ ያዕቆብ ወልደ ሥላሴ፣ የሮያል ፎም ስፕሪንግ ፍራሽና የፕላስቲክ ውጤቶች ማምረቻ የኦፕሬሽን ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚ

የኢትዮጵያ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ወደ ተሻለ ደረጃ ከፍ እንዲል በኢንቨስትመንት ዘርፉ የተሰማሩ ተቋሞችን መደገፍ የግድ እንደሚል ይታመናል፡፡ መንግሥት ሊያደርግ ከሚችለው ድጋፍ አንዱ ደግሞ የውጭ...

‹‹የግንባታ ሠራተኞች የሚያስፈልገውን ክህሎት እንዲያሟሉ ትምህርታቸው በሥራ ላይ ልምምድ የታገዘ መሆን አለበት›› አቶ ሙሉጌታ ዘለቀ፣ የናሽናል ኮንስትራክሽን ሪልስቴት መሥራች

ናሽናል ኮንስትራክሽን ሪልስቴት የተመሠረተው በ2003 ዓ.ም. ነው፡፡ ላለፉት 13 ዓመታትም በተለይ ለቅይጥ አገልግሎት የሚውሉ ሕንፃዎችን ለደንበኞቹ በመሥራት ይታወቃል፡፡ ኢንጆይ ጀነራል ትሬዲንግ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል...

‹‹የኤድስ በሽታ ከ10 እስከ 24 ዕድሜ ክልል ባሉ ልጆች በሁለት እጥፍ እየጨመረ ነው›› ሲስተር ፈለቀች አንዳርጌ፣ በአዲስ አበባ ጤና ቢሮ የኤችአይቪ ኤድስ ዘርፍ...

የኤችአይቪ ኤድስ ሥርጭት ከቦታ ቦታ ቢለያይም እየጨመረ ስለመምጣቱ ይነገራል፡፡ አዲስ አበባም የችግሩ ሰለባ ከሆኑ የአገሪቱ ክፍሎች አንዷ ናት፡፡ ሲስተር ፈለቀች አንዳርጌ በአዲስ አበባ ጤና...