Friday, July 12, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዓለምየሱዳኑ አል ቡርሃን ሲቪሎች ተወያይተው የሽግግር መንግሥት እንዲያቋቁሙ ጥሪ አቀረቡ

የሱዳኑ አል ቡርሃን ሲቪሎች ተወያይተው የሽግግር መንግሥት እንዲያቋቁሙ ጥሪ አቀረቡ

ቀን:

ሱዳንን ለ30 ዓመታት ያህል የመሯት የቀድሞው የሱዳን ፕሬዚዳንት ኦማር አል በሽር እ.ኤ.አ. በሚያዝያ 2019 በመፈንቅለ መንግሥት ከሥልጣን ከተወገዱ በኋላ ሱዳናውያን በፈለጉት መሪ የመተዳደር ዕድል አላገኙም፡፡

በሽር ከሥልጣን እንዲወርዱ ምሁራንን ጨምሮ የተለያዩ የሲቪል ማኅበረሰብ አባላት፣ የዴሞክራሲ አቀንቃኞችና ፖለቲከኞች የተሳተፉበት አብዮት ቢካሄድም፣ ዛሬም ሱዳናውያን ጥያቄያቸው አልተመለሰም፡፡

በሽር ከሥልጣን ከተነሱ ማግሥት ጀምሮ በሱዳን መከላከያና በሲቪሎች  በኩል የነበረው ሽኩቻ፣ ሱዳን በሁለቱም ጥምረት እንድትመራ፣ ጥምር የሽግግር መንግሥቱም አጠቃላይ ምርጫ አድርጎ በሱዳን የሲቪል መንግሥት ሥልጣን እንዲቆጣጠር ከስምምነት ተደርሶ የነበረ ቢሆንም፣ ለዚህ ፍንጭ የሆነ አሠራር አልተስተዋለም፡፡

የሽግግር መንግሥቱ ጠቅላይ ሚኒስትር የነበሩት አብደላ ሃምዶክ በሱዳን ለውጥ ለማምጣት ጥረት ቢያደርጉም፣ አብሯቸው ከሚሠራው የሱዳን መከላከያ ጋር ስምምነት ባለመፈጠሩ፣ እሳቸውም በመከላከያው እ.ኤ.አ. በጥቅምት 2021 መፈንቅለ መንግሥት እንደተደረገባቸው ይታወሳል፡፡

የሱዳን ፖለቲከኛ፣ የሱዳን ጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥና በሽግግር መንግሥቱ የመከላከያ ካውንስሉ ሊቀመንበር አብዱል ፈታህ አል ቡርሃን መፈንቅለ መንግሥቱን መርተው ሱዳንን በወታደራዊ አገዛዝ ሥር ባደረጉ በዘጠነኛ ወራቸው ደግሞ፣  በሱዳናውያን ጠንካራ ተቃውሞ ተነስቶባቸዋል፡፡

አል ቡርሃን የሲቪል ሽግግር መንግሥቱን ገልብጠው ሱዳንን በወታደራዊ አገዛዝ ሥር ካደረጉ በኋላ በርካታ መለስተኛ ተቃውሞ ያስተናገዱ ቢሆንም፣ ባለፈው ሳምንት እንደተጀመረው ዓይነት ከፍተኛ ተቃውሞ አልገጠማቸውም፡፡

ባለፈው ሳምንት ተጀምሮ ስድስተኛ ቀኑን የያዘው ሕዝባዊ ተቃውሞ ዋና አጀንዳ አል ቡርሃን ከሥልጣን ይውረዱ፣ ሲቪል የሽግግር መንግሥት ይቋቋም እንዲሁም በሱዳን በምርጫ የሚያሸንፍ ፓርቲ አገሪቱን ይግዛ የሚል ነው፡፡

በአል ቡርሃን መፈንቅለ መንግሥት ከሥልጣን ተሰናብተው በሕዝቡ ተቃውሞ ወደ ሥልጣን የተመለሱትና በኋላም ‹‹በፈቃዴ ሥልጣን ለቅቄያለሁ›› ባሉት የቀድሞ የሱዳን ሽግግር መንግሥት ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሃምዶክ ጊዜም መከላከያው ከጥምር የሽግግር መንግሥቱ እንዲወጣ የብዙ ፓርቲዎች ጥያቄም ነበር፡፡

በጥምር ሽግግር መንግሥቱ ወቅት የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ሲቪል ሶሳይቲና ምሁራን መከላከያው ከሽግግር መንግሥቱ እንዲወጣ በተደጋጋሚ ከመጠየቅ ባለፈም በማንኛውም አገራዊ አጀንዳ ከመከላከያ መሪዎች ጋር እንደማይወያዩ ሲገልጹም ነበር፡፡

ከባለፈው ሳምንት ጀምሮ ደግሞ በሱዳን ዋና ከተማ ካርቱምና በአንዳንድ አካባቢዎች ‹‹ወታደራዊ አገዛዝ ያብቃ›› የሚል ተቃውሞ ተጀምሯል፡፡

ምሁራንን ጨምሮ በሺዎች የሚቆጠሩ ሱዳናውያን ተቃውሟቸውን ማድረግ ከጀመሩ ወዲህ ዘጠኝ ሰዎች በመከላከያ መገደላቸውን ዓለም አቀፍ ሚዲያዎች ዘግበዋል፡፡

የፀጥታ አካላት ተቃውሞውን ለመበትን የሚጠቀሙት ከፍተኛ ምት ያለው ውኃ፣ አስለቃሽ ጭስና የጦር መሣሪያ (ጥይት) መሆኑን ደግሞ የሕክምና ባለሙያዎችና የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ)ን ጠቅሶ ቪኦኤ የዘገበ ሲሆን፣ ተቃዋሚዎችም ጎማ በማቃጠልና መንገድ በመዝጋት ተቃውሟቸውን እንደሚገልጹ አስታውቋል፡፡

አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ ለተቃውሞ የወጡትን ጠቅሶ እንዳሰፈረው፣ ወታደራዊ አገዛዙ ሥልጣን እስካልለቀቀ ድረስ ተቃውሞው ይቀጥላል፡፡

‹‹አብዮታችን ግቡን እስኪመታ ድረስ ተቃውሟችን ይቀጥላል፤›› የሚሉት አብዮተኞች ነፃነት፣ ሰላም፣ ፍትሕ፣ የሲቪል አገዛዝ እንዲሰፍንና መከላከያው ወደ ካምፑ እንዲገባ እንደሚፈልጉም አስታውቀዋል፡፡

እሑድ ሰኔ 26 ቀን 2014 ዓ.ም. የመከላከያ መኪኖችን ጨምሮ በርካታ ቁጥር ያላቸው የደኅንነት አካላትና ፈጥኖ ደራሽ ኃይሎች በካርቱም ጎዳናዎች ላይ መታየታቸውን ያሰፈረው ቪኦኤ፣ ፈጥኖ ደራሽ ኃይሎች የሚባሉት እ.ኤ.አ. በ2003 በምዕራብ ሱዳን በምትገኘው ዳርፉር ለተቀሰቀሰው ግጭት ተጠያቂ እንደነበሩም አስታውሷል፡፡

በቅርቡ በወታደራዊ መንግሥቱ ላይ ተነስቶ የነበረውን ተቃውሞ ለመበተንም ተሳትፈዋል በሚል እንደሚኮነኑ አስፍሯል፡፡

አልበሽር ከሥልጣን ከተነሱ በኋላ በአገሪቱ ዴሞክራሲያዊ መንግሥት እንዲመሠረት የተደረገው ጥረትና የሕዝቡም አብዮት ላለፉት ሦስት ዓመታት ያህል አልተሳካም፡፡

የምሥራቅ አፍሪካ በይነ መንግሥታት (ኢጋድ)ን ጨምሮ ተመድና አፍሪካ ኅብረት በወታደሮቹና በሲቪል መካከል ውይይት እንዲደረግ ያደረጉት ጥረትም እንዲሁ፡፡

ዋና የሚባሉት ሲቪል ፖለቲከኞችና ምሁራን ከወታደራዊ ክፍሉ ጋር አንወያይም፣ ወታደራዊ ክፍሉ ለመወያየት መቀመጥ የለበትም፣ ሱዳን የምትመራው በሲቪል አስተዳደር መሆን አለበት በማለታቸውም ውይይቶች ሳይሳኩ ቀርተዋል፡፡

ሰሞኑን የተቀሰቀሰውን ተቃውሞ ተከትሎ ደግሞ በአል ቡርሃን የሚመራው ወታደራዊ አገዛዝ ‹‹ማንኛውም የፖለቲካ ውይይት ውስጥ አንገባም፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ተወያይተው ሲቪል የሽግግር መንግሥት ያቋቁሙ፤›› ማለቱን ሮይተርስ ዘግቧል፡፡

አል ቡርሃን እንዳሉት፣ መከላከያው በውይይት ላለመሳተፍ ውሳኔ ያሳለፈው፣ የፖለቲካና አብዮታዊ ቡድኖች መንግሥት እንዲመሠረቱ ለማስቻል ነው፡፡

ከአል በሽር መፈንቅለ መንግሥት በኋላ በርካታ የሲቪል ፖለቲከኞች ከመከላከያው ጋር ድርድር ከመቀመጥ ራሳቸውን አግልለው የነበረ በመሆኑ፣ የአል ቡርሃን ውሳኔ ለሲቪል ፖለቲከኞች ወደ ሱዳን ፖለቲካ መቀላቀል በር ይከፍታል ተብሏል፡፡

አል ቡርሃንም፣ የሲቪል አካላት ሱዳንን ወደ ዴሞክራሲያዊ ሽግግር ለማምጣት ወሳኝ ውይይት እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበው መከላከያው የውይይቱን ውጤት ያስተገብራል ብለዋል፡፡

አል ቡርሃን ይህንን ይበሉ እንጂ፣ በየቀኑ ቁጥራቸው እየጨመረ የመጣው ተቃዋሚ ሠልፈኞች፣ ‹‹አል ቡርሃን ከሥልጣን አሁኑኑ ይልቀቁ›› በማለት ተቃውሟቸውን ቀጥለዋል፡፡

የሲቪልና የመከላከያ አካላት የተጣመሩበትና በአል ቡርሃን የሚመራው የሱዳን ሽግግር መንግሥት ሉዓላዊ ካውንስል አዲስ መንግሥት ከተመሠረተ በኋላ እንደሚፈርስ አል ቡርሃን በቴሌቪዥን ባደረጉት ንግግር ቢያስታውቁም፣ በተቃዋሚዎቹ በኩል ጥርጣሬ እንዳለ አልጀዚራ ዘግቧል፡፡

የዴሞክራሲ አቀንቃኝ ቡድኖችም፣ አዲስ መንግሥት መመሥረት ረዥም ጊዜ ይወስዳል፣ ወታደራዊ መንግሥቱ በሥልጣን እንዲቆይ ያደርጋል፣ በመሆኑም ወታደራዊ አገዛዙ ሥልጣን ይልቀቅ ብለዋል፡፡

የጄኔራል አል ቡርሃን ንግግር በምሁራንና በዴሞክራሲ አቀንቃኞች በኩል እምብዛም ተቀባይነት አላገኘም፡፡ ተቃዋሚዎች እንደሚሉትም፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ውይይት አድርገው መንግሥት እስኪመሠርቱ ወታደራዊ አገዛዙ በሥልጣን መቆየት የለበትም፡፡

አል ቡርሃን ከዚህ ቀደም ሥልጣን ለመያዝ ያነሳሳቸው በፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል ያለው ልዩነት እንደሆነ መጠቆማቸውን ያስታወሱት ሲቪሎች፣ አሁንም የፖለቲካ ፓርቲዎቹ በአጭር ጊዜ ከስምምነት ካልደረሱ የአል ቡርሃን በሥልጣን የመቆየት ዕድል ሰፊ በመሆኑ የአል ቡርሃንን አካሄድ እንደማይቀበሉ እየገለጹ ነው፡፡

 እሳቸው አሁኑኑ ሥልጣን ለቀው ሲቪል የሽግግር መንግሥት እንዲቋቋምና የፖለቲካ ፓርቲዎችም በሲቪል የሽግግር መንግሥት ሥር ሆነው እንዲወያዩ ለማድረግ ተቃውሟቸውን እንደሚቀጥሉ አስታውቀዋል፡፡

በአል ቡርሃን የሚመራው ወታደራዊ ክፍል ሱዳንን ላለፉት ዘጠኝ ወራት በመራበት ወቅት በተካሄዱ የተቃውሞ ሠልፎች 133 ሰዎች ተገድለዋል፡፡ ታዛቢዎች እንደሚሉትም፣ ከእነዚህ ውስጥ 18ቱ ሕፃናት ናቸው፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የሰብዓዊ መብት ጉዳይና የመንግሥት አቋም

ሰኔ ወር አጋማሽ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) ከፍተኛ የሰብዓዊ...

ከሰሜኑ ጦርነት አገግሞ በሁለት እግሩ ለመቆምና ወደ ባንክነት ለመሸጋገር የተለመው ደደቢት ማክሮ ፋይናንስ

በኢትዮጵያ የፋይናንስ ኢንዱስትሪ ውስጥ በቀዳሚነት ስማቸው ከሚጠቀሱት ውስጥ ደደቢት...