ኤል አውቶ ኢንጂነሪንግ ከዘጠኝ ወራት በፊት ያለ ቀረጥ ያስገባቸውን ያልተገጣጠሙ መኪኖች ቀረጥ በመክፈል፣ የተገጣጠሙ አዳዲስ መኪኖችን ለላዳ አሽከርካሪዎች አስተላለፈ፡፡
ከሁለት ዓመት በፊት 10,500 አሮጌ የላዳ ታክሲዎችን በአዲስ ለመቀየር ከከተማ አስተዳደሩ ኃላፊነት የወሰደው ኤል አውቶ ኢንጂነሪንግ፣ በከፊል ያልተገጣጠሙ መኪኖችን ሙሉ ለሙሉ በመገጣጠም በአጠቃላይ 387ቱን አስተላልፏል፡፡
በአጠቃላይ ከተገጣጠሙት 267 መኪኖች ውስጥ 79ኙን ሰኔ 25 ቀን 2014 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ከተማ ለሚገኙ የላዳ አሽከርካሪዎች ያስረከበ ሲሆን፣ የአንዱ መኪና ዋጋ 800 ሺሕ ብር መሆኑን የድርጅቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ በቀለ አበበ ተናግረዋል።
‹‹በአዲስ አበባ ትራንስፖርት ቢሮ መመርያ መሠረት ከ1300 ሲሲ በላይ ጉልበት ያላቸውን መኪኖች ብቻ ያለ ቀረጥ በማስገባት መገጣጠም የሚቻል ሲሆን፣ አሁን የተላለፉት ደግሞ 1000 ሲሲ በመሆናቸው ከደንበኞች ጋር ተጨማሪ የቀረጥ ክፍያውን በመስማማት አስረክበናል፤›› ሲሉ አቶ በቀለ ገልጸዋል።
በከተማዋ ከሚገኙ 185 ማኅበራት ውስጥ 25 ስታር እና 120 ስታር በተባሉ የትራንስፖርት ማኅበራት ለተደራጁ የላዳ አሽከርካሪዎች መኪኖቹን የተላለፉ ሲሆን፣ ለረዥም ዓመታት በተለያዩ ምክንያቶች ዘግይቶ የነበሩት መኪኖች መረከባቸው ደስታን እንደፈጠረላቸው ተናግረዋል፡፡
ኤል አውቶ ከሰባት ወራት በፊት ወደ አገር ውስጥ ገብተው በሦስት የጉምሩክ ጣቢያዎች ማለትም ሞጆ፣ ዱከምና ድሬዳዋ የሚገኙትን ያልተገጣጠሙ መኪኖች በዚህ ሳምንት መገጣጠም ይጀምራል ተብሏል፡፡
ያለ ቀረጥ የገቡ በከፊል ያልተገጣጠሙ መኪኖችን ከመጋዘን አውጥቶ ለመገጣጠም የሚፈቅድ መመርያ በመፅደቁ፣ በዱከምና በድሬዳዋ ኢንዱስትሪ ዞን በሚገኙ ፋብሪካዎች ይገጣጠማሉ ሲሉ አቶ በቀለ ተናግረዋል፡፡
የመኪኖቹን መገጣጠም እንዳይከናወን ምክንያት ከሆኑት መካከል መኪኖቹን ከቀረጥ ነፃ ማስገባት የሚያስችለውን መመርያ አውጥቶ ማፅደቅ የግድ ስለነበር፣ አሁን ግን መመርያው ፀድቆ ለድርጅቱ ደብዳቤ የደረሰው መሆኑን አቶ በቀለ ገልጸዋል፡፡ እነዚህ ከቀረጥ ነፃ ገብተው የሚገጣጠሙ መኪኖች ዋጋቸው አሁን ከተላለፉት በአንፃሩ ቅናሽ ይኖረዋል ብለዋል፡፡
ኤል አውቶ ኢንጂነሪንግ ከሦስት ዓመት በፊት ቃል በገባው መሠረት በመጀመርያ ዙር ሦስት ሺሕ ተሽከርካሪዎች ለማስረከብ ስምምነት የፈጸመ ቢሆንም፣ በተለያዩ ምክንያቶች ዘግይቶ ለበርካታ የላዳ አሽከርካሪዎች ዘንድ ቅሬታ ፈጥሮ ነበር፡፡
አሽከርካሪዎቹ 130 ሺሕ ብር ቅድመ ክፍያ ከፈጸሙ በኋላ ድርጅቱ በተጠቀሰው ጊዜ ውስጥ መኪኖቹን አላስረከበም ነበር፡፡ ድርጅቱ አሮጌ የላዳ ታክሲዎችን በአዲስ ለመቀየር ስምምነት ካደረገበት ጊዜ ጀምሮ ባለፈው ዓመት 120፣ እንዲሁም በዚህ ዓመት 267 በአጠቃላይ 387 አዳዲስ መኪኖችን ማስረከቡን አስታውቋል።
ዘንድሮ ከተላለፉት መኪኖች ውስጥ በባህር ዳር፣ በጎንደር፣ በደሴ፣ በሐዋሳ፣ በአዳማና በጂማ የሚገኙ የድርጅቱ ቅርንጫፎች ይጠቀሳሉ።
አቶ በቀለ የቀረጥ ነፃ መመርያው በመፅደቁ ተጨማሪ 120 በከፊል ያልተገጣጠሙ መኪኖችን በማስመጣት እንደሚገጣጠም የገለጹ ሲሆን፣ በተጨማሪም 3,000 ለሚሆኑት ኤልሲ በመክፈት ለማስገባት እየተዘጋጁ መሆናቸውን አስረድተዋል።