Tuesday, November 28, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊበወንድ ሕፃናት ላይ የሚፈጸሙ ወሲባዊ ጥቃቶች መበራከታቸው ተገለጸ

በወንድ ሕፃናት ላይ የሚፈጸሙ ወሲባዊ ጥቃቶች መበራከታቸው ተገለጸ

ቀን:

በመጤ ልማዳዊ ድርጊቶች ምክንያት በወንድ ሕፃናት ላይ የሚፈጸሙ ወሲባዊ ጥቃቶች መበርከታቸውን የአዲስ አበባ ከተማ ሴቶች ሕፃናትና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ አስታውቋል፡፡

‹‹በሕፃናት ላይ የሚፈጸሙ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችን በጋራ እንከላከል›› በሚል መሪ ቃል እየተከበረ ያለው የዓለም ሕፃናት ቀን የማጠቃለያ ፌስቲቫል አስመልክቶ ቢሮው ሰኔ 28 ቀን 2014 ዓ.ም. መግለጫውን ሰጥቷል፡፡

ምክትል ቢሮ ኃላፊና የሕፃናት ዘርፍ ኃላፊው ታምራት ዘለዓለም (ዶ/ር) እንደገለጹት፣ በአሁኑ ጊዜ በሕፃናት ላይ የሚፈጸሙ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች ዓይነቶቻቸው እየጨመረ መጥቷል፡፡

በተለይ በወንድ ሕፃናት ላይ ወሲባዊ ጥቃቶች መበራከታቸውን የሚያሳዩ መረጃዎች በእጃቸው እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡

በወንድ ሕፃናት ላይ የሚፈጸሙ ወሲባዊ ጥቃቶች መበራከታቸው ተገለጸ | Ethiopian Reporter | ሪፖርተር

ድርጊቱ በብዛት የሚፈጸምባቸው ከአሥር ዓመት በታች የሆኑ ሕፃናት ላይ ሲሆን፣ የሰባትና የዘጠኝ ዓመት ወንድ ሕፃናት ላይ እንዲሁ እንደሚደርስባቸው ተናግረዋል፡፡ ከወንድ ሕፃናት በተጨማሪ በሴት ሕፃናትም ላይ ልዩ ልዩ ወሲባዊ ጥቃቶች እንደሚደርሱባቸውም ጭምር፡፡

ጥቃቱ የሚፈጸመው በአዋቂዎች ብቻ ሳይሆኑ በእኩዮቻቸው መሆኑን ያስረዱት ኃላፊው እነዚህን ችግሮች ለመቅረፍ የማኅበረሰቡን ግንዛቤ ማሳደግና በሕግ ተጠያቂነት እንዳለ ለማሳወቅ እየተሠራ ይገኛል ብለዋል፡፡

በማወቅና ባለማወቅ በሕፃናት አዕምሮ አጓጉል ነገር የሚዘሩ መኖራቸውን ሕፃናቱ ድርጊቱን ሲለማመዷቸው እንደሚታዩና አዋቂዎችም በዚሁ ተግባር ውስጥ እንዳሉም ገልጸዋል፡፡

በቅርቡ የተፈጸመውን ድርጊት ያነሱት ኃላፊው፣ ለሕግ ቀርበው እንደተፈረደባቸውና በሕግ ክትትል ሥር የሚገኙ በርካታ ጉዳዮች መኖራቸውን አስረድተዋል፡፡

በሌላ በኩልም አካላዊ ጥቃቶችም በሕፃናት ላይ እንደሚደርሱ፣ መደብደብን እንደ መብት የሚቆጥሩ መኖራቸውን የተናገሩት ኃላፊው በተለይም ሕፃናቱ የሚሟገትላቸው ባለመኖሩ ጉዳቱ እንደሚያመዝንና በየቀኑ የጉዳት ሰለባ የሆኑ ሕፃናት ወደ ቢሮው እንደሚመጡ ገልጸዋል፡፡

በዋን እስቶፕ ሴንተር ከሚገኙ መረጃዎች ለማመን የሚከብዱ ቁጥራቸው ከፍ ያሉ ወንድና ሴት ሕፃናት ላይ ልዩ ልየ የሆኑ ወሲባዊ ጥቃቶች ይደርሱባቸዋል ብለዋል፡፡

እንደ ምክትል ቢሮ ኃላፊው ማብራርያ፣ በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ከዚህ በፊት በውል ከሚታወቁ የእንጥል ማስቧጠጥ፣ የግግ መንቀል፣ የሴት ልጅ ግርዛት፣ ያለዕድሜ ጋብቻ የመሳሰሉት ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች በዘለለ ከዘመኑ የቴክኖሎጂ ዕድገት፣ የሕዝብ ቁጥር መጨመር፣ ከሉላዊነት (ግሎባላይዜሽን) ጋር ተያይዞ የመጡት አዳዲስ በሕፃናት ላይ እየተፈፀሙ ያሉ መጤ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችንም ጭምር ማኅበረሰቡ በቅጡ መገንዘብ  አለበት፡፡

 የሕፃናትን መብትና ደኅንነት ጥበቃ ላይ ኅብረተሰቡ በባለቤትነት እንዲሳተፍና እንዲሠራ ለማስቻል ቢሮው ከሰኔ 9 የአፍሪካ ሕፃናት ቀን ጋር በማያያዝ ሰፊ የንቅናቄ መድረኮችና ልዩ ልዩ የግንዛቤ ማስጨበጫዎች ሲያከናወን መምጣቱንም ገልጸዋል፡፡

የቢሮው ኃላፊ ሐና የሺንጉሥ (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ የግንዛቤ ማስጨበጫ ንቅናቄ ከመፍጠር በዘለለ ለሕፃናት ጥበቃ አገልግሎት የሚያስፈልጉ ልዩ ልዩ መመርያዎችንና የአሠራር ማዕቀፎችን ቢሮው አዘጋጅቷል ብለዋል፡፡ የሕፃናትን መብትና ደኅንነት ከማስጠበቅ አንፃር ከሁሉም ክፍላተ ከተማ ለተውጣጡ የቤተሰብ አስተዳዳሪዎች፣ ለባለሙያዎች፣ ለመምህራንና ለፖሊሶች እንዲሁም ጉዳዩ ለሚመለከታቸው የሕግ አካላት የግንዛቤ ማስጨበጫ አጫጭር ሥልጠናዎች መሰጠታቸውንም ጠቁመዋል፡፡

ጥቃት የደረሰባቸውን ሕፃናት በተመለከተ ደግሞ ተገቢው የሕግ ከለላና ድጋፍ እንዲያገኙ እየተደረገ መሆኑንም ሳይገልጹ አላለፉም፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ለሲኒመር ትሬዲንግ አ/ማ አባላት በሙሉ የጠቅላላ ጉባኤ የስብሰባ ጥሪ

ለሲኒመር ትሬዲንግ አ/ማ አባላት በሙሉ የጠቅላላ ጉባኤ የስብሰባ ጥሪ ሲኒመር ትሬዲንግ...

የባህር በር በቀጣናዊ ተዛምዶ ውስጥ

በበቀለ ሹሜ መግቢያ በ2010 ዓ.ም. መጋቢት ማለቂያን ይዞ ዓብይ አህመድ በጠቅላይ...

ሥጋት ያስቀራል ተብሎ የሚታሰበው የጫኝና አውራጅ መመርያ

በአዲስ አበባ ከተማ በሕገወጥ መልኩ በመደራጀት ማኅበረሰቡ ላይ እንግልትና...

ማወቅ ወይስ አለማወቅ – ድፍረት ወይስ ፍርኃት?

በአሰፋ አደፍርስ ወገኖቼ ፈርተንም ደፍረንም የትም አንደርስምና ለአገራችን ሰላምና ክብር...