ባለፈው ሳምንት መገባደጃ የተካሄደው የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ (ኢዜማ) ፓርቲ ምርጫ ትኩረት ከሳቡ የፖለቲካ ጉዳዮች አንዱ ነበር፡፡ ብርሃኑ ነጋ (ፕሮፌሰር)፣ እንዲሁም ዮሐንስ መኮንን (አርክቴክት) የፓርቲው መሪና ምክትል መሪ ሆነው ሲመረጡ፣ አቶ አበበ አካሉ ደግሞ የፓርቲው ዋና ጸሐፊ ሆነው ተመርጠዋል፡፡ እስከ እሑድ እኩለ ሌሊት ሲጠበቅ የቆየው የፓርቲ የአመራሮች ምርጫ ለሊቀመንበርና ለምክትል ሊቀመንበርነት አዳዲስ ሰዎችን አስመርጧል፡፡
ጫኔ ከበደ (ዶ/ር) በሊቀመንበርነት ሲመረጡ፣ አማኑኤል ኤርሞ (ዶ/ር) ደግሞ በምክትል ሊቀመንበርነት መመረጣቸው ይፋ ሆኗል፡፡ በፋይናንስ ኃላፊነት አቶ አንድነት ሽፈራውን ማስመረጡንም ፓርቲው ይፋ አድርጓል፡፡ በምደባ ሳይሆን በአባላት ምርጫ የተለያዩ የኃላፊነት ቦታዎች ላይ የሚቀመጡ ሰዎችን ፓርቲው መወሰኑ አዲስ ነገር አልነበረም፡፡ ልክ እንደ ኢዜማ ሁሉ ሌሎች ፓርቲዎችም ጠቅላላ ጉባዔ ማድረጋቸውና በአባላት ድምፅ አመራሮቻቸውን መወሰናቸው የተለመደ ነው፡፡ ከዚህ ይልቅ በምርጫው ወቅት የታየው ፉክክርና የምረጡኝ ቅስቀሳ ከሁሉም የተለየ እንደሆነ ነው ብዙዎች እየመሰከሩለት የሚገኘው፡፡
ብዙ ደጋፊዎች እንዳሉት የሚገመተው ኢዜማ ከሰሞኑ ያካሄደው ምርጫ በተቃዋሚዎቹ ዘንድ ጭምር ተጠባቂ ነበር፡፡ አንዳንዶች፣ ‹‹ኢዜማ ብልፅግናን መረጠ፤›› በማለት የብርሃኑ ነጋ (ፕሮፌሰር) መመረጥን ሲተቹ፣ ሌሎች በበኩላቸው፣ ‹‹ፓርቲው የገዥው ብልፅግና ፓርቲ ተለጣፊ ሆኖ ይቀጥላል፤›› በማለት አሉታዊ ግምታቸቸውን ሰጥተዋል፡፡ ራሱን ችሎ ቢቆም ወይም የበለጠ ቢጠናከር፣ እንዲሁም የፖለቲካ ውክልና በማጣት ፅንፍ በወጣ የብሔር ፖለቲካ ሲወዛገብ የቆየውን የኢትዮጵያዊ ብሔርተኝነት ደጋፊ የሆነውን ሕዝብ ቢያንቀሳቅስ፣ ኢዜማ ጠንካራ የፖለቲካ ድርጅት እንደሚሆን ግምታቸውን ሲያስቀምጡ ነበር፡፡
በብዙ መንገዶች የዜግነት ፖለቲካ ያራምዳሉ ከሚባሉ ፓርቲዎች አንዱ የሆነው ኢዜማ፣ የኢትዮጵያዊ ብሔርተኝነት (የአንድነት ኃይሉን) ወካይ ፓርቲ ነው ይባላል፡፡ በምርጫው ሒደት ለአመራርነት ተፎካካሪ ሆነው የቀረቡ ዕጩዎች በመካከላቸው የታየው የሚዲያ መተቻቸት፣ ፉክክርና ሽኩቻ የበለጠ ተጋግሎ ፓርቲውን ለመከፋፈል እንዳይዳርገው ሲሠጋም ነበር፡፡ ከዚህ ቀደም ሰፊ የሕዝብ ንቅናቄ ፈጥረው፣ ነገር ግን ብዙም ሳይሰነብቱ የመበታተንና የመከፋፈል ዕጣ እንደ ገጠማቸው እንደ ቅንጅት ወይም አንድነት ፓርቲዎች ያለ አጋጣሚ፣ በኢዜማ ውስጥም ሊፈጠር ይችላል የሚለው ሥጋት አይሎ ነው የሰነበተው፡፡
የኢዜማ መከፋፈል ወይም በውስጡ አንጃ መፈጠር ደግሞ ፓርቲውን ከማዳከም አልፎ፣ የፖለቲካ ውክልና እያጣ የመጣውን የኢትዮጵያዊ ብሔርተኝነት (አንድነት) ኃይሉን የበለጠ አማራጭ ለማጣት ያጋልጠዋል የሚለው ፍራቻ ጎልቶ ነው የከረመው፡፡
ከአቶ አንዷለም አራጌ ጎን በመሆን ለፓርቲው ምክትል መሪነት ሲፎካከሩ የከረሙት አቶ ሀብታሙ ኪታባ፣ በምርጫው ዋዜማ ደጋፊዎች እንዳይደናገጡ ተናግረው ነበር፡፡ ‹‹ዴሞክራሲን መናገር፣ ዴሞክራሲን ማስተማርና ዴሞክራሲን መተግበር በጣም ይለያያል፤›› ሲሉ በምርጫው ዋዜማ የተናገሩት አቶ ሀብታሙ፣ እያንዳንዱ ዜጋ መደናገጥ እንደሌለበት በመጠቆም፣ ‹‹በእኛ በኩል በጠቅላላ ጉባዔው ማንም ቢመረጥ በጋራ ለመሥራት ዝግጁ ነን፤›› በማለት ነበር የተናገሩት፡፡
የኢዜማ የአመራሮች ምርጫ ፉክክር ሲጀምር ዕጩ ተፎካካሪዎች በሚዲያዎች ጠንከር ያሉ ትችቶች ሲወራወሩ መታየታቸው፣ ፓርቲው ወዴት እያዘገመ ነው የሚል ስሜት አጭሮ ነበር፡፡ በተለይ በመሪነት ለመመረጥ በሚፎካከሩት በአቶ አንዷለምና ብርሃኑ (ፕሮፌሰር) መካከል ልዩነቶች መስፋታቸውን፣ በምርጫው ዋዜማ ከነበረው ድባብ በቀላሉ መገንዘብ ይቻል ነበር፡፡
የፓርቲው ምክትል መሪ በመሆን የተመረጡት የኪነ ሕንፃ ባለሙያው አቶ ዮሐንስ፣ ሥጋቱ የውጭ ታዛቢዎች ብቻ ሳይሆን በውስጥ ያሉ አባላትም ጭምር ነበር ይላሉ፡፡ ዕጩ ተፎካካሪዎች ከታች የመጡበት የምርጫ ወረዳ ድረስ ገብተውና በተለያዩ ክልሎች ተንቀሳቅሰው የምረጡኝ ቅስቀሳ ሲያድርጉ መቆየታቸውን አቶ ዮሐንስ ያስረዳሉ፡፡ ‹‹የምርጫው ዓላማ የውስጥ ዴሞክራሲ ልምምድ አካል ነው፡፡ በፕሮግራማችን መሠረት የሚካሄድ ምርጫ ነው፡፡ በነፃነት የፈለጋችሁትን መምረጥ ትችላላችሁ፡፡ አልተመረጥኩም ብሎ ጠመንጃ የሚመዝም ሆነ አንጃ የሚፈጥር ኃይል አይኖርም ብለን በቃልም ሆነ በሰነድ ጭምር ለፓርቲው አባላት ቃል ገብተናል፤›› በማለት ነበር ፓርቲው የተከተለውን የምርጫ ሒደት የዘረዘሩት፡፡
አቶ ዮሐንስ የምርጫው ሒደት ሥጋት የፈጠረበትን ሌሎች ምክንያቶች ሲያስቀምጡም፣ አንደኛው መነሻ የተለመደው የፖለቲካ ባህል መሆኑን ያመለክታሉ፡፡ ‹‹በኢትዮጵያ ገዥ ፓርቲዎችን ጨምሮ ጠቅላላ ጉባዔ የሚካሄድበትና የአመራር ምርጫ የሚደረግበት ወቅት ብዙ ጊዜ አስጨናቂና በውዝግቦች የተሞላ ነው፤›› ሲሉ ይገልጹታል፡፡ ከዚህ አንፃር የኢዜማ አመራሮች ምርጫ ሲቃረብ ይኼው ሥጋት አይሎ እንደነበር የጠቆሙት አቶ ዮሐንስ፣ በዋዜማው የነበሩ የሚዲያ ቃላት መወራወሮችን በመመካከር በረድ እንዲሉ ማድረጋቸው፣ ፓርቲው የተሳካ ጠቅላላ ጉባዔና የአመራሮች ምርጫ ለማድረግ እንደረዳው ነው የገለጹት፡፡
ከብርሃኑ (ፕሮፌሰር) በተቃራኒ ተሠልፈው ለፓርቲ መሪነት የተፎካከሩት አቶ አንዷለም፣ ከምርጫው ቀን ቀደም ብሎ በተቀናቃኛቸው ላይ ጠንከር ያሉ ትችቶችን ሲሰነዝሩ ቆይተዋል፡፡ ይሁን እንጂ በምርጫው ዕለት ምሽት ሁለቱ ተፎካካሪዎች ሲተቃቀፉና መልካም ምኞት ሲገላለጹ መታየታቸው፣ ለብዙዎች አስገራሚ ትዕይንት ነበር የሆነው፡፡ ሁኔታው ከዚህ ቀደም በኢትዮጵያ ፖለቲካ ያልታየና አዲስ የዴሞክራሲ ባህል በኢዜማ ውስጥ እያቆጠቆጠ ነው የሚል ግምት በአንድ ወገን አሰጥቷል፡፡ ይሁን እንጂ ይህን ለመቀበል የተቸገሩ ወገኖች በሁለቱ ተፎካካሪ ግለሰቦች መካከል የተፈጠረው ልዩነት፣ በምርጫው ይጠገናል ብለው እንደማያምኑና ፓርቲውንም ለመከፋፈል እንደሚያበቃው እየገመቱ ነው፡፡
ወደ 900 አባላት በተገኙበት ጠቅላላ ጉባዔ የተካሄደው የአመራር ምርጫ ልክ እንደ ምረጡኝ ዘመቻው ሁሉ ከፍተኛ ፉክክር እንደታየበት ነው ፓርቲው ይፋ ያደረገው፡፡ ብርሃኑ (ፕሮፌሰር) 549 ድምፅ ወይም 62 በመቶ የጉባዔተኛውን ድጋፍ በማግኘት በአብላጫ ድምፅ ማሸናፋቸው ሲገለጽ፣ አቶ አንዷለም ደግሞ 326 ድምፅ ማግኘታቸው ተነግሯል፡፡ ይህ ሁኔታ ደግሞ ሁለቱ በተቃራኒ ቆመው ለመሪነት ሲፎካከሩ የነበሩ አመራሮች፣ በጉባዔተኛው ዘንድ ቀላል የማይባል ድጋፍ እንዳላቸው የሚጠቁም ነበር፡፡
በምርጫ ፉክክሩ ወቅት በፓርቲው ውስጥ ለውጥ ሊመጣ እንደሚገባ ሲሞግቱ የቆዩት አቶ አንዷለም፣ በተፎካካሪያቸው ላይ ሲያነሱዋቸው ከነበሩ ቅሬታዎች አኳያ የሁለቱ ወገኖች ፉክክር ወዳልተፈለገ አቅጣጫ እንዳይሄድ ቢያሠጋም፣ በምርጫው ዕለት ግን የሆነው ከዚህ የተለየ ነበር፡፡ በምርጫው ዋዜማ አቶ አንዷለም ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ ግን፣ ፉክክሩ ሁሉ ፓርቲውን ጠንካራ መሠረት ላይ ለመገንባት የሚደረግ ጥረት መሆኑን አስታውቀው ነበር፡፡
‹‹ኢዜማ ይፀናል፡፡ ኢዜማ ሐሳብ ነበር፡፡ አሁን ደምና ሥጋ እያለበስነው ነው፡፡ የዛሬ ሦስት ዓመት ደግሞ ከዚህ የተሻለ ውብ ምርጫ እናደርጋለን፤›› ሲሉ የተናገሩት አቶ አንዷለም፣ የምርጫ ሒደቱ የፓርቲ ዴሞክራሲ ግንባታ እንጂ፣ ፓርቲውን የመከፋፈልም ሆነ የማፍረስ ዓላማ እንደሌለው ቃል ገብተው ነበር፡፡
የኢዜማ ሰሞነኛ የአመራሮች ምርጫና ጠቅላላ ጉባዔ አዲስና ያልተለመዱ ሒደቶችን ማሳየቱ፣ በብዙዎች ዘንድ በጎ ግብረ መልስ እያገኘ ነው የሚገኘው፡፡ በምርጫ ሒደቱ ሲፎካከሩ የቆዩና በምርጫው ያላሸናፉ ኃይሎች ያነሷቸውን ጥያቄዎችና ሥጋቶችን ፓርቲው ቸል ሳይል ማስተናገድ እንዳለበት የጠየቁ በርካቶች ናቸው፡፡ ድርጅቱ በምርጫው ሒደትና በፉክክሩ ወቅት ያጋጠሙትን ፈተናዎች መማሪያ በማድረግ ራሱን እንዲያሻሽል የጠየቁም ብዙ ናቸው፡፡ ከሁሉ በላይ ግን ኢዜማ ያሳየው የጠቅላላ ጉባዔና የአመራሮች ምርጫ ዴሞክራሲዊ ጅማሮ በሌሎች ዘንድ ሰፍቶ፣ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ባህል እንዲሆን ምኞታቸውን የገለጹ ቁጥራቸው በርካታ ሆኖ ነው የተገኘው፡፡ በተለያዩ ማኅበራዊ የትስስር ገጾች ግርጌዎችና ብሎጎች ላይም ይኼው ሲንፀባረቅ ነበር የከረመው፡፡

ስለምርጫው፣ ስለጠቅላላ ጉባዔና ስለፓርቲው ቀጣይ አቅጣጫዎች ከሪፖርተር ጋር በስልክ ሰፊ ቆይታ ያደረጉት የፓርቲው አዲስ ተመራጭ ምክትል መሪ፣ ‹‹ከእነ ጉድለቱም ቢሆን በዚህ ምርጫ አዲስ የዴሞክራሲ ባህል አሳይተናል፤›› ሲሉ ነው የተናገሩት፡፡
በወለጋና በተለያዩ የኢትዮጵያ አካባቢዎች የደረሱ ግድያዎችና ሐዘኖች የአገሪቱን የፖለቲካ ድባብ የለወጡት ቢሆንም፣ ‹‹በዚህ ፈታኝ ወቅትም ውስጥ ሆነን ከባድ ፈተናን መሻገር የቻልንበትን ዴሞክራሲዊ ምርጫ ማሳካት ችለናል፤›› ሲሉ አቶ ዮሐንስ ገልጸዋል፡፡
‹‹ከዚህ ቀደም የፓርቲዎች ጠቅላላ ጉባዔ ደረሰ ወይም ምርጫ ሊደረግ ነው ሲባል፣ እጅግ ሲፈተኑ እያየን ነው የኖርነው፡፡ አሁን እሱን አስቸጋሪ ሁኔታ ኢዜማ አልፎ የተሳካ ዴሞክሲያዊ የአመራር ምርጫና ጠቅላላ ጉባዔ አካሄዷል፡፡ በምርጫው ሒደት ከእኛም ልምድ ማጣት የተነሳ በየሚዲያውና በየአደባባዩ ስህተት መሥራታችንን መደበቅ አንችልም፡፡ እንዲህ ተነጋግረውማ አብረው መቀጠል ይቸገራሉ የሚል ግምት በሕዝቡ ዘንድ ያደረውም በዚህ የተነሳ ነው፡፡ ነገር ግን መስመር ስቶ የነበረውን የሚዲያ አጠቃቀማችንን ወዲያው በማረማችን እንደ ፓርቲ ተጠቅመናል፤›› ሲሉ ነበር የሒደቱ ፈታኝ ምዕራፍ እንዴት እንደታለፈ ያስረዱት፡፡
‹‹በአሁኑ ምርጫ ዕድል ያላገኙ ወገኖች ካሸነፉት ጋር በጋራ መቆማችንን፣ በዚህ የምርጫና ጉባዔ ሒደት ያሸነፈው ፓርቲችን መሆኑን፣ የመነቃቀፉ ጊዜ አብቅቶ ተቃቅፎ በጋራ የመቆሙ ጊዜ መጀመሩን ምርጫው እንደተጠናቀቀ አሳይተናል፤›› በማለት ምክትል መሪው ተናግረዋል፡፡ ‹‹ፉክክሩ ተዘርግቶ ትብብሩ መከፈቱን አሳይተናል፤›› ሲሉ የጠቀሱት አቶ ዮሐንስ፣ ፓርቲያቸው ያለፈበት የምርጫ ሒደት ራስን ከማጠናከርና ለቀጣይ ትግል ከማዘጋጀት በዘለለ የመከፋፈልም ሆነ የአንጃ ሥጋት እንደማይኖርበት ነው ያሰመሩበት፡፡
‹‹እኛ እንኳን ጓደኞቻችንን ቀርቶ ለአገር ሰላምና አንድነት ሲባል በማያሳምን ምርጫ ሥልጣን ላይ የወጣውን ብልፅግናንም የተሸከምን ነን፤›› ሲሉ የተናገሩት አቶ ዮሐንስ፣ ፓርቲዎች ዴሞክራሲያዊ የምርጫ ሥርዓት የሰፈነባት ኢትዮጵያ መገንባት ከፈለጉ፣ በመሠረታዊነት ራሳቸውን በውስጣዊ ዴሞክራሲ መፈተን እንዳለባቸው ነው ያሳሰቡት፡፡ ከዚህ አንፃር ፓርቲያቸው ከሰሞኑ ባካሄደው የተሳካ ውስጣዊ ዴሞክራሲ የሚፈልገውን መልዕክት ለሌሎች ማስተላለፉን ገልጸዋል፡፡ ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን መገንባት የሚመኝ ሁሉ አስቸጋሪ ቢሆንም እንኳን ወሳኝ ውስጣዊ የዴሞክራሲ ሒደት ማለፍ ይኖርበታምል ብለዋል፡፡
‹‹ከኢዜማ የተሻለ፣ ሁሉንም አሰባሳቢ የሆነ የፖለቲካ ፕሮግራምና ርዕዮተ ዓለም ያለው ፓርቲ በኢትዮጵያ አለ ብዬ አላምንም፤›› ሲሉ የተናገሩት አቶ ዮሐንስ፣ ከዚህ አንፃር ኢዜማ ሁሉንም ኢትዮጵያዊ ወካይ ፓርቲ ሆኖ መቀጠል በሚያስችል የተሟላ ተክለ ቁመና ላይ እንደሚገኝ ነው በማጠቃለያቸው ያወሱት፡፡