Friday, December 8, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የነዳጅ ኮታና አዲሱ የነዳጅ ዋጋ ማስተካከያ ይፋ ተደረገ

ተዛማጅ ፅሁፎች

  • በቤንዚንና ናፍጣ ላይ የ29.7 እና 38 በመቶ ጭማሪ ተደርጓል

መንግሥት ዛሬ ረዕቡ ሰኔ 29 ቀን 2014 ዓ.ም. ባስጀመረው የነዳጅ ድጎማ ሥርዓት ተጠቃሚ ለሚሆኑ የተለያዩ ዓይነት ተሽከርካሪዎች የደለደለውን ከሰባት እስከ 102 ሊትር የሚደርስ ዕለታዊ የነዳጅ ኮታ ትናንት ሰኔ 28 ቀን 2014 ዓ.ም. ይፋ አደረገ፡፡

የሐምሌ ወር የነዳጅ መሸጫ ዋጋም ይፋ የተደረገ ሲሆን፣ በቤንዚን ላይ የ29.7 በመቶ፣ በናፍጣና ኬሮሲን ላይ የ38 በመቶ ጭማሪ ተደርጓል፡፡

ከታሰበለት ሁለት ቀናት ቀደም ብሎ በተጀመረው የነዳጅ ድጎማ ሥርዓት ተጠቃሚ የሚሆኑ 175,000 ተሽከርካሪዎች ተለይተው፣ 164,345 ለሚደርሱት መረጃ በማደረጃት፣ በመጨረሻም 140,000 የሚሆኑት ተሽከርካሪዎች በቴሌ ብር መመዝገባቸው ታውቋል፡፡

ተደጓሚ ተሽከርካሪዎቹ በአምስት የተለያዩ ክፍሎች መደራጀታቸው የተገለጸ ሲሆን፣ እነዚህም ባለ ሦስት እግር ተሽከርካሪዎች፣ ከ12 እስከ 14 ተሳፋሪ የሚጭኑ ታክሲዎች፣ ሚኒባስ (አገር አቋራጭ)፣ ከ14 እስከ 47 ወንበር ያላቸው መለስተኛ (ሚድ ባስ) ተሽከርካሪዎች እንዲሁም አገር አቋራጭ አውቶቡስ የሚባሉት ናቸው፡፡

በትራንስፖርትና ሎጀስቲክስ ሚኒስቴር የመንገድ ደኅንነትና መንገድ ፈንድ ምክትል ዋና ዳይሬክተርና የታለመለት ድጎማ ፕሮጀክት አስተባባሪ አቶ አብዱልበር ሸምሱ እንዳስታወቁት፣ እነዚህ ተሽከርካሪዎች በቀን ምን ያህል ነዳጅ ነው የሚደጎሙት የሚለው ገደብ ተቀምጦለታል፡፡

ከሚደጎሙት 115,699 የባለ ሦስት እግር ተሽከርካሪዎች በቀን ውስጥ ሰባት ሊትር በድጎማ ሥርዓቱ መሠረት ነዳጅ መቅዳት የሚችሉ ሲሆን፣ በተለያዩ ከተሞች ውስጥ የሚገኙት 11,320 የሚደርሱ ታክሲዎች ደግሞ 25 ሊትር የሚቀዱ ይሆናል ተብሏል፡፡

አነስተኛ አገር አቋራጭ (ሚኒባስ) የሚባሉት 17,340 ተሽርካሪዎች በቀን 65 ሊትር እንዲቀዱ የተፈቀደ ሲሆን፣ መለስተኛ (ሚዲ ባስ) በሚባለው ምድብ ውስጥ የሚገኙ 17,118 ተሽከርካሪዎች 94 ሊትር  እንዲሁም 2,890 የሚደርሱት የከተማ አውቶቡሶች ደግሞ በቀን ውስጥ እስከ 102 ሊትር ነዳጅ እንዲቀዱ መደረጉን የታለመለት ድጎማ ፕሮጀከት አስተባባሪው አስታውቀዋል፡፡ ከዚህ ጎን ለጎን ለመንግሥት ሠራተኞች ሰርቪስ የሚሰጡ ተሽከርካሪዎች ደግሞ በቀን 25 ሊትር እየቀዱ አገልግሎት እንዲሰጡ የተወሰነ ሲሆን፣ እንዲሁም ከአዲስ አበባ ተነስተው ወደ የተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የሚሄዱትና ከ230 በላይ የስምሪት መስመር ያላቸው የአገር አቋራጭ አውቶቡሶች ደግሞ በቀን እስከ 65 ሊትር ነዳጅ መቅዳት ይችላሉ ተብሏል፡፡

በተያያዘም የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ከዛሬ ሰኔ 29 ቀን 2014 ዓ.ም. እስከ ሐምሌ 30 ቀን 2014 ዓ.ም. ድረስ የሚቆይ የነዳጅ ምርቶች የችርቻሮ ዋጋ ጭማሪ አድርጓል።

በአዲሱ ታሪፍ መሠረት ቤንዚን በሊትር 47.83 የሚሸጥ ሲሆን ይህም ከዚህ ቀደም ከነበረበት የመሸጫ ዋጋ የ29.7 በመቶ የዋጋ ጭማሪ የተደረገበት ነው፡፡ በሌላ በኩል ተመሳሳይ የችርቻሮ መሸጫ ዋጋ ባላቸው ነጭ ናፍጣና ኬሮሲን ላይ ከዚህ ቀደም ይሸጥበት ከነበረበት ዋጋ የ38 በመቶ ጭማሪ ተደርጎ በሊትር 49.02 ብር መሸጥ ተጀምሯል፡፡  

የተዘጋጀው የታለመለት የነዳጅ ድጎማ ሥርዓት እያንዳንዱ ተሽከርካሪ ከአንድ ጊዜ በላይ እንዳይጠቀም የተሽከርካሪ የመለያ ቁጥሮችን (ቻንሲ፣ ሰሌዳ) የሚጠቀም ሲሆን፣ ማደያዎች ላይ ተሽከርካሪዎቹ ተደጓሚ መሆናቸው የሚገልጽ መረጃን ለማደያ ባለሙያዎች በማቅረብ አሽከርካሪዎች በቀዱበት ቅፅበት የድጎማ መጠኑን እንዲያገኝ የሚያስችል መሆኑ ተገልጿል፡፡

የለማው ሲስተም የዕለት ድጎማ ለሚፈቀድለት ተሽርከርካሪ ከዕለቱ ሌላ በሌላ ቀን ተጨማሪ አገልግሎት ለማግኘት የማያስችል ሲሆን፣ ነገር ግን አንዳንድ ተሽከርካሪዎች ከሥራ ባህሪቸው አንፃር በሳምንት የሚጠቀሙባቸውን ቀናቶች ተለይተው የሚጠቀሙበት ሁኔታ በቀጣይ ይመቻቻል ተብሏል፡፡ በሌላ በኩል በዚህ ወቅት ምን ያህል ተሽከርካሪ ተደጉሟል፣ ምን ያህሉ ተሽከርካሪ ነዳጅ ቀድቷል፣ አልቀዳም የሚሉ መረጃዎችን የሚመለከታቸው አካላት ከሲስተሙ ማግኘት እንደሚችሉ ተገልጿል፡፡

አቶ አብዱልበር እንዳስታወቁት፣ ለታለመለት የነዳጅ ድጎማ ሥርዓት የተመረጡ ተሽከርካሪዎች ስቲከር መለጠፍ ይኖርባቸዋል፡፡ ከተዘጋጁት ሁለት ስቲከሮች በነጭ ቀለም የተዘጋጀው በክልል ለተደራጁ ተሽከርካሪዎች ግልጋሎት የሚውል ሲሆን፣ ባለ ሰማያዊ ቀለም ስቲከሩ ደግሞ በፌዴራል ደረጃ ለተደራጁት ተሽከርካሪዎች ይውላል፡፡

‹‹ማንኛውም የድጎማ ነዳጅ ተጠቃሚ ተሽከርካሪ የቀዳውን ነዳጅ ለሕዝብ ትራንስፖርት ማዋል ይኖርበታል፡፡ ለሕዝብ ትራንስፖርት ሳያውል ላልሆነ መንገድ ሲጠቀም ከተገኘ አስፈላጊው አስተዳደራዊ ዕርምጃ በሚመለከተው መዋቅር የሚወሰድበት ይሆናል፤›› ሲሉ የታለመለት ድጎማ ፕሮጀከት አስተባባሪው ተናግረዋል፡፡

የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር በወቅታዊ የነዳጅ ግብይት ዙሪያና  በታለመለት የነዳጅ ድጎማ ዝርዝር ጉዳይ ከትራንስፓርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር፣ ከነዳጅና ኢነርጃ ባለሥልጣን ጋር በመሆን በዋና መሥሪያ ቤቱ ሰኔ 28 ቀን 2014 ዓ.ም. መግለጫ ሰጥቶ ነበር፡፡

የነዳጅና ኢነርጂ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ ሳህረላ አብዱላሂ እንደገለጹት፣ እስከ ሰኔ 25 ቀን 2014 ዓ.ም. ድረስ በአገሪቱ ከሚገኙት 1,020 የነዳጅ ማደያዎች ውስጥ 860 የሚሆኑት ለታለመለት የነዳጅ ድጎማ አተገባበር አስፋላጊውን ምዝገባ አጠናቀዋል፡፡

የቴሌ ብር ወይም የኔትወርክ መቆራረጥ በሚያጋጥምበት ጊዜ አገልግሎቱ እንዲቀጥል የሚያስችል አማራጭ መቀመጡ የተገለጸ ሲሆን፣ ይህም 500 ሺሕ የሚደርሱ ደረሰኞች ተዘጋጅተው በአገሪቱ ውስጥ ለሚገኙት የነዳጅ ማደያዎች ከአጠቃቀም ሥልጠና ጋር መሠራጩትን ዋና ዳይሬክተሯ አስረድተዋል፡፡

ከጭነት መኪኖች ጋር ተያይዞ ተሸከርካሪዎቹ አገልግሎት የሚሰጡት ከመንግሥት ታሪፍ ውጭ በራሳቸው የድርድር ውሳኔ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ የታለመለት ነዳጅ ድጎማ ተጠቃሚ አለመሆናቸው አሁንም ከግምት ውስጥ ሊያዝ ይገባል ሲል ባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ አስታውቋል፡፡

በታለመለት የነዳጅ ድጎማ ውስጥ የማይካቱት የቤት ተሽከርካሪዎችን ጨምሮ የግል ድርጅቶች፣ ኢምባሲዎችና ሌሎች ዓለም አቀፍ ተቋማት ውስጥ የሚገኙ አንድ ሚሊዮንና ከዚያ ላይ የሚደርሱ ተሸካርካሪዎች ያሉ ሲሆን፣ እነዚህ ተሽከርካሪዎች በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ እስከዚህ ወቅት ድረስ በመንግሥት ይደረግ ከነበረው የድጎማ ሥርዓት እንዲወጡ ይደረጋል ሲሉ የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትሩ አቶ ገብረ መስቀል ጫላ ተናግረዋል።

በሌላ በኩል የድጎማ ተጠቃሚ እንዲሆኑ የተለዩ የሕዝብ ማጓጓዣ ተሽከርካሪዎች በአንፃሩ የሚደረግላቸው ድጎማ ሙሉ ለሙሉ ሳይነሳ ለአምስት ዓመታት ይቆያሉ መባሉ ይታወሳል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች