Tuesday, February 27, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

‹‹እኛ በጩኸትና በፉጨት በአንጃና በጠብመንጃ አናምንም›› ዮሐንስ መኮንን (አርክቴክት)፣ የኢዜማ ምክትል መሪ

በኪነ ሕንፃ (አርክቴክቸር) ሙያቸው በሰፊው ይታወቃሉ፡፡ በማኅበራዊ የትስስር ገጾች ተሳትፏቸውም እንዲሁ፡፡ በተለይ በተሰማሩበት ሙያና በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ትኩረት የሚስቡ ጽሑፎችን በማኅበራዊ የትስስር ገጾቻቸው በማስነበብ በስፋት ይታወቃሉ፡፡ የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ (ኢዜማ) ፓርቲ ሲመሠረት በአባልነት ተቀላቅለው ወደ ፖለቲካ ተሳትፎ ገቡት ዮሐንስ መኮንን (አርክቴክት) በአጭር ጊዜ ውስጥ ወደ ፓርቲው ከፍተኛ አመራርነት መምጣት ችለዋል፡፡ ከሰሞኑ ፓርቲው ባካሄደው ጠቅላላ ጉባዔ በተደረገው የአመራሮች ምርጫም የኢዜማ ምክትል መሪ ሆነው ለመመረጥ የበቁ ሲሆን፣ ብዙ ስለተባለለት የምርጫ ሒደትና ተያያዥ ጉዳች ከዮናስ አማረ ጋር ያደረጉት ቆይታ እንደሚከተለው ቀርቧል፡፡

ሪፖርተር፡- ከሰሞኑ ፓርቲያችሁ ኢዜማ ያካሄደው ምርጫ ምን ዓይነት ገጽታ ነበረው? ስለሒደቱ አጠቃላይ ምሥል ቢሰጡን?

ዮሐንስ (አርክቴክት)፡- ያካሄድነው የውስጥ ፓርቲ ምርጫ ሲሆን፣ የዴሞክራሲ ልምምዳችንን ማሳደጊያ አጋጣሚ ነው ማለት እንችላለን፡፡ ሁለተኛው እንደ አገር እንዲፈጠር ለምንፈልገው ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ምሳሌም መሠረትም እንዲሆን በማሰብ ያደረግነው ነው፡፡ ሦስተኛው የምርጫ ሒደቱ ግብ ደግሞ ገዥው ፓርቲን ጨምሮ ከተፎካካሪዎቻችን በሐሳብም ሆነ በፓርቲ ዲሲፕሊን ያለንን ብልጫ የምናሳይበት አጋጣሚ እንዲሆን አስበን ያካሄድነው ነው፡፡ ማን ይመረጥ ከሚለው ባሻገር የምርጫ ሒደቱ እነዚህን ሦስት ግቦች ያሳካንበት ሒደት ነበር፡፡ ምርጫው በፕሮግራማችንም ሆነ በሕገ ደንባችን በግልጽ በተቀመጠ መርህ የሚካሄድ ነው፡፡ በኢዜማ ውስጥ ሁለት ክንፎች አሉ፡፡ የመንግሥትና የፓርቲ ልዩነትን ከወዲሁ ለመለማመድ በሚያስችል መንገድ ፓርቲው ነው የተደራጀው፡፡ በምደባ ሳይሆን ከወረዳ ጀምሮ በየወቅቱ በሚካሄድ ምርጫ አመራሮች እንዲወሰኑ አድርገናል፡፡ ይህን ሕግ በመከተል የተደረገ ምርጫ ነው፡፡

በስትራቴጂካዊ ግባችን አማካይነት አገር ለመምራት ዕድል ብናገኝና መንግሥት ብንሆን ለቆምንለት ዓላማ ታማኝ እንደሆንን ከወዲሁ ለማሳየት አስበን ያካሄድነው ምርጫ ነው፡፡ እንደ አገር እንዲገነባ የምንፈልገውን ዴሞክራሲ በውስጣችን ተለማምደን ለሕዝባችን ለማሳየት ዕድል እንዲሆን በማሰብ ያደረግነው ነው፡፡

ሪፖርተር፡- በዚህ ምርጫ ዴሞክራሲያዊ ልምምድን በተመለከተ ለሌሎች ለማስተላለፍ የፈለጋችሁትን መልዕክት በእርግጥ አስተላልፈንበታል ብላችሁ ታስባላችሁ? በተለይ ለተፎካካሪ የፖለቲካ ኃይሎች?

ዮሐንስ (አርክቴክት)፡- በትክክል፡፡ እንዳለመታደል ሆኖ አሁን እንደ አገር ያለንበት የሰላም መታጣት፣ የዜጎች ሞትና መፈናቀል እጅግ ልብ የሚሰብር መሆኑን እንገነዘባለን፡፡ ይህ የቀውስ ዜና መደራረብ የኢዜማ የምርጫ ሒደትን ጥላ እንደሚያጠላበት ቢታወቅም፣ ነገር ግን በዚህ የምርጫ ሒደት ያሳካነው ድል ቀላል የሚባል አይደለም፡፡ አገራችን በአሳዛኝ ክስተቶች የተሞላች ባትሆን ኖሮ ስኬቱን እንደ ፓርቲ ብቻ ሳይሆን እንደ አገርም ባከበርነው ነበር፡፡ ገዥውን ፓርቲ ጨምሮ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ጠቅላላ ጉባዔና የውስጥ ምርጫ እንዴት ሲያደርጉ እንደቆዩ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ዓይቶታል፡፡ ነጮቹ ‹‹ክሪስታል ክሊር›› እንደሚሉት የእኛ በዴሞክራሲያዊነቱ ከሁሉም የተለየ ነው ብል ማጋነን አይደለም፡፡ በገዥው ፓርቲ ውስጥ ራሱ የአገርና የፓርቲው መሪ ተቀምጦ፣ ራሱ ጠቋሚ፣ መራጭና ተመራጭ ሆኖ ሲመረጥ ዓይተናል፡፡ ኢዜማ ውስጥ ግን ይህ አልነበረም፡፡ የፓርቲው መሪ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ የራሱ የምርጫ ወረዳ ወርዶ፣ የፓርቲው ሊቀመንበር አቶ የሺዋስ አሰፋም በወረዳው ሄዶ ለመመረጥ ድጋፍ ይዞ መጥቶ ነው ለምርጫ ሲወዳደሩ የነበረው፡፡ ለአመራርነት የተፎካከርን ሁሉ በየክልሉ ተጉዘን፣ በየምርጫ ወረዳዎች ተዟዙረን፣ አባሎቻችንን ለምርጫው ቀስቅሰንና ድጋፍ አሰባስበን ነው ለምርጫው የቀረብነው፡፡ አባሎቻችን ባሉበት ሁሉ ሄደን ሐሳባችንን አስረድተንና ተፎካክረን ነው ለምርጫ የቀረብነው፡፡ ይህ ከሚጻፈውም ሆነ ከሚነገረው በላይ መሥራት የምንፈልገውን ነገር በተግባር በግልጽ ያሳየንበት አጋጣሚ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- አገሪቱ ፅንፍ በረገጠ የብሔር ፖለቲካ እየተናጠች ትገኛለች፡፡ በዚህ መሀል ደግሞ እንደ የእናንተ ዓይነት የዜግነት ፖለቲካ እናራምዳለን የሚሉ ኃይሎችም አሉ፡፡ የብሔር ፖለቲካ ገናን በሆነበት በዚህ ወቅት የዜግነት ፖለቲካን የሚደግፈው ማኅበረሰብ በኢዜማ መወከል ይችላል ወይ? የአንድነት ኃይሉ (ኢትዮጵያዊ ብሔርተኝነት ደጋፊው) ምን ዕድሎችና አማራጮች አሉት?

ዮሐንስ (አርክቴክት)፡- ሁለት ነገሮችን አብሬ ላንሳልህ፡፡ መጀመሪያ አንድ ፓርቲ እታገልለታለሁ የሚለው ጽንሰ ሐሳብ ወይም ርዕዮተ ዓለም አለው፡፡ የሚታገልለት ሐሳብ ደግሞ ሁሉንም አሰባሳቢ መሆኑን መጀመሪያ መጠየቅ አለበት፡፡ በዚህ ሐሳብ ዙሪያ ሰዎች ይሰባሰባሉ ወይ ብሎ መፈተሽ አለበት፡፡ በዚህ ረገድ ደግሞ በንድፈ ሐሳብ (ርዕዮተ ዓለም) ከታየ ከኢዜማ በተሻለ ሁሉንም ወገን አሰባሳቢ የሆነ ሐሳብ ያለው ፓርቲ የለም እላለሁ፡፡ ኢዜማ የተመሠረተበትና የሚኖርላቸው አራት መሠረታዊ ዓላማዎች አሉት፡፡ ከአራቱ ውስጥ ሁለቱ የጋራና ከሁሉም ጋር ተባብረን የምንሠራባቸው ጉዳዮች ናቸው፡፡ አንደኛው መሠረታዊ ጉዳይ የአገር ሉዓላዊነት፣ ሰላምና ደኅንነት የማስጠበቅ ጉዳይ ነው፡፡ ሁለተኛው ደግሞ በአገሪቱ የዴሞክራሲ መደላድል ተፈጥሮ ማየት ነው፡፡ እነዚህ ሁለት ጉዳዮች ከማንም ለመርሆዎቹ ከቆመ ወገን ጋር በትብብር የምንሠራቸው ጉዳዮች ሲሆኑ የማንፎካከርባቸው ናቸው፡፡

ሦስተኛው ግን የራሱ የድርጅቱ መሠረታዊ አጀንዳ ሲሆን፣ ጠንካራ አማራጭ ያለው ድርጅት መፍጠር ነው፡፡ ጠንካራ ዴሞክራሲያዊ የሐሳብ ግንብ መፍጠር ዓላማችን ሲሆን፣ ይህ ደግሞ በማይቋረጥ ዑደት በረዥም ጊዜ የምንሠራው እንጂ በአንድ ጀንበር የሚፈጠር አይደለም፡፡ አራተኛው ዓላማችን ደግሞ በዴሞክራሲ መንገድ ተወዳድሮ የመንግሥትን ሥልጣን በመያዝ ሐሳቦቻችንን ዕውን ማድረግ ነው፡፡ እነዚህ አራት የኢዜማ ዓላማዎች ደግሞ አይጠቅሙም ወይም አይበጁም የሚል ወገን እስካሁን አልገጠመኝም፡፡

ሁለተኛው መነሳት ያለበት መሠረታዊ ጉዳይ ደግሞ ከንድፈ ሐሳብ ባለፈ መሬት ላይ ወርዶ አባላትና መመልመልና ደጋፊን ማሰባሰብ ነው፡፡ ኢዜማ በየእርከኑ ወደ ኅብረተሰቡ ወርዶ በዜግነት ፖለቲካ የሚያምኑ አባላትንና ደጋፊዎችን ለማሰባሰብ ጥረት አድርጓል ወይ የሚለው ጉዳይ ቀጥሎ ይመጣል፡፡ በኢትዮጵያ በዜግነት ፖለቲካ የሚያምኑ ዜጎች አሉ፡፡ በቋንቋ፣ በዘር፣ በብሔር ወይም በሃይማኖት መሰባሰብ መለያዬ አይደለም የሚሉና በዜግነት ወይም በኢትዮጵያዊነት መሰባሰብን የሚያስቀድሙ ሰዎች አሉ፡፡ የብሔር ፖለቲካ በአገሪቱ ያመጣውን ጣጣ በውል የሚገነዘቡ፣ ሥልጡን የዜግነት ፖለቲካ አስተሳሰብን የሚከተሉ ቅይጥ ማኅበረሰቦች በኢትዮጵያ አሉ፡፡ እነዚህ ወገኖች ኢዜማን እንደ አማራጭ የፖለቲካ ኃይል እንዲያዩት የሠራነውን ሥራ ጥንካሬ ከጠየቅከኝ ግን አሁንም ጉድለቶች አሉብን ነው የምልህ፡፡ የእነዚህ ጉድለቶች ምንጭ ደግሞ ሁለት ናቸው፡፡ ከተመሠረትንበት ዕድሜ አንፃር ወረዳዎች ላይ ብንሠራም በሦስት አራት ዓመታት ያሰብነውን ያህል አለመሄዳችንን እገነዘባለሁ፡፡ ሁለተኛውና ትልቁ ምክንያት ብዬ የማየው ግን በኢትዮጵያ ባለፉት 40 እና 50 ዓመታት የተለመደው የፖለቲካ ባህል የፈጠረው ችግር ነው፡፡

የኢትዮጵያ ፖለቲካ የለመዳቸው ሁለት ነገሮች አሉ፡፡ አንዱ ጩኸት ነው፡፡ በትንሽ በትልቁ መቃወም፣ መጋጨትና መነታረክ ልማድ ሆኗል፡፡ ሁለተኛው ጩኸትና ግጭቱን ተከትሎ የውስጥ መከፋፈልና አንጃ መፍጠር አልያም የጠብመንጃ አፈሙዝ ማዞር የተለመደ ነው፡፡ እኛ ደጋግመን እንደምንለው በጩኸትና በፉጨት አናምንም፣ በአንጃና በጠብመንጃም አናምንም፡፡ ሁሌም የሠለጠነና የሰከነ አዲስ የፖለቲካ መንገድ መከተል አለብን ብለን እናምናለን፡፡ ይኼ አዲስ አቅጣጫ ደግሞ በደንብ ስላልታየ የዜጎችን ሙሉ መተማመንና ድጋፍ ለማግኘት ብዙ ሥራ እንደሚያስፈልግ እገነዘባለሁ፡፡ ባልከው ልክ የዜግነት ፖለቲካን የሚደግፉ ወገኖችን ለማሰባሰብ ብዙ ጥረት ይጠይቀናል፡፡ ነገር ግን ከተለመደው የፖለቲካ አካሄድ መውጣት አለብን ብለን እናምናለን፡፡

ትልቁን ሥዕል አገርን ማስቀደም አለብን፡፡ ወደፊትም ሆነ ሥልጣንም የሚባሉ ነገሮች የሚኖሩት አገር ስትኖር ነውና ሥልጣንን ሳይሆን ትልቁ ሥዕል አገርን ማስቀደም ላይ አተኩረን፣ ከሁሉም ጋር ተጋግዘንና ተረባርበን እንሥራ የሚለው ሐሳብ ገዥ መሆን አለበት፡፡ ነገር ግን ይህን ትልቅ ሐሳብ ዜጎች እኩል ይሁንታ እንዲሰጡትና እንድንለማመደው ብዙ መሥራት ይጠይቀናል፡፡ እርግጠኛ ሆኜ መናገር የምችለው ግን ጊዜው ሊረዝም ቢችልም፣ ኢዜማ ሥልጡን የሆነ የዜግነት ፖለቲካን የሚቀበሉና በማኅበራዊ ፍትሕ የሚያምኑ ጠንካራ የሐሳብ ብሎክ መገንባቱ የማይቀር ነው፡፡ ሌሎች የዜግነት ፖለቲካን የሚቀበሉ የፖለቲካ ፓርቲዎችን ጭምር የሚያሰባስብ ጠንካራ የሐሳብ ብሎክ እንደሚሆን አልጠራጠርም፡፡ በንድፈ ሐሳብ ደረጃ ይህን የሚያረጋግጥ ሐሳብ አለን፡፡ በተጨባጭ በተግባር የመተርጎሙ ሥራ ላይ ግን ሒደቱን ብንጀምረውም ገና ብዙ ይቀረናል፡፡   

ሪፖርተር፡- ኢዜማ ራሱን ከመገምገም ባለፈ አሁን አገሪቱ የምትገኝበትን ተጨባጭ ሁኔታ በቅጡ ገምግሟል ወይ? ወቅቱ የሚጠይቀውን ትግል ለማካሄድ በሚያስችል መንገድ ላይ ነው ወይ ሰሞነኛውን ምርጫስ ያካሄዳችሁት?

ዮሐንስ (አርክቴክት)፡- ጥሩ ጥያቄ ነው፡፡ አንድ ተቋም ሁሌም ቢሆን የሚሠራበትን ነባራዊ ሁኔታ በመገምገም አቋሙን ያስተካክላል፡፡ የፖለቲካ ፓርቲ ሲኮን ደግሞ ይህ ኃላፊነት ከበድ ይላል፡፡ በአንድ አገር ያሉ ሕዝቦችን አሰባስቦ ለመንቀሳቀስ ወይም አንድ የሆነ የኢኮኖሚ ማኅበረሰብ ለመፍጠር የሚታገል የፖለቲካ ድርጅት በዚህ ረገድ ብዙ ሥራ ይጠብቀዋል፡፡ በየጊዜው ማጥናትና ራሱን ማስተካከል አለበት፡፡ እኛ ለምሳሌ ሁለት ሦስት ጥናቶችን በተለያዩ ጉዳዮች ላይ አድርገናል፡፡ ባለፈው ዓመት ብሔራዊ ምርጫ ከመደረጉ በፊት፣ እየተደረገ ሳለና ከተካሄደ በኋላ ተደጋጋሚ ጥናቶችን አድርገናል፡፡ ጥናቱ የተዛባ እንዳይሆን ጥንቃቄ በማድረግ ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ በአንድ ጉዳይ ላይ ሁለትና ሦስት ጥናቶችን አድርገናል፡፡ እሱ ብቻም አይደለም፡፡ በወቅታዊ አገራዊ ጉዳዮች ላይ በተለይ በሰላምና ደኅንነት ላይ ጥናቶችን አድርገናል፡፡ ጥናቶቹ ሁለት መሠረታዊ ዓላማዎች ያላቸው ሲሆን፣ ለራሳችን ከማዋል ባለፈ ለሚመለከታቸው አገራዊ ተቋማት ግብዓት እንዲሆኑም ጥናቶቹን እንሰጣለን፡፡ ለምሳሌ በሰላምና ፀጥታ ላይ ያካሄድነውን ጥናት ከእነ መፍትሔ ምክረ ሐሳቦቻቸው የጥናት ግኝቶቻችንን እንሰጣለን፡፡ ችግሮች የሚከሰቱበትን ሁኔታ ከመጠቆም ባለፈ እንዳይከሰቱ መከላከያ፣ ወይም ከተከሰቱ በኋላ መውጫ መንገዶቻቸውን እንጠቁማለን፡፡ መንግሥት ተብሎ ለተቋቋመው አገራዊ ተቋም አሉ ብለን ያጠናናቸውን ሥጋቶች መጠቆም አንዱ የጥናቶቻችን ግብ ነው፡፡

ሁለተኛው ደግሞ ችግሮችን ለሕዝብ ማመላከት ሲሆን፣ ሕዝቡ ማወቅ ይገባዋል በምንላቸው ጉዳዮች ላይ ያካሄድናቸውን ጥናቶች ጋዜጣዊ መግለጫ በማዘጋጀት ለሕዝብ ይፋ እናደርጋለን፡፡ ለምሳሌ በመሬት ወረራ፣ በኮንዶሚኒየም ወረራና በሕገወጥነት ላይ ያደረግነውን ጥናት ለሕዝብ ይፋ አድርገናል፡፡ ሌላው በእነዚህ ጥናቶች የአገሪቱን ነባራዊ ሁኔታ በትልቅ መረጃ በመተንተን የፓርቲያችንን አካሄዶች እንወስንበታለን፡፡ ከዚህ አንፃር አሁን አገራችን የምትገኝበትን ሁኔታ ሳስቀምጥ፣ ኢትዮጵያችን ፈታኝ በሆነ የታሪክ መታጠፊያ ቅርቃር ውስጥ የቆመች ናት፡፡ በዚህ ወሳኝ ወቅት የምንወስዳቸው ማንኛውም ዕርምጃዎች በጥንቃቄ፣ በጥናትና በብልኃት ላይ የተመሠረቱ ካልሆኑ ምናልባትም ወደ የማንመለስበት ገደል ልንገባ እንችላለን፡፡ ካልተጠነቀቅን እንደ አገርና እንደ ሕዝብ ልንወድቅ እንችላለን፡፡

ይህን መሰል ፈታኝ የታሪክ አጋጣሚ ከአሁን ቀደም ገጥሞን አያውቅም፡፡ ከዚህ ቀደም ኢትዮጵያን ከረሃብና ከችግር አላቆ ዴሞክራሲዊ ሥርዓት ለመገንባት ሁለት ወሳኝ የታሪክ አጋጣሚዎች አግኝተን እናውቃለን፡፡ አንደኛው የ1966 ዓ.ም. አብዮት ሲሆን፣ እንደሚታወሰው ደመወዝ ለማስጨመር ለተቃውሞ የወጡ ወታደሮች አብዮቱን መነተፉትና ዕድሉ መክኖ/ባክኖ ቀረ፡፡ ሁለተኛው ዕድል በ1983 ዓ.ም. ደርግ ወድቆ ሕወሓት/ኢሕአዴግ የተቆጣጠረበት አጋጣሚ ነበር፡፡ በወቅቱ ተፈጥሮ የነበረው የዴሞክራሲ ተስፋ ብዙ የፖለቲካ ፓርቲዎች እንዲመሠረቱና አማራጭ ሐሳባቸውን ወደ አደባባይ እንዲያወጡ ዕድልና አገር የመቀየር ተስፋን ቢፈጥርም እሱም መልሶ ጨልሟል፡፡ የጊዜው ዕድል የአንድ የፖለቲካ ኃይል መግነንን አስከተለ፡፡ በሒደትም ቡድኑ ወደ አንድ አካባቢያዊ ስብስብ የበላይነት፣ በመጨረሻም አንድ ቤተሰብ የሚመስል ኃይል ፍፁም የበላይነትን አስከተለ፡፡ ይህም በመሆኑ በ2010 ዓ.ም. ግድም በአገሪቱ ከዳር እስከዳር ሕዝባዊ አመፅ እንዲቀጣጠል ምክንያት ፈጠረ፡፡ ይህም ሦስተኛው ዴሞክራሲ መገንቢያ የለውጥ ዕድል እንዲፈጠር መነሻ ሆኗል፡፡ አሁን ያለነው በዚህ የለውጥ ምዕራፍ ላይ ሲሆን፣ በአግባቡ ከያዝነው ከበፊቶቹ ይልቅ አገር የመቀየር ሰፊ ዕድል አለን፡፡ ከፉክክር ይልቅ መተባበር ላይ በማተኮር አገሪቱ ያጋጠማት መለወጥ ዕድል እንዳይባክን ከሠራን ተስፋ አለን፡፡ በዚህ ወቅት ገጠመን ሁኔታ እንደ 1966 ዓ.ም. ወይም የ1983 ዓ.ም. ዓይነት አለመሆኑን መረዳትም አስፈላጊ ነው፡፡ በእነዚያ ሁለት ለውጥ ወቅቶች ቢያንስ እንደ አገር ለመቀጠል ሥጋት አልነበረብንም፡፡ ንጉሡ በመውደቃቸው አገር ትፈረካከሳለች የሚል ሥጋት አልገጠመንም፡፡ ደርግ በመውደቁና ሕወሓት/ኢሕአዴግ ወደ ሥልጣን መምጣቱ እንደ ሕዝብ አብሮ ለመኖር ፈተና አልፈጠረብንም፡፡ አሁን ግን የገጠመን ሁኔታ ከሁለቱ ፍፁም የተለየ ነው፡፡

አሁን መንግሥት የሚባለውን ተቋም ካፈረስን እንደ አገር ለመቀጠል የማንችልበት ሥጋት አለ ብለን ነው የአገሪቱን ገጽታ የምናስቀምጠው፡፡ ስለዚህ የቅድሚያ ቅድሚያ የመጀመሪያው ስትራቴጂካዊ ግባችን በዚያም በዚህም ተመርጦ ሥልጣን ላይ መቀመጥ ሳይሆን፣ አገር ማፅናት ነው ግባችን፡፡ መጀመሪያ ለሁላችንም መቆሚያም መቀመጫም የምትሆን ኢትዮጵያ የምትባል አገር ታስፈልገናለች ብለን እናምናለን፡፡ ይህን ለማጣት ደግሞ ከፍተኛ ሥጋት አለ ብለን እናምናለን፡፡ ሕወሓት የከፈተው ጦርነት ሰፍቶ ወደ አዲስ አበባ መድረስ ቢችል ኖሮ ሪፈረንደም በማድረግ አገር ለመበተን በግልጽ ወስኖ ነበር እኮ፡፡ ዛሬም ቢሆን መርጠው ባልተወለዱበት በዘራቸውና በማንነታቸው እየተለዩ በየቦታው የሚታረዱ ዜጎች ቁጥር ማየሉ፣ እንደ አገር የምንቀጥልበት ዕድል ጫፍ ላይ የተንጠለጠለ መሆኑን የሚያሳይ ነው፡፡ ከዚህ አንፃር የምንወስዳቸው ዕርምጃዎች የበለጠ የሚያጋጩ ወይም ያለውን ፖለቲካ መካረር የሚያባብሱ መሆን የለባቸውም፡፡ ዕርምጃዎቻችን ለአመፅና ለግርግር የሚጋብዙ መሆን የለባቸውም፡፡

በሰከነና በሠለጠነ መንገድ ሐሳቦች መስተናገድ አለባቸው ብለን እናምናለን፡፡ ከልዩነት ይልቅ ወደ አንድነት የሚገፋ መንገድን መከተል አስፈላጊ ነው እንላለን፡፡ ይህ በራሱ ዋጋ ሊያስከፍል ይችላል፡፡ ይህንን ዓላማ የሚረዳ ደጋፊና አባል ማፍራት ያስፈልጋል፡፡ ነገር ግን ጊዜ ቢወስድም ውጤቱን እያየነው ነው የምንገኘው፡፡

ሪፖርተር፡- ዋጋ ያስከፍላል የሚለውን ከብሔራዊ ምርጫ ውጤታችሁ ጋር ማስተሳሰር ይቻላል?

ዮሐንስ (አርክቴክት)፡- አዎን በትክክል እንደ እሱ ነው የሆነው፡፡ በተለይ በምርጫው ወቅት አስቀድመን፣ በመካከሉና ከተደረገ በኋላ ምን ገጽታ እንደነበረው ሳይንሳዊ ጥናቶች አካሂደናል፡፡ ምርጫው የተካሄደበት ድባብ አገሪቱ በጦርነት መካከል የነበረችበት፣ ግብፅ ግድቡን እመታለሁ የምትልበት፣ የሱዳን ጦር ብዙ ኪሎ ሜትር ድንበር ዘልቆ የገባበት፣ ጂቡቲ የሠፈሩ የኃያላን ጦሮች ወደ መሀል አገር ልንገባ ነው የሚሉበት ወቅት ስለነበር የምርጫውን ውጤትም በእጅጉ ቀይሮታል፡፡ በየትኛውም አገር ቢሆን በጥናት እንደተረጋገጠው እንዲህ ባሉ ውጥረቶች ምርጫዎች ሲካሄዱ ዜጎች የሚሰጡት ውሳኔ ፍፁም ወደ አንድ አቅጣጫ ይቀየራል፡፡ ከእነ አደጋውም ቢሆን በዚህ መሰል ሁኔታ ሥልጣን ለያዘው ኃይል ድምፅ መስጠትን ዜጎች ይመርጣሉ፣ አዲስ ከመምረጥ ይልቅ፡፡ ይህን ዓይነቱ እውነታ ነው በእኛ አገር የተደገመው፡፡ ሕዝቡ ጦርነቱን መቀልበስ፣ ግድቡን መሙላትና አገራዊ ሥጋቶችን መቅረፍ ቀዳሚ ነው ብሎ ስላመነ ብልፅግናን በሰፊው ደግፏል የሚል ግምገማ ነው ያለን፡፡ ለእኛ አሁን ከሚሆን በቀጣይ ምርጫዎች ድምፅ ልስጣቸው ያለ ይመስላል፡፡                    

የተመሠረትንበት ጊዜ አጭር እንደ መሆኑ ለሕዝቡ ሰሞኑን በውስጥ ምርጫ እንዳሳየነው፣ ለዴሞክራሲ ያለንን ታማኝነትና ቁርጠኝነት ለማሳየት አለመቻላችን ሌላው እንቅፋት ነበር፡፡ በየመንገዱ ተጣላን/ተኳረፍን ብለን የማንቆም መሆናችንን ሰሞኑን እንዳደረግነው ገና በደንብ ለሕዝቡ አላሳየንም፡፡ የምርጫው ውጤት የእነዚህና ብዙ ድምር ውጤቶች እንጂ ኢዜማ በያዘው የፖለቲካ አቋም፣ ብቃት ወይም በአንድ ነገር ብቻ የመጣ ነው አንለውም፡፡

ሪፖርተር፡- ከሰሞኑ በተደረገው በኢዜማ የአመራሮች ምርጫ በዕጩዎች መካከል በሚዲያው የተነሱ ውዝግቦችና አንዳንድ መጓተቶች ነበሩ፡፡ ይህ ደግሞ ፓርቲውን ለመከፋፈልና ለመበተን ይዳርገዋል የሚል ሥጋት ፈጥሮ ነበር፡፡ ይህ ሁኔታ በምርጫው ዕለት ተቋጭቷል፡፡ ሥጋቱስ ተቀርፏል ወይ?

ዮሐንስ (አርክቴክት)፡- የውጭ ተመልካቾች ወይም ታዛቢዎች ብቻ ሳይሆን የአባሎቻችንም ሥጋት ነበር፡፡ በኢዜማ ምርጫ ሒደት ዕጩ ከሆንክ ከተማ ብቻ ተቀምጠህ ሳይሆን፣ ታች ምርጫ ወረዳዎች ድረስ ወርደህ አባላትን ለድጋፍ መቀስቀስ ይጠበቅብሃል፡፡ እኔ ወሎ ወልድያ አካባቢ ነበርኩ፡፡ ሰሜን ጎንደር፣ ደቡብ ጎንደርና ደብረ ታቦር ነበርኩ፡፡ ዕጩዎች ከሰሜን እስከ ደቡብ በርካታ ቦታዎች ሄደን ቀስቅሰናል፣ ያልደረስንበት ቦታ የለም፡፡ አባሎቻችንን በአካል አግኝተናል፡፡ እኔ ባለሁበት ቡድን ተሰማርተን ቅስቀሳ ስናካሂድ ለአባላት ያስገነዘብነው ከሥጋት ነፃ እንዲሆኑ ነበር፡፡ ሒደቱ የውስጥ ዴሞክራሲ ልምምድ እንጂ ሌላ ዓላማ እንደሌለው ነግረናቸዋል፡፡ ለአባላቱ በፓርቲው ፕሮግራም መሠረት መሪዎችን የመምረጥ ሒደት ሌላ ጉዳይ አለመሆኑን ነግረን የፈለጉትን እንዲመርጡ አስረድተናል፡፡ እኔ በነበርኩበት ቡድን ለአባላቱ የነገርናቸው እኛን ቢመርጡ የምንሠራውን ሥራ ብቻ ሳይሆን፣ ባይመርጡም ከተመረጠው ጋር ተባብረን በጋራ በፓርቲው ውስጥ መሥራታችንን እንደምንቀጥል የሚያረጋግጥ ጭምር ነበር፡፡ አንጃ የምንፈጥርና ጠብመንጃ የምናነሳ እንዳልሆንን ቃል ገብተንላቸዋል፡፡ ይህን ያደረግነው ደግሞ ሥጋቱ የአባሎቻችን ጭምር ስለነበር ነው፡፡

እስካሁን በኢትዮጵያ በነበረው የፖለቲካ ባህል ጠቅላላ ጉባዔ ሲመጣና የአመራር ምርጫ በፓርቲዎች ሲደረግ፣ ሁሌም ውጥረት መታየቱ የተለመደ ነው፡፡ ምክንያቱም በጠቅላላ ጉባዔዎች የማን ሐሳብ ነጥሮና የበላይነት አግኝቶ ይወጣል የሚል ሥጋት ብቻ ሳይሆን፣ ውጥረቱ በጉባዔው ማግሥት ውዝግብ ስለሚወልድ ነው፡፡ በገዥው ፓርቲ ከጥቂት ወራት በፊት እንዳየነው ከጠቅላላ ጉባዔ በኋላ አባላትን በደብዳቤ ሲያባርሩ ዓይተናል፡፡ ሌሎች ፓርቲዎች አንዳንድ አባሎቻቸውን አሰናብተዋል፡፡ አንዳንዶች ደግሞ በውዝግብ የተነሳ የጠቅላላ ጉባዔ ስብሰባችሁን ድገሙ የተባሉ አሉ፡፡ ከዚህ አንፃር ጠቅላላ ጉባዔ ሲመጣና የአመራር ምርጫ ሲደረግ በፓርቲዎች አካባቢ የተለመደ ነውና በኢዜማ ዙሪያም ሥጋቱ ቢነሳ አይፈረድም፡፡ እንደ ፓርቲ የውስጠ ዴሞክራሲ ምርጫ ልምምድ አናሳ በመሆኑ፣ እንዲሁም እንደ አገር ዴሞክራሲ ባህላችን ባለማደጉ ሥጋቱ ቢነሳ አይፈረድም፡፡ እንደ ግለሰብም ቢሆን ያለን የዴሞክራሲ ልምምድ ያላደገ በመሆኑ፣ በምርጫው ሒደት ከተለመደው ወጣ ያለና ስሜት የሚኮረኩር አካሄድን የተከተሉ እንዲሆኑ በር ከፍቷል፡፡ ግለሰባዊ ማንነቶች ላይ ያተኮሩ ንግግሮች ጭምር በምርጫው ቅስቀሳ ወቅት መሰማታቸው እከሌ በዚህ ደረጃ ተናግሮማ ከኢዜማ ጋር አይቀጥልም የሚል አስተያየት የሚሰጡ ሰዎች አጋጥመውኛል፡፡ ይህ ግን ከእኛ ልምድ ማነስ የተነሳ አደባባይ የሠራናቸው ስህተቶች ፈጠሩት አስተያየት እንጂ የተጨበጠ ሥጋት አልነበረም፡፡ እነዚህን ስህተቶችም ወዲያው ለማረም በመሞከር ችግሮችን ቀርፈናል፡፡ እኔ የነበርኩበት ቡድን ለምሳሌ ወዲያው ከወሰደው ዕርምጃ መካከል የሚዲያ ቅስቀሳዎችን ቁጥብ ማድረግ ነበር፡፡ ያለንን ዴሞክራሲያዊ እሴት ለመሸጥ እንጂ፣ አባሎችን ወይም ተፎካካሪዎችን ለመወንጀል ሚዲያ ላይ አንወጣም ብለን ወሰንን፡፡ ይቅርታ እየጠየቅን ቀጠሮ የያዝንላቸውን የሚዲያ ፕሮግራሞቻችንን ሰርዘናል፡፡ ይህን ያደረግነው ደግሞ መስመር የሳቱ አካሄዶችን በማየታችን ነበር፡፡ ይህንን በማድረጋችን እንደ ኢዜማም እንደ አገርም ተጠቅመናል ብዬ እገምታለሁ፡፡

የምርጫው ዋና ዓላማ እንደ ፓርቲ ከተፎካካሪዎቻችን አንፃር ያለንን የሐሳብና የዴሞክራሲ ብልጫ ማሳየት ነው፡፡ ከልምድ ማነስ የተነሳ ሊፎካከረኝ በዕጩነት የቀረበን የትግል ጓድ በአደባባይ ግለሰባዊ ጉዳዮች ውስጥ ጭምር እገባሁ የምኮንነው ከሆነ፣ ምናልባት አብሮ ለመቀጠል አስቸጋሪ ስለሚሆን እሱ እንዲታረም አድርገናል፡፡ ሆኖም የምርጫ ፉክክሩ በሚካሄድበት አጋማሽ በወሰድነው የጥንቃቄ ዕርምጃ የተነሳ ችግሩ ሊቀረፍ ችሏል፡፡ ገለልተኛ ብለን የሰየምነው ምርጫ አስፈጻሚ አካል ሁላችንንም ዕጩዎችን ሰብስቦ የአካሄድ ዕርምት እንዲካሄድ ማሳሰቢያ ስለሰጠን እሱን ተከትለናል፡፡ በመጨረሻ ምርጫው ሲካሄድም በግሌ ያየሁት የሕዝብ አስተያየትም በጎ ነበር፡፡ ማንም ቢመረጥ ያሸነፈው ፓርቲው እንጂ ተሸናፊ የለም የሚለው ሐሳብ ሚዛን ደፍቶ ነው ያገኘሁት፡፡ በአሁኑ ለመመረጥ ዕድል ያላገኙ አባላት ተሸናፊ ሳይሆኑ ያሸነፈው ኢዜማ ነው ብለው ከአሸናፊዎች ጋር በጋራ ቆመናል፡፡ ያሸነፈው ኢዜማ ነው፣ ያሸነፈው ፕሮግራማችን ነው ብለን እንደ ጋራ አሸናፊዎች ተቃቅፈን በጋራ መቆማችንን አሳይተናል፡፡ የመነቃቀፉ ጊዜ አብቅቶ የመተቃቀፉ ጊዜ መጀመሩን፣ የፉክክሩን በር ዘግተን የትብብሩን በር መክፈታችንን አሳይተናል፡፡ በሒደት ያሳነው ጨዋነት የምርጫውን አጠቃላይ ውጤት አሳምሮታል እላለሁ፡፡

እንደምታስታውሰው በአብላጫ ድምፅ ተመርጫለሁ ያለው ብልፅግና ራሱ ያለፈውን ብሔራዊ ምርጫ ፍትሐዊ ነው ብሎ አልበየነውም፡፡ ብዙ ሰዎች ስላልሞቱብን አገራዊው ምርጫ ቢያንስ ሰላማዊ ነው ተብሎ ነበር የታለፈው፡፡ ይህን ምርጫ እንኳ ለአገር ሰላም ሲባል በሚያስማሙን ጉዳዮች በጋራ እንሠራን አገርን ማስቀጠል ይሻላል ብለን አሳማኝ ባይሆንም ውጤቱን ደግፈነዋል፡፡ እንኳን የትግል ጓዶቻችንን ራሱ ብልፅግናን የተሸከምን ሰዎች ነን፡፡ የውስጥ ዴሞክራሲ ምርጫው የፈለገውን ያህል መጓተትም ሆነ ውዝግብ ቢፈጥር፣ እንደ ኢዜማ አብሮ ለመቀጠል ግን አንዳችም ሥጋት የለብንም ብዬ ነው የምናገረው፡፡      

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

ተዛማጅ ፅሁፎች

‹‹የዋጋ ንረቱን ለማርገብ የተተገበረው የገንዘብ ፖሊሲ ውጤታማ ነው ለማለት ያስቸግራል›› አቶ አሰግድ ገብረመድህን፣ የፋይናንስ ባለሙያና አማካሪ

የዓለም ኢኮኖሚ በተለያዩ ተግዳሮቶች እየተፈተነ ነው፡፡ በተለይ የዋጋ ንረት መጠኑ ይለያይ እንጂ፣ የእያንዳንዱን አገር በር አንኳኩቷል፡፡ መንግሥታት ይህንን ችግር ለማርገብ የተለያዩ የፖሊሲ ዕርምጃዎችን እየወሰዱ...

‹‹በአመራሮቻችን የተነሳ የፓርቲያችን ህልውና ጥያቄ ውስጥ ገብቷል›› አቶ አበባው ደሳለው፣ የአብን አባልና የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል

የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) በአማራ ከተመሠረቱ የፖለቲካ ፓርቲዎች በአመዛኙ የተሻለ ሕዝባዊ ድጋፍ ያገኘ፣ ከሦስት ዓመታት በፊት በአገር አቀፍ ደረጃ በተካሄደው ስድስተኛው አገራዊ ምርጫ ተወዳዳሪ...

‹‹የግሉን ዘርፍ በመዋቅር መለያየት የነበሩ ችግሮችን ከማባባስ ውጪ መፍትሔ አያመጣም›› አቶ ሺበሺ ቤተማርያም፣ የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ዋና ጸሐፊ

አቶ ሺበሺ ቤተማርያም በኢኮኖሚክስ፣ በኢኮኖሚ ፖሊሲና ዕቅድ የመጀመሪያና ሁለተኛ ዲግሪያቸውን በማግኘት ለ36 ዓመታት የዘለቀ የሥራ ልምድ እንዳላቸው ይናገራሉ፡፡ በዕቅድና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴር፣ በዓለም አቀፍ...