ላለፉት አራት ዓመታት ሲዘጋጅ የነበረው የአፈር መረጃ ሥርዓት ተጠናቆ ወደ ሥራ መግባቱን የግብርና ሚኒስቴር አስታወቀ። የመረጃ ሥርዓቱ በዋናነት በሁሉም የአገሪቱ ክፍሎች የሚገኝና ለተለያዩ ዓላማዎች የሚውል አፈርን መረጃ በመሰብሰብ፣ ለተጠቃሚዎች በግልጽ የሚቀመጥበት ሥርዓት መሆኑን በግብርና ሚኒስቴር ከፍተኛ የአፈር ካርታ ዝግጅት ባለሙያ ወ/ሮ ንጋት ተሰማ ገልጸዋል።
ለእርሻም ሆነ ለተለያዩ ከአፈር ጋር ተዛማጅነት ላላቸው አገልግሎቶች ጥቅም ላይ የሚውለው ይህ የመረጃ ሥርዓት፣ ከአፈር ጋር የተያያዙ በርካታ መረጃዎችን የያዘ መሆኑን ተናግረዋል። የአፈሩን ይዘት፣ አሲዳማነት፣ ዓይነቱንና ሌሎችም መረጃዎች የሚካተቱበት መሆኑንና ይህም ለመንግሥት፣ ለተመራማሪዎች፣ ለኢንቨስተሮችና ለሌሎችም ጥቅም ክፍት የሚሆን ነው ብለዋል።
ከዚህ ቀደም አፈርን በተመለከተ በቂ የመረጃ ሥርዓት ባለመኖሩ ለምርምር ሥራዎች፣ ለኢንቨስትመንትና ለተለያዩ አገልግሎቶች ሲፈለግ መረጃ ማግኘት አስቸጋሪ እንደነበር ወ/ሮ ንጋት ገልጸዋል። ይህንን መነሻ በማድረግም ባለፉት አራት ዓመታት ግብርና ሚኒስቴር ከኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኤጀንሲ፣ ከጀርመን ዓለም አቀፍ ትብብር ኤጀንሲ (GIZ) ጋር በመሆን ይህንን ሥርዓት ማዘጋጀቱን አብራርተዋል።
በተጨማሪም የማዳበሪያ አጠቃቀምን ጨምሮ በአፈር ላይ ለሚደረጉ የማሻሻያ ሥራዎችም መረጃው እንደሚያገለግል ተናግረዋል። በዚህ መነሻነትም የፖሊሲ ዝግጅትን ጨምሮ ለተለያዩ በሰብል ላይ ለሚሠሩ ሥራዎች በቂ መረጃ ለማግኘት ይጠቅማል ብለዋል።
መረጃዎቹ ለሁሉም ተጠቃሚ ቀላል በሆነ መንገድ በድረ ገጽና በሞባይል ስልክ መተግበሪያዎች ጭምር መቅረቡን፣ በቀጣይ ወር በ400 ወረዳዎች ተግባራዊ እንደሚደረግ አስረድተዋል። በ2015 ዓ.ም. ሙሉ በሙሉ ወደ ሥራ እንደሚገባም ወ/ሮ ንጋት ገልጸዋል።
ከተለያዩ አካባቢዎች የሚሰበሰቡ ከናሙና እስከ ትንተና ያሉት የአፈር መረጃዎች፣ በግልጽ የሚቀመጡበት ሥርዓት መሆኑንም ተናግረዋል።