Wednesday, February 1, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ተሟገትበጀት አሁንም ለምን የአገር ሆድ ቁርጠት ይሆናል?

በጀት አሁንም ለምን የአገር ሆድ ቁርጠት ይሆናል?

ቀን:

በገነት ዓለሙ

ሰኔ ሰላሳን፣ ዛሬም ጭምር ብዙ ሰው ያውቀዋል፡፡ ሰኔ ሰላሳን የሚያውቀው ትንሹም ትልቁም ነው፡፡ ጡረታ ዕድሜ ውስጥ በገባን፣ ወይም እየገባን ባለን በእኛ ትውልድ ዘመን ውስጥ ሰኔ ሰላሳ የኢትዮጵያ ትምህርት ቤቶች የአካዴሚ ካሌንደር የመጨረሻ ቀን ነበር፡፡ ዛሬ እንዲህ ያለ፣ እንዲህ የሚባል ነገር ስለመኖሩ አላውቅም፡፡ ሰኔ ሰላሳ ዛሬም ጭልጭል የሚልና ግርግርም ያለበት አሁንም በግዱ የሚታወቅበት አንድ ነገር አለ ‹‹የበጀት መዝጊያ›› ቀን ነው፡፡

ከሐምሌ አንድ ቀን ጀምሮ እስከሚቀጥለው የካሌንደር ዓመት ሰኔ ሰላሳ ቀን ድረስ ያለው ጊዜ ግን፣ ከዚህ በላይ ሕገ መንግሥታዊ ቦታና ፋይዳ ያለው የአገር የበጀት ዓመት ነው፡፡ የመንግሥት የአገር ገንዘብ የሒሳብ ዓመት ነው፡፡

የዘመናዊት ኢትዮጵያ የመንግሥት ገንዘብ (ፐብሊክ ፋይናንስ) ወግ ማዕረግ ያለው ሕገ መንግሥታዊ ከፍታና ቦታ ላይ የወጣው በ1948 ዓ.ም. የተሻሻለው የአገሪቱ ሕገ መንግሥት ማዕቀፍ ውስጥ ነው፡፡ እስከ 1966 ዓ.ም. መጨረሻ ድረስ (በ1967 መጀመርያ ላይ የታገደው) ፀንቶ የኖረው ይህ ሕገ መንግሥት እንደ አዲስና አዲስ ባቋቋመው ሥርዓት ብቻ ሳይሆን ከታገደ በኋላ፣ ከታገደ በኋላ ብቻ ሳይሆን በሌሎችም ሕገ መንግሥቶች ከተተካ ወዲህ ባጎደለው ሥርዓትና አሠራር ይታወቃል፡፡ የመንግሥት ገንዘብ (ፐብሊክ ፋይናንስ) የአገር ሆድ ቁርጠት መሆኑ እየባሰበት መጥቷልና ይህን ጉዳይ ለመረዳት በዚህ ሕገ መንግሥት ስለመንግሥት ገንዘብ የተደነገገውን፣ ራሱን የቻለ አንድ ምዕራፍ ያለውን የፐብሊክ ፋይናንስ ድንጋጌዎች በዝርዝር እንመልከት፡፡ ይህ ሕገ መንግሥት እንዴት አድርጎ መሠረታዊና የሥር የመሠረት የጨዋታ ሕጎችን እንደሚዘረጋና እንደሚያቋቁም እንይ፡፡

  • በሕግ ካልሆነ በቀር ታክስ፣ ቀረጥ፣ ግብር፣ ኤክሳይስ ቀረጥ አይጣልም፣ አይጨመርም፣ አይቀነስም፣ ወይም አይፋቅም፡፡ በሕግ ካልተፈቀደ በቀር በሕግ የተወሰነውን ማናቸውንም ታክስ ቀረጥ፣ ግብር ወይም ኤክሳይስ ቀረጥ ከመክፈል የሚያስቀር ነገር የለም፡፡
  • ማናቸውም የመንግሥት ገቢ ገንዘብ በሕግ እንደተፈቀደው ካልሆነ በቀር ወጪ አይሆንም፡፡
  • የበጀት ዓመት በልዩ ሕግ ይወሰናል፡፡ በንጉሠ ነገሥቱ ፈቃድና ሕግ በሚፈቅደው መሠረት የሚኒስትሮች ምክር ቤት ለመጪው ዓመት በሥራ ላይ የሚውለው በጀት የሚፈቅድበትን የበጀት አሳብ ጨምሮ የሕግ አሳብ እያሰናዳ በየዓመቱ ለፓርላሜንት ያቀርባል፡፡
  • ፓርላሜንቱ የቀረበለትን በጀት በዝርዝር መርምሮ አንድ በአንድ ድምፅ ይሰጥበታል፡፡ ስለወጪ በበጀቱ ከተመለከተው ከጠቅላላ ገንዘብ በላይ ፓርላሜንቱ በማናቸውም አኳኃን መጨመር አይችልም፡፡ በተባለው በጀት ውስጥ የቀረበውን ለድንገተኛ ወጪ የሚሆነውን ገንዘብ ፓርላሜንቱ ይወስናል፡፡ ለንጉሠ ነገሥቱ እንዲቀርብ ፓርላሜንቱ በበጀቱ ላይ ድምፅ መስጠቱን እጅግ ቢያንስ አዲሱ የበጀት ዓመት ከሚጀምርበት ከአንድ ወር በፊት መጨረስ አለበት፡፡
  • ከላይ በተወሰነው መሠረት የቀረበውን የሕጉን አሳብ ፓርላሜንቱ ሳይቀበለው የቀረ እንደሆነና አዲሱ የበጀት ዓመት ከመጀመሩ በፊት ሕግ ሆኖ ያልታወጀ እንደሆነ፣ አዲሱ የበጀት ሕግ እስኪታወጅ ድረስ የዚያው የቀድሞ ዓመት በጀት ሲሠራበት ይቆያል፡፡
  • ማናቸውም የበጀት ዓመት ተጨማሪ ገንዘብ በሚያስቸኩል አኳኃን ያስፈለገ እንደሆነ ለጉዳዩ አግባብ ያለው ሚኒስትር ወይም ሚኒስትሮች ተጨማሪውን በጀት ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ያቀርባሉ፡፡ ንጉሠ ነገሥቱም ሲፈቅድ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ተገቢ የሆነውን የሕግ አሳብ አዘጋጅቶ አስቀድሞ ለሕግ መምርያ ምክር ቤት ሊያቀርብ ይችላል፡፡
  • በዚህ ሕገ መንግሥት በተደነገገው መሠረት (የሕግ አወጣጥ ሥርዓቱን ተከትሎ በሚወጣ ሕግ) በሚገባ በቆመው ሕግ ካልተፈቀደ በቀር፣ በንጉሠ ነገሥቱ መንግሥት ግዛት ውስጥና በውጭ አገርም ቢሆን በማናቸውም የመንግሥት መሥሪያ ቤት ስም ሆኖ የብድር ውል መዋዋል ወይም ዋስትና መስጠት አይቻልም፡፡
  • እያንዳንዱ የበጀት ዓመት በተፈጸመ በአራት ወር ውስጥ የሚኒስትሮች ምክር ቤት የዚያውኑ የተፈጸመውን ዓመት የገቢና የወጪ ሙሉ ራፖር ለንጉሠ ነገሥቱና ለፓርላሜንቱ ያቀርባል፣ ራፖሩም ወዲያውኑ ለዋናው ኦዲተር ይላካል፡፡ ኦዲተሩም በራፐሩ ላይ ያለውን አስተያየት በሦስት ወር ውስጥ ለንጉሠ ነገሥቱና ለፓርላሜንቱ ያቀርባል፡፡
  • ይህን ሁሉ የሚዘረዝረው፣ እዚህ ውስጥ በግልጽ የምናያቸውን መርሆዎች (ለምሳሌ ያለ ሕግ ታክስ አይጣልም፣ ያለ ሕግ ገንዘብ ወጪ አይሆንም፣ ከሁሉም በላይ ደግሞ በአገር ውስጥም በውጭ አገርም የመንግሥት መሥሪያ ቤት ወይም በመንግሥት መሥሪያ ቤት ስም የብድር ውል አይፈራረሙም፣ ዋስትናም አይሰጥም)፣ እንዲሁም የበጀት የጊዜ ሠሌዳዎች የሚያቋቁመው በሕገ መንግሥት ደረጃ ያለ ሕግ ነው፡፡ የአገር የምርመራ ወይም ኦዲትና የቁጥጥር ሕግ ደግሞ የተቀረውን ያሟላል፡፡

ሕገ መንግሥቱ የበጀት ዓመቱ በልዩ ሕግ ይወሰናል ባለው መሠረት፣ አሁንም ሥራ ላይ ያለው የአገሪቷ የበጀት ዓመት አዋጅ (አዋጅ ቁጥር 162/51 በአዋጅ ቁጥር 196/1955 እንደተሻሻለ የወጣው በ1948 ዓ.ም. ሕገ መንግሥት መሠረት በ1951 ዓ.ም. ነው፡፡ የኢትዮጵያ የበጀት ዓመት ሕግ የአገሪቱን የበጀት ዓመት፣ ከካሌንደር ዓመቱ የተለየ፣ ከሐምሌ አንድ ቀን ጀምሮ እስከሚቀጥለው ዓመት ሰኔ 30 ቀን ድረስ ላለው የአንድ ዓመት ጊዜ አድርጎ ወሰነ፣ አቋቋመ፡፡ ይህን የበጀት ዓመት በሕግ ያቋቋመው ሕግ የፀናው በነጋሪት ጋዜጣ ከወጣበት ከነሐሴ 21 ቀን 1951 ዓ.ም. ጀምሮ በመሆኑ፣ ይህ ሕግ/አዋጅ ከሚፀናበት ቀን ጀምሮ ያለው የሚቀጥለው የመጀመርያው የበጀት ዓመት ከመስከረም 1 ቀን 1952 ዓ.ም. እስከ ሰኔ 30 ቀን 1952 ዓ.ም. ድረስ እንዲሆን በሕግ ተወሰነ፡፡ በዚሁ በበጀት አዋጁ በራሱ ድንጋጌ መሠረትም ለመጪው ዓመት በሥራ ላይ የሚውለው በጀት እጅግ ቢዘገይ ከመጋቢት 15 ቀን በፊት ለምክር ቤቱ መቅረብ እንዳለበት ተደነገገ፡፡

ይህን ሁሉ ዝርዝር በዋነኛነት የደነገገውና የአገርም ሕግ አድርጎ ሥርዓት የዘረጋው መሠረትም የጣለው የ1948 ዓ.ም. ሕገ መንግሥት በመሆኑ ከዚህ ሕገ መንግሥት መታገድ ጋር ዋና ዋና የመንግሥት ፋይናንስ፣ የበጀት አፀዳደቅ መርሆዎችና ተጓዳኝ የዚህ ጉዳይ ጓዝ ጉዝጓዞች ተከታትለው በመጡ ወይም በወጡ ሕገ መንግሥቶች (የ1980ም ሆነ የ1987) ወይም ሕገ መንግሥት አከል የፋይናንስ አስተዳደር ሕጎች ስላልተተኩ፣ ቀድሞ ተቋቁሞ የነበረው የአሠራር ልምድ የበጀት የጊዜ ሰንጠረዥና እሱንም የማክበር ዲሲፕሊን ሟሸሸ፡፡ መተኪያ የሌለውና አላስፈላጊ የሆነ የቢሻኝ ፎርማሊቲ ሆነ፡፡

ልብ እናድርግ የአገራችንን የበጀት አፀዳደቅ የሚወስነው፣ ይወስን የነበረው ሕግ የ1948 ዓ.ም. ሕገ መንግሥት ፓርላሜንት በበጀቱ ላይ ድምፅ መስጠቱን እጅግ ቢያንስ አዲሱ የበጀት ዓመት ከሚጀምርበት ከአንድ ወር በፊት መጨረስ አለበት ይላል፡፡ ወይም ይል ነበር፡፡ ቢያንስ ቢያንስ ከግንቦት 30 በፊት ማለት ነው፡፡ ከዚያ በፊት ያለ፣ ማለትም ከግንቦት 30 በፊት ያለ የጊዜ ሰሌዳ የሚያቋቁም ሕግም አለ፣  ወይም ነበር፡፡ እሱም የበጀት አዋጁ ነው፡፡ እስከ ሰኔ 30 ቀን 1952 ዓ.ም. ድረስ ያለውን ጊዜ በኢትዮጵያ የመጀመርያው የበጀት ዓመት አድርጎ ያቋቋመው ሕግ በአንቀጽ 3 ለመጪው ዓመት በሥራ ላይ የሚውለው በጀት እጅግ ቢዘገይ ከመጋቢት 15 ቀን በፊት ለምክር ቤቱ መቅረብ አለበት ይል ነበር፡፡

የደርግ የወታደራዊ መንግሥት የ17 ዓመትና የኢሕአዴግ የ27 ዓመት ሕግና ደንብ እንዳሻ የሚጣልና የሚነሳበት፣ የአስተዳደር ዘመን አሽቀንጥረው የጣሉትና የረመረሙት የበጀት ሕግና አሠራር ከዚያ በኋላ በወጡት የአገር የፋይናንስ አስተዳደር ሕግ ይመራ ሲባል እንኳን ያማረበት ሲሆን አልታየም፡፡ ለምሳሌ አሁን ሥራ ላይ ያለው ከላይ የጠቀስናቸውን የቀድሞ የሕግ ማዕቀፎች የተካው ሕግ የኢትዮጵያ ፌዴራል መንግሥቱ የፋይናንስ አስተዳደር አዋጅ ቁጥር 648/2001 (በአዋጅ ቁጥር 970/2008 እንደተሻሻለ) ነው፡፡ ይህ ሕግ በጀት ስለማፅደቅና ስለመወሰን ሲደነግግ (በአንቀጽ 22) የገንዘብ ሚኒስትሩ ለተከታዩ የበጀት ዓመት የሚያስፈልገውን በጀት ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ያቀርባል፣ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በመገኘት በሚኒስትሮች ምክር ቤት ተደግፎ ስለተላከው በጀት ማብራሪያ ይሰጣል፣ የዓመቱ በጀት እስከ ሰኔ 30 ቀን በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ፀድቆ ሁሉም የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች እስከ ሐምሌ 7 ቀን እንዲያውቁት ያደርጋል፣ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የፀደቀው በጀት በነጋሪት ጋዜጣ ታትሞ ይወጣል ይላል፡፡

ይህን የሚለው የፋይናንስ አስተዳደር አዋጅ በትርጉም ክፍሉ ‹‹የበጀት ዓመት›› ማለት ከሐምሌ 1 ቀን እስከ ሰኔ 30 ቀን ያለው ጊዜ ነው ማለቱ ባይቀርም፣ የአገሪቱን የበጀት ዓመት ያቋቋመው 64ኛውን የበጀት ዓመት ራሱን ያስቆጠረው ሕግ ራሱን ስለማክበሩ/አክብሮ ስለመጠበቁ እንኳን አይናገርም፡፡ ‹‹የዓመቱ በጀት እስከ ሰኔ 30 ቀን በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ፀድቆ ሁሉም የመንግሥት መሥሪያ ቤቶችና የክልል መንግሥታት እስከ ሐምሌ 7 ቀን እንዲያውቁት ይደረጋል›› ማለት ድረስ የሚታገስ፣ በዚያ ላይ ደግሞ በሕጉ አጻጻፍ ቅደም ተከተል መሠረት ከዚያ በኋላ ማለትም ከሰኔ 30 በኋላ፣ በነጋሪት ጋዜጣ ታትሞ ይወጣል ተብሎ ያን ያህል በሕግ አወጣጥ ረገድ ‹‹ደንታ ቢስ›› የተኮነበት የበጀት ሕግ በጣም፣ በጣም ሲበዛ ለውጥና ማሻሻል የሚጠይቅ ሆኖ ሲጣራና ሶጮህ ይሰማል፡፡

የ2015 በጀት ዓመት፣ ማለትም ከሐምሌ 1 ቀን 2014 ዓ.ም. ጀምሮ እስከ ሰኔ  30 ቀን 2015 ዓ.ም. ድረስ ባለው ጊዜ ውስጥ የሚፈጸመው የአንድ የበጀት ዓመት ጊዜ፣ የበጀት አዋጅ ረቂቅ ለምክር ቤቱ በይፋ የቀረበው ግንቦት 30 ቀን 2014 ዓ.ም. ነው፡፡ ያኔ በተሰማና በቀረበ የገንዘብ ሚኒስትሩ የበጀት ንግግር አማካይነት ነው፡፡ በዚህ የጊዜ መቃን ውስጥ በራሱ የሰኔ ወር ከሁለተኛ እስከ አምስተኛ ያሉ ሳምንቶች ምን ሆነው የበጀቱን ተራ ‹‹የግብር ይውጣ›› የሚባል የስሚ ትኩረት እንዳጡ ግራ የሚገባ ጉዳይ ነው፡፡ የዓመቱ በጀት እስከ ሰኔ 30 ቀን በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ይፀድቃል የሚል ሕግ ያለው በጀት ሰኔ 30 ሳምንት ውስጥ ‹‹ሥራ አለህ›› አለመባሉ፣ ምክር ቤቱም ማክሰኞ ዕለት መደበኛ ስብሰባውን ሳያደርግ መቅረቱ በምንም ዓይነት ምክንያት የሚያብራሩት ነገር አይደለም፡፡ አዎ ጊዜው፣ ተደጋግሞ እንደተነገረው ኃላፊነት የጎደለው ፖለቲካ የደራበት፣ የማኅበራዊ ሚዲያ ውሸት፣ አክሳሪ ብሽሽቅና አላታሚ ፕሮፓጋንዳ ገንዘብ እያገኘ የነሰረበት ወቅት ነው፡፡ ይህን ወቅት የጥፋትና የትርምስ ኃይሎችን፣ የለውጥ ተጠናዋቾችን፣ ከለውጥ ኃይሎችና ከምልዓተ ሕዝቡ ጋር ሆኖ መጋፈጥ እንጂ ሌላ የተሻለ፣ ሻል ያለ የቀጠሮ ቀን ፍለጋ መሄድ ግዴታን መወጣት አይደለም፡፡ መደበኛ ሥራን መሥራትም አይደለም፡፡ ይልቁንም መሻሻልና ለውጥ የሚገባውን የበጀት አፀዳደቅ የቆየ፣ ያረጀና ያፈጀ አሠራር የመረቀ ነው፡፡

ኢትዮጵያ ሰማይ ላይ ለውጥ የዳመነው፣ በዚህ የበጀት ጉዳይ ላይ የተወሰነውን በሚመለከት ጉዳይም ቢሆን፣ መንግሥት በተለይም የአስፈጻሚው ዘርፍ የበጀት የጊዜ ሰንጠረዥን አያከብርም፣ ይህንን አክብር የሚለው ሕግ እንኳን የለውም ብሎ ብቻ አይደለም፡፡ ይህ መታረም፣ በጭረሽ መደገም የሌለበት ስህተትና ጥፋት ነው፡፡ ከለውጥና ከሽግግሩ ጋር አብረው የመጡ የቅን ልቦና ስሜቶችና በጎም ምኞቶች አለመታደል ሆኖ አቻ፣ አጉልና አፍራሽ ነገሮች ጋር እየተጣበቁ ሲከሰቱ ታይተዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጠበቅ ተደርገው ቢጠየቁ፣ ጠበቅ አድርገው ከምር ቢከራከሯቸው ይገፉበት አይገፉበት እንደሆነ አላውቅም እንጂ፣ በጀት ባልተመደበልን ጉዳይ ፓርላማው አይጠይቀኝም፣ ፓርላው የሚጠይቀኝ በሰጠኝ ገንዘብ ልክ ነው ሲሉ የሰማሁ ይመስኛል፡፡ ሲመስለኝ የዚህ መከራከሪያ ይዘት ለምኜ ያመጣሁት ሀብት አይመለከታችሁም ማለት ዓይነት ነው፡፡ የሥራው ሕግ ግን፣ የመንግሥት ሥልጣንን የሚገዛው ሕግ ግን ይህን አይፈቅድም፡፡ ይህን አይመርቅም፡፡ መንግሥት በሕግ ያልተፈቀደ ገንዘብ አይሰበስብም፡፡ ብድር ብቻ ሳይሆን ስጦታም፡፡ የመንግሥት ሕግ በመንግሥት ስም የሚበደረውን፣ የሚደራደረውን፣ የሚለምነውንም፣ የሚመፀወተውንም ዓይነትና ባለሥልጣን ይወስናል፣ መወሰንን ያገባኛል ማለትን ይገዛል፡፡

የፕሮጀክት ሥራን መቆጣጠር ብቻ ሳይሆን፣ ራሱ የፕሮጀክት ሥራ (ትልቅም ሆነ ትንሽ) አስፈላጊ መሆኑ አስቀድሞ መፈቀድ ሳያስፈልገው እንደ እንጉዳይ ሊፈላ ይችላል ያለ ማነው? ይህን የመሰለ ነገር በከፋ ልቦና ሳይሆን በቅን ልቦና መነጋገር በጣም ተገቢ ነው፡፡

ከዚህ የበለጠ የሚያንገበግብና የሚቆረቁር የበጀትን መሠረታዊ ፖለሲ መርህና ሕግ የሚጥስ እየተለመደ የመጣ፣ ተቃውሞ ገጠመኝም ብሎ ሕጋዊና ሰላማዊ እንዲሁም ዴሞክራሲያዊ ተቃውሞ ገጠመኝም ብሎ የሚያኮርፍ፣ ሲገፋም ‹‹ቂም›› ቢጤ የሚይዝ፣ ሲከፋም ተቃውሞን በድሮ በጥንቱ፣ ትተነው በመጣነው መንገድ አወራርዳለሁ የሚል የምላሽ ዓይነት አለ፡፡ እግረ መንገዴን፣ ለውጡን የሚመራው መንግሥት በተለይም ደግሞ አገር በደረሰችበት የውጣ ውረድ ደረጃ ለውጡንና ሽግግሩን ከክሽፈት ለማዳን ብርቱ ግብግብ ላይ የሚገኘውን የለውጡን ድጋፍ መንከባከብና ማገዝ ያለበት የመንግሥት አመራር ተራ የሕግ ጥሰት ውስጥ ደጋግሞ በመዘፈቅ፣ ‹‹አላዋቂ ሳሚ›› ዓይነት አላስፈላጊና የማያጣድፉ ውሳኔዎችን በችኩልነት በመውሰድ፣ ሕግ ማስከበር ተግባሩ ውስጥ የገዛ ራሱን የሕግ አክባሪነት የውኃ ልክ በማስገመት፣ ወዘተ የለውጥ ድጋፍ ስሜት ከማሻከርና ከመረበሽ የተደጋገሙ ስህተቶችና ጥፋቶች መቆጠብ አለበትም እላለሁ፡፡

ወደ በጀትና ወደ መንግሥት ፋይናንስ እንመለስና ቀደም ብዬ ያነሳሁትንና ያተኮርኩበትንም የአንድ አገርን የመንግሥት የበጀት ሥልጣን ከፍተኛ ቦታ ደግሜ ላስታውስ፡፡ የመንግሥት ሥልጣን በአስፈጻሚው፣ በሕግ አውጪውና በሕግ ተርጓሚው ተከፋፍሎና እንዲጠባበቁ ተደርጎ በተደላደለበት ሥርዓተ መንግሥት የካዝናው ሥልጣን ፈረንጆች ‹‹The power of the Purse›› ይሉታል፡፡ የሕግ አውጪው ነው፡፡ በአገራችን ለተወካዮች ምክር ቤት የተሰጠው ይህ በጀት የማፅደቅ፣ በጀቱን ለየባለበጀት መሥሪያ ቤቱ የማደላደል ብቻ ሳይሆን፣ በዚያም ሥርና ከዚያም በታች በየወጪ አርዕስቱ የመሸንሸን ሥልጣን፣ የሕግ አውጪው የመንግሥት አካል ሥልጣን ነው፡፡ ይህ አንዱ ገጽታ ብቻ ነው፡፡ ‹‹የበጀት›› ወይም የካዝና የመንግሥት ሥልጣን ወደ ካዝናው የሚገባውን የመንግሥት ገንዘብ ምንጭም ይወስናል፡፡ ያለ ሕግ ገንዘብ አይሰበሰብም፡፡ ከታክስም ሆነ ታክስ ካልሆነ ገቢ፣ እንዲሁም ከብድርም ሆነ ከዕርዳታ ምንም ገንዘብ ያለ ሕግ አውጪው አካል ውሳኔ ወደ ካዝናው አይገባም፡፡ ለዚህ ነው የብድርና ሌሎችም ውሎች የማፅደቅ ሥልጣን የሕግ አውጪው አካል የሆነው፡፡

እነዚህ ሁሉ ሥልጣኖች በሚቆጣጠሩትና ኃላፊም ተጠያቂም በሚሆኑበት አሠራር፣ ወደ መንግሥት ካዝና ወደ መንግሥት ግምጃ ቤት የሚገባው ገቢ ያለዚህ በጀት ሕግ ውጪ አይሆኑም፡፡ የእያንዳንዱ የበጀት ዓመት አዋጅ እንደሚያሳየው የበጀት ሕግ የአገርን ገንዘብ ለመንግሥት ‹‹… ወጪ ሆኖ እንዲከፈል›› ማዘዣ ፈቃድ ነው፡፡ ለምሳሌ የ2015 በጀት ዓመት የፌዴራል መንግሥት የበጀት አዋጅ ረቂቅ፣ ከሐምሌ 1 ቀን 2014 ዓ.ም. ጀምሮ እስከ ሰኔ 30 ቀን 2015 ዓ.ም. በሚፈጸመው በአንድ የበጀት ዓመት ጊዜ ውስጥ የፌዴራል መንግሥት ከሚገኘው ገቢና ከሌላ ገንዘብ ላይ ከዚህ ጋር በተያያዘው ሰንጠረዥ ውስጥ ለተጠቀሱ ሥራዎችና አገልግሎቶች ቀጥሎ እንደተመለከተው፣

ሀ. ለመደበኛ ወጪዎች                       ብር 345,116,460,530

ለ. ለካፒታል ወጪዎች                       ብር 218,112,877,804

ሐ. ለክልሎች የሚሰጥ ድጋፍ                  ብር 209,380,714,780

መ. ለዘላቂ የልማት ግቦች ማስፈጸሚያ ድጋፍ     ብር 14,000,000,000

ጠቅላላ ድምር                               ብር 786,610,053,114

(ሰባት መቶ ሰማንያ ስድስት ቢሊዮን ስድስት መቶ አሥር ሚሊዮን ሃምሳ ሦስት ሺሕ አንድ መቶ አሥራ አራት ብር) ለፌዴራል መንግሥት ወጪ ሆኖ እንዲከፈል በዚህ አዋጅ ተፈቅዷል ይላል፡፡

የፈቃዱ ወሰን ይህ ብቻ አይደለም፡፡ በጀት የመንግሥት የመጪው ዓመት ዕቅድ/ፕላን ገንዘባዊ ምሥል ነው፡፡ የገንዘብ መግለጫ ነው፡፡ ከፍላጎትና ከጥያቆት አንፃር የማንም አገር ሀብት ውስን ነው፡፡ የአሜሪካም ጭምር፡፡ እንዲያውም ምኑም ከምን አድርጌ ላብቃቃው ከሚባል የአገራችን ተበድሮም ተለቅቶም የተሰባሰበ ሀብት ውስጥ፣ ለእኔ ለእኔ የሚለው፣ ስጡኝ ብሎ የጦፈ ውድድርና ፉክክር የሚያደርገው የመንግሥት ዘርፍና መሥሪያ ቤት ብዙ ነው፡፡ እንዲህ ያለ የበጀት ጥያቄ ቀርቦ፣ ለዚያውም እያንዳንዱ ባለበጀት መሥሪያ ቤት ለሚያቀርበው የበጀት መጠን ጣሪያ ተበጅቶ፣ የቀረበው የበጀት ልክ ከእነ ምክንያት ተመርምሮ፣ ተፈትኖ፣ ማብራሪያና መከላከያ ተሰጥቶበት መከራውን ዓይቶ ነው የሚያልፈው (ቢያንስ ቢያንስ ወጉ እንዲህ ያለ ነው ይባላል)፡፡ እንዲህ ያለ ሥርዓትና አሠራር ውስጥ መዓት የማይታለፉ የሚፈታተኑ፣ ግን መቆረጥ የሚገባቸው የፖሊሲ ውሳኔዎች ይሰጣሉ፡፡ ለምሳሌ ከጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ይልቅ የወህኒ ቤቶች አስተዳደር ይብሳል ተብሎ የመጀመርያው የተከለከለውና ለሁለተኛው የተሰጠ የተወሰነ የገንዘብ መጠን ይኖራል፡፡ አሁንም ለምሳሌ ያህል ነው ምርጫ ቦርድና መከላከያ ተፎካክረው፣ ከፍተኛ ግብግብ ውስጥ ገብተው በአንፃራዊነት መከላከያ ታገስ ተብሎ ምርጫ ቦርድ ቅድሚያ ያገኘበት አጋጣሚ ይኖራል፡፡

እንዲህ ተደርጎ ለአንዱ ከልክሎ ለሌላው ሲሰጥ፣ ከአንዱ አንገብጋቢ ፍላጎት ወስዶ ለሌላው አንተ ትብሳለህ ተብሎ ገንዘብ ሲመደብ የአገር የመጀመርያ ቅድሚያ ይህ ሳይሆን ያኛው ነው ብሎ መወሰን ነው፡፡ እንዲህ ባለ አሠራር ውስጥ አልፎ የተመደበ በጀት ሳይሠራበት ሲቀር ቢቃጠል ምን ይባላል? ሥራውን ሳይሠራው የቀረው መሥሪያ ቤት እሠራዋለሁ፣ አንገብጋቢ ነው ያለውን ሥራ ሳይሠራ የመቅረት አሳዛኝና ራሱን የቻለ ጥፋት ብቻ ሳይሆን፣ ሌላውንም የመንግሥት ሥራ ነጥቆ የጎዳ፣ በሌላውም የመንግሥት ሥራ መሰናክል የፈጠረ ድርብ ጥፋት ነው፡፡

እዚህ ውስጥ ደግሞ ሌላ የምናየው ትርጉሙንና ምክንያቱን፣ እንዲሁም የሥልጣኑን ምንጭ ማንም ሲነግረን የማንሰማው ነገር፣ አንዱ ክልል ለሌላው ክልል አንዱ የፌዴራል ወይም የክልል የመንግሥት ባለበጀት መሥሪያ ቤት ለሌለው (ባለበጀት መሥሪያ በትም ሆነ ሌላ ሌላ አካል) ይህን ያህል በሚሊዮን ሰጠ ሲባል መስማታችን በቃ መደበኛ የአገር አሠራር ሆኗል፡፡ ዜናዎች ውስጥ የምንሰማቸውን ክልሎች፣ ባለበጀት የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች፣ ለሌሎች ክልሎች፣ ለመንግሥት መሥሪያ ቤቶች፣ እንዲሁም የመንግሥት መሥሪያ ቤት ላልሆኑ ተቀባዮች ይህን ያህል ገንዘብ ‹‹ለገሱ›› ሰጡ ይለናል፡፡ እውነት ነው ወይ? ባለበጀት መሥሪያ ቤቶች ይህን ያህል የመደበችላቸው የዕርዳታና የስጦታ፣ የልግስናና የበጀት መደብ አለ ወይ? አንድ ባለበጀት መሥሪያ ቤት እንዲህ ያለ አባ መስጠት የሚሆንበት የተመደበለት የወጪ አርዕስት አለ ወይ? አገር በመከራና በችግር የሚያፈራውን ወደ ግምጃ ቤት ገብቶ በበጀት ሕግና በአፈጻጸሙ መሠረት መተዳደር ያለበትን የደሃ አገር ገንዘብ ከአንድ ባለበጀት መሥሪያ ቤት ወደ ሌላ ሊተላለፍ የሚችልበት ሁኔታ ቢኖር በሕግ የበጀት ዝውውር ሲፈቀድ ነው የምናየው፡፡ ግን ከዚህ የተለየ በተለይም የበጀት ሕግን የሚረጋግጥና በአገር ዕቅድ ላይ የሚያስከፋ አሠራር ነው፡፡ መረዳዳትና መደጋገፍ ጥሩ ነው፡፡ መረዳዳትንና መደጋገፍን፣ አዛኝነትን ጥሩና ተገቢ የሚያደርገው ደግሞ በተለይም መንግሥታዊ አሠራር ውስጥ ሕጋዊ ሲሆን ነው፡፡ ለውጡና ሽግግሩ ሊያስተካክላቸው ከሚገቡ ጉዳዮች መካከል አንዱ ለመንግሥት በጀት ሕግ መገዛት፣ ከዚያ ሕግ በላይ አለመሆኑን ማረጋገጥ ጭምር ነው፡፡ ሰኔ 30 በተቃረበና በመጣ ቁጥር መንግሥት የበጀት ዲሲፕሊን የለውም እያልን መጮህ በጭራሽ መደገም የለበትም፡፡  

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊዋን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ በወቅታዊ ፀጥታና ደህንነት ጉዳዮች ላይ የቀረበላቸውን ምክረ ሐሳብ እያደመጡ ነው]

ችግሩ ምን እንደሆነ በትክልል ለይተነዋል ግን ግን ምን? በይፋ መናገር አልነበረብንም። ለምን? ችግሩን...

የ12ኛ ክፍል የብሔራዊ ፈተና ውጤትና እንደምታው

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት (UNESCO) የትምህርትን...

ንግድ ባንክ ከቪዛና ማስተር ካርድ ጋር ተደራድሮ ያስጀመረው የገንዘብ ማስተላለፊያ ቴክኖሎጂና ፋይዳው

ከውጭ ወደ አገር በሕጋዊ መንገድ የሚላክ ገንዘብ (ሬሚታንስ) መጠን...

ይኼ አመላችን የት ያደርሰን ይሆን?

እነሆ ከፒያሳ ወደ ካዛንቺስ። ‹‹አዳም ሆይ በግንባር ወዝ ትበላለህ››...